
ካዛንቺስ በኮሪዶርና መልሶ ልማቱ ተሞሽራለች፤ የሰሞኑም ዜና ይኸው ሆኗል። የትናንቷ ካዛንቺስ ታሪክ መሆኗን የዛሬዋና የወደፊቷ ካዛንቺስ ደግሞ በኮሪዶር ልማቱ አምራ ደምቃ ታይታለች።
ካዛንቺስ በብዙ መንገድ ለውጥ አሳይታለች። ከግቢ ገብርኤል ማዞሪያ ጀምሮ ከመናሃሪያ ጀምሮ የቀድሞው ኤሌክትሪክ አገልግሎት የነበረበት አካባቢን ይዞ እስከ ኡራኤል፣ እስከ ሴቶች አደባባይ ያለው አካባቢ ፍጹም ተለውጧል። ካዛንቺስ በአጭር ጊዜ ውሰጥ በብዙ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ደምቃለች።
ለተሽከርካሪ የተጣበቡና የተጨናነቁ የነበሩ እነዚያ መንገዶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በሰፊው ተገንብተዋል። በካዛንቺስ መናኸሪያ አካባቢ መስቀለኛ መንገድ ወደ ቤተመንግሥት የሚያስወጣ ወደ ሴቶች አደባባባይ የሚወስድ መንገድ እንዲሁም ከካዛንቺስ ባምቢስ መገናኛ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሁሉ በልማቱ መሠረታዊ ለውጥ ተደርጎበታል። መንገዶቹ በግራና በቀኝ ሶስት ሶስት ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግዱ ተደርገው ነው የተገነቡት።
በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች እንደተካሄዱት የኮሪዶር ልማት ሥራዎች በካዛንቺስም የእግረኞች መንገዶች የዓይነ ስውራን መንገድን አካተው በሰፊውና በጥራት ተገንብተዋል። ያልነበሩ አዲስ አበባ የማታውቃቸው የብስክሌት መንገዶች ካዛንቺስም ድምቀት አላብሰዋታል። ሳሩ የዛፍ ችግኞቹ ወዘተ ሌሎች ውብቶች ናቸው።
የቴሌኮም፣ የውሃ የመብራት ገመዶች፣ ኬብሎች ቱቦዎች በመሬት ውስጥ እንዲያልፉ በመደረጋቸው እነዚህን መሠረተ ልማቶች እንደ ቀድሞ ከመሬት በላይ አይታዩም። መሬት ጉያ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። የኤሌክትሪክ የስልክ ወዘተ ገመድ ወዘተ ትብትብ አየር ላይ እንዳይታይ ተደርጓል። የአረንጓዴ ውበት ሥራዎች በስፋት ለምተዋል፤ በዚህም ካዛንቺስ ውብና ፅዱ ሆኖ መታየት ችላለች።
የመንገድ መብራት ያልነበረባቸው አካባቢዎች ባለመብራት ሆነዋል፤ ለዚያውም ባለዘመናዊ መብራት። አሁን የተተከሉት የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች ባለ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ናቸው። በቅርቡ ቦሌ አካባቢ ተግባራዊ መሆን የጀመሩት ደረጃቸውን የጠበቁ እና የኤሌክትሪክ ቻርጅ አገልግሎት የተገጠመላቸው ብልህ የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች በካዛንቺስም ተተከልው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው።
መንገዶቹ የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊ እንዲሆን አርገውታል። የቀድሞው የትራፊክ መጨናነቅ ታሪክ ተደርጓል፤ ለተሽከርካሪው ለብስክሌቱ ለእግረኛው ለየብቻቸው ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች መገንባታቸው የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ አስችሏል።
ፋውንቴኖች ሌሎች የካዛንቺስ ውበቶች ናቸው። በቀድሞው ካዛንቺስ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሥሪያ ቤት አካባቢ የተገነባው የውሃ ፋውንቴን በከተማዋ በኮሪደር ልማቱ ከተሠሩት ለየት ያለ ነው። ፋውንቴኑ ዝናብ በሌለበት ሁኔታ ከጣሪያ ላይ ውሃ ሲወርድ የሚታይበት ነው።
ፋውንቴኖቹ የሚለቁት ውሃና ውሃውን የሚለቁባቸው መንገዶች ፣ የአረንጓዴ ሥፍራዎቹ ውብት፣ አበቦቹ ተደማምረው ሲታዩ አካባቢውን አዲስ የአየር ሁኔታ የተፈጠረበትም አስመስለውታል፤ ንፁህ እና ነፋሻማ እንዲሆን አድርገውታል።
በአጠቃላይ ካዛንቺስ በመልሶ ግንባታና ኮሪዶር ልማቷ፣ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ማድረግ እንደሚቻል በሚገባ ማሳየት ያስቻለ ነው። ካዛንቺስ የከተማዋ ዓለም አቀፍ መዲናነት ማስጠበቅንም ዓላማ አርጎ የተጀመረው የኮሪዶር ልማት ሥራ ሌላ አስረጂ ሆና ዳግም ተሠርታለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ በተካሄዱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች አዲስ አበባ እውነትም አዲስ አበባ እየሆነች ነው፤ በትክክል ስሟን እያገኘች ነው ሲሉ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና በኮሪዶር ልማቱ የተሠማራ ድርጅት ኢንጂነር አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
በካዛንቺስ መልሶ ግንባታና ኮሪዶር ልማት ሥራ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አንዱ ብራዘርስ ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው። የድርጅቱ ሳይት ኢንጂነር ዮሐንስ መቻል እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ እንደ ሀገር ሰፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ደግሞ በኮሪዶር ልማት ሥራው በግልፅ በሚታይና ህብረተሰቡ በሚገባ በሚያውቀው መልኩ እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
ድርጅቱ፤ በካዛንቺስ የኮሪደር ልማት በሁለት ፕላዛዎችና የአረንጓዴ ውበት ሥራዎች ላይ ተሳትፏል። ከግቢ ገብርኤል /ቤተመንግሥት/ ጀምሮ አስከ ኡራኤል ያለውን እና ትላልቅ የሚባሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በተመረቁ የካዛንቺስ አካባቢዎች ሁለት ትላልቅ ፕላዛዎች ይገኛሉ።
በካዛንቺስ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሥሪያ ቤት በነበረበት ቦታ ላይ የህፃናት ማጫወቻ፣ የመጻህፍት መደብር፣ ስፔስ ካፊን ያካተተ ቤተ ፋውንቴን የተሰኘ የአርት ጋለሪ ተገንብቷል። የጋላሪው ጣሪያ ከመስታወት የተሠራ ሲሆን፣ ውሃ ከጣሪያው እየፈሰሰ ከጎን እና ከጎኑ ደግሞ የሚጮሁ ፋውንቴኖች አሉበት።
ከካዛንቺስ በመለስ ፋውዴሽን አድርጎ ሴቶች አደባባይ ድረስ ያለውም ሌላው በኮሪዶር ልማቱ የለማ አካባቢ ነው። በዚህ መስመር በሴቶች አዳባባይ የሕዝብ መገልገያዎች፣ መጸዳጃ ቤት፣ የህፃናት መጫወቻዎች ያሉበት እና ሙሉ ለሙሉ ከላይ ሙሉ ካዛንቺስን በሚባል ደረጃ ያካተተ የአረንጓዴ ውበት ሥራዎች መሠራታቸውን ኢንጂነር ዮሀንስ አስረድተዋል።
እስከ አሁን በከተማዋ ከተገነቡ ፋውንቴኖች ትልቅ የሚባለው የ “ሪንግ ፋውንቴን” ግንባታም እየተካሄደ መሆኑን ኢንጂነሩ ገልጸዋል። ይህ ፋውንቴን እየተገነባ ያለው ቀድሞ የስድስት ኪሎ ታክሲ በሚያዝበት ሰፊ ሥፍራ ላይ ነው።
ይህ የግንባታ ፕሮጀክት ከአንዱ ኮለን አስከ ሌላኛው ድረስ 50 ሜትር ራዲየስ አለው፤ ክቡ የመሃሉ ክፍል ከአንድ ሺህ 300 ሜትር ስኴር ሜትር በላይ ይሰፋል። ዙሪያው ሙሉ ለሙሉ ሲለካም ወደ 148 ስኬር ሜትር የሚሆን ፋውንቴን እየተሠራለት ይገኛል።
ፋውንቴኑ ከመሬት ወደ ላይ ሲታይ ከላይ ወደታች የሚፈስ ውሃ ያለው ሲሆን፤ ሁለት ድልድዮችም ይኖሩታል። መሃሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማስተናገድ ያስችላል።
ፋውንቴኑ የምግብ ኮርት ያለበት፣ ባህላዊ ነገሮች የሚሠሩበት፣ ደረጃውን የጠበቀና ብዙ ሰው ማስተናገድ የሚያስችል ግዙፍ ካፌ እንዲሁም አምፊ ቲያትር እንዳለው አብራርተዋል። ሰርጎችን፣ መንግሥታዊ ፕሮግራሞችን፣ እንዲሁም ስብሰባዎችን ለማካሄድ የሚያስችል ሰፊ ቦታ መሆኑንም አስረድተዋል።
የዚህ ፕሮጀክት ሥራ እስካሁን ድርጅቱ ሠርቶ የማያውቀው እንደ ሀገርም የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸው፣ ከፋውንቴኑ የሚወጣው ውሃም ከመሬት ስድስት ሜትር ከ 50 በላይ ሆኖ ወደታች የሚፈስ ነው ብለዋል። የህፃናት መጫወቻ ቦታም እንዳለው ጠቁመዋል። የዚህ ፕሮጀክት ግንባታም ከ50 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰው፣ በቅርቡ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት እንደሚገባም አመልክተዋል።
በካዛንቺስ አሁን በግንባታ ላይ የሚገኘው የመጨረሻ ሳይት መሆኑን ጠቁመው፣ ሌሎች ሥራዎች ተጠናቅቀው ርክክብ መደረጉን ገልጸዋል። ድርጅቱ በኮሪዶር ልማቱ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም በአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት እውቅና እንደተሰጠውም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በጋርመንት፣ ጎሮ፣ ስድስት ኪሎ አካባቢም በኮሪደር ልማቱ ፕሮጀክቶች ላይ እየሠራ ይገኛል። ከክልል ጅማ ፣ ጅግጂጋ፣ አሶሳ፣ አምቦና በመሳሰሉ ከተሞች የኮሪዶር ልማት ፕሮጀክቶች እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
በካዛንቺስ ኮሪዶር ልማት በተሠራው የብስክሌት መንገድ ሲገለገል ያገኘነው ወጣት እዩኤል ገብረሕይወት በበኩሉ፤ ካዛንቺስ ተወልዶ ማደጉን ጠቅሶ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ብስክሌት እንደሚጠቀም ይናገራል። ቀደም ሲል የራሱ ብሰክሌት ባይኖረውም እየተከራየ ይገለገል ነበረ።
አሁን የራሱ ብስክሌት አለው፤ እሱን ተጠቅሞ ቢዩ ዴሊቨሪ በሚባለው ተቋም እቃ በማድረስ ሥራ ላይ መሠማራቱን ይናገራል። ቀድሞ በነበረው ሁኔታ ብስክሌት ከተማ ውስጥ ማሽከርከሩ ለትራፊክ አደጋ ያጋልጥ እንደነበር አስታውሶ፣ ራሱን ለመጠበቅ ሲል አንዳንድ ቦታዎች ላይ እየወረደ ብስክሌቱን በመገፋት ድጋሚ ያሽከረክር እንደነበር ተናግሯል። አሁን ግን በተዘጋጀው የብስክሌት መንገድ ላይ ያለምንም ስጋት እያሽከረከረ ወደፈለገው ሥፍራ መድረስ እየቻለ መሆኑን አስታውቋል።
እሱ እንዳለው፤ የብስክሌት መንገዱም ጥሩ ተደርጎ ተሠርቷል። አንደኛ መንገዱ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው፤ በፍጥነት በመሄድ ለደንበኛው እቃውን በወቅቱ ለማድረስ እየረዳው ነው፤ በብስክሌት መንገዱ ላይ ብስክሌት ብቻ የሚሄድበት በመሆኑ መጨናነቅ አይገጥምም። ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማሽከርከር ይቻላል። የብስክሌት መንገዱ በመስመር የተለየ መሆኑን ጠቅሶ፣ በነጻነት ለመገልገል እያስቻለው መሆኑን አመላክቷል።
ወጣት እዩኤል የቀድሞዋ ካዛንቺስ ከአሁኗ ጋር ስትነጻጸር ብዙ ልዩነት እንዳላት ተናግሯል። የቀድሞዋ የተሳለጠ የትራፊከ ሥርዓት አልነበራትም። አሁን ከመንገድ መሠረተ ልማት ከመብራትና ከመሳሰሉት አኳያ መሠረታዊ ለውጦች ተደርገዋል። መሠረተ ልማቶች በሚገባ ተገንብተዋል።
ፊት መንገድ ለማደስ ብዙ ጊዜ ይወስድ እንደነበር አስታውሶ፣ አሁን በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው በራሱ ትልቅና ፈጣን ለውጥ መሆኑን ተናግሯል።
ካዛንቺስ አካባቢ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሰላም ተካ እንደተናገሩት፤ የካዛንቺስ የኮሪዶር ልማት ሥራዎች በፍጥነት መከናወናቸውን ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታው በዚሁ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የቀድሞዋ እና የአሁኗ ከዛንቺስ ብዙ ልዩነቶች እንዳሏቸው ጠቅሰው፣ ካዛንቺስ ከመፍረሱ በፊት በአንድ አስፓልት መንገድ ላይ ሰውም፣ ብስክሌቱም ተሽከርካሪውም እየተጋፋ ይገለገል እንደነበር አስታውሰዋል።
በካዛንቺስ አሁን ግን በስድስት ወራት ውስጥ የታየውን ለውጥ አስደማሚ ሲሉ ገልጸውታል። በካዛንቺስ አካባቢ ሠራተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሥራውን በቅርበት ሲመለከቱ መቆየታቸውን ይገልፃሉ። የመኪና መንገዱ ስፋት ለተሽከርካሪ ምቹ መሆኑን ጠቅሰው፣ የብስክሌቱን የእግረኛውም መንገዶች በስፋት መሠራታቸውንና ይህም አንዱ የአንዱ መንገድ ላይ የሚገባበት ሁኔታ እንደሌለ ተናግረዋል።
በሌሎችም አካባቢዎች ይሄ ልማት በተጀመረው ፍጥነት ቢቀጥል ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው፣ የአንዳንድ አካባቢዎች የኮሪዶር ልማት የካዛንቺሱን ያህል ፈጣን ሆኖ እንዳላገኙት ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በኮሪዶር ልማት ሥራው የሰውና የመኪና መንገድ በግልጽ ተለይቷል። ሰው መንገድ የሚያቋርጥበት ሥፍራ በሚገባ ተለይቷል፤ ይህን መጣስ ያስቀጣል። ይህም አደጋን በመቀነሱ የራሱ በጎ ሚና ይኖረዋል። ተጨማሪ የትራፊክ መብራት እንዲኖሩም ጠይቀዋል። አሽከርካሪዎችም ፍጥነታቸውን የሚገድቡበት ሁኔታ ቢፈጠር አደጋን መቀነስ ይቻላል ሲሉም ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካዛንቺስ ኮሪዶር ልማትን በይፋ መመረቃቸው ይታወቃል። የዚህን ኮሪዶር ልማት መመረቅ አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ሰው የላቡን ፍሬ ይበላል የሚለው ሃሳብ በካዛንቺስ ሥራ ግልጥ ብሎ መታየቱን አስታውቀዋል። ከጥቂት ወራት በፊት ካዛንቺስ የነበረው መልክ ዛሬ ከምናየው ጋር በእጅጉ የተራራቀ ነው ሲሉ አስታውሰው፣ ፊት ለኑሮና በብዙ መልኩ ለሰው ልጅ ምቹ የማይባል አካባቢ እንደነበር ገልጸዋል። በጥቂት ወራት ውስጥ በካዛንቺስ የተገኘው ውጤት የሚያኮራ ሥራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በየትኛውም ሀገር የሚታየው ዘመናዊነት ለውጥና መሻሻል የሚገለጸው በእዚህ መንገድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘመኑ የሚባሉ ከተሞች አረንጓዴና ንጹህ የሆኑ ከተሞች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገጽታ በእጅጉ የቀየረን ሥራ አለማድነቅ ንፉግነት ነው ሲሉ ባሰፈሩት ጽሁፍ በካዛንቺስ በጥቅሉም በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪዶር ልማት ያስገኛቸውን ትሩፋቶች አለማድነቅ ትክክል አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
የኮሪዶር ልማቱ ካዛንቺስን ውብ በማድረግ አካባቢውን ካላበሰው አዳዲስ ሀሴትን የሚፈጥሩና ለእይታ የሚማርኩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና ጽዱ አካባቢን ለነዋሪው በመለገስ ሌላ አዳዲስ ተጨማሪ የመዝናኛ ሥፍራን ለከተማዋ በተለይም ለነዋሪዎቿ አበርክቷል ብለዋል። የከተማዋን ገጽታ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገው ይህ ግንባታ የኢትዮጵያ ብልፅግና እና ትንሣዔ አይቀሬ መሆኑንም ያመላከተ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት ፤ የኮሪዶር ልማቱ ሁሉን ያቀናጀ የከተማ ግንባታ (ስማርት ሲቲ) አካል በመሆኑ ለሀገሪቱ ዘመናዊ ከተማ ግንባታ ሞዴል ተደርጎ ይወሰዳል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም