ኮሪዶር ልማት – የፍትሐዊነት ማሳያ

ከተማና ከተሜነት አይቀሬዎች ስለመሆናቸው፣ ከተሞች የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ ማዕከላት እየሆኑ እንደሚመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች አብክረው ያስገነዝባሉ። ለእዚህ በቂ ዝግጅት አርጎ መሥራት እንደሚገባም ይመክራሉ። በፕላን ላይ የተመሰረቱ ከተሞችን መገንባት፣ ለእዚህም የሚመጥኑ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንዲሁም በነዋሪዎች ዘንድ የከተሜነት አመለካከት እየጎለበተ እንዲሄድ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይታመናል።

በኢትዮጵያ ከተማ እየቀደመ፣ ፕላን እየተጣሰ ከተሞች ለውስብስብ ችግሮች ተዳርገው ኖረዋል። የከተሞች አስተዳደሮችና የመንግሥታት ቁርጠኝነት ማነስና የአቅም ውስንነቶች፣ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ከተሞችን በፕላን ለመምራት፣ መሰረተ ልማቶቻቸውን ለመዘርጋት እንዳይቻል አርገው ቆይተዋል።

ይህን ችግር የተረዳው የለውጡ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪዶር ልማት በማካሄድ የከተማዋን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ሰው ተኮር በሆነው ልማቱ ለተነሺዎች መኖሪያ ቤት እንዲሁም ለባለይዞታዎች ቦታና ካሳ በመስጠት ነው ወደ ሥራው የገባው። በልማቱ መንገዶችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በመገንባት ብቻ በሰፊው ሰርቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመጀመሪያው ዙር የኮሪዶር ልማት ብቻ 33 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ። ባለሀብቶችን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ተቋማትን ማኅበረሰቡን በማስተባበር ጭምር ልማቱ እየተካሄደ ይገኛል። ልማቱ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገበት፣ ስኬታማ ሥራዎችም እየታዩበት ነው።

ሳምንቱን ለሰባት ቀናት፣ በቀን ለ24 ሰዓት እየተካሄደ ባለው የኮሪዶር ልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ ተችሏል። ይህም በከተማ አዲስ የሥራ ባሕል ተወስዷል፡፡

በኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽ ለመቀየር፣ መሰረተ ልማቶችን ለማዘመን ወዘተ በስፋት ተሠርቷል፤ እየተሠራም ነው። የተሽከርካሪ፣ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችና የእግረኛ መንገዶችን በአዲስ መልኩ መገንባት ተችሏል፤ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም፣ የውሃ፣ የፍሳሽ ቆሻሻ፣ ወዘተ መሰረተ ልማቶች በምድር ውስጥ እንዲዘረጉ እየተደረገ ነው። አረንጓዴ ሥፍራዎችን የማልማት፣ በፋውንቴሽኖችና በመብራቶች ከተማዋን የማስዋብ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ናቸው።

የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ የትራንስፖርት ተርሚናሎች፣ የፓርኪንግ ሥፍራዎች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ ማረፊያ ሥፍራዎች፣ የሕጻናት መጫወቻዎች፣ የወንዝ ዳር ሰፋፊ ልማቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

የኮሪዶር ልማቱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ሳቢና ተመራጭ ከተማ ማድረግ፣ ቱሪዝምንና ኢንቨስትመንትን እንድትስብ ማስቻልም ሌሎች ዓላማዎቹ ናቸው።

በመጀመሪያው ዙር የኮሪዶር ልማት የከተማዋን ዋና ዋና እንደ ታሪካዊ ሥፍራዎች ያሉትን፣ የስብሰባ ማዕከላትን፣ ወዘተ ማገናኘትንም ዓላማው አርጎ ተሰርቷል። በእዚህ ሲኤምሲ የሚገኘውን አዲስ ኢንተርናሽናል ኮኔክሽን ማዕከል፣ ከጫካ ፕሮጀክት፣ ከዓድዋ ድል መታሰቢያና በአካባቢው ካሉ ታሪክ ሥፍራዎች ጋር የማስተሳሰር ተግባርም ተከናውኗል። የሜክሲኮ ሳር ቤት ቄራ ወሎ ሰፈር ቦሌ መንገድ የኮሪዶር ልማትም በእዚሁ በመጀመሪያው ዙር የተካሄደ ነው፡፡

የአንደኛው ዙር የኮሪዶር ልማት እንደተጠናቀቀ በዚህ የተገኘውን ተሞክሮ ጭምር በመቀመር በቀጥታ የተገባው ወደ ሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማት ነው፡፡, መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማት እየተከናወኑ ካሉት መካከል የካዛንችስ፣ የሜክሲኮ መስቀል አደባባይ መገናኛ፣ የኮሪዶር ልማት ሥራዎች ይጠቀሳሉ። የአራት ኪሎ ሽሮ ሜዳ እንጦጦ ማርያም እጽዋት ማዕከል፣ ቀበና ወንዝ ልማት ኮሪደር፣ የእንጦጦ ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር፣ ሳር ቤት ካርል አደባባይ ብስራተ ገብርኤል አቦ ማዞሪያ ላፍቶ አደባባይ ሀና ፉሪ ኮሪደርም በእዚሁ በሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው። የሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማትም በአብዛኛው እየተጠናቀቀ ነው። ከተጠናቀቁት መካከልም የካዛንችስ ኮሪደርና መልሶ ልማት አንዱ ነው።

በአዲስ አበባ የተጀመረው “የኮሪዶር ልማት” ሥራ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል። በዚህ ሀዋሳ፣ ሀረር፣ ጅማና የመሳሰሉት ከተሞች በልማቱ ብዙ ርቀት ሄደዋል። በልማቱ የበርካታ ከተሞችን መሠረተ ልማት በማሻሻል አካታች ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ይገኛል። በልማቱ የበርካታ ከተሞች የተጎሳቆሉ ሰፈሮች ተቀይረው ዘመናዊ፣ ውብና ምቹ የመኖሪያ፣ የሥራና የመዝናኛ ማዕከል እየሆኑም መጥተዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በኮሪደር ልማቱ በየከተሞቹ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ 192ቱ ተጠናቀዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት (የእግረኛ፣ የሳይክል፣ የተሽከርካሪ)፣ የመኪና ፓርኪንግ፣ የልጆች መጫወቻ ሥፍራ፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ ፋውንቴኖች፣ አደባባዮች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ፓርኮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እና የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጂንግ ስቴሽን በኮሪደር ልማቱ ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የኮሪዶር ልማቱ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና የአገልግሎት/ዩቲሊቲ/ መስመሮች ዝርጋታ ሥራዎችን በተሻለ ቅንጅት ለማከናወን አቅም መፍጠሩን ሚኒስትሯ ጠቅሰው፤ ስምንት ከተሞች የመጀመሪያ ዙር የኮሪዶር ልማት ሥራዎችን አጠናቀው ወደ ሁለተኛ ዙር መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በመጀመሪያው እና በሁለተኛ ዙር የኮሪዶር ልማት ሥራዎች ወደ ትግበራ ምዕራፍ ከገቡት 45 ከተሞች በአጠቃላይ 149 ሺህ 697 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

የኮሪዶር ልማት ፕሮጀክቶችን ሂደት በመከታተል እና በመገምገም እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያዎችን በማድረግ ስኬታማነቱንና አፈፃፀሙን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች በመሄድ የኮሪዶር ልማት ሂደቱ ምን ላይ እንዳለ ለማየትና የአዲስ አበባን ተሞክሮ ግንዛቤ ለመፍጠር መሠራቱን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህም ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሀሮማያ፣ ጎንደር፣ ሮቤ፣ ሻሸመኔ፣ ጅግጅጋ፣ ቦንጋ፣ ጅማ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሃዋሳ፣ ዲላ፣ ባሕር ዳር፣ ነቀምቴ፣ ወራቤ፣ ሆሳዕና፣አርባ ምንጭ፣ሚዛን አማን፣ ቢሾፍቱ፣ ሸገር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ጋምቤላ፣ ሰመራ ከተሞችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።

ባደጉት ሀገሮች የከተማ ልማት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን ዘመናዊ የከተማ ልማት የተጀመረው በዚህ የኮሪዶር ልማት ነው። አንዳንድ ያደጉ ሀገራት ሕንፃ ግንባታ ላይ መሰረት ያደረገ የከተማ ልማትን ተግባራዊ አድርገዋል፤ ይህም ለዜጎች እንቅስቃሴ ትኩረት ያልሰጠ ነው።

ለአብነት የ”ኒው ዮርክ” ከተማ ልማት ሕንፃ ግንባታ ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው እንደሲንጋፖር፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስና ዱባይ ያሉ ከተሞች ደግሞ ውበት እና ብርሃናማ ከተማ ለመገንባት ጥረት መሥራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ “ኮሪደር ልማት” ካደጉ ሀገራት አንፃር ሲታይ ዘግይቶ የተጀመረ መሆኑ በርካታ ጠቀሜታዎችን አስገኝቷል ሲሉም ሚኒስትሯ ተናግረው፣ የሌሎች ሀገራት የከተማ ልማት ስህተቶች እንዳይደገሙ፣ ወድቀው ሲነሱ ያገኙትን ልምድ የመጠቀም እድል እንዲኖር፣ እንዲሁም የአሁኑንና የቀጣዩን ትውልድ ፍላጎት ያስተሳሰረ ሥራ ለመሥራት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የክትመት ታሪክ አላት። እንደ እድል ሆኖ የኢትዮጵያ ከተሞች የጉስቁልና ማሳያ እና ከደረጃ በታች የሆኑ መሰረተ ልማቶችና መኖሪያ ቤቶች የሚገኙባቸው ሆነው ቆይተዋል። 54 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ከተማ/አዲስ አበባን ጨምሮ/ መሰረተ ልማታቸው በዓለም ደረጃ ከተቀመጠው ደረጃ በታች ነው።

ይህንን ያረጀና ያፈጀ የከተማ አካባቢን ለመለወጥ በቁጭት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሀገር እድገት አንዱ ማሳያ የከተሞች ልማት ምጣኔና ጥራት መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፤ ለዚህም ምቹ ፖሊሲ ተቀርጿል። በቀድሞ ፖሊሲ የከተሞችን እድገት በገጠሮች እድገት ላይ ጥገኛ ያደረገ ነበር። ይህም ከተሞች እንዲረሱ ያደረገ ነው ብለዋል።

በተለይ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ ከተሞቻችንን የጥገኞችና ሸማቾች እንዲሁም የጉስቁልና ማሳያ ሳይሆን የብልጽግንና የአዳዲስ ሃሳቦች እንዲሁም የምርምር መፍለቂያ ማዕከል እናደርጋቸዋለን በሚል ሰፊ ርብርብ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በዚህም በአዲስ አበባና በሌሎች ክልል ከተሞች የተከናወነው የኮሪዶር ልማት በሌሎች ሀገራት ግርምት መፍጠሩን ጠቅሰው፣ ይህም ልማት ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊነትን ጭምር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል። ምክንያቱም በኢንቨስትመንት ስም ታጥረው የነበሩ ቦታዎች ተወስደው ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች ተተክተዋል ብለዋል።

ይህንንም አብነት ጠቅሰው እንዳብራሩት፤ በኮሪደር ልማቱ ለተነሱ ወገኖች ብቻ 11 ሺህ 571 ቤቶች ተሰጥቷል። በልማቱ ከፈረሱት ቤቶች 90 በመቶው የመንግሥት የኪራይ ቤቶች ናቸው። በቤቶቹ ሳደባል ሆነው የሚኖሩም ነበሩ። ለእነዚህም ጭምር መኖሪያ ቤት የተሰጠበት ሁኔታ አለ።

የኮሪዶር ልማቱ ሰው ተኮር ነው ስንልም በምክንያት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ቀደም ሲል የመንገድና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ሲከናወኑ ቢቆይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማሕበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉ እንዳልነበሩ ተናግረዋል። አሁን የሰዎችን ክብር የሚመጥን፣ አረንጓዴና ለመኖር ምቹ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ አንድ ቆሻሻ አካባቢ ያደገ ልጅ እና በንጽህ አካባቢ ሌላ ልጅ ያደገ ዓለምን እና አካባቢያቸውን የሚያዩበት መንገድ ይለያያል። ከዚህ አንፃር የኮሪዶር ልማቱ የስብዕና እና የትውልድ ግንባታ እንዲዳብር ያደርጋል። የኢትዮጵያ ከተሞችም በአገልግሎታቸው የዜጎችን የአገልግሎት እርካታ ከፍ ከማድረግ ባለፈ የኮሪዶር ልማቱ ተወዳዳሪ ከተሞች እንዲፈጠሩ በማድረግ ረገድ አስተዋጽዖ እንዲሚያበረክት አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪዶር ልማት፤ አምስት መስመሮችን የያዘ ነበር። በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ሲኤምሲ ይገኙበታል።

የከተማ አስተዳደሩ፤ በመጀመሪያው ዙር የኮሪዶር ልማት በድምሩ 48 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ግንባታ አካሂዷል። የምዕራፍ ሁለት የኮሪዶር ልማትም እየተጠናቀቀ ይገኛል። ይህም 43 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ይህም ቦሌ፣ ለሚ ኩራ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞችን ያካተተ ነው።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት መጠናቀቅን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት የኮሪዶርና መልሶ ግንባታ ሲካሄድባቸው ከቆዩ ስምንት ዐበይት ኮሪደሮች አንዱ የካዛንቺስ አካባቢ ነው። የዚህ ግንባታ ተጠናቆ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት የካዛንቺስ መልሶ ማልማት በአገልግሎትም በእኩል ተጠቃሚነትም ኅብረተሰብን እንዲያገለግል የተቀረፀ ነው። “በአስደናቂ ፍጥነት አጭር ጊዜ የተጠናቀቀው የካዛንቺስ ኮሪደርና መልሶ ልማት ለዘመነ የከተማ ልማት ሥራ ለአረንጓዴ፣ ንፁህ እና ዘመናዊ የከተማ ማዕከላት መሠረት የሚጥል ነው።” ብለዋል።

የኮሪዶር ልማቱን ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ የመገንባት እና ከከተሜነት እድገት ጋር የተሳሳረ ልማት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ይህም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ልማት ለዜጎቻችን ያቀረብንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች ከምንሠራው የኮሪዶር ልማት ባሻገር፤ የገጠር ኮሪደር ልማት ጀምረናል። ይህም ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ኑሮ ይገባቸዋል በሚል የተጀመረ ነው። የተሟላ ብልጽግናን የምናረጋግጠውም በዚሁ መንገድ ነው ብለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሀገራዊ የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተር ፕላን ዝግጅት 70 በመቶ እንደደረሰ አስታውቋል። ከዚህ ጎን ለጎን ለሀገራዊ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት መሪ ፕላን የማስፈፀሚያ መመሪያ ሰነድ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛልም ብለዋል።

አጠቃላይ የፕላን ዝግጅቱ ካላፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ134 የከተማ ፕላኖች (65 በመቶ) ጭማሪ ማሳየቱን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በፕላን የሚመሩ ከተሞች ሽፋን 2016 ከነበረበት 87 ነጥብ ሁለት በመቶ ወደ 88 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጿል።

በተመሳሳይ ከገጠር ማዕከላት ስኬች ፕላን ዝግጅት ጋር በተያያዘ የገጠር ልማት ማዕከላትን ማሕበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ልማትና አገልግልቶችን የሚያበረታቱ አንድ ሺህ 930 ስኬች ፕላኖችን በማዘጋጀት በፕላን የሚመሩ የገጠር የልማት ማዕከላት ሽፋኑ በ2016 ከነበረበት 51 ነጥብ አምስት በመቶ ወደ 67 ነጥብ ሶስት በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን አመልክቷል።

ከፕላን ዝግጅቱ ባሻገር የከተሞች ፕላን አፈጻጸም በከተማ ፕላን አዋጅ፣ ስትራቴጂ፣ ማኑዋልና ስታንዳርድ መሠረት ስለመፈፀሙ የክትትል ሥራዎችን እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You