
በአዲስ አበባ ከተማ ከቀናት በፊት በትምህርት ቤቶች፣ በክፍለ ከተሞችና በተለያዩ አደረጃጀቶች «በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል 13ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነበር። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት የፀደቀበትን ቀን ተከትሎ ህዳር 29 ቀን በየዓመቱ በሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለነበራቸው ሚና እና ስለበዓሉ ያላቸውን ስሜት ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በበዓሉ አስፈላጊነት ላይ ቢስማሙም ዓላማውን የሳተ ነው ይላሉ።
«በዓሉ ህዝቦች ይተዋወቁ የሚል መንፈስ ስላለው መከበሩን የምኮንነው አይደለም። አያያዙ ላይ ነው ችግሩ። በዓሉን የሚያከብሩት ኢህአዴግና አጋሮቹ ናቸው።» በማለት ሀሳባቸውን ያካፈሉን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በዓሉ የህዝብ መቀራረብ ፈጥሯል። ወይም ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን አጠናክሯል፤ የሚል እምነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ፡፡
በዓሉ ላለፉት 12 ዓመታት ሲከበር አንድነትንና መፈቃቀርን ፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ባለፉት ጊዜያቶች የተስተዋሉትና አሁን ድረስ የቀጠለው ህዝቦች ከቀያቸው መፈናቀል፣ የእርስ በርስ የከፋ ግጭትና ግድያ ባልተከሰተ ነበር የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ የበዓሉ ታዳሚ ወደየአካባቢው ሲመለስ አብሮት የኖረውን ሰው የሚያፈናቅልና እስከ ሞት የሚያስከትል ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ የበዓሉ ፋይዳ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባና ዓላማውንም እንደሳተ ያስረዳሉ፡፡
በ13ኛው በዓል ላይም አዲስ ነገር እንደማይጠብቁ የሚገልጹት ፕሮፌሰር በየነ የዘንድሮው በዓል ምሁራን ከወቅታዊ የሀገሪቷ ሁኔታ ጋር ያገናዘበ በጥናት ላይ መሰረት ያደረገ ሀሳብ የሚያቀርቡበት መድረክ ተዘጋጅቶ በየአካባቢው ህብረተሰቡን በማሳተፍ ውይይትና ክርክር ቢካሄድ እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲያቸው ባለፉት በዓላት ስለነበረው ተሳትፎም እንደተናገሩት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረበት ወቅት ጥሪ ይደረግለት ነበር። ከምክር ቤት ከወጣ ወዲህ ግን ተጋብዘው እንደማያውቁና ስለበዓሉ አከባበር በመገናኛ ብዙኃን ከመስማት ያለፈ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው፤ መገናኛ ብዙኃንም በዓሉን ሲዘግቡ አሰማምረው ማቅረባቸው ክፍተቱ እንዲሸፈን እንዳደረገ ይናገራሉ፡፡
የፕሮፌሰር በየነን ሀሳብ የሚጋሩት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና የበዓሉን አስፈላጊነት ቢያምኑም በዓሉ በማስመሰልና በድግስ የታጀበ ከመሆን ባለፈ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በማቀራረብ አዎንታዊ ሚና አልነበረውም ይላሉ። በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ እየተደረገና ብዙ ሰዎችንም የሚያሳትፍ ቢሆንም በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን በተቃራኒው እንደሆነና በህዝቦች መካከል ቅራኔና ጥላቻ ያተረፈ በዓል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ዶክተር መረራ እንዳሉት ፓርቲያቸው ባገኘው መድረክ ሁሉ በሀገሪቷ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ሀሳብ ቢሰጥም ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም በበዓሉ ላይ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎ አልነበረውም። በዓሉ ከማስመሰል ወጥቶ በህዝቦች መካከል እውነተኛ አንድነት እንዲፈጠር የመቻቻልና በእኩልነት የሚያስተናግድ የፖለቲካ ሥርዓት መፈጠር አለበት። በትክክል በህዝብ አንድነት ላይ ከተሠራ በዓሉ መከበሩ ችግር አይኖረውም።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ(ኢዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው ፓርቲያቸው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል አስፈላጊነት ላይ ግምገማ ባያካሂድም ለበዓሉ እየተጋበዘ እንደማንኛውም ተሳታፊ ከመካፈል ባለፈ በውይይትም ሆነ በተለያየ መንገድ ሀሳብ በማቅረብ ይህ ነው የሚባል ሚና እንዳልነበራቸው ተናግረዋል። በዓሉ ፖለቲካዊ ይዘት እንደነበረው የሚገልጹት ዶክተር ጫኔ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነታችን አልታወቀም የሚል ጥያቄ እንዳያነሱ ኩርፊያን ለመቀነስ መጠቀሚያነት እንዳገለገለ ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ጫኔ ማብራሪያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ባሳተፈ መልኩ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እኩልነት የሚያረጋግጥ ሥራ ቢሠራና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የፈለጉትን መሪ የመምረጥና የመሻር መብት ቢኖራቸው ውጤታማ መሆን ይቻል ነበር። ህገመንግሥቱ እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል። ለበዓሉ ዝግጅት የሚወጣው ገንዘብ ለማህበራዊ አገልግሎት ቢውል ህዝቡ የበለጠ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ለምለም መንግሥቱ