ማንም በዓይነ ህሊናው ዓመታትን ወደኋላ ቢቃኝ በዘመኑ የነበራቸውን ድንቅ ውበት መገመት ይቻለዋል።ዛሬም ከዕድሜ ማምሻቸው ቆመው ይህ አይፈዜ ውበት ከእሳቸው ጋር ነው። ከዚህ ማንነት ጀርባ ደግሞ መልካም አንደበትና በግልጽ የሚስተዋል ብርታት መገለጫቸው ሆኗል።
ዛሬ ዕድሜ ከሕመም ተባብረው ቢፈትኗቸውም ሴትየዋ የዋዛ አይደሉም። ንግግራቸው በምክንያት፣ ጨዋታቸው፣ በለዛ ነው።ሁሌም ላመኑበት ጉዳይ በቀላሉ እጅ አይሰጡም።ስሜታቸው አይሸሽግም።ግልጽነታቸው፣ ቁጣ ሳቃቸው ከፊታቸው ይነበባል።
አሁን ትናንትን በነበሩበት ሕይወት ላይ አልቆሙም። ‹‹ነበር›› ይሉት ታሪክ ዘመናትን ደራርቦ ከኋላቸው ቀርቷል። ዛሬም ግን ለሚወዱት ሙያና ለእናት ሀገራቸው የሚሰጡት ክብር በእጅጉ ከፍ ያለ ነው። በእነዚህ እውነታዎች ውስጥ ደግሞ ብዙ ሀቆች አሉ። በእነዚህ ሀቆች ውስጥ ጥንካሬና ብርታት፣ ደስታና ሀዘን፣ መውደቅና መነሳት ደምቀው ተስለዋል።
ከሲስተር የትናየት በቀለ ጋር የነበረኝ ቆይታ በልዩ፣ መደመም የተሞላ ነበር። በውስጠታቸው ካየሁት ብርታት ባሻገር ከአንደበታቸው የሰማሁት እውነት በእጅጉ አስገርሞኛል። ድንቅ የሀገር ታሪክና አይረሴ ትዝታዎችን ተረኩልኝ።ውቧን ወይዘሮ አለማድነቅ አልቻልኩም። ለስንብት በክብር እጄን እስክዘረጋ በአድናቆት አብሬያቸው ልዘልቅ ግድ አለኝ።
1930 ዓ.ም በኬንያ ሰማይ ስር …
ወቅቱ ወራሪው የኢጣሊያ ጦር ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ክፉ ዘመን ነው። የዛኔ ሀገራቸውን ከጠላት የሚታደጉ ጀግኖች በዱር በገደሉ፣ በጫካ በዱሩ በቆራጥነት ይዋደቁ ነበር።‹‹እምቢኝ›› ባይነታቸው፣ ነፃነታቸውን እስኪያነጋ መከራን የከፈሉ፣ የሞት ጽዋን የተጎነጩ፣ ሙሉ አካላቸውን አጥተው ሀብት ንብረታቸውን የበተኑ ዕልፍ ናቸው።
1930 ዓ.ም የኢጣሊያ ጦር በማን አለብኝነት ኢትዮጵያን ይዞ ግዛቱን ሊያሰፋ፣ የሚሮጥበት ወሳኝ ጊዜ።ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ተጋድሎ ትግሉ ተፋፍሞ ቀጥሏል። እነዚህን የጭንቅ ጊዚያት ለመሸሸ አጋጣሚውን ያገኙ ጥቂቶች ሀገር ጥለው ተሰደዋል።ባህር ቆርጠው፣ ወንዝ ተሻግረው ርቀዋል።
አቶ በቀለና ቤተሰቦቻቸው ቤት ንብረታቸውን ትተው የኬንያ ምድርን በስደት ይኖሩባት ከያዙ ጊዚያት አስቆጥረዋል።የሰው ሀገር ሕይወት እንደራስ አይሆንም።ትዝታው፣ ናፍቆቱ ይፈትናል።ሀገር፣ ወገን በጦርነት ሲያዝ፣ በጠላት ሲወጋ ደግሞ ሕመሙ ከባድ ነው።
በሰው ሀገር ደርሶ ሆድ ይብሳል፣ ሳቅ ፈገግታ ብርቅ ነው።ደስታና ፌሽታ ሩቅ ነው።ሁሌም ልብ ካለበት ኮብልሎ ይሄዳል፣ ዓይን ዕንባን ይሞላል።የሀገር ምድር ችግር ፣ የወገን እልቂት ጥቃቱ ያስቆጫል፣ ደም ያስነባል፣ ይህ እውነት ለመላው ቤተሰብ አይሽሬ ቁስል ከሆነ ውሎ አድሯል።
ከቀናት በአንዱ በኬንያ ሰማይ ስር እንዲህ ሆነ።ሐምሌ 30 ቀን 1930 ዓም። ነፍሰ ጡሯ የአባወራው ሚስት በድንገቴ ምጥ ተያዙ።አሁን ሌላ የሰው ሀገር ሰው ሊታከል ነው።ደቂቃ ሰዓታት ተቆጠሩ።ምጥ በረታ።ወዳጅ ዘመድ ጭንቅ ገባ። ጥቂት ቆይቶ ፣ ሃሳብ በዕልልታ ተተካ። ይህችን ዓለም በለቅሶ የተቀበለች አንዲት ቆንጅዬ ጨቅላ የአቶ በቀለን ቤተሰብ በእንግድነት ተቀላቀለች።
የአዲሷ ልጅ መወለድ በቤተሰቡ ዘንድ ታላቅ ደስታ አሰፈነ። ዘመኑ ለኢትዮጵያውያን የጦርነትና፣ የመከራ ጊዜ ነው።በዚህ መሀል የመጣው የምስራች ስጋት፣ ሀዘኑን አሽንፎ እፎይታን አላብሷል። በሰው ሀገር ለዛውም በስደት ለተወለደችው ድንቅዬ ስጦታ ወላጆቿ ስም መረጡ፣ አማረጡ።
ከስያሜዎቹ መሀል አንደኛው ሚዛን ደፍቶ አሸነፈ። ሀገር ምድሯን ርቃ በባዕዳን መሀል የተወለደችው ብላቴና ‹‹የትናየት›› ተብላ ተሰየመች። ትንሸዋ የትናየት በኬንያዋ ‹‹ታቤታ›› ምድር ‹‹ዳዴ›› ብላ ልጅነቷን ጀመረች። ወላጆቿ በስስት እያዩ እስከ ሶስት ዓመት አሳደጓት። ከሶስት ዓመታት በኋላ ወራሪው የኢጣልያ ጦር ከኢትዮጵያ ምድር በሽንፈት ተዋርዶ መባረሩ ተሰማ።ይህ በመላው ዓለም የተዳረሰ አኩሪ ዜና ለጥቁር አፍሪካውያን ኃያል ብርታት ሆነ።ኬንያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትን ለነፃነት ትግል አነሳሳ።
የየትናየት ቤተሰቦች ከድል ማግሥት ሀገራቸውን ናፈቁ።ጊዜ አልፈጁም። በስደት የቆዩባትን ኬንያን ተሰናብተው ወደ እናት ምድራቸው አመሩ።ሕይወት በአዲስ መልክ ተጀመረ። ‹‹ጨርቄን፣ ማቄን›› ሳይሉ የሀገራቸውን ምድር ረገጡ። በወቅቱ የየትናየት አያት ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ብቻቸውን አልሆነም።ስደተኛውን የመድኃኔዓለም ታቦት አስከትለው ነበር።
አዲስ አበባ ሲደርሱ ስድስት ኪሎ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት አካባቢ ከሚገኝ ቦታ ታቦቱን በክብር አስቀመጡ።ቦታው የንጉሳውያን ቤተሰቦች ርስት የነበረ ሰፊ ሜዳ ነው።ውሎ አድሮ በዚሁ ስፍራ ቤተክርስቲያን ታነጸ ። ‹‹ምስካየ ኅዙናን ›› መድኃኔዓለም የሚል ስያሜ ተችሮትም ምዕምናንን አሰባሰበ።ዛሬም ድረስ ያንን ክፉ ዘመን የሚዘክረው የስደተኛው መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በክብር እንደቆመ ይገኛል።
ሕይወት ከድል ማግስት …
የየትናየት ወላጆች ከድል ማግስት በአዲስ አበባ ኑሮን ቀጥለዋል።አባት ለዘመኑ ሥልጣን ቅርብ ነበሩና በሹመት ወደ ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ሊሄዱ ተዘጋጁ።ቀሪው ቤተሰብ በቤት መቆየት ነበረበት። የአባወራው ባለቤት ከእናታቸው ጋር አዲስ አበባ እንዲቀመጡ ሆነ።የትናየት ከአባቷ መነጠል አልፈለገችም። እሳቸውን ተከትላ ሐረር ለመሄድ ጓዟን ሸከፈች።
የትናየት ለአባቷ የተለየ ፍቅርና አክብሮት አላት።በየደረሱበት አብራቸው ብትሄድ፣ ኑሯቸውን ብትጋራ ትወዳለች።በወቅቱም ይህ ውሳኔ ከእሷ ነበር።ሐረርጌ አባቷን ተከትላ ሃሳቧን መፈጸም።አባትና ልጅ ከልብ ይዋደዳሉ። እሳቸው ሥራ ውለው ሲገቡ ዓይኗን ማየት ይናፍቃሉ፣ በሰስት እያስተዋሉ ራሷን ይዳስሷታል።ይህ የዘወትር ልምዳቸው ነው።
ሐረርና የትናየት ዓመታትን በአብሮነት አሳለፉ። በከተማዋ የልጅነት ዓለሟን ቀጨች። የወጣትነት ዕድሜዋ አብቦ እስኪታይ ሕይወቷን በነፃነት ተራመደች።አባት በተሻለ ሹመት ዳግም አዲስ አበባ እስኪመለሱ ከጎናቸው አልራቀችም።የሐረርን ብርቱካን ከአባቷ ጣፋጭ ፍቅር ጋር እያጣጣመች አብራቸው ዘለቀች።
አባት አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የአፄ ኃይለሥላሴ ዓይን አረፈባቸው። ንጉሡ። ለምክርና ለአስፈላጊ ሥራዎች ሁሉ ከጎናቸው ቢሆኑ ምርጫቸው ነው።ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ከቤታቸው እያራቀ ጊዚያቸውን መሻማቱ አልቀረም። ይህ ዘመን ለሴቶች ቀርቶ ለበርካታ ወንዶች ጭምር ትምህርት ብርቅ የሆነበት ጊዜ ነበር።
የትናየት ግን ሴትነቷ አላሸነፍትም። በዘመኑ በነበረው እቴጌ መነን፣ ትምህርት ቤት ገብታ በጥንካሬ መማር ጀመረች። ጥቂት ቆይታ ደግሞ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት መዛወርን ፈለገች። ከሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ለመውጣት የከለከላት አልነበረም።
በወቅቱ እናቷና አያቷ ዘንድ መቀመጥ ምርጫዋ ሆነ። በትምህርት ቤቱ እስከ አስረኛ ክፍል የዘለቀችው የትናየት ከዚህ በኋላ የነበራት ጊዜ ለሌላ ታላቅ ዓላማ አዘጋጃት።
1950 ዓ.ም
በልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል /የአሁኑ ጦር ኃይሎች/ ለነርሲንግ ትምህርት የታጨችው ወጣት ዕድሉን ባገኘች ጊዜ በአግባቡ ተጠቀመችው። ሙያና ፍላጎት ተጣምረው የውስጧን ዕውቀት ገለጡ።ዕለት በዕለት ጠንክራ በብርታት ሙያውን ቀሰመች። ያሰበችው ተሳካ፣ ዕቅድ ዓላማዋ ዕውን ሆነ።
1950 ዓ.ም የተጀመረውና በውጭ ሀገር ዜጎች የታገዘውን የነርሲንግ ትምህርት በ1953 ዓ.ም በስኬት አጠናቃ ለምርቃት በቃች። ከዚህ በኋላ የነበረው ጊዜ ለእሷ ሥራውን ፍቅዳ ለገባችው ወጣት የተለየ ነበር። የዛኔ አይደለም በሴት ልጅ በብዙኃኑ ወንዶች የማይደፈረው የሕክምና ሙያ በነሲስተር የትናየት መተግበሩ ብርቅ የሚያሰኝ ነበር።
በልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል ሙያዋን በጥሩ ሥነ ምግባር ያስመሰከረችው ወጣት ውሎ አዳሯን ከልብ ወደደችው። ያለ አንዳች መሰልቸትና መዘናጋት ጊዜና ዕውቀቷን ሰጥታ በሥራዋ አተኮረች። ይህ እውነት ሌላውን ዕድል ለመክፈት አልዘገየም። መልካም ዓይኖች በሲስተር የትናየት ላይ አተኮሩ። የሙያ ፍቅሯና የሥራ ብርታቷ ሚዛን ደፍቶ ይታይ ያዘ።
እንግሊዝ ለንደን …
ሲስተር የትናየት ወርቃማዎቹን የሥራ ዓመታት እንደዘለቀች በአስተዳደሩ ዘርፍ ሙያዋን የሚያጠናክር የትምህርት ዕድል አገኘች። ይህ አጋጣሚ ለእንግሊዝ ሀገር ጉዞ ከታጩት ጥቂት ሴቶች መሀል አንዷ አደረጋት።በዘመኑ ይህ ዓይነቱ ዕድል እንደቀላል የሚታይ አይደለም።ሀገር ቆርጦ፣ ባህር ተሻግሮ፣ ዕውቀትን መቅሰም፣ ለጥቂቶች፣ በጥቂቶች ብቻ የሚሆን እንጂ።
ወጣቷ የትናየት የውጭ ሀገሩን የትምህርት ዕድል ባገኘች ማግሥት በሙሉ ልብና ወኔ ጓዟን ሸክፋ ተነሳች። ከታሰበው ጥግ ለመድረስም ሀገሯን ተሰናብታ ወደ እንግሊዝ ለንደን አቀናች። የእንግሊዝ ሀገር ቆይታዋ መልካም የሚባል ነበር።ከእሷ መሰል የውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር ሙያዋን አዳበረች፣ ሰፊ ልምድም ቀሰመች።
በለንደን ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቆይታዋ በመልካም እንደ ተቋጨ ከሀገሯ የወሰደ እግሯ መልሶ ወደ እናት ምድሯ አገባት። 1958 ዓ.ም በተሻለ ልምድና ዕውቀት የዳበረ ማንነቷ ዳግም ከልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ሊያደርሳት ግድ አለ።እስከ 1959 ዓ.ም በሆስፒታሉ ሙያዋን በብቃት ተወጣች።ቀጣዩ የሲስተር መንገድ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አመራ።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ሲስተር የትናየት ከ1966 ዓመታት ጀምሮ በጥምረት ዘለቁ። ከደርግ መንግሥት እስከ ኢህአዴግ ለውጥ ድረስ ያለመታከት የሠራችው ባለሙያ ዓመታት በጨመሩ ቁጥር ስለሥራዋ፣ ማሰቧ አልቀረም። ያለፈችበት መንገድ ለሙያዋ ክብር የሚሰጥ ፣ ለሕሙማን ሕይወት አብዝቶ የሚጨነቅ ነው።
ከ1959 ዓ.ም በኋላ የየትናየት ሙያ ከነበረችበት ተሻግሮ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደረሰ። በስፍራው ተገኝታ የነርስነት ሙያዋን በብቃት ተወጣች። እስከ 1966 ዓ.ም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ሲስተር የትናየት ዓመታትን በጥምረት ዘለቁ።
ትዳርና ልጆች…
ሲስተር የትናየት ከምንም በላይ ስለሙያዋ ትታገላለች፣ ለእሷ ሕይወቷ ለሰዎች መድረስ፣ ሕሙማንን መፈወስ ነው። እንዲህ መሆኑ ስለግል ሕይወቷ እንዳታስብ ምክንያት ሆኗል። ባልንጀሮቿ በዕድሜያቸው ሲዳሩ ሲኳሉ እሷ እስከ አርባኛ ዓመቷ መዳረሻ ትዳር ይሉትን አላሰበችውም። ውሎ አድሮ ግን ከትዳር አጋሯ ተጣምራ ሶስት ልጆችን አከታትላ ወለደች።
ትዳሯ ብዙ አልዘለቀም። በ1978 ዓ.ም ለፍቺ ብትበቃ የብቸኝነት ሕይወት ግድ አላት።ልጆቹን አባታቸው ዘንድ ትታ ትኩረቷን ሙሉ ሥራዋ ላይ ጣለች።የቤት ኪራይን ሕይወት አየችው። በውጣ ውረዶች ተመላለሰች። እንዲያም ሆኖ አልከፋትም። ትኩረቷ ሁሉ በምትወደው ሥራ ላይ ሆነ። በዚህ መሀል ላፈራችው ቤት ንብረት መታገሏ አልቀረም። አስራ ሶስት ዓመታትን በፍርድ ቤት ምልልስ አሳለፈች። በትዳር መሀል የፈራቸው ሀብት ንብረት ከፍቺና ከባለቤቷ ሞት በኋላ በብዙ አሟገታት።
የትናየት በፍርድ ሂደቱ ደስተኛ አይደለችም። ሚዛናዊ እንዳልሆነ ታምናለች። በእሷ ዕምነት ከአባት ጋር ያደጉት ልጆቿ ጥሩ ነገር ሲሰሙ አልኖሩም። ይህ እውነታም ከእናታቸው ሲያጨቃጭቃቸው ቆይቷል።ከደርግ መንግሥት እስከ ኢህአዴግ ለውጥ ድረስ ያለመታከት የሠራችው ባለሙያ ዓመታት በጨመሩ ቁጥር ስለሥራዋ፣ መጨነቅ ያዘች።
ያለፈችበት መንገድ ላለችበት ሙያና ሙያተኛ ክብር ይሰጣል።በዚህ ዘርፍ ያለፉ አብዛኞች ስለሰው ልጆች መኖር ይጨነቃሉ። ምንጊዜም የእነሱ ግብና ርካታ የታማሚውን ጤና መጠበቅ፣ ሕይወቱን ማትረፍ ላይ ነው።ይህ ዓይነቱ ሀቅ በሲስተር የትናየትና መሰል ባልደረቦቿ ልቦና ውስጥ ደምቆ የተነቀሰ ማህተም ሆኗል።
ሲስተር አንዳንዴ የምታስተውለው ድርጊት ከማንነቷ አልስማማ፣ ከሙያ ቃልኪዳኗ ጋር አልሰምር እያላት ትፈተናለች።ብዙ ጊዜ ውስጧ እየታዘበ ፣ ህሊናዋ እየቆሰለ ልትታገለው ሞከረች። እንዲያም ሆኖ ሥራዋን አልበደለችም።እየቆረቆራትም ቢሆን በመንገዷ ቀጠለች።
አሁን ሲስተር የትናየት በሥራ ደክማለች።የዕድሜዋ መግፋትና የኑሮ አለመመቸት ጤናዋ ላይ ችግር እያመጣ ነው። የትናንቷ ብርቱ፣ የቀድሞዋ ቆንጆ፣ ከሀገሪቱ የመጀመሪያዎቹ ነርሶች ከፊት የምትሰለፈው ጠንካራ ዛሬ እጅ እየሰጠች ነው።ደጋግሞ የሚጎበኛት የእግር ሕመም ፋታ እየሰጣት አይደለም።በየጊዜው ያማታል።
ከቀናት በአንዱ በድንገት ወድቃ ተሰበረች።ሕመሙ በእጅጉ አሰቃያት። በሆስፒታል ተመላልሳ ታከመች፣ ‹‹መንዝ›› ድረስ ሄዳ በወጌሻ ታሸች። ሕመሙ በቀላሉ የሚተዋት አልሆነም።ሲስተር በሕክምናው ሙያ ዓመታትን ዘልቃለች።በራሷ ላይ ያኘችው ውጤት ግን በተለይ በመንግሥት ሆስፒታሎች እሷ የምታውቀውን ያህል ፍሬማ አልሆነላትም።በዚህ ከልቧ ታዝናለች ።
ሕይወት በሌላ መንገድ …
‹‹የወደቁትን አንሱ›› በተባለው የነዳያን መርጃ ማዕከል ተገኝቻለሁ። ሕይወት በአንድ መንገድ ያገናኛቸው በርካታ ሰዎችን እያየሁ ነው። በአንድ ዌልቸር ላይ የተቀመጡትን መልከ መልካም ወይዘሮ እንደዋዛ አይቼ ማለፍ አልተቻለኝም። ቆንጆ ናቸው። ዕድሜ ቢጫናቸውም ውበታቸው አልተደበቀም። ለሰማንያ ሰድስት ዓመቷ አዛውንትን ቀርቤ በአክብሮት ሰላምታ አቀረብኩ። ‹‹ሲስተር የትናየት በቀለ›› ሲሉ ራሳቸውን አስተዋወቁኝ።
ከሲስተር ጋር ብዙ አወጋን። ጤናቸው በመጠኑም ቢሆን ጥሩ መሆኑን ነገሩኝ። ያለፉበት የኑሮ መንገድ ሻካራማና ጠመዝማዛ ነው። የሕይወት ክፉ አጋጣሚ ከትናንት አሻግሮ ዛሬ ላይ ቢያደርሳቸው በዚህ ስፍራ ሊገኙ ግድ ብሏል።
ከአፄው ዘመን እስከ ደርግ መንግሥት፣ ብሎም እስከ ኢህአዴግ ለውጥ ድረስ ያለመታከት የዘለቀ ጉዞ፣ ሰላሳ ስድስት ዓመታት ፣ ለሙያ ፍቅር የታገለ ማንነት፣ ባሕር ተሻግሮ ዕውቀት የቀሰመ ባለውለታ አዕምሮ፣ እነሆ! ዛሬ በችግሮች ተፈትኖ ከዚህ ተገኝቷል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም