
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን እንደ ስሟ ውብና አበባ ለማድረግ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባሮች መካከል የኮሪዶር ልማት ተጠቃሹ ነው:: በኮሪዶር ልማቱ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ፣ ለጎብኚዎቿ፣ ለሥራ፣ ወዘተ፣ ምቹ ለማድረግ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት እየተሠራ ይገኛል::
በመጀመሪያው ዙር የኮሪዶር ልማት በተጎሳቆሉት የፒያሳ፣ ሠራተኛ ሰፈር፣ አራት ኪሎ፣ አቧሬ አካባቢዎች የመንግሥት ቤት ተከራይተው የሚኖሩትን በማንሳት ወደ ሌላ አካባቢዎች ምትክ ቤት በመስጠት የተሻለ አካባቢ እንዲኖሩ አድርጓል፤ ለባለይዞታዎች ደግሞ ምትክ መሬትና ካሣ በመስጠት አንስቷል:: ይህን ካደረገ በኋላም የአካባቢዎቹን መሠረተ ልማት በአዲስ ወደ መገንባት ገብቷል::
በዚህ ግንባታ የመስቀል አደባባይ ቦሌ፣ የሜክሲኮ ሳር ቤት፣ ቄራ ወሎ ሰፈር መንገዶችን ጨምሮ በርካታ ጎዳናዎች የማስፋፊያና የእግረኛ መንገድ ግንባታዎች ተካሂደውላቸዋል::
በሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማትም የካዛንችስ አካባቢን የደከመ ገጽታ መቀየር ያስቻለ የመንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ ወዘተ ሥራዎች ተካሂደው በቅርቡ ተመርቋል:: በዚህ ዙር ከሜክሲኮ መስቀል አደባባይ መገናኛ፣ ከሣር ቤት ካርል አደባባይ አቦ ላፍቶ ወዘተ ግንባታቸው እየተካሄደ ይገኛል:: ሌሎች መንገዶች ላይም ተመሳሳይ ግንባታ እየተካሄደ ነው:: እነዚህ ለአብነት የተጠቀሱ ናቸው::
በዚህ ልማት እነዚህ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆኑ የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶችን ጭምር የማስፋት የእግረኛ፣ የብስክሌት መንገዶች በሰፊው የመገንባት ሥራዎች ተሠርተዋል:: የውሃ የአሌክትሪክ፣ የፍሳሽ፣ የቴሌኮምና የመሳሰሉት መስመሮችም ከምድር በታች እንዲዘረጉ በማድረግ ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የሸረሪት ድር የሚመስል የኤሌክትሪክና የስልክ መስመሮች መሬት ውስጥ እንዲቀበሩ ተደርጓል::
የአረንጓዴ ስፍራዎች በስፋት ተፈጥረዋል፤ የወንዝ ዳር ልማትም እንዲሁ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል:: ሕንፃዎች በወጣላቸው ስታንዳርድ መሠረት ቀለም እንዲቀቡ ውጪያቸው ላይ መብራት እንዲገጥምላቸው ተደርጓል:: ፋውንቴኖች፣ የመፀዳጃ ቤቶች፣ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የታክሲና የአውቶብስ ተርሚናሎች፣ የካፌ አገልግሎት መስጫዎች፣ የምድር ውስጥ መተላለፊያዎች፣ ወዘተ ተገንብተዋል::
ዘመናዊ የመንገድ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ተተክለዋል፤ ምሰሶዎቹ ለደኅንነት መጠበቅ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ካሜራዎች፣ ዘመናዊ መብራቶች፣ ዲጂታል የማስታወቂያ ሰሌዳዎች የተገጠሙላቸውም ናቸው::
የእነዚህ መሠረተ ልማቶች መገንባት ግንባታዎቹ በተካሄዱባቸው አካባቢዎች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፤ የከተማዋ ገጽታ በእጅጉ ተቀይሯል፤ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች መሳለጥ ችለዋል፤ ወዘተ.
የኮሪዶር ልማቱ ፋይዳዎች ከዚህም ይሻገራሉ:: የአደጋ ስጋትን በመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል:: በተለይ በወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ በተዘረጉ አዳዲስ መሠረተ ልማቶች የአደጋ ስጋትን መቀነስ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል::
”ወቅታዊ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ለዘላቂ ደኅንነታችን ዋስትና” በሚል መሪ ሀሳብ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ከትናንት በስቲያ በተካሄደበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ ለአደጋ ስጋት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በቂ መሠረተ ልማት አለመኖር ነው። በፒያሳና ሠራተኛ ሰፈር አካባቢ ይደርስ ለነበረው ጎርፍ ምክንያቱ በቂ መሠረተ ልማት አለመኖሩ ነው:: አካባቢውን በኮሪዶር ልማት በማልማት በሰዎች ላይ ይደርስ የነበረውን አደጋ መቀነስ መቻሉም ተመላክቷል::
የኮሪዶር ልማቱ የአደጋ ስጋትን በመቀነስ በኩል ስላመጣው ለውጥ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመጋፈጥ ለዜጎች ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የኮሪዶር ልማቱ የአደጋ ስጋትን በመቀነስ በኩል አስተዋፅዖ ያደርጋል::
በአዲስ አበባ በኮሪዶር ልማቱ እየተከናወነ ያለው የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራ ከርዳታ ይልቅ በልማት ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ መፍጠር ያስቻለ ነው ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፣ በመዲናዋ እየተከናወነ ባለው የኮሪዶር ልማት የመንገድ፣ የመብራት እና የቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታዎች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባታቸው የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን በእጅጉ እንዲቀነስ እያስቻለ መሆኑን አስታውቀዋል:: የተለዩ የአደጋ ስጋት ቦታዎችን ለማሳወቅና በቅንጅት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ እያስቻለ ነው ብለዋል።
አደጋን አስቀድሞ ለመከላከልና አደጋ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን በቅንጅት ማከናወን የሚቻልበትን አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንጂነሩ ወንድሙ እንዳብራሩት፤ በአዲስ አበባ የአደጋ ስጋት ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እና ከአደጋ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ በቂ መሠረተ ልማቶች ባለመኖራቸው በርካታ ሰዎች የአደጋ ተጋላጭና ጉዳት ሲደርስባቸው ቆይቷል። ለአብነት በፒያሳና በካሳንችስ በቂ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የጎርፍ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነበር።
የተጠላለፉ የኤሌክትሪክ መስመሮችና የኤሌክትሪክ መስመሮችን የሚነኩ ዛፎች በብዛት መኖርም ሌላው የዜጎች የአደጋ ተጋላጭነት ደረጃን ያሳደገ ሁኔታ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በኮሪዶር ልማቱ መሠረተ ልማትን ከማሟላት ባለፈ ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የአደጋ ተጋላጭነት ወደሌለበት ቦታ የማዘዋወር ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል። በኮሪዶር ልማቱ መልሶ ማልማት የተሠራባቸው አካባቢዎች የነበሩ ቤቶች የሰው ልጅን ክብር የማይመጥኑ እና ቤት ለመባል ራሱ ብቁ ያልነበሩ ናቸው ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህም ብቻ ሳይሆን በቂ መሠረተ ልማት በአካባቢው አልነበረም። ይህንን ሁኔታ በኮሪዶር ልማት ሥራው በመቀየር ታሪክ መሥራት ተችሏል ብለዋል።
ከአደጋ ሥጋት ቦታው የተነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች የተሻለና ለመኖሪያ ምቹ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ወዳሉበት ቦታ እንዲዘዋወሩ መደረጉን ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ አዲስ አበባ ከሦስት ዓመት በፊት ውብና ምቹ መሠረተ ልማት አልነበራትም። ኮሪዶር ልማቱ ባመጣው እሳቤ በከተማዋ መሠረተ ልማትን ማሟላት ብቻ ሳይሆን በአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠት የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ ተሠርቷል። በዚህም የአደጋ ተጋላጭነት ደረጃንም መቀነስ ተችሏል።
በተለይ በወንዝ ዳርቻ ልማት በተከናወነው ተግባር በአብዛኛው ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ቦታዎችን ከአደጋ ስጋት ነፃ ማድረግ ተችሏል። አስቀድሞ ወንዞች ቆሻሻ የሚጣሉባቸው ሥፍራዎች ነበሩ። በዚህ ምክንያት በቂ ጎርፍ መሸከም ባለመቻላቸው የየአካባቢውን ነዋሪዎች ለጎርፍ፣ ለመሬት መንሸራተት፣ ለቤት መደርመስ አደጋ እንዲጋለጡ አርገው ኖረዋል::
በኮሪዶር ልማቱ ከተማዋን ለኑሮ፣ ለሥራና ለጎብኚ ምቹ ከማድረግ እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር በተጨማሪ የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን መቀነስ ተችሏል:: በዚህም በበርካታ ነዋሪዎች ላይ ይደርስ የነበረን ጉዳት መቀነስ ላይ ተደርሷል።
የመኪና መንገዶች ስፋት ጠባብ መሆን በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፣ የአብዛኛዎቹ መንገዶች አንደኛው መስመር አሽከርካሪዎች መኪናዎቻቸውን ያቆሙባቸው ስለነበር የትራፊክ መጨናነቅ እንዲፈጠር ሲያደርግ ኖሯል ብለዋል። በዚህም የአደጋ ምላሽ ሰጪ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት አደጋው የደረሰበት ቦታ እንዳይደርሱ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ተናግረው፣ ይህን ችግር የኮሪዶር ልማቱ ፈቷል ሲሉ ጠቅሰዋል።
በኮሪዶር ልማቱ የተገነቡ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የታክሲ ማቆሚያና ማውረጃ ቦታዎች የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት በማሳለጥ ከዚህ በፊት የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ የቀነሱና ለአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።
የአደጋ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የውሃ መሠረተ ልማት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በኮሪዶር ልማቱ የተዘረጉ በቂ የውሃ መሠረተ ልማቶች መዘርጋታቸውን አስታውቀዋል::
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ አብዛኛዎቹ የከተማዋ የውሃ መሠረተ ልማቶች ከተገነቡ የቆዩና በቂ የውሃ መጠን የሚሸከሙ አልነበሩም። በዚህም የተነሳ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ተሽከርካሪዎች ውሃ ሊቀዱ ሄደው ታንከሮቻቸውን ለመሙላት ረጅም ሰዓት የሚጠብቁባቸው ሁኔታዎች ነበሩ:: እነዚህ መሠረተ ልማቶች በኮሪዶር ልማቱ ተቀይረዋል።
የእሳት አደጋ መኪኖች ታንከሮቻቸውን ውሃ የሚሞሉባቸው ቦታዎች ሩቅ ነበሩ። በኮሪዶር ልማቱ እነዚህ መሠረተ ልማቶች በየግማሽ ኪሎ ሜትሩ እንዲኖሩ ማድረግ ተችሏል።
በዚህም የአደጋ ምላሽ ሰጪ ተሽከርካሪዎች ሩቅ ቦታ የማይሄዱበትና በቅርብ ውሃ ማግኘት የሚችሉበት መሠረተ ልማት ተገንብቷል። ይህም የአደጋ ጊዜ ምላሽ አቅምን ያሳደገ ሥራ ነው ብለዋል።
በኮሪዶር ልማቱ የምንገነባቸው መሠረተ ልማቶች ዛሬ የምንፈልገውን ብቻ የሚመልሱ አይደሉም ሲሉም ጠቅሰው፣ ለነገም ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መሠረተ ልማት መዘርጋት የተቻለበት ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል::
እንደ ኢንጂነር ወንድሙ ማብራሪያ፤ ሌላኛው በኮሪዶር ልማት የተከናወነው ተግባር የቴሌኮም መሠረተ ልማትን የማሻሻል ሥራ ነው። የቴሌኮም ተደራሽነት መስፋቱ የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱን ለማሳደግ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል ዕድል ፈጥሯል። በሁሉም የኮሪዶር ልማት በተካሄደባቸው ቦታዎች የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች መዘርጋት የሚቻልባቸው ሁኔታዎችንም መፍጠር ተችሏል። ይህም በአደጋ ጊዜ ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል::
የከተማችንን ደኅንነት ለመጠበቅ የደኅንነት ካሜራዎችን ለመግጠም፣ አደጋን አስቀድሞ በመተንበይ የመከላከያ ርምጃዎችን ለማከናወን፣ የአደጋ ጊዜ ደውሎችን ለማዘጋጀት የሚያስችል መሠረት መጣል የተቻለበት ሥራ መሠራቱን አመልክተዋል።
ከዚህ ባለፈ አደጋን የማሳወቂያ ቴክኖሎጂ ለአብነት የአየር ሁኔታ መረጃን የሚሰጥና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ወደፊት በኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ እንዲገጠም ይደረጋል። ይህም አዲስ አበባን ስማርት ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከኮሪዶር ልማቱ አንዱ የተገኘው ውጤት የመሠረተ ልማት ተቋማት ያመጡት ቅንጅት ነው። ከኮሪዶር ልማቱ በፊት አንዱ የመሠረተ ልማት ተቋም ያለማውን ሌላኛው የሚያፈርስባቸው በርካታ ሁኔታዎች ነበሩ። የተገነቡት መሠረተ ልማቶችም በቀላሉ የሚወድሙና ለአደጋ የሚያጋልጡ አሠራሮች ተግባራዊ ይደረግባቸው ነበር።
አሁን ሁሉም መሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ዛሬ የማይፈልጉት እንኳ ቢሆን ነገ ለሚዘረጉት መሠረተ ልማት በቂ የሆነ ቦታ እንዲያኖራቸው ያደርጋል። በዚህም ለመብራት፣ የቴሌኮም፣ የውሃና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ማስፋፊያ የሚሆን ክፍት ቦታ የማስቀመጥ ሥራ ተሠርቷል።
የኮሪዶር ልማቱ አንድ የመሠረተ ልማት ተቋም ልማት ካከናወነ በኋላ ሌላኛው መጥቶ የሚያፈርስበት ሁኔታ እንዳይኖር ተደርጎ የተሠራ መሆኑን ተናግረው፣ ጥገና እንኳን ቢያስፈልግ በቀላሉ ጥገና ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ቀላል እንዲሆኑ ተደርገዋል ብለዋል። ለአዳዲስ መሠረተ ልማቶች የሚሆን መጠባበቂያ ጭምር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። ከዚህ በኋላ ስለመሠረተ ልማት ቅንጅት የማናወራበት፣ አንዱ የሠራውን ሌላኛው ማፍረስ የማይችልበትን እና ተቋማት በተጨባጭ በጋራ መሥራት የሚችሉበትን አሠራር ማስቀመጥ መቻሉን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ አስቀድሞ በነበሩ የከተማ ፕላኖች ወንዞች እያሉ የሉም በሚል አካባቢው ለሌላ ልማት የሚውልበት፣ ሕገወጥ ወረራ የሚከናወንበት እና ሰዎች ለአደጋ ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ነበር። ይህንን ለመቅረፍ በአሥረኛው የአዲስ አበባ የከተማ ፕላን ክለሳ በማድረግ የወንዝ ዳርቻዎች ጥብቅ ቦታዎች እንዲሆኑ ተደርጓል።
በአካባቢው ግንባታዎችን ማከናወን ከተፈለገም ወንዞቹ ላይ ጉዳት በማያደርስና ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ እንዲሆን አሠራር ተቀምጧል። የአደጋ ስጋት ባለባቸው ቦታዎች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እንዲነሱ፣ አካባቢውም እንዲለማ ይደረጋል። ይህም በወንዝ ዳር ልማት በሚከናወንባቸው ቦታዎች ተግባራዊ ተደርጓል።
በዚህም የወንዝ ዳርቻዎቹ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ የተሠራ ሲሆን፣ ወደፊት የከተማ ግብርናና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጡበት ቦታ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ወንዞቻችንን ከብክነት የመከላከል ሥራም ጎን ለጎን እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ ለወንዞች የሰጠው አመለካከት አሉታዊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ወንዞቻችን ለዘመናት እንዲጎዱ አድርጓል። አሁን ግን ይህንን ሃሳብ ለመለወጥ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም