በአፍሪካ ጨዋታዎች የደመቀው የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ ሀገሩ ይገባል

ከትናንት በስቲያ በተጠናቀቀው የአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ምሽት ወደ ሀገሩ ይገባል፡፡ በጋና አክራ ሲካሄድ በቆየው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያ ልዑካን በኦሊምፒክ ከፍተኛ ተሳትፎ ባላት የቦክስና የብስክሌት እንዲሁም ውጤታማ በሆነችበት የአትሌቲክስ ስፖርት በርካታ ሜዳሊያዎች መመዝገባቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ውድድር በመካፈል የሀገሩን ስምና ባንዲራ በአህጉር አቀፉ የውድድር መድረክ ያውለበለበው ልዑክ ምሽት 2ሰዓት ከ30 ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳል፡፡ ቡድኑ ደማቅ አቀባበል የሚደረግለት መሆኑን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አስታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በ9 የስፖርት ዓይነቶች በዚህ ውድድር ላይ የተካፈለው የኢትዮጵያ ቡድን ቀዝቃዛ አጀማመር ቢያደርግም ፍጻሜው ግን ያማረ ሊሆን ችሏል፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት በርካታ ሜዳሊያዎች ከመመዝገባቸው ባለፈ በታሪክ የመጀመሪያ የሆኑ ድሎችም በተለያዩ ስፖርቶች ተመዝግበዋል፡፡ በአንጻሩ ከተሳትፎ ባለፈ ተፎካካሪ ሊሆኑ ያልቻሉ በርካታ ስፖርቶችም ታይተዋል፡፡ ይህ ውድድር በኦሊምፒክ መርህ መሰረት የሚደረግ መሆኑን ተከትሎ በአንዳንድ ስፖርቶች እንደ ማጣሪያ ሆኖም ያገለግላል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ልዑክ በተለይ በ5ቱ የኦሊምፒክ ስፖርቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ በብስክሌት፣ ቦክስ እና ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርቶች ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ወደ ውድድሩ ያቀና ሲሆን ውጤታማ የሆነው በሶስቱ ብቻ ነው፡፡

የመጀመሪያው ሜዳሊያ የተመዘገበው በብስክሌት ሲሆን፤ በምሥራቅ አፍሪካ ከኤርትራ ቀጥሎ በአንጻራዊነት የተሻለ የሚባለው የኢትዮጵያ ቡድን በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ ነበር፡፡ በዚህም ከ23 ዓመት በታች የወንዶች የግል ውድድር ብስክሌት ጋላቢው ኪያ ሮጎራ ብቸኛውን የብር ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡ በአንድ ሜዳሊያ ብቻ ረጅም ቀናትን የቆየው የኢትዮጵያ ቡድን የአፍሪካ ጨዋታ ሊጠናቀቅ አምስት ቀናት ብቻ ሲቀሩት በተጀመረው የአትሌቲክስ ውድድር ተከታትለው በተመዘገቡት ሜዳሊያዎች በደረጃ ሰንጠረዡ ለውጥ ሊያመጣ ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ባልተለመደ ሁኔታ ከረጅም ርቀት ባለፈ በአጭር ርቀት እንዲሁም በሜዳ ተግባራት የተሳተፈ ይሁን እንጂ፤ ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ርቀቶች ውጪ ሜዳሊያ የተገኘው በምርኩዝ ዝላይ ሶስተኛ ደረጃን የያዘው አትሌት አበራ ዓለሙ ብቻ ነው፡፡

በ47 ወንድ እና 40ሴቶች በጥቅሉ 87 አትሌቶች በውድድሩ ላይ የተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከፍተኛውን የሜዳሊያ ቁጥር በማስመዝገብ አሁንም የሀገር ኩራት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ 47 ውድድሮች በሚካሄዱበት አትሌቲክስ 50 የአፍሪካ ሀገራት ከ640 በላይ የሚሆኑ አትሌቶቻቸውን ያፎካከሩ ሲሆን፤ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን መቀላቀል የቻሉት ደግሞ 27ቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ቡድን ናይጄሪያን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡ ቡድኑ 7 የወርቅ፣ 7 የብር እና 4የነሃስ በድምሩ 18ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ጎረቤት ሀገር ኬንያን በከፍተኛ ብልጫ ማስከተልም ችሏል፡፡

ሌላኛው ውጤት የተመዘገበው ስፖርት ኢትዮጵያ ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎች ላይ በርካታ ተሳትፎ ባላት የቦክስ ስፖርት ነው፡፡ በጥቂት ሜዳሊያዎች ብቻ ተገድባ የቆየችው ኢትዮጵያ በጋና አክራ በተደረገው የአፍሪካ ጨዋታዎች ግን ስኬታማነቷን አስመስክራለች፡፡ 7 ቦክሰኞችን ያሰለፈው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን 3 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ስኬታማ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየበት በሚገኘው የቦክስ ስፖርት የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ መግባት ከቻሉ 22 ሀገራት መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች፡፡ በሴቶች የቦክስ ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ሁለት የቡጢ ተፋላሚዎች ደግሞ ታሪኩን መጋራት ችለዋል፡፡

በ52 ኪሎ ግራም ቤተልሄም ገዛኸኝ የሞሮኮ ተጋጣሚዋን በማሸነፍ ቀዳሚዋ ስትሆን፤ በ66ኪሎ ግራም ቤተል ወልዱ ደግሞ ቀጣዩን ድል ለሀገሯ አስገኝታለች፡፡ በወንዶች 75 ኪሎ ግራም የተሳተፈው ተመስገን ምትኩም የነሐስ ሜዳሊያውን ማጥለቅ ችሏል፡፡ በዚህም ከረጅም ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ውጤታማነቷን ልታረጋግጥ ችላለች፡፡ ይኸውም ከጥቂት ወራት በኋላ በፓሪስ ለሚካሄደው ኦሊምፒክ ከተሳትፎ ባለፈ ውጤት ሊመዘገብ ይችላል የሚል ተስፋን የሚያጭር ሆኗል፡፡

በጥቅሉ ኢትዮጵያ በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ 9 የወርቅ፣ 8የብር እና 5 የነሐስ በድምሩ 22 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ውድድሯን ደምድማለ

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You