ሩሲያ ብሔራዊ የኀዘን ቀን አወጀች

ሩሲያ ብሔራዊ የኀዘን ቀን አወጀች።
ሩሲያ ከሞስኮ በቅርብ ርቀት ላይ በተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ላይ በተቃጣው ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ለማስብ ብሔራዊ የኅዘን ቀን በማወጅ ሰንደቅ ዓላማዋን ዝቅ አድርጋ እያውለበለበች ነው።
ይህ ጥቃት ከሁለት አስርተ ዓመታት ወዲህ በሩሲያ ውስጥ የተከሰተ እጅግ ከባዱ ነው ተብሏል።
አራት ሕጻናትን ጨምሮ 133 ሰዎች እንዲገደሉ እና ለ150 ሰዎች እንዲቆስሉ ምክንያት ከሆነው ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያሉትን እንደሚያድኑ እና እንደሚቀጡ የዛቱት ፕሬዚዳንት ፑቲን የኀዘን ቀን አውጀዋል።
ፑቲን ጥቃቱን አስመልክተው በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው “ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መጽናናትን ከልቤ እመኛለሁ” ብለዋል።
“መላ ሀገሪቱ እና መላው ሕዝብ ከእናንተ ጋር እያዘነ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል ፑቲን።
ለጥቃቱ እስላሚክ ስቴት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቢገልጽም፣ ፑቲን ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ነበር ካሏቸው አጥቂዎች ጋር ግንኙነት ያለውን ታጣቂ ቡድን ስም በይፋ አልጠቀሱም።
ፑቲን በዩክሬን በኩል መንገድ ከፍተው አጥቂዎቹን ለማስወጣት የሞከሩ ነበሩ ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን “ዓለም አቀፍ ሽብር” ሲሉ በጠሩት በዚህ ጥቃት ዩክሬን ተሳትፎ የለኝም ስትል አስተባብላለች።
ሰዎች ባለፈው ዓርብ እለት አራት ታጣቂዎች ገብተው ግድያ በፈጸሙበት 6200 መቀመጫ ባለው የክሮከስ ሲቲ አዳራሽ የአበባ ጉንጉን እያስቀመጡ ናቸው ሲል የዘገበው አልዓይን ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You