ለቀጣዩ የግብርናው ዘርፍ ስኬት መንደርደሪያ ሽልማት

የኢትዮጵያ መንግሥት ግብርና ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት መሠረት መሆኑን በሚገባ በመገንዘብ በወሰዳቸው አያሌ ርምጃዎች የዘርፍን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እየተቻለ ነው። በዘርፉ የሚለማው መሬት እንዲሁም የሚገኘው በየዓመቱ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል።

በግብርናው ዘርፍ ካለው እምቅ አቅም፣ ሀገር ከዘርፉ ከምትጠብቀው ሀብት አኳያ ሲታይ ግን ይህ ምርትና ምርታማነት ማደግ እንደሚጠበቅበትና ለእዚሀም በግብርናው ዘርፍ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲያስገነዘብ ቆይቷል።

ይህን ተከትሎም ግብርናውን ከተለመደው አሠራር በማውጣት በዓመት አንዴ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆኖ ሲመርትበት ከነበረው ሁኔታ በማውጣት በመስኖ ማልማት ውስጥ ተግብቷል። በመስኖ ማልማት ውስጥ መግባትና የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ብቻም ሳይሆን በመስኖ ስንዴ ልማት ከሀገርም አልፎ ተጠቃሽ ስንዴ አምራች መሆን ተችሏል።

ይህ እውን ሊሆን የቻለው ደግሞ መንግሥት ዘርፉን ለማዘመን፣ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት፣ እንደ ማዳበሪያ ላሉት ግብቶች በየዓመቱ በቢሊዮኖች ብር ድጎማ በማድረግ፣ ለሜካናይዜሽን ትኩረት በመስጠት፣ ለሜካናይዜሽን እርሻ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረውን የኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋትና በመሳሰሉት ላይ በወሰዳቸው ርምጃዎች ነው። በዚህም ሀገሪቱ በዝናብ ጥገኝነት ብቻ ታምርት ከነበረበት ሁኔታ እየወጣች ትገኛለች። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ እየታየ ያለው ለውጥ ለእዚህ ጉልህ ማሳያ ነው።

የመስኖ ልማቱ የሀገሪቱን ታሪክ መቀየር ጀምሯል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት መደበኛውን የዝናብ ወቅት ብቻ ጠብቆ ሲሰራ የነበረው የግብርና ሥራ በመስኖ ልማትና በሜካናይዜሽን መታገዝ ጀምሯል። ምርትና ምርታማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፤ ሀገሪቷ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት በማገዝ ምርትና ምርታማነቱን ከእጅ ወደ አፍ ታሪኩ ለማውጣት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው። በድርቅና በመሳሰሉት ወቅቶች የርዳታ ስንዴ ፍለጋ ወደ ውጭ ከማማተር ወጥታለች።

ሀገሪቱ ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ የምትችልበትን መንገድ ጠርጋ መጓዝ ጀምራለች። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመመደብ ስንዴ ከውጭ ማስገባቱ ቀርቷል፤ በምትኩ ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተጀምሯል።

ይህን ልማት የሚመራው የግብርና ሚኒስቴርም በተለይ በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ባከናወነው ስኬታማ ተግባር በቅርቡ በተከናወነ የስኬት ሽልማት መርሃ ግብር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሽልማት ተበርክቶለታል። ሚኒስቴሩን ጨምሮ አምስት የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተቀበሉበት ወቅት የሀገሪቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስኬቶች ተዘርዝረዋል። እኛም በዛሬው የስኬት ዓምዳችን የሚኒስቴሩን የስንዴ ልማት ስኬት እንዳስሳለን።

የምግብ ዋስትና ማረጋገጫና የሀገር የኢኮኖሚ መሠረት የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ እያስመዘገበ ያለውን አበረታች ውጤት ሲነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀዳሚነት የሚመጣው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ነው። ይህ የግብርናውን ዘርፍ ከስኬታማ ተቋማት መካከል ያቆመው አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባር ሀገሪቱ በስንዴ ልማት እውን ሊሆን የቻለው በመንግሥት ቁርጠኛነት ነው።

መንግሥት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን ከጀመረ ወደ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ወደዚህ ሀገራዊ ልማት ሲገባም ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ ነው። የፌዴራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ሀገራዊ ጉዳይ የጋራ ዕቅድ አውጥተው መክረው ፤ ዘክረው ነው ልማቱ ወደ መሬት ያወረዱት።

ዕቅዱም በቅድሚያ በቆላማ አካባቢዎች የቆላ መስኖ ስንዴ ልማት በሚል ተጀመረ። ይህ ልማት በቀጣዩቹ ዓመታት ቆላ፣ ደጋ ፣ ወይና ደጋ ሳይል በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ተተግብሮ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ልማቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሀገሪቱም በዓመት አንዴ እልፍ ቢል ሁለቴ ታምርት ከነበረበት ሶስቴ ወደ ማምረት ተሸጋግራለች።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ሀገሪቱ ስንዴ ከውጭ ሀገር የምታስመጣበትን ሁኔታ አስቀርቷል፤ ለእዚህ ይውል የነበረውን የውጭ ምንዛሬም አድኗል። በመንግሥት ቁርጠኝነት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማነቱ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በቆላማው የሀገሪቱ ክፍል አሀዱ ተብሎ በተጀመረበት ዓመት 100 ሺ ኩንታል ስንዴ ነበር የተገኘው፤ በ2016 ዓ.ም ደግሞ 120 ሚሊየን ኩንታል ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው።

የስንዴ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን በተደረገው ብርቱ ጥረት የተመዘገበው ውጤት የግብርናውን ዘርፍ ስኬታማ አድርጎታል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በይቻላል መንፈስ ስንዴን በመስኖ አልምታ ሕዝቡን ልታጠግብ ከራሷ አልፋም ለሌሎች ልትተርፍ የጀመረችው ጉዞ አበረታች ውጤት አስመዝግቧል። ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት የራሷን የስንዴ ፍጆታ ከመሸፈን አልፋ ለጎረቤት ሀገሮች ስንዴ መላክ ጀምራለች።

ባለፋት አራት ተከታታይ ዓመታት እንዲሁም ዘንድሮ እየተካሄደ ባለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለተገኘው አመርቂ ውጤት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት፣ የመንግሥት የተቀናጀ የፋይናንስ ድጋፍና ሀገራዊ የስንዴ የመስኖ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው በተለያዩ ወገኖች ይጠቀሳል።

እነዚህና መሰል ጥረቶችንና የተመዘገበውን ስኬት የተረዱ ኢትዮጵያውያን፣ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ልማቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ስንዴ አምራች ሀገር መሆን እንድትችል እያደረጋት ስለመሆኑ ምስክርነት ሲሰጡ ይደመጣል።

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንኳን ለራሳችን ለሌሎች የሚተርፍ ስንዴ ማልማት እንችላለን፤ ለዚህም መንገዱን ጀምረነዋል›› ሲሉ እንደተናገሩትም ሀገሪቱ በበጋ መስኖ አምርታ ብቻ በብዙ ሚሊዮኖች ኩንታል የሚቆጠር ስንዴ ማምረት ችላለች። ከምርቱም ከሀገራዊ ፍጆታ የተረፈውን ለጎረቤት ሀገሮች መላክም ተችሏል። በየዓመቱ እየጨመረ የመጣው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና ምርትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም ሀገሪቱን ስንዴ ለውጭ ገበያ እስከ ማቅረብ አድርሷታል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የዓለም አቀፍና አህገሪዊ ተቋማት፣ በሀገሮችም አድንቆትን ማትረፍ ችሏል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና በተደጋጋሚ አድንቀውታል፤ ሀገሪቱ በስንዴ ምርት ራሷን መቻሏን ጠቅሰው፣ በልማቱ የተገኘው ስኬት አፍሪካንም የሚያኮራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣልያን ሮም ከዓለም ምግብ ድርጅት /ፋኦ/ የተቀበሉት ሽልማትም በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባሮች ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ ያመለክታል። አንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች ከፍተኛ ባለስልጣናትም ይህን የኢትዮጵያን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጎብኝተው አድናቆታቸውን ሰጥተዋል፤ ተሞክሮም ወስደዋል።

አሀዛዊ መረጃዎችም የስንዴ ልማቱ በመኽር ወቅትና በበጋ መስኖ ልማቱ ምርታማነቱ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያሉ። በ2011 ዓ.ም በመኸር ወቅት በስንዴ ዘር የተሸፈነው መሬት አንድ ነጥብ ሰባት አምስት ሚሊዮን ሄክታር ሲሆን፤ ከዚህም 48 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ነበር የተገኘው።

በዘንድሮ 2015/16 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት በዘር የተሸፈነው መሬት ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል። ከዚህም 134 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

በ2011 ዓ.ም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 100 ሺ ኩንታል የስንዴ ምርት የተገኘ ሲሆን፣ በ2016 ዓ.ም ደግሞ በዚሁ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 120 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው።

በሌላ መረጃ በ2014 በጀት ዓመት በሀገር ደረጃ 60 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ የስንዴ ምርት ማግኘት የተቻለ ሲሆን፤ በ2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጋ መስኖ ከለማው አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዲሁም ከመኸር የስንዴ ማሳ 153 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በ2011 ዓ.ም በሶስት ሺ አምስት መቶ ሄክታር መሬት ላይ ማልማት መጀመሩን አስታውሰው፣ በተያዘው 2016 የምርት ዘመን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ይህ አሀዝ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን አስታውቀዋል።

በልማቱም ከፍተኛ ልምድ እንደተገኘበት ጠቅሰው፣ ይህንኑ ልምድ ማዳበርና ማካፈል በመቻሉ በቅርቡ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዕውቅና ሰጥቷል ሲሉ ገልጸዋል። የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት የሰጠው ዕውቅናም በግብርና ሥራ ውስጥ የተሳተፉ አርሶና አርብቶ አደሮችን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን ነው ያስታወቁት። ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ የረሃብ ምሳሌ ከመሆን ወጥታ አሁን በትክክለኛው የልማት መንገድ እየተጓዘች መሆኗን እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ፕሮግራም ባስመዘገበችው ውጤት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። በልማቱ የተገኘው ስኬትም የግብርና ሚኒስቴር ዕውቅና ተችሮታል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማትን በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በተካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ለኢትዮ ቴሌኮም የስኬት ሽልማት አበርክተዋል። በስኬት ስማቸው የተጠሩ ተቋማት በሰሩት ሥራ ለምስጋና የበቁት በዋናነት በሀገር ደረጃ ባላቸው ስኬት እንዳልሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ በአህጉር ደረጃ ባላቸው የመወዳደር አቅምና ባስገኙት ውጤት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ስኬት አዳጊ ነው፤ ስኬት አላቂ አይደለም። ስኬት ከአንደኛው ማይልስቶን ወደሚቀጥለው ማይልስቶን በአዳዲስ ትልምና ዕቅድ በአዳዲስ ፍላጎት በየጊዜው የሚያድግ እንጂ የሚቆም አይደለም›› ሲሉ አስገንዝበዋል። ‹‹ማይልስቶን የሚለው ሃሳብ የመጣው በየመንገዱ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ስንጓዝ የደረስንበትን ኪሎ ሜትር የሚያሳዩ ድንጋዮችን ታሳቢ በማድረግ ነው። ›› ሲሉ ገልጸዋል። የተሸለሙት ተቋማትም ከጅምሩ አሁን በደረሱበት ማይልስቶን ያሳኩትን ነገር ዕውቅና ለመስጠት እንጂ ጨርሰዋል ለማለት አይደለም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ግብርና በሚመለከት የዛሬ ሶስትና አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ታስገባ ነበር። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ስንዴ ከሚያመርቱ ሀገራት በዝቅተኛ ደረጃ የምትታይም ነበረች።

‹‹ዛሬ በአፍሪካ አንደኛ ስንዴ አምራች ብቻ ሳንሆን በአፍሪካ ሁለተኛ ስንዴ አምራቾችን በእጥፍ ደረጃ እንበልጣለን። ይህ ትልቅ ድል ነው፤ ነገር ግን ማይልስቶን ነው።›› ሲሉ አስታውቀው፣ ‹‹ጨረስን ሳይሆን ጉዞ ጀምረን የተወሰነ ኪሎ ሜትር ወደኋላ አስቀርተን ከፊታችን ምን ያህል እንደሚቀረን ለማወቅ ዕድል ሰጠን ማለት ነው›› ብለዋል።

ሀገሪቱ ግብርናው ዘርፍ በሩዝ፣ ግብርና በሻይ፣ ግብርና በቡና ከሁሉም በላይ ግብርና በሌማት ትሩፋት በዶሮ፣ በእንቁላል፣ በሥጋ በወተት ከአፍሪካ አንደኛ አምራች የሚለውን ስያሜ እስከምንይዝ ድረስ ይሄኛው ማይልስቶን ለሚቀጥለው ማይልስቶን መሸጋገሪያ እንጂ የመጨረሻው ማለት እንዳልሆነም አስታውቀዋል።

ከሁሉም በላይ ግብርናን ስንሸልም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን እየሸለምንና ዕውቅና እየሰጠን እንደሆነና ልፋትና ውጤታቸውን የማንዘነጋ መሆናችንን እያመላከትን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የግብርና ሚኒስትሩ የወሰዱት ሽልማት የመላው የኢትጵያውያን አርሶ አደሮች የመጀመሪያው ማይልስቶን መዳረሻና ዕውቅና መስጫ መሆኑ ሊታሰብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በተለያዩ የግብርና ዘርፎች የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በሙሉ አዳዲስ ድሎችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርጉ ያላቸውን ሙሉ እምነትም አስታውቀዋል።

መረጃዎች እንደሚያመላክተት፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በርዳታ የምትቀበለውን ስንዴ ጨምሮ በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ ስታስገባ ኖራለች። ለዚህ የስንዴ ግዢም በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታወጣም ነበር።

ይሁንና ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ በሙሉ ከመተካት ባለፈ ስንዴን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ችላለች። በተለይም የኩታ ገጠም የግብርና ሥራና የበጋ መስኖ ልማት ሥራዎቿን በማቀላጠፍ የጥረቷን ፍሬ ከራሷ አልፋ ለዓለም ማሳየት ችላለች። የዓለም ምግብ ድርጅት ሽልማት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ የስንዴ ልማቱ አድናቆት ከዚሁ የመነጩ ናቸው ማለት ይቻላል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You