በዘር ማጥፋት የተጠረጠረው ትውልደ ሩዋንዳዊ በአሜሪካ በቁጥጥር ሥር ዋለ

 

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1994 ላይ በሩዋንዳ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተሳትፏል የተባለ የሩዋንዳ ተወላጅ በአሜሪካዋ ኦሃዮ ግዛት በቁጥጥር ሥር ዋለ።

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ፣ ኤሪክ ታባሮ ሺሚዬ የተባለውን ግለሰብ ሰዎች እንዲገደሉ ማድረግን ጨምሮ በጅምላ ግድያ የነበረውን ተሳትፎ በመደበቅ ከሶታል።

ሺሚዬ በአሜሪካ በሐሰት ስደተኛ ሆኖ እንዲቆይ ፈቃድ በማግኘቱ ከአውሮፓውያኑ 1995 ጀምሮ በኦሃዮ ኑሮውን ማድረጉን ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ግለሰቡ ቀደም ብሎም በዘር ማጥፋት መሳተፉን አስተባብሏል።

ቦስተን በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

የሀገር ውስጥ የወንጀል ምርመራ ልዩ ወኪል ማይክል ክሮል በመግለጫቸው እንዳሉት ሺሚዬ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አሳዛኝ ክስተት ከሆኑት መካከል አንዱ በሆነው የዘር ጭፍጨፋ ያለውን ተሳትፎ ለመሸፈን በመዋሸቱ ነው የተከሰሰው።

ሺሚዬ በ2019 የዘር ጭፍጨፋ በመፈፀም ጥፋተኛ በተባለው ጂን ሊዮናርድ ቴጋንያ የፍርድ ሒደት ላይ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

የፍርድ ቤቱ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ከሆነ ሺሚዬ ቱትሲዎች ምስማር ባለው እንጨት ጭንቅላታቸውን በመምታትና በስለት በመግደል በግሉ ተሳትፏል።

ሺሚዬ ሩዋንዳን ለቆ የወጣው በ1994 አጋማሽ ላይ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ወደ አሜሪካ ለመግባት የሀገሪቷን የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ዋሽቷል ተብሎ ወደተከሰሰበት ኬንያ ተጉዟል።

በዚህም በማጭበርበር፣ መረጃዎችን በመደበቅ እና በመሸፋፈን፣ ፍትሕን በማደናቀፍ እና በዳኞች ፊት በሐሰት ምስክርነት በመስጠት ክስ ቀርቦበታል።

የሺሚዬ ተከላካይ ጠበቃ ዴቪድ ጆንሰን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለመጠየቅ ቢቢሲ ስልክ ቢደውልላቸውም ምላሽ አልሰጡም።

እንደ አውሮፓውያኑ 1994 በሩዋንዳ በተፈፀመው የዘር ጭፍጨፋ በ100 ቀናት ውስጥ በሁቲ ጽንፈኞች በተፈፀመው ግድያ ወደ 800 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።

የዘር ጭፍጨፋው በቁጥር አነስተኛ የሆኑትን የቱትሲ ማኅበረሰቦችን እንዲሁም የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን እና በአጋጣሚ የተገኙ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ነበር።

በተያያዘ ከአስርታት ዓመት በፊት ሩዋንዳ ውስጥ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት በገንዘብ ደግፏል ተብሎ የተከሰሰው የ88 ዓመቱ አዛውንት በጤና ችግር ምክንያት ፍርድ ቤት ለመቆም ብቁ አይደለም ሲል የተባበሩት መንግሥታት ፍርድ ቤት ከወራት በፊት መወሰኑ የሚታወስ ነው።

የተከሳሹ ግለሰብ ፊሊሺዬን ካቡጋ ጠበቃ ከዕድሜ መግፋት ጋር በሚያጋጥም የአዕምሮ ችግር እንዳለበት በመግለጽ ፍርድ ቤት አቤቱታውን አቅርቦ ነበር።

ግለሰቡ የዘር ማጥፋቱ ከተፈጸመ በኋላ ለ26 ዓመታት ተሰውሮ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ከሦስት ዓመት በፊት ነበር ፓሪስ ውስጥ የተያዘው።

ካቡጋ 800 ሺህ የሚሆኑ ቱትሲዎችን እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን ጨፍጭፈዋል የሚባሉትን የሁቱ ጎሳ ሚሊሻዎችን በገንዘብ ደግፏል ተብሎ ቢከሰስም፣ እሱ ግን ክሱን አስተብብሏል።

በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ለአስርተ ዓመታት በተደረገው ጥረት ውስጥ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ችሎቱ የፊሊሺዬን ካቡጋ የጤና ሁኔታ እንዲመረመር ዕድል ለመስጠት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ሂደቱ እንዲቆም ማዘዙ ይታወሳል።

የፍርድ ቤቱ ሰነዶች እንደሚያሳዩት የተከሳሹ 88 ዓመት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን በትክክለኛው ዕድሜው ላይ አንዳንድ አለመግባባቶች አሉ።

ፊሊሺዬን ካቡጋ በአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ በሻይ እርሻ ልማት ላይ ተሰማርቶ ከፍተኛ ሃብትን ያገኘ ሲሆን፣ በዘር ማጥፋቱ ወቅት ለሁቱ ገዳይ ቡድኖች አባላት ገጀራ ለመግዛት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ተብሎ ተከሷል።

የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ይነዛ የነበረው አርቲኤልኤም (RTLM) ራዲዮ ጣቢያ ባለቤትም ነበር።

ፈሊሴ ካቡጋ በዘር ማጥፋት ወንጀል ከሚፈለጉት ሰዎች ቁጥር አንዱ ብቻም ሳይሆን አየሁት ለሚል 5 ሚሊዮን የሚያሸልም ውድ ወንጀለኛ ነበር።

በተጨማሪም ይህ ሃብታም ነጋዴ በነበረው የሬዲዮ ጣቢያ አማካይነት ሁቱዎች ቱትሲዎችን እንዲገድሉ የሚያነሳሱ ጥቃት አባባሽ የጥላቻ ንግግሮችን በማሰራጨት የዘር ማጥፋቱን አበረታቷል ተብሎ ተከሷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You