የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሻሻል

ለማንኛቸውም መሰረተ ልማቶች መሰረት የሚጥለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ነው። በጤናና በትምህርት ተቋማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በመስኖና ግድብ ግንባታዎች እና በሁሉም ዘርፎች የሚሰሩ ግንባታዎች በዋነኛነት የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን የሚጠይቁ ናቸው። የግብአቶቹ አቅርቦት መሳለጥና አለመሳለጥ፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋልና አለመዋል በመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ ወጪ፣ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅና አለመጠናቀቅ ላይ ተጽኦኖ ያሳድራሉ፤ በአጠቃላይ በዘርፉ ምርታማነት ላይ የራሳቸውን ተጽእኖ ያሳርፋሉ።

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሻሻል እና ኢንዱስትሪውን ለማዘመን ከ20 ዓመታት በፊት የተደረጉ ጥናቶች እስካሁን ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ ጥናቶች አሁን ሊጠቅሙ ቢችሉም፣ ተጨማሪ ጥናቶችን ማድረግ እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉ ምርታማነት ላይም በየጊዜው ለውጦች ይታያሉ። በተለይም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከውጭ የሚመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና በሀገር ውስጥ የሚፈጠሩት የተሻሻሉ አሰራሮችና በየጊዜው የሚታዩ ለውጦች በኮንስትራክሽን ምርታማነት ላይ ያላቸውን ለውጥ በተመለከተ በየጊዜው ጥናቶች ይደረጋሉ። ጥናቶቹም ሳይት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ከተቀመጠው ስታንዳርድ አንፃር የመፈፀም አቅማቸውን በማየት የግንባታ ተቋሞቹ ምን ላይ እንደሚገኙ እና ውጤታማነታቸውን እንዲለኩ የሚያግዙ ናቸው።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሰው ኃይል እና የማሸነሪ እንዲሁም የግብዓት አቅርቦት፣ የፈረቃ ስራ የመሳሰሉ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ምርታማነት መሻሻል የራሳቸው ሚና አላቸው። ዘርፉን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ካላቸው ነገሮች አንዱ የሰው ኃይል አደረጃጀት እና ተገቢ የስራ ሰዓት ቁጥጥር መሆኑም መረጃዎች ያመላክታሉ። እየጨመረ በሚሄደው የግንባታ ግብዓት ዋጋ ምክንያትም የግንባታ ባለቤቶች ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጋቸው ይልቅ በቂ የሰው ኃይል በመመደብ እና 24 ሰዓት በማሰራት ምርታማነቱን ማሻሻል ያስችላል። በቂ የሰው ኃይል መድቦ እና ፕሮጀክቱን በፈረቃ መስራት ፕሮጀክቶች ሲቆዩ ከሚመጣው የዋጋ እና የግብዓት ጭማሪ አኳያ ወጪ የሚቀንስ ስለመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡

በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የአሰራር ሥርዓት ማሻሻያ ዳይሬክተር ኢንጂነር አበራ አውግቸው እንዳሉት፤ የኮንስትራክሸን ዘርፉ ምርታማነት አንድ ስራ ከተከናወነ በኋላ የተገኘው ውጤት ስራውን ለመስራት ጥቅም ላይ ከዋለው ግብዓት ጋር የሚነፃፀርበት ነው። የፕሮጀክቶችን ምርታማነት ለማሻሻል እና በጊዜ ከማጠናቀቅ አኳያ ስራዎችን በፈረቃ መስራትም ወጪ ብቻ እንዳለው በአንዳንድ ወገኖች ይታሰባል። ነገር ግን በፈረቃ መስራት ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ አሁን ከሚታየው ከዋጋ ግሸበት አንጻር የሚገኝ ትርፍ አለ። እንዲሁም የሰው ኃይሉን እና ማሸነሪውን ሌላ ስራ በማዋል ኮንትራክተሩ ተጨማሪ ስራዎችን ለማግኘት ያስችለዋል። እነዚህን ታሳቢ አድርጎ ሙያዊ የሆኑ እይታዎችን በመስጠት የመስራት ክፍተት እንዳለም ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ።

አንድን ግንባታ ለማጠናቀቅ ጥቅም ላይ የዋለው ካፒታል፣ የሰው ኃይል፣ ኢነርጂ፣ አገልግሎቶች፣ ማቴሪያሎችን በመጠቀም የተገኘውን ወይም የተመረተው የአንድ የኮንስትራክሽን ውጤት የሚነፃፀርበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ አንፃር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የምርታማነት ደረጃ ለማሻሻል ውስጣዊ ምክንያት የሆነው የሰው ኃይሉ እና የውጫዊ ምክንያቶች የሆኑት ካፒታል፣ ኢነርጂ፣ አገልግሎቶች፣ ማቴሪያሎችን የመሳሰሉት የየራሳቸው ሚና አላቸው። ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ምርታማነት ተፅዕኖ ካላቸው መካከል ዋንኛዎቹ የሰው ኃይሉ እና የማሸነሪ አቅርቦት መሆናቸውን ያመላክታሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዋነኛ ሚና የሚጫወቱ ኩባንያዎችና የፕሮጀክት ባለሙያዎችን አቅም መገንባት ላይ አተኩሮ ይሰራል። የኮንስትራክሽን የስራ ሂደት እና የምርታማነት ደረጃ ምን እንደሚመስል ጥናት ማድረግ እና ጥናቱ ላይ ተመርኩዞ ለኢንዱስትሪው መነሻ የሚሆን የምርታማነት መመሪያ ሰነድ ያዘጋጃል። በቅርቡም በኢንስቲትዩቱ የኮንስትራክሽን ምርታማነት ከማሳደግ አኳያ በተለይም የሰው ኃይል እና የማሽነሪ ምርታማነት ላይ ያተኮረ ጥናት ተካሄዷል።

በጥናቱም መጀመሪያ እንደ ግብ ተይዞ የተሰራው ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አንፃር ምርታማነት የሚታቀድ እና የሚለካ ራሱን የቻለ ቁልፍ ተግባር ለማድረግ እንዲሁም አሁን ያለው የሠራተኛው ምርታማነት፣ አማካይ የሰው ኃይሉ፣ የማምረት ደረጃ የሚፈተሽበት ነው። ሠራተኛው ስራ ላይ በተሰማራበት ወቅት ምን ያህሉን የስራ ሰዓት ቀጥታ ለምርት አስተዋፅኦ ባለው መልኩ አውሎታል የሚለውን የስራ ናሙና በመውሰድ በጥናቱ ለማወቅ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።

በተጨማሪም ጥናቱ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮችን ለመለየት እና በጉዳዮቹ ላይ ክትትል በማድረግ፣ እርምጃ በመውሰድ ምርታማነቱን ለማሻሻል መሆኑንም አመላክተዋል።

በጥናቱ በአንድ ጊዜ ይሄን ያህል ማምረት ይቻላል ወይም ደግሞ ከኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ከካሳ ጥየቃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲነሱ ለመፍታት ስላለው ፋይዳም አብራርተዋል። ጥናቱ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣ የፕሮጀክት አመራር ለማሳደግ፣ ዘመናዊ አሠራርን ለማስፈን፣ የካሳ እና የክስ ጉዳዮች የመሳሰሉትን ለመዳኘት ጠቀሜታዎች መሆኑን ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ። በአጠቃላይ ጥናቱ ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ እና አቅሙ የጎለበተ ለማድረግ እና ሁልጊዜም አፈጻጸሙን እየለካ ለመሄድ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ የምርታማነት ዓላማ ካልተቀመጠ እና ካልተለካ ወዴት እንደሚሄድ የማይታወቅና የቁጥጥር ስራ ለማከናወንም የማያስችል በመሆኑ የተመላከተ ሲሆን፤ ጥናቱ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዳይሬክተሩ፤ ጥናቱ በኮንትራክተሮች ዘንድ በዋጋ ዝግጅት ጊዜ የሚፈለግ አንዱ ቁልፍ ግብዓት ነው። ለአብነት ‹‹አንድ ሜትር ኪዩብ ለማምረት ስንት ሠራተኞች ያስፈልገኛል? እነኚህ ሰራተኞች ደግሞ በሰዓት ምን ያህል ያመርታሉ? የሚለውን አንድ ኮንትራክተር ወይም የፕሮጀክት ባለቤት ካላወቀ የፕሮጀክት ዋጋውን መስራት አያስችለውም›› ይላሉ።

ኢንጂነር አበራ እንደገለፁት፤ እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም ‹‹Ethiopian Construction Production Norm (ECPN)3 እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም አካባቢም (ECPN)5 በሚል ጥናቶች ተደርገዋል፤ እነዚህ ሰነዶች እስካሁንም በኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪው ጥቅም ላይ እየዋሉ ናቸው። ሰነዶቹ በአማካይ ከሃያ ዓመት በላይ የሆኑ ሲሆን፣ ነገር ግን ምርታማነት ደግሞ በየወቅቱ በፕሮጀክት ትግበራ ላይ በተዘረጉ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶች እና የቴክኖሎጂዎች ግብዓት ይቀየራል።በመሆኑም ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመጓዝ ያስችል ዘንድ በየጊዜው ጥናቶች እየተጠኑ ወቅታዊ ይደረጋሉ። ከዚህ ቀደም የተደረጉት ጥናቶችም እስካሁን እያገለገሉ እና ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ መዘንጋት የለበትም።

ቀደም ብለው የተጠኑት እና አሁን ደግሞ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አነሳሽነት እየተካሄደ ያለው የምርታማነት ጥናት የአጠናን ስልቱም የተለየ መሆኑን ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ። የቀደሙት በአብዛኛው ከኮንትራክተሮች በተሰበሰበ መረጃ፣ ከጨረታ እና ከመሳሰሉ የተሰበሰቡ መረጃዎችን ተመርኩው የተካሄዱ መሆናቸውን አንስተው፤ የአሁኑ ግን ዘመናዊ እና ሳይንሱ የደረሰበት የኮንስትራክሽን ምርታማነት የሚለካበትን ስርዓት ለመከተል የመረጃ ሰብሳቢዎች የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ከሳይት ላይ ቆመው የሚሰበስቡበት እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህም ሰፊ እና ትልቅ ሀብት የሚፈልግ ስራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዋናነት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ የሚገኘውም ጥቂት ሆነው ነገር ግን ድርሻቸው እና ተፅኖኣቸው የ80 በመቶ ድርሻ ያላቸውን ተግባራት በመምረጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጥናቱም በሰው ኃይሉ እና በማሽነሪ ምርታማነት ላይ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው የጥናቱ ፕሮጀክት ሂደትም በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በሙከራ ደረጃ ተከናውኗል። ይህም የፕሮጀክት ስልቱ የመጀመሪያ መሆኑና አገራዊ ተደርጎ ሲሰራ ለሚመጡ ችግሮች ቀደም ብሎ መፍትሄ ለማስቀመጥ ስለሚያስችል ይህን መሰረት ነው ብለዋል።

በመቀጠልም በ2012፣ 2013ዓ.ም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ኮረናን ታሳቢ ያደረገው አሰራር የሚተገበር በመሆኑ የተነሳ፤ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ላይ ያሉትን በመተው የአርክቴክቸር እና የኢንጂነሪንግ ምርታማነት፤ የምህንድስናው ዘርፍ ላይ ያተኮረ እንደነበረ አመላክተዋል።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በ2013 ዓ.ም በተደረገው ጥናትም በዋነኛነት የምህንድስና ስራዎች፣ የአርክቴክቸር እና የኢንጂነሪንግ ስራዎችን መለካት የሚቻል መሆኑን ለማወቅ ተሞክሯል። እነዚህ ስራዎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮችንም ለመለየት ጥረት ተደርጓል። የጥናቱ ሁለተኛው ክፍልም በዋናነትም በአርክቴክቸር እና በኢንጂነሪንግ የማማከር ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ተቋማትም በተመሳሳይ አሰራራቸውን የመፈተሽና በቀጣይ የዘርፉን ምርታማነት ለማሻሻል ምን ማድረግ እንደሚገባ ያሳየ መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህን ተከትሎም በ2014 እና 2015 ዓ.ም በሰባት ከተሞች ሀገር አቀፍ የህንፃውን ዘርፍ ምርታማነት ጥናት በማድረግ ሀገር አቀፍ የህንፃው ዘርፍ ጥናትን ለመስራት መሞከሩን ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ይህን ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያትም የኮንስትራክሸን ዘርፉ ምርታማነት በሰው ኃይል፣ በተቋማዊ አደረጃጀት እና አካባቢያዊ በሆኑ ጉዳዮች እና የአሰራር ልምዶች ተፅዕኖ ውስጥ የወደቀ በመሆኑ ነው።

በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ የተሰራው የምርታማነት ጥናት ሰመራ፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭ፣ መቀሌ እና ባህርዳር ላይ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በቀጥታ መጠቀም ተገቢ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም የኮንስትራክሽን ምርታማነት ስራዎች በአካባቢያዊ ጉዳዮች፣ በአሰራር ልምዶች እና ስልቶች ተቋማዊ በሆኑ እና ሰዋዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተወሰነ ነው። በሌሎችም ቦታ ተግባራዊ ለማድረግ በየቦታው እነዚህ ነገሮች ታሳቢ አድርጎ መውሰድ አስፈላጊ ስለሆነ ከ2014 እና 2015 ዓ.ም በሰባት ከተሞች አገር አቀፍ የህንፃው ዘርፍ ምርታማነት ጥናት ተደርጓል።

ጥናቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አማካሪነት የተሰራ ነው። በተለይም ከአዲስ አበባ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከሀዋሳ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከባህርዳር የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከድሬዳዋ እና ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እና ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ የተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ጥናቱም ዩኒቨርሲቲዎችን ከሚገኙበት አካባቢ ጋር በማገናኘት የተካሄደ ሲሆን፣ በሀዋሳ ከተማና በዙሪያው ከሀዋሳ ዩኒቪርስቲ፤ በጅማ እና አካባቢውም ከጅማ ዩኒቨርስቲ፤ በድሬዳዋ አካባቢ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፤ አፋር አካባቢ ከሰመራ ዩኒቨርስቲ፤ በባህርዳር አካባቢው ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ብዙ ቦታዎችን ባማከለ መልኩ የሀገር አቀፍ የምርታማነት ጥናት መካሄዱን ጠቁመዋል።

የጥናቱ ዋነኛ ግብ ሠራተኞች ሳይት ላይ በሚውሉበት ሰዓት ምን ያህል የስራ ሰዓቱን ሥራው ላይ ያውላሉ የሚለው የተካተተበተ ነው። ይህም በአንድ ፈረቃ ሲሰራ ስምንት ሰዓት ይሰራል ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም ከስምንት ሰዓቱ ውስጥ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ያለው ስራ መስራት፣ የማቴሪያል ግብዓቶችን ማጓጓዝ፣ ያለስራ መንቀሳቀስ፣ ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ መረጃዎችን መጠየቅ በሚሉ ዘርፎች የተከፋፈሉ ቼክሊስቶች ያሉት ነው። በእነዚህ ቼክሊስቶች ውስጥም አንድ ሠራተኛ ይጠናል። በዚህ መሰረት ኢንስቲትዩት በሙከራ ደረጃ ባደረገው ጥናት በአማካይ 40 በመቶ ብቻ ቀጥተኛ ውጤት ባለው ስራ ላይ ይውል እንደነበር መታየቱን ጠቁመዋል። ይህም በቀጣይ የሠራተኞች አካባቢ በመፈተሽ ቀጥተኛ ውጤት ያለው ስራ እንዲጨምር በማድረግ የግንባታ ሂደቱን ምርታማነት ማሻሻል ያስችላል።

አሁን ላይ ጥናቱ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ዳይሬክተሩ እንደገለጹት በየምዕራፉ የተሰራ መሆኑን ነው። እሳቸው እንዳሉት፤ የሙከራ ጥናቱ ተሰርቶም ከባለድርሻ አካላት ጋር ለምክክር ቀርቧል። የተገኘው ጠቅላላ ውጤት ለኢንዱስትሪው ተደራሽ ተደርጓል። የአገር አቀፉ የህንፃ ስራዎች ጥናትም በማጠናቀቅ ከባለድርሻዎች ጋር ምክክር በማድረግ እና ተጨማሪ ግብዓት በማከል የጥናቱ ሰነድም በዋናነት ለኮንስትራክሽን ስራዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን እና ለሚኒስትር መስሪያቤቱ በመላክ ለሁሉም የኢንዱስትሪው ተጠቃሚዎች ተደራሽ የሚሆንበት ሂደት ደርሷል። ስራዎቹ በየደረጃው በተጠናቀቁ ቁጥርም ለኢንዱስትሪው ተደራሽ የሚደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንን ጥናት ተከትሎም የመንገዱን ዘርፍ ለማጥናት እና የመነሻ ሰነዶችንም ለማዘጋጀት በዋነኛነትም ፕሮጀክቱ የሚመራው በመንገዶች አስተዳደር ስር በመሆኑ እና በእነሱም በኩል ተነሳሸነት እንዳለ ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በከተማ እና መሰረተ ልማት ስር አቻ ተጠሪ ተቋም በመሆኑ ይህንን ስራ ቢያከናውኑት ይሻላል በሚል የመንገዱን ዘርፍ መነሻ ጥናቱን ለመንገዶች አስተዳደር መሰጠቱን አመላክተዋል።

የውሃ ነክ ስራዎች ጥናትንም በ2016 እና 2017 ዓ.ም ለመስራት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን በማድረግም ቢያንስ የህንጻውን የውሃ እና የመንገድ ዘርፉን ያማከለ ሀገር አቀፍ የኮንስትራክሸን ምርታማነት የሰው ኃይል እና የማሸነሪ ምርታማነት ማሻሻል የሚረዳ ጥናት ታሰቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። አሁን የተጀመሩት የውሃ ስራዎች ዘርፍ ጥናቱም ሲጠናቀቅ በተመሳሳይ ለኢንዱስትሪው ተደራሽ የሚደረግ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You