አካል ጉዳተኛነታቸው ከመሥራት አልገደባቸውም፤ ይልቁንም አቅማቸው የሚፈቅደውን ለመሥራት አነሳሳቸው። ቁጭ ብለው መሥራት የሚችሉትን ሥራ በመምረጥም የጫማ ማስዋብ ሥራ ጀመሩ።
ጫማ የማስዋብ ሥራቸውን የጀመሩት ትምህርት እንዲጨርሱ ፣ ትምህርታቸውን መጨረሳቸው ደግሞ የጫማ ማስዋብ ሥራቸውን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው እንዲያደርጉ አስቻሏቸው።
ይህን ሥራቸውን ቀስ በቀስ እያሳደጉ መጥተው ከጫማ ማስዋብ ወደ ቆዳ ውጤቶች ማምረት የተሸጋገሩት የዛሬው ስኬት እንግዳችን የአሰፋ የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅት ባለቤትና መሥራች አቶ አሰፋ ሹንባጋ ናቸው፡፡
አቶ አሰፋ የአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። አካል ጉዳተኛ መሆናቸው ሥራ ፈጣሪ አድርጓቸዋል፤ አካል ጉዳተኝነታቸው ምንም ሳያግዳቸው በጫማ ማስዋብ የጀመሩትን ሥራ እያሳደጉ ትልቅ ደረጃ መድረሳቸውን ይገልጻሉ። ከዚህም አልፈው ለሌሎች ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር መቻላቸውን ይናገራሉ።
አቶ አሰፋ ከመጀመሪያው አንስተው ፍላጎታቸው በትንሹ ጀምረው ትልቅ ደረጃ መድረስ ነው። ‹‹የጫማ ማሳመሩን ሥራ ሲጀምር አካል ጉዳተኛ መሆኔ ችግሮች እንዲበረቱብኝ ቢያደርግም፣ ችግሮቹን አልፋቸዋለሁ፤ ሥራውንም እችለዋለሁ ብዬ በማሰብ ስለጀመርኩ ተግዳሮቶቹን ሁሉ እንደየአመጣጣቸው አልፌያቸዋለሁ፤ የኮቪድ ጊዜውን ከባድ ፈተናም ሳይቀር አልፌዋለሁ›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሰዎች አልችልም ብለው ራሳቸውን ከማሳመን ይልቅ እንደሚችሉና ፈተናዎችን እንደሚያልፉ ደጋግመው ለራሳቸው መንገር እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ ራሳቸውን ካሳመኑ ያሰቡበት ቦታ እንደሚደርሱ የእርሳቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንደተናገሩት፤ አቶ አሰፋ ሥራን አሀዱ ብለው የጀመሩበት የጫማ ማስዋብ (ሊስትሮ) ሥራ ብዙ ልምዶች የቀሰሙበት ነው፤ ይህም አሁን ላሉበት ደረጃ አብቅቷቸዋል። ሥራቸውን በየጊዜው ለማሳደግ ያላቸው ጽኑ ፍላጎት የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት መክፈት አስችሏቸዋል ፡፡
ጫማ በሚያስውቡበት ወቅት ከጫማ ማስዋብ ባለፈ ጫማዎችንም የመስፋት፣ ሶል የመቀየርና የማደስ ሥራ ሲሠሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ይህንን አጠናክረው በማስቀጠልና በማስፋት ጫማ፣ ቦርሳና የመሳሰሉትን የቆዳ ውጤቶች ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ከጫማ ማስዋብ፣ መስፋትና ማደስ ሥራ ብዙ ልምዶችን አግኝቻለሁ፤ ከቆዳ ውጤቶች ጋር እንድተዋወቅ አድርገውኛል። አሁን ላለሁበት ደረጃ መሠረት ሆነውኛል›› የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግና በማሳደግ በቆዳ ምርቶች ኢንዱስትሪ እንዲሰማሩ ምክንያት እንደሆኗቸው ይገልጻሉ።
አቶ አሰፋ ጫማ በማስዋብ ባጠራቀሙት ሦስት ሺህ ብር መነሻ የቆዳ ውጤቶች ማምረት የጀመሩ ሲሆን ድርጅታቸው ወደ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋግሮ እየሠራ ይገኛል። የቆዳ ምርቶች መሥራት ሲጀምሩም የሥራቸው መጀመሪያ ያደረጉት ጫማ መሥራትን እንደነበር አስታውሰዋል።
ለሥራው የሚያስፈልገውን የመሥሪያ ቦታ ለማግኘት በጠየቁት መሠረት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ማምረቻ ሼድ ሰጥቶቸዋል። ይህን ይዘውም በ2009 ዓ.ም አሰፋ የቆዳ ውጤቶች አምራች የተሰኘ ድርጅት ከፍተው የቆዳ ምርቶችን ወደ ማምረት በስፋት መግባታቸውን ይገልጻሉ። ጫማዎችን ከመሥራት ጎን ለጎን ፣ ቦርሳ ፣ ቀበቶ ፣ ዋሌት እና የመሳሰሉትን አጠቃላይ የቆዳ ምርቶች ወደ ማምረት መግባትም ሥራውን እያጠናከሩ መምጣታቸውን አጫውተውናል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅታቸው ከህጻናት ጀምሮ እስከ አዋቂ ድረስ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘመኑን የተከተሉ ተፈላጊ የቆዳ ውጤቶችን ያመርታል። ነጠላ ጫማዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጫማዎችን፣ የተማሪ ቦርሳዎችን፣ የኪስ ቦርሳዎችን፣ ቀበቶዎችን እና ሌሎች የቆዳ ምርቶች እያመረተ ይገኛል።
አቶ አሰፋ ቀስ በቀስ ከቀድሞው አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድር በመውሰድ ሥራውን ማስፋፋታቸውን ጠቅሰው፣ የምርቶቻቸውን አይነት መጨመር መቻላቸውንም ይገልጻሉ። የተማሪ ቦርሳዎችን ለየት ባለ መልኩ እያመረቱ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ክልሎች እንደሚልኩ ጠቅሰዋል።
አቶ አሰፋ እንደተናገሩት፤ የድርጅቱ ምርቶች በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ፣ የምርቶቹም ፈላጊዎች እንዲበዙ ለማድረግ አሁንም ጠንክረው እየሠሩ ናቸው። ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀደም ሲል ተሰጥቷቸው ከነበረው 12 ካሬ የመሥሪያ ቦታ በተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ ተጨምሮላቸው የመሥሪያ ቦታቸው ሃያ ካሬ ደርሶላቸዋል። ይህም የበለጠ እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡
‹‹ሥራችን ታይቶ ከዚህም በላይ እንደምንሠራ ታምኖበት ነው የማስፋፊያ ቦታ የተሰጠን›› የሚሉት አቶ አሰፋ፤ አሁን ተጨማሪ ማሽኖችን አስገብተው ሥራውን ለማስፋፋት አቅደዋል። ሌላ ተጨማሪ ማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ ማቅረባቸውን ይገልጻሉ። ለዚህም ምላሽ ሲያገኙ ሥራዎቻቸውን ከዚህ የበለጠ በማስፋፋት ትልቅ ድርጅት የመመሥረትና ለብዙ ሰዎችም የሥራ እድል ለመፍጠር አቅደው እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለቆዳ ምርቶች የሚውሉ ግብዓቶች ወይም መለዋወጫዎች (አክሰሰሪዎች) ከውጭ እንደሚመጡ ጠቅሰው፣ የመለዋወጫ (አክሰሰሪ) እጥረት እንዲሁም የቆዳ ዋጋ መናር እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቁመዋል ።
‹‹የቆዳ ዋጋ ርካሽ ነበር ፤ አሁን በሬ ታርዶ ቆዳው የትም እየተጣለ በሌላ በኩል ደግሞ የቆዳ ዋጋ እየናረ ነው ሲሉ አመልክተዋል። ማምረቻው የሚያስፈልገው ኬሚካል ከውጭ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ የዚህም ዋጋ ውድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አሰፋ እንዳሉት፤ እንደ ኬሚካልና አክስስሪ አይነት ግብዓቶችን ከውጭ በሚያስመጡትም ሆነ በሚያመርቱ ድርጅቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት አለበት፤ ይህ ሲሆን ግብዓቶችንና አክሰሰሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ይቻላል።
ይህ ሲሆን የቆዳ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ አይቸግርም። መንግሥት በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ ተኪ ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ሁሉ በቆዳው ዘርፍ የሚሠሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ድጋፍ ሊያደርግም ይገባል።
ተኪ ምርት አምራቾች ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባውን ምርት ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝም ማድረግ አለባቸው።
ድርጅቱ መሸጫ ቦታ እንደሌለውና በቂ የገበያ ትስስር መፍጠር እንዳልቻለም አስታውቀው፣ አብዛኛዎቹን ምርቶቹን እየሸጠ ያለው በማምረቻ ቦታው ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል። ይህም ምርቶቹን በሚፈልገው ልክ እያመረተ ለተጠቃሚ ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት መሆኑን ያስረዳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የገበያ ትስስር እንደልብ ቢገኝና በሚፈልገው ልክ መሥራት ቢቻል የቆዳ ውጤቶች ሰፊ ሥራ የሚሠራባቸው ብዙ አይነት ምርቶች የሚመረትባቸው ናቸው፣ በዚህ ልክ ቢሠራ ከራስ አልፎ ለሌሎች አካል ጉዳተኞችና ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል።
የድርጅቱ ምርቶች ህብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ ተመሳሳይ ምርቶች ሌላ ቦታ ላይ ዋጋቸው ከእጥፍ በላይ እንደሆነና ይሄ አግባብነት እንደሌለውም አስገንዝበዋል።
በገበያ ላይ 6ሺህ እና 5ሺህ ብር የሚባሉ ጫማዎች እኛ ጋር አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ይገኛሉ ሲሉም አመልክተው፣ ቀበቶ እንዲሁ በሌላ ገበያ 900 ብር እንደሚሸጥ ጠቅሰው፣ የእሳቸው ድርጅት ግን ዋጋ በግማሽ ያህል እንደሚቀንስ ገልጸዋል። ምርቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እየቀረቡ ያሉት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን ጠቅሰው፣ የድርጅታቸው ምርቶች ጥራት የተሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ድርጅታቸው በሙሉ አቅሙ እያመረተ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የገበያ የገበያ ትስስሩ ቢሰፋ ከፍተኛ የማምረት አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል። ወደፊት የማስሪያና መሸጫ ቦታዎች ከተመቻቹ ምርቶቹን በእጥፍ በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ልምዶችን እየቀሰመ ጫማዎችን መጀመሪያ ከሚሠራበት መንገድ በተለየ ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ ማምረት ጀምሯል። ወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል። ምርቶቹን ለማስተዋወቅ ማህበራዊ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም እያስተዋወቀ መሆኑንም አመልክተዋል።
መንግሥት ለተኪ ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ አምራቾችን እየደገፈ ነው። የቆዳ ውጤት አምራቾችም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲችሉ ድጋፍ የሚያደርግ አካል እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው፣ ድጋፉ ከተገኘና የገበያ ትስስሩ ከተመቻቸ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ እኔ ለዚህ ደረጃ እንድበቃ አስችሎኛል ሲሉም ተናግረው፣ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ አካላት የተለያዩ ድጋፎች እንዳደረጉላቸው አስታውቀዋል። የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በሚያዘጋጀው አውደርዕዮች ላይ እንዲሳተፉ እድሉም እንደተመቻላቸውና እየተጠቀሙበት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የድርጅቱ ምርቶች ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የሚተኩና ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ድርጅቱ ምርቶቹ በቀጣይም ይበልጥ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ አድርጎ በመሥራት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ያሉትን እድሎች ይጠቀማል ብለዋል።
በአውደ ርዕይና በባዛሮች ላይ ምርቶችችን እየገዙ ወደ ሀገራቸው ይዘው የሚሄዱ የውጭ ሀገር ዜጎች ምርቶቻቸውን ሲያደንቁ እንደሚሰሙም ይገልጻሉ። ‹‹ አንድ ምርት ከውጭ ስለመጣ ብቻ ጥራቱን የጠበቀ ይመስለንና እንታለል ነበር›› ሲሉ ጠቅሰው፣ አንድ ምርት በሀገር ውስጥ ስለተመረተ ብቻ ጥራት እንደሌለው አድርገን መቁጠር የለብንም ብለዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የድርጅታቸው ምርቶች ጊዜያቸውን የጠበቁና ፋሽኑን የተከተሉ ናቸው። በክረምት የተማሪ ቦርሳዎች በብዛት በመሥራት፣ ለሙቀት የሚሆኑ ጫማዎች ይሠራሉ። በበጋ ነጠላ ጫማዎች፣ የኪስ ቦርሳዎችን ቀበቶዎችን በመሥራት ወቅቱን የጠበቀ ምርት ይመራታል።
‹‹የድርጅቱ ደንበኞች የሚፈልጉትን አይነት ምርት በሚፈልጉት ጊዜ ስለሚያገኙ መርጠው ይገዛሉ›› ሲሉ ገልጸው፣ በሚገዙት ምርትም ደስተኛ መሆናቸውን ከሚሰጡን ግብረ መልስ እየተረዳን ነው ብለዋል።
አቶ አሰፋ እንዳሉት፤ ምርቶቹ ከቆዳ የሚሠሩ ስለሆነ በጥንቃቄ ከተያዙ ቀለማቸው ሳይቀይርና ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ ሊያገለግሉ ይችላሉ። ሁሉም ሰው የሀገሩን ምርት ቢገዛ አንደኛ ሀገሩን ያሳድጋል፣ ሁለተኛ ከውጭ ምርቶቹን ለማምጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል። ስለዚህ ሁሉም ሰው የሀገሩን ምርት መጠቀም፣ በሀገር ምርት መኩራት ይኖርበታል።
ድርጅታቸው ለስድስት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠሩን፣ ካፒታላቸውም ከሶስት ሺህ ስድስት መቶ ሺህ መድረሱን አስታውቀዋል። ድርጅቱ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻርም ህብረተሰቡን በሚያሳተፉ ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፍ አቶ አሰፋ ገልጸዋል። የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ፤ ማዕድ በማጋራት ካላቸው እያካፈሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹አካል ጉዳተኛ ብሆንም መሥራት በመቻሌ ከራሴ አልፌ ሌላውን ለመርዳት ችያለሁ፤ እኔ ኖሮኝ ሌላው ሲራብ ማየት አልፈልግም ፤ባለኝ አቅምና በምችለው መጠን በሚጠበቅብኝ ሁሉ ለመርዳት ጥረት እያደረኩ ነው›› ይላሉ፡፡
አካል ጉዳተኛ ሆነው ብዙ የሚሠሩ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱና እጅ ሳይኖራቸው በእግራቸው የሚሠሩ አካል ጉዳተኛ አሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት መስጠት ከተቻለ ከማንም በላይ መሥራት እንደሚችሉ አቶ አሰፋ እሳቸው ምስክር መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ‹‹አካል ጉዳተኛ ነኝ፤ መሥራት አልችልም ብለው የማይሠሩ ሰዎች የሚሠሩትን እያዩ ተሞክሮ ወሰደው ቢሠሩ የሰው ርዳታ ሳይጠብቁ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች መትረፍ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም