በሴኔጋል በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ የአሸናፊነት ግምት ተሰጣቸው

በሴኔጋል በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ አሸናፊ እንደሚሆኑ ግምት ተሰጠ። በርካታ ተቀናቃኞች ሽንፈታቸውን አምነው መቀበላቸውም ተሰምቷል።

ከሦስት ዓመታት አለመረጋጋት እና በሥልጣን ላይ በነበሩት ማኪ ሳል ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ሚሊዮኖች እሑድ በተደረገው ሠላማዊ ምርጫ ተሳትፈዋል። ለፕሬዚዳንትነት 19 እጩዎች በምርጫው ቀርበው ነበር።

የገዢው ፓርቲ ተወካይ አማዱ ባ ተሸንፈዋል የሚሉ ሪፖርቶችን ውድቅ በማድረግ አሸናፊውን ለመወሰን ሁለተኛ ዙር ምርጫ ይካሄዳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። የ44 ዓመቱ ፋዬ ከምርጫው በፊት ታስረው በነበሩት በኡስማን ሶንኮ የሚመራው የፓስቴፍ ፓርቲ አባል ናቸው። ሶንኮ በቀረበባቸው የስም ማጥፋት ክስ ከውድድሩ ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በቴሌቪዥን በታወጀው የመጀመሪያው ውጤት ፋዬ አብላጫ ድምጽ ማግኘታቸው ሲነገር በዋና ከተማዋ ዳካር ጎዳናዎች ላይ በርካቶች ደስታቸውን ገልጸዋል። ደጋፊዎቹ ርችቶችን ሲተኩሱ፣ የሴኔጋልን ባንዲራ ሲያውለበልቡ እና ቩቩዜላዎችን ሲነፉ ታይተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ አምስት የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ፋዬን አሸናፊ አድርገው አውጀዋል። አንታ ባባካር ንጎም ከፍተኛ ግምት ካገኙ እጩዎች አንዱ የነበሩ ሲሆን ባወጡት መግለጫ ለፋዬ ስኬትን ተመኝተዋል። ሌላኛው ተቀናቃኝ ሶንኮ እንዲሁ ፋዬን ደግፈዋል።

የወቅቱ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በዚህ ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ተሳታፊ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይህን በሴኔጋል ታሪክ በእጩነት ያልቀረቡ በሥልጣን ላይ ያሉ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት አድርጓቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ የሚመሩት የገዥ ፓርቲያቸው ጥምረት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የ62 ዓመቱን ባ እጩ አድርጎ አቅርቦ ነበር። የባ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን “ከእኛ ባለሙያዎች ቡድን የተገኘውን ውጤት ከግምት ውስጥ በማስገባት በጣም ከከፋ ወደ ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንደምንሄድ እርግጠኞች ነን” ብሏል።

ሴኔጋል ወደ 18 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል። እስካሁን ከ15 ሺህ 633 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ምን ያህሉ እንደተቆጠሩ ግልጽ አይደለም። የመጨረሻ የምርጫ ውጤቶች ዛሬ ማክሰኞ እንደሚጠበቁ የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም

Recommended For You