በተሽከርካሪ ጭስ እና የድምፅ ብክለት የምትታወቀው አዲስ አበባን ወደኋላ ትተን ሽቅብ እየወጣን፤ ከመሬት ወለል በላይ 3 ሺ 200 ከፍታ ላይ እንገኛለን። ከሽሮ ሜዳ ተነስቶ እንጦጦ ማርያም በሚዘልቀው ሰፊ አስፋልት ሽቅብ ወጣን። በዚያ ተራራማ ስፍራ ቁልቁል ሲመለከቱ በሰፊ ብራና ላይ እንደተሳለ የከተማ አምሳያ አዲስ አበባ ቁልጭ ብላ ትታያለች።
አንዳንዱ የሚኖርባት ከተማ ይበልጥ በግልጽ እንድትታየው በኮረብታው ላይ ወጥቶ እጁን እየጠቆመ ያ ሕንጻ ያኛውስ አካባቢ የት ነው? እያለ ይጠይቃል። ገሚሱ መልስ ይሰጣል። ቅኝታችንን ቀጥለናል፤ መዳረሻችን ግን የብዙዎች ተስፋ ሊሆን ወደተገነባው ተቋም ነውና ጉዟችን አላበቃም። እንጦጦ ማርያም ስንደርስ ወደቀኝ ታጥፈን ገባን። ሌላ አዲስ የአስፋልት መንገድ ተቀበለን። የምንሄድበትን ቦታ በትክክል አናውቀውም ነበርና ሰዎችን እየጠየቅን ጉዟችንን ቀጠልን።
ፕሮጀክቶቹ በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት ከጫካ በመልቀም ለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጀምረው የተጠናቀቁም የልማት ሥራዎች ነበሩ። ፕሮጀክቱ ባለ 5 ወለል አምስት ሕንፃዎች የያዘ ሲሆን፤ እነዚህ ሕንጻዎች ደግሞ 200 አባወራዎችን የሚይዙ፣ ሁሉም ቤቶች ዘመናዊ ሆነው የተሠሩ ከመሆናቸውም በላይ የመኖሪያ መንደሩ ውብ ምድረ ግቢ አረንጓዴ ስፍራዎች አካቶ በ 14 ሺ 625 ካሬ ሜትር ላይ እንዲያርፍ የሆነ ነው።
ይኸው ፕሮጀክት ጉለሌ እንጀራ ማዕከልን ይዟል፤ ይህ ለከተማዋ ሁለተኛው የእንጀራ ፋብሪካ ሲሆን፤ በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ 551 እናቶች የሥራ እድል የፈጠረ ነው። የእንጀራ ማዕከሉ በውስጡ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ሕንጻዎች፣ የሕጻናት ማቆያ፣ የእህል ማከማቻ፣ ወፍጮ ቤት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ያካተተ ነው።
450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ የተገጠመለት ይህ ማዕከል፤ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያና ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽን፣ ሁለት ወፍጮዎች አሉት። 551 እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው ይሠሩበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በእንጀራ ማዕከሉ ውስጥ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው እናቶች ከዚህ በፊት በአካባቢው እንጨት በመልቀም ሲተዳደሩ የነበሩ፣ ምንም ገቢ የሌላቸው እና የኑሮ ጫና የበረታባቸው ናቸው።
ወይዘሮ ሠናይት ደምሴም በእድሜ ጠና ያሉ ሲሆን፤ የእዚህ እንጀራ መጋጋሪያ ፋብሪካ አባል ናቸው። ተወልደው ያደጉት ጋሞጎፋ ነው። በእናትና አባታቸው ቤት ከእህት ከወንድሞቻቸው ጋር እንደ ማንኛውም የአካባቢው ሕጻን ቢያድጉም የመማር እድልን ግን አላገኙም ነበር።
ወይዘሮ ሠናይት ተወልደው ባደጉባቸው የልጅነት ጊዜዎች ብዙ የማይረሱ ትዝታዎች አሏቸው። ከእኩዮቻቸው ጋር መጫወቱ መቦረቅ እንደ ሴት ልጅ ደግሞ ቤት ገብቶ እናትን ማገዙ በዓላት ሲመጡ የተለያዩ ምግቦችን እየተመገቡ በሀገር ሽማግሌዎች መልካም ምኞትን እየተለዋወጡ አክስት አጎት ጎረቤት ጋር እየተዘዋወሩ መብላት መጠጣት ብቻ ብዙ የማይረሷቸው ትዝታዎች ያሏቸው እናት ናቸው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ጋሞ ጎፋ ሆነው ከአዲስ አበባ ሰው ከመጣ እንደ ብርቅ ስለሚታይ አዲስ አበባ ምን ትመስላለች? ምን አለ? ከጎሞ ጎፋ በምን ትለያለች? የሚለውን ለመስማት የሚደረግ ግብግብን ሲያስቡት ያስቃቸዋል። ይሔ ሃሳብ ወደኋላ ጎተታቸው። ‹‹የትውልድ አካባቢዬ ጋሞ ጎፋ ለእኔ ትልቅ ትዝታዬ ነው በማለትም የኋሊት እያሰቡ መተከዝ ጀመሩ።››
በዚህ መልኩ በቤተሰብ በዘመድ አዝማድ በአብሮ አደግ ጓደኛ ተከበው ይኑሩ እንጂ አዲስ አበባ ይሉት ሀገርን ማየት ግን ሕልማቸው ነበር። በእርግጥ ሕልሙ የእሳቸው ብቻ ሳይሆን የሁሉ የእድሜ እኩዮቻቸው የመጨረሻ ግብ አዲስ አበባ ገብቶ ዘናጭ አማርኛ ተናጋሪ ሠርቶ ብዙ ብር የሚያገኝ መሆን ነበር።
“…..እውነት ለመናገር በሀገሬ ላይ ስኖር ያን ያህል ጎሎብኛል የምለው ነገር አልነበረም። ያደግነው እንደ ሁሉም የአካባቢው ታዳጊዎች ገጠር ያፈራውን ሁሉ በልተን ጠጥተን ከብት ጠብቀን ቤተሰብ በሥራ ረድተን ነው። ነገር ግን ደግሞ አዲስ አበባን ማየት ብሎም ሠርቶ ሀብታም መሆን እንፈለግ ነበር።” በማለት ሁኔታውን በማስታወስ ይናገራሉ።
በሞቀ የጉጉታቸው ዘመን ገና በሕፃንነታቸው ሄደው ያላዩዋትን አዲስ አበባ እድሜያቸው ከፍ ሲልና ችግሮችን እቋቋማለሁ ብለው በሚያስቡበት እድሜ ላይ ሲደርሱ አዲስ አበባ መግባታቸው አልቀረም። ብር እንደ አፈር ይታፈስባታል፤ ዘመናዊ ኑሮ ይኖርባታል፤ የተባለችውን አዲስ አበባም ለማየት አክስታቸው ዘንድ ዘለቁ።
“…….አዲስ አበባ የመጣሁት በልጅነቴ፤ አንድ ብር ከ 90 ሳንቲም ትራንስፖርት ከፍዬ ነው። ስመጣም በጣም ደስ እያለኝ ሠርቼ ሀብታም እሆናለሁ ብዬ እየጓጓሁ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ አማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ይቻላል ስላሉኝ፤ የመጣሁት እሱንም ለመልመድ በጉጉትና በከፍተኛ ፍላጎት ነው። ከመጣሁ በኋላም ያረፍኩት በቀጥታ አክስቴ ቤት ነበር “ይላሉ ወይዘሮ ሠናይት።
ወይዘሮ ሠናይት አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ፤ ያረፉባቸው አክስታቸው የበቆሎ ዱቄት እያዘጋጁ አስፈጭተው ለገበያ የሚያቀርቡ ነበሩና እርሳቸውም የተቀላቀሉት የሥራ ዘርፍ ይኸው የዱቄት ሥራ ነበር። ነገር ግን አክስታቸው እርሳቸውን ጨምሮ የራሳቸውንም ልጆች በዚህ ሥራና በሚያገኙት ገቢ ማስተዳደር እጅጉን ከብዷቸው ነበር። እናም ሌላ የሥራ ዘርፍ መቀየር እንዳለባቸው በማሰብ ፊታቸውን ወደ እንጦጦ ጫካ አዞሩ።
እንጦጦ ጫካ እንደ ወይዘሮ ሠናይት አክስት ያሉ በርካታ እናቶች ሌሊት ተነስተው ከጀብ ጋር ተጋፍተው የሚሠሩበት ቦታ ነው። ጅብ ብቻ አይደለም፤ በጫካ ውስጥ የሚደርስባቸውን ፆታዊ ጥቃት ሁሉ ተቋቁመው ብርድ እና ፀሐይ ሳይበግራቸው፤ እንጨት ለቅመው ያንን ቁልቁለት ካዘሉት እንጨት ጋር የሚወድቁ እየመሰሉ ወርደው ዳገቱንም ወጥተው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት ነው። ለእነወይዘሮ ሠናይት ቦታው ቤታቸውን የሚደግፉበት የብዙዎች ባለውለታ ሊባል የሚችል ነው።
እናም የወይዘሮ ሠናይት አክስት የዱቄት ሽያጩ አልሆን አላዋጣ ሲላቸው በቀጥታ እንግዳዋን የእህታቸውን ልጅ ሠናይትን ይዘው ያመሩት ወደዚሁ ጫካ ነው። በጫካውም እንጨት እየለቀሙ መሸጥን መተዳደሪያቸው አደረጉት።
“……..እንግዲህ ብር ይታፈስባታል የተባለችው አዲስ አበባ እንደ ጠበኳት ባላገኛትም ባለው ሁኔታ ራሴን ማስተዳደር ነበረብኝና አክስቴን ተከትዬ እንጦጦ ጫካ ገባሁ። በዛም ሌሊት ወጥተን እንጨት እየለቀምን አስረን ተሸክመን ወደከተማ እያመጣን ሁለትና ሦስት ብር እየሸጥን መኖር ጀመርን” ይላሉ።
በእዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ግን ወይዘሮ ሠናይት ትዳር መመሥረትን አሰቡ፤ በሻማ ሥራ የሚተዳደሩት የትዳር ጓደኛቸውንም አገኙ። አሁን የባሰ ኑሮ እየከበደ የቤተሰብ ኃላፊነት እየሰፋ ወይዘሮ ሠናይትም ከቀደመው ጊዜ በይበልጥ እየተቸገሩና እየተማረሩ ቢመጡም፤ ኑሮን ማሸነፍ ግድ ነበርና ሳይታክቱ እንጨት ለቀማቸውን ገፉበት።
“…….ባለቤቴን የተዋወቅሁት አክስቴ ጋር ዱቄት እየፈጨሁ በምሸጥበት ጊዜ ነው። በወቅቱ ልጅም ስለነበርኩ መልኬም ያምር ነበር። ወድጃታለሁ አስተዳድራታለሁ ብሎ ከአክስቴ ቤት ወጥቼ ወደ ትዳር ገባሁኝ። ከተጋባን በኋላ ግን እንደቃሉ መሆን አልቻለም። በሚፈለገው ልክም ቤቱን የሚያስተዳደር ሰው አልነበረም። እኔም ቁጭ ብዬ አልራብም በማለት ከአክስቴ ጋር ጀምሬው የነበረውን የጫካ እንጨት ለቀማ ሥራ ቀጠልኩበት። በወቅቱ እሱ ሻማ እየሠራ ይሸጥ ነበር። ብቻ ትዳር ጥሩ ነው። በሚል እየተቸገርንም ቢሆን አብረን መኖር ቀጠልን።” ይላሉ።
ከትዳር በኋላ አብዛኛው ባለትዳር እንደሚያደርገው ልጅ መጣ ወይዘሮ ሠናይትም ነፍሰጡር ሆኑ። በዚህን ጊዜ ባለቤታቸው በይበልጥ ተቀየሩ ወይዘሮ ሠናይትም ያረገዙትን ልጅ ወለዱ። ይህንን ጊዜ ባለቤታቸው ውጪ ውጪ ማየት ጀመሩ። እጅ ያልሰጡት ወይዘሮ ሠናይት የወለዷት ልጃቸው ጠንከር እስከምትል ድረስ ጫካ መሄዳቸውን ተውና በቤታቸው ውስጥ ዳቦ (ሽልጦ) እየጋገሩ መሸጥ ጀመሩ።
“……..ያረገዝኩት እንደ አገባሁ ነው። አሁን የመጀመሪያ ልጄ እኩያዬ ትመስላለች። ያገባሁት ሰው ያን ያህል ቤቱን የሚወድና የሚያስተዳድር ባይሆንም፤ በሚመጣበት ጊዜ ብቻ የባልነት ተግባሩን ፈጽሞ ይሔዳል። በዚህ ሁኔታ እኔም በላይ በላይ ስምንት ልጆችን ወለድኩ። እርሱም ከተለያዩ ሴቶች ጋር ሲሄድና ልጅ ሲወልድ እንደዚህ የምታደርገው ለምንድ ነው? ስለው ይደበድበኝ ነበር። አንገቴን ደፍቼ ስምንት ያህል ልጆቼን ማሳደጌን ቀጠልኩ ” ይላሉ።
ወይዘሮ ሠናይት አራስ ሲሆኑ፤ በቤታቸው ዳቦ ጋግረው እየሸጡ ጠንከር ሲሉ ጫካ ሄደው ቅጠል ለቅመው እየሸጡ ብቻቸውን በሚባል ደረጃ ልጆቻቸውን ማሳደግን ተያያዙት። “……በወቅቱ ትምህርት በፈረቃ ስለነበር በተለይም ልጆች አደግ ካሉ በኋላ የከሰዓት ተማሪ የሆኑትን ጠዋት ጫካ አብረውኝ እንዲሄዱ በማድረግ
እንጨት ለቅመን እንመጣለን። የከሰዓት ፈረቃ ተማሪዎቹ ማታ ሲመለሱ ደግሞ በቤት ውስጥ የጋገርኩትን ዳቦ አውጥተን መንገድ ዳር አብረን እንሸጣለን። ጠዋት ያልተሸጠውን ቅጠልም ከዳቦው ጋር አብረን እያወጣን መንገድ ላይ እየከመርን እንሸጣለን” በማለት ያለፉበትን የሕይወት ውጣ ውረድ ይናገራሉ።
ወይዘሮ ሠናይት ልጆቼ አባት አላቸው እርሱም ኃላፊነቱን ይወጣ ብለው የሚቀመጡ እናት አይደሉም። ከዛ ይልቅ የባለቤታቸውን መማገጥ ችለው ቤት መጥተው የሚደበድቧቸውንም ታግሰው የልጆቻቸው እድገት የእርሳቸው ብቻ ኃላፊነት እንደሆነ አስበው ደፋ ቀና ብለው ማሳደጋቸውን ቀጠሉ።
“…ስምንቱንም ልጆቼን ያሳደግኩት ብቻዬን ነው፤ የሚገርመው እኔ ልጆቼን ሳሳድግ ይከብደኝ የነበረው ነገር ሌሊት እንጨት ለቀማ ሄጄ የለቀምኩትን ሽጬ እቤት እስክመለስ ድረስ ልጆቹን የሚጠብቅልኝ ሰው አለማግኘቴ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ሲያግዘኝ ግን ጥሩ ጎረቤቶች ስለነበሩኝ ልጆቼን እነሱ ቤት አስተኝቼ እሄዳለሁ። ስመለስ ለእነሱም በቤታቸው ምግብ የሚያበስሉበት እንጨት ለቅሜ ይዤላቸው እሄዳለው፤ ውሃ የሚቀዳው ራቅ ካለ ቦኖ ስለነበር ለጎረቤቶቼ ረጅም ርቀት ሄጄ ውሃ ቀድቼ አመጣላቸው ነበር። እንዲህ እያልኩ ልጆቼ አደጉ።” ይላሉ።
ወይዘሮ ሠናይት ልጆቻቸውን እንዲህ በማሳደጋቸው ዛሬ ላይ ደስተኛ ቢሆኑም፤ በጫካ ያሳለፏቸው አስከፊ ጊዜያትን ሲያስታውሱ በእጅጉ ያዝናሉ፤ ይንገፈገፋሉም። ግን ምን ይደረግ ልብስ እና ጫማ ባይኖር ቀን ይሰጣል። ሆድ ግን አንድ ቀን ባዶውን ቢውል ማደሩ ይከብደዋል። ስለዚህ እኔም ሆንኩ ልጆቼ በረሃብ ማለቅ የለብንም ብዬ ሁሉንም ተቋቁሜ ለዓመታት በእንጦጦ ጫካ ውስጥ እንጨት ፍለጋ ከዛም ተሸክሜ ገዢ ፍለጋ ብዙ ተንከራትቻለሁ።›› በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
“…….ጫካ ውስጥ የሚፈራው አውሬ ብቻ አይደለም። አውሬ እንደውም ምንም አያደርገንም። ግን በጣም ብዙ ባለጌ ሰዎች አሉ። ሴትነታችንን የሚጠቀሙትን ደፋሪዎች ሁሉ ማለፍ ግድ ነው። ብዙ እናቶች ልጆች ሴቶች በተደጋጋሚ ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች ይደፈራሉ፤ ያለፍላጎታቸው ያረግዛሉ። አባቱን የማያውቁትን ቢያውቁትም ዳቦ የማይገዛላቸውን ሰው ልጆች ተቸግረው ያሳድጋሉ። ይህ እንግዲህ በእንጦጦ ጫካ ውስጥ ቅጠል በመልቀም የሚኖሩ ሴቶች ሕይወት ነው”በማለት ይንገፈገፋሉ።
‹‹በተለይም እንጨት ሲለቀም የደን ጠባቂ ተብለው በቦታው የሚቀመጡት ሰዎች ባልታሰበ ሰዓት ብቅ እያሉ ቀኑን ሙሉ ለፍተን ደክመን ያከማቸነውን እንጨት እርጥብ እንጨት ቀላቅለሻል በሚል ምክንያት ይወርሷቸዋል። በዚህ ጊዜ ለልጆች ዳቦ መግዣ እንኳን ይጠፋል። የተራቡ ልጆች ፊት ዳቦ ሳይዙ መገኘት እንዴት እንደሚከብድ ማንም ቢሆን የሚያውቀው ነው።›› ይላሉ።
‹‹…ነገር ግን የእለት ጉርሳችን በጫካው ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፤ ዛሬ ተወረሰብን ነገ አንሄድም አንልም። ከደጉ ያጋጥመን በእኛ ላይ ምንም አይድረስ በሠላም ገብተን እንውጣ ብለን ሲነጋ ወደዛው ጫካ እንሄዳለን። የዕድል ቀናችን ከሆነ ካሰብነውም በላይ ትርፍ አግኝተን እንገባለን። ዕድል ከእኛ ካልነበረች ደግሞ ዳግም ሊወረስብን ወይም ደግሞ ገዢ ልናጣ እንችላለን።›› በማለት ይናገራሉ።
‹‹ከሁሉም በላይ የክረምት ጊዜ የእኛን የጫካ እንጨት ለቀማ ያከፋዋል›› የሚሉት ወይዘሮ ሠናይት፤ ‹‹አካባቢው እንኳን በክረምት በበጋም ቀዝቃዛ እንዲሁም ጉም ነው። ክረምት ሲሆን ደግሞ ይብሳል። በዛ ላይ የምንለቅመው እንጨት እርጥብ ይሆናል። ልንሸከመው ስንል በጣም ይከብዳል። እንደምንም ብለን ወደ ከተማ ካወጣነው በኋላ በጅምላ የሚገዛን ሰው ላናገኝ እንችላለን። በዚህን ጊዜ ተሸክመን መንደር ለመንደር ዞረን ለመሸጥ እንገደዳለን። ይህ ደግሞ ለተለያዩ ሕመሞች አጋልጦናል።›› ይላሉ።
ወይዘሮ ሠናይት የኑሮ ክብደት፣ ልጆችን አርግዞ መውለድ ብቻ ሳይሆን ያልተመቻቸ ሕይወት ለበርካታ ጊዜያት በሕመም ውስጥ እንዲያሳልፉ እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ። ከአንጀት መታጠፍ ጀምሮ ብዙ ችግሮች ገጥመዋቸውም ተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውንም ያብራራሉ። እነዚህ ክስተቶች ደግሞ ዛሬ ላይ ወይዘሮ ሠናይት ከእድሜ መግፋት ጋር ተደማምረው ወገባቸው በቀበቶ ግጥም ተደርጎ ታስሮ እንዲንቀሳቀሱ ምክንያት እንደሆናቸውም ያብራራሉ።
እንደወይዘሮ ሠናይት ገለፃ፤ ዛሬ ላይ መንግሥት ሴቶች በተለያየ መልክ ራሳቸውን እንዲችሉ ከወንዶች ጥገኝነት እንዲወጡ ብዙ ይሠራል። የተጠቀሙም ብዙዎች ናቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕጻናት ተማሪዎች ለደንብ ልብስ ለደብተር ለሆድ ሳይጨነቁ ትምህርታቸውን እንዲማሩ አድርጓል። ያን ጊዜ በተለይም ልጆቻቸው ተማሪ ሆነው ይህ አልነበረም፤ መማር ከፈለጉ ቀን ሥራ መሥራት ድንጋይ መሸከም መላላክ ነበረባቸው። ምክንያቱም እርሳቸው ደብተር ገዝተው ዩኒፎርም አሟልተው ሆዳቸውንም ሞልተው ትምህርት ቤት መላክ አይችሉም ነበር።
‹‹የእኔ ልጆች ያለፉት በዚህ ሕይወት ውስጥ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ በትምህርታቸው እንዳይገፉ ከዛ ይልቅ ሌሎች የሕይወት መንገዶችን በተለይም ከእኔ ጥገኝነት ወጥተው በልተው የሚያድሩባቸውን መንገዶች መፈለግን ጀመሩ።›› በማለት ይናጋራሉ።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ያሳደጓቸው ልጆች፤ ምንም እንኳን ከኑሯቸው ተርፏቸው እናታቸውን ቁጭ አድርገው መጦር ደረጃ ላይ ባይደርሱም ሁሉም ለኑሯቸው የሚበቃ ሥራን እየሠሩ ቤተሰብ መሥርተው እየኖሩ እንዳሉ ያስረዳሉ።
“…እግዚአብሔር ይመስገን፤ ልጆቼን ለፍቼ ማሳደጌ ዛሬ ላይ በተመቻቸ ሁኔታም ባይሆን ያገኙትን እያካፈሉኝ ቢያንስ እንጨት ሳልሸከም እንድኖር አድርገውኛል። በዓለም ሲመጣ ያላቸውን ይሰጡኛል፤ አሁን ከእኔ ጋር ያለው የመጨረሻው ልጄ ብቻ ነው” ይላሉ።
ወይዘሮ ሠናይት ለዓመታት እንጨት የለቀሙበት እንጦጦ ጫካ ዛሬ ላይ ሊክሳቸው ያሰበ ይመስላል። የዘመናት ድካማቸውን አረፍ አድርጎ በስተርጅና የሚጦሩበትን ነገር እነሆም ብሏል። ዛሬ ወይዘሮ ሠናይትና መሰሎቻቸው ከዓመታት ድካም በኋላ እንደ ዜጋ የአቅማቸውን ሠርተው ጤናቸውና ሥራ ሰዓታቸው ተጠብቆ በሰርቪስ ደርሰው ተመልሰው የሚሠሩት ሥራ በአቅራቢያቸው ተተክሎላቸዋል። በቅርቡ የተመረቀው ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት ለእነዚህ እናቶች በረከትን ይዞ የመጣ ይመስላል። በፕሮጀክቱ ውስጥ ከ551 በላይ የሚሆኑ እናቶችን እንጀራ በመጋገርና መሸጥ ሥራ ላይ አሰማርቶ ሊያግዛቸውም ዝግጅቱን አጠናቆ ተመርቆ ወደ ሥራ ከገባ ሳምንታትን አስቆጥሯል።
“……. እኔ የወለድኩት ቀላል አይደለም፤ እነሱን ለማሳደግ የለፋሁትንም የማውቀው እኔው ብቻ ነኝ። በተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና እድርጌያለሁ፤ ያ ግን ለመውለድ አይደለም ባለብኝ የሥራ ጫና ምክንያት አንጀቴ በተደጋጋሚ እየታጠፈ ስለነበር ነው። አሁን ላይ ይህ ሁሉ ነገር አቅሜን አሟጦታል። እናም ጫካ ወጥቼ እንጨት መልቀም የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሼ ነበር። ልጆቼ ያገኟትን ከቤተሰባቸውና ከልጆቻቸው እየቀነሱ ቢያካፍሉኝም፣ አነስተኛ የቀበሌ ቤት ቢኖረኝም ውሃ መብራት እድር የሚባሉትን ነገሮች ግን የምሸፍንበት እቸገራለሁ፤ እነዚህን ወጪዎቼን ለመሸፈን ያግዘኛል ያልኩትን ጥጥ እየፈተልኩ እየሸጥኩ ቀዳዳውን ለመሙላት እሞክር ነበር ” ይላሉ ።
“……..ከንቲባችን በእንጦጦ ጫካ ውስጥ የእለት ጉርሳችንን ለማግኘት እንባዝን የነበርንን ሴቶች ራስ ለማስቻል በሚል ይህንን የመሰለ ፕሮጀክት ነድፈው ወደሥራ አስገብተውልናል። ዛሬ ላይ ከሥራው ባሻገር የምንውልበት ቦታ በራሱ ጤና የሚሰጥ ነው። እኔና መሰሎቼ እንጀራ እንጋግራለን እንሸጣለን በዛም የምናገኘውን ገቢም ተካፍለን ኑሯችንን እንደጉማለን ብለን እየሠራን ነው” የወይዘሮ ሠናይት ተስፋ ነው።
ወይዘሮ ሠናይትና አብረዋቸው የሚሠሩት ከአራት መቶ ያላነሱ እንጨት ተሸካሚ ሴቶች የብርሃን ምልክትን አይተዋል። አሁን እንጨት ለቀማ ጫካ መሄድ እዛም ከሰውና ከአውሬ ጋር የሚያደርጉትን የሞት ሽረት ግብግብ ትተዋል። ከቤታቸው ሰብስቦ በሚያመጣቸው ሰርቪስ ሥራቸው ላይ ይገኛሉ፤ ሊጥ ማቡካት፣አብሲት መጣል፤ ሊጥ ቀድቶ ለጋጋሪዎች ማቀበል እንዲሁም እንጀራ መጋገር በሚል የሥራ ዝርዝራቸው ወጥቷል፤ በዚህ መሠረትም የግማሽ ቀን የሥራ ጊዜያቸውን አሳልፈው ወደ ቤተሰባቸው ወደ ልጆቻቸው በሰርቪሳቸው ይመለሳሉ።
“……..እኔ ዛሬ ላይ ቆሜ ስሄድ ጤነኛ እመስላለሁ። ግን የምንቀሳቀሰው ወገቤን በቀበቶ ደግፌ ነው። ይህም ቢሆን ዛሬ ላይ ያለሁበትን ነገር ሳስበው በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን በክብር ሥራ ውዬ እየገባሁ ነው። ወደፊት ሥራው አድጎና ተጠናክሮ ሲሄድ ደግሞ ሕይወቴ በብዙ መልኩ እንደሚለወጥ እርግጠኛ ነኝ።” ይላሉ።
አሁን ላይ ወይዘሮ ሠናይት በእድሜያቸው እንዲሁም በጤና ሁኔታቸው ምክንያት እንደ ሌሎቹ ተሯሩጠው ማቡካት መጋገር ባይችሉም ልምዳቸውን ተጠቅመው ግን ስለ ቡኮው አብሲቱ እንዲሁም ስለሚጋገረው እንጀራ ጥራት እየተዘዋወሩ ይቆጣጠሩ ዘንድ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ይህንን የሥራ ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ ሲወጡም ተመልክተናል።
“……..አሁን ያየነው እና የጀመርነው ሥራ ገና ጅምር ነው። ገንዘብ ወደማግኘት አልገባንም ግን የምናየው ነገር በራሱ ሳይበሉ የሚያጠግብ ሆኖብናል። ወደሥራ ብዬ ስመጣ እንዴት እንደምደሰት የማውቀው እኔ ነኝ” ይላሉ።
ወይዘሮ ሠናይት አብረዋቸው ለሚሠሩት እንጨት ተሸካሚዎች “……ምናልባት ዛሬ ላይ የምናገኘው ነገር ላይኖር ቢኖርም በቂ ላይሆን ይችላል፤ በዚህም ቤታችን ኑሯችን ጎሎም ይሆናል። ነገር ግን ጫካ ከአውሬ ጋር ተጋፍተን ሴትነታችንን አደጋ ውስጥ ከተን እንኖር ከነበረው ኑሮ ጋር ፍጹም አይገናኝም። በመሆኑ ሁሉም ሠራተኞች ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን አርቆ ማየት አለባቸው። ዛሬ ብንቸገር ነገ እንለወጣለን ብለን ማሰብ ይገባናል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም