የልጅነት ምኞቷን ያሳካች የመብራት ጌጥ አምራች

የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን አርክቴክት ሣራ ስዩም፤ የልጅነት ምኞቷን ለመኖር ብዙም አልተቸገረችም:: ከአስተዳደጓ ጀምሮ አሳምራለሁ ብላ በምታደርገው ጥረት የቤት ዕቃ ስትጨርስ ቤተሰቦቿ አላስደነገጧትም፣ እየቀጡ አላማረሯትም:: የሚያበረታታት እንጂ የሚያጥላላ አላጋጠማትም::

መቁረጥ፣ መቀጠል እና ቅርጻ ቅርፆችን መፍጠር አንዳንዴም ብሎን ፈቶ መግጠምን የመሳሰሉት መዝናኛዎቿ፤ የልጅነት ጨዋታዋ ምንጭ ከመሆን አለፉ:: በማንም ሳይጎዱ እና ሳይሰበሩ ከሰውነቷ እኩልም በውስጧ አደጉ:: በዚህ ውስጥም የማስዋብ እና ቅርፅ የማውጣት ፍላጎት ሃሳብ በውስጧ እየተጸነሰ መጣ::

ቀለማትን እና ቅርፆችን በጥልቀት የማየት ተሰጥኦን የተጎናፀፈችው አርክቴክት ሣራ፤ ሰሜን ሸዋ ፍቼ ከተማ ተወልዳ፤ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸር የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች:: ዕድለኛ ሆና ትምህርቷ ከልጅነት ፍላጎቷ ጋር ተቀራረበ:: ያሰበችው የሚሳካላት፤ የያዘችው የሚባረክላት ናትና፤ አሁንም የምትወደውን እየሠራች ትገኛለች::

ከልጅነት ፍላጎት ባሻገር፤ አርክቴክቸር ስትማር ስለ ዲዛይን ማወቅ መጀመሯ፤ የዲዛይን መሠረታዊ ሕግጋትን (ፕሪንስፕሎችን) መረዳቷ የበለጠ ሕይወቷ በሥነ ውበት ላይ እንዲመሠረት ዕድሉን ፈጠረላት::

አርክቴክት ሣራ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት የመብራት ጌጥ ለመሥራት ሃሳብ አልነበራትም:: በዲዛይን እና ጌጣጌጥ ሥራ ውስጥ መግባት ትፈልግ ነበር:: ገና ትምህርቷን ለማጠናቀቅ የመመረቂያ ጥናት ስታካሂድ፤ ሕይወቷ በአንድ መንገድ ላይ መጓዝ ጀመረ:: ለመመረቅ ጥቂት ሲቀራት ሞዴል ለመሥራት መርካቶ ሄደች:: የተቆራረጡ ቆዳዎችን በኪሎ እየገዛች የእጅ ጌጦችን እየሠራች መሸጥ ጀመረች::

ቆራርጣ የቀጠለቻቸው ቆዳዎች የእጅ ጌጥ ሆኑ፤ በብዙዎችም ተወደዱላት:: የምትሠራቸው ጌጣጌጦችና ቅርጻ ቅርጾችም ሆኑ የቀለም ቅንብራቸው በብዙዎች እየተወደዱ ከሰዎች የመቀራረብ ዕድል አገኘችባቸው::

ከደንበኞቿ መካከል አንዷ ‹‹ለምን ኤግዚቢሽን ላይ ይዘሽ አትቀርቢም?›› ስትል ጥያቄ አቀረበችላት:: ሣራ ሃሳቡ ቢኖራትም ግንኙነት የመፍጠሪያ መንገድ አጥታ እንደቆየች ገልፃ፤ ኤግዚቢሽን መሳተፍ መጀመሯን ትናገራለች::

ኢግዚቢሽኖቹ ሥራዎቿን አደባባይ ለማውጣት አስቻሏት፤ በሰፊው ተረካቢም አገኘች:: ምርቶቹን ወደ ውጭ መላክም ጀመረች:: ሰዎች ጥሩ ምርት እንደሚፈልጉና ምርቶች በጥራት ከተሠሩ የትኛውም ሰው ከመግዛት ወደ ኋላ እንደማይል ያረጋገጠችው ሣራ፣ ‹‹የእጅ ጌጥ መሥራት ደስ ይላል፤ ብዙዎች በዚህ ተማርከዋል፤ የገበያ ችግር አልነበረብኝም›› ትላለች::

ሆኖም በእጅ ጌጥ ምርት ብቻ መርካት አልቻለችም:: ከተማረችበት ሞያ በተወሰነ መልኩ እየራቀች መምጣቷ ቅር እያሰኛት መጣ:: በተማረችው ሞያ አዲስ ነገር መፍጠር ፈለገች:: አዲስ ነገር ለመሥራት ስታቅድ፤ ሥራዋ ከፍ ብሎ ቤቶችን እና ቢሮዎችን ማስዋብ እንዲሆን አሰበች::

የቤት ውበት (ኢንቴሪየር ዲዛይን) ምርጥ ሊሆንላት እንደሚችል ገመተች:: ለማስዋብ የተፈጠረች ናትና እሱኑም ተያያዘችው፤ እየተዋጣላትም መጣ:: ሰዎችን ቀጥራ ስታሠራ እና ስትሠራ በሥራዋ ሂደት ለቤት ማስዋቢያ የሚያገለግሉ፤ አሁን በኢትዮጵያ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማግኘት ያለው ችግር ምንድን ነው? ብላ መጠየቋን ቀጠለች::

ቤት የማስዋብ ሥራ ስታከናውን የምትፈልጋቸው የእንጨት ሥራ ውጤቶች፤ ሶፋ፣ ቁም ሳጥን፣ ኪችን ካቢኔት፣ ሴራሚክ፣ ታየልስ እንዲሁም ሌሎች ከውጭ የሚመጡ ቢሆንም፣ በሀገር ውስጥ እንደሚመረቱም አወቀች:: የቤት ሥነ ውበት ( ኢንቴሪየር ዲዛይን ) ስትሠራ እና ቤቶችን ስታስውብ በኢትዮጵያ ከማምረት አንፃር የጎደለውን ስታይ፤ ያልተለመዱ የተለዩ የመብራት ጌጣጌጦችን ማግኘት ከባድ መሆኑን እየተረዳች መጣች::

ከሥራ አጋሮቿ ጋር ሆና የፈለጉትን ብቻ ሳይሆን የማይፈልጉትን የተጋነኑ የቅንጦት የመብራት ጌጦችን ይሠራሉ ብለው ወዳመኑባቸው ድርጅቶች ሄዱ፤ ያገኙት መልስ ግን ‹‹ እኛ የመብራት ጌጥ አናመርትም፤ ጌጡ የሚመጣው ከውጭ ነው::›› የሚል ነበር::

በተደጋጋሚ በቤት ሥነ ውበት ላይ የሚሠሩ ሰዎች በብዛት እና በጥራት እንዲሁም በተለየ ዲዛይን የመብራት ጌጥ ለማግኘት ተቸግረው እንደነበር እንዲሁም ከውጭ ከማምጣት ውጭ የሚያመርቱ አለመኖራቸውን አረጋገጠች::

‹‹የመብራት ጌጥ በኢትዮጵያ መቶ በመቶ የሚመጣው ከውጭ ነበር:: ሆቴል ምርቱን ከአስመጪዎች በተጨማሪ ሪል ስቴት ገንቢዎች እንዲሁም ግለሰቦች ሳይቀሩ ለቢሮ እና ለቤታቸው ከውጭ ያስመጣሉ::›› የምትለዋ አርክቴክት ሣራ፤ ጌጡ ሲመጣ ለመጓጓዝ ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ፣ በሚፈለግበት ጊዜም እንደማይገኝ ትናገራለች::

‹‹የዲዛይን አማራጮች የሉም:: አንድ ጊዜ በብዛት ሲፈለግ ለምሳሌ 500 ጌጥ ከተገዛ በኋላ አሥር ተጨማሪ ቢፈለግ፤ ገበያው ላይ አይኖርም›› ስትል ገልጻ፡ ‹‹ከውጭ የሚገዛውን የመብራት ጌጥ በመርከብ ለማጓጓዝ ያለውን ሂደት መከተል ይጠይቃል፤ ይህ ውጣ ውረድ በቀላሉ አይታይም›› ትላለች::

ከእነዚህ ሁሉ በተጨማሪም የመብራት ጌጡን ለማስመጣት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል አመልክታ፣ ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ በማስገባት፤ በሀገር ውስጥ ማምረት የግድ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሷን ትገልፃለች::

እንደ አርክቴክት ሣራ ገለፃ፤ ምርቱን ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ ግምት ውስጥ በማስገባቷ ለሚፈለገው ዓላማ መሆን የሚችል ብዛት እና የሚፈለገውን ዲዛይን ለማግኘት በውጭ ምርት ላይ የተመሠረተውን የመብራት ጌጥ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እና ትልቅ ለውጥ ማምጣት ግዴታዋ መሆኑን በማሰብ ለራሷ ቃል ገባች::

አንድ ኪሎ ሽቦ በመግዛት በአንድ መብራት ሥራ የቤት ማስዋቡ ተጀመረ፤ ወረቀት እና ጨርቆችን በማጣጠፍ እንዲሁም የእንጨት ቅርፆችን በማውጣት ሙከራዋን አጠናከረች:: ‹‹ጥራቱ የተጓደለ ‹ግዢው› ብባል የማልገዛውን ዕቃ ገበያ ላይ ይዤ አልወጣም:: በማለትም ለአምስት ዓመታት በሙከራ ሥራ ላይ ቆይቼለሁ::›› ስትል አርክቴክት ሣራ ተናግራለች::

በሂደት ግን አድናቆትን ያተረፉ ጌጦችን መሥራት ውስጥ ገባች:: በምታደርጋቸው የቤት ሥነ ውበት ሥራዋ ላይ የራሷን የመብራት ጌጥ መጠቀም ጀመረች:: ብዙዎች እየተደሰቱ፤ ‹‹ውበቱ የተለየ ነው›› ማለት ሲጀምሩ፤ ጌጦቹን ራሷ እንደሠራቻቸው ተናገረች::

ሰዎች የመብራት ጌጦቹን እየወደዱ ሲመጡ፤ እየተደዋወሉ እየተጠራሩ ከእርሷ የመብራት ጌጦችን መግዛት ጀመሩ:: ጌጦቹን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር፤ ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ መሆኑን አረጋገጠች:: በብዛት ወደ ማምረት ለመግባት ራሷን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልጋት አምና ነገሮችን መስመር ማስያዝ እንዳለባት ተረዳች::

ምን ምን ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለባቸው የሚሉትን በመለየት ሰፋ ወዳለ ምርት እንዴት መቀየር እንደምትችል ደጋግማ ያሰበችው አርክቴክቷ፣ በብዛት ማምረት ስለሚቻልባቸው መንገዶች፣ ስለገበያ ሰንሰለት፣ የሰው ሀብትን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል በማሰብ ራሷን የሚያበቃትን ሥልጠና መውሰዷንም ታስታውሳለች::

ከአምፖል አቃፊ እና ከአምፖሎች ውጭ ከ70 በመቶ በላይ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን ማለትም ብረት፣ እንጨት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ክር፣ ወረቀት እና ፕላስቲክ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተመረቱ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ጨምሮ በመጠቀም ጌጦቹን ማምረት ጀመረች:: የግብዓት እጥረት እንዳይፈጠር ብሎኖች እና ሚስማሮችን ራሷ ማምረቱን ተያያዘችው:: ሌሎች እንስት አጋሮችን በማሳተፍ፤ የመብራት ጌጥ ማምረቱን ሥራ ውጤታማ አደረገችው::

በዚህ ሥራ ለሆቴሎች፤ ለካፌ እና ለሬስቶራንቶች በመሥራት ታዋቂነትን እያተረፈች የመጣች ሲሆን፣ ለግለሰቦች መኝታ ቤቶች ግድግዳ እና ኮርኒስ ላይ የሚንጠለጠሉ፤ መሬት ላይ የሚቆሙ ጌጦችን እየሠራች፤ የመብራት ጌጥ የሚያመርት ቡስካ ላይት የሚል ድርጅት ለማቋቋም በቃች::

በሀገሪቱ ከተሞችን የሚያዘምን የኮሪደር ልማት እየተካሄደ ነው:: ልማቱ ደግሞ ከሥነ ውበት ጋር ተያይዟል:: ስለዚህ ጥራት ያላቸው የመብራት ጌጣጌጦች የሚፈለጉበት ወቅት ነው:: ለዚያ ደግሞ ጥራቱን የጠበቀ ዕቃ ይፈለጋል:: አርክቴክት ሣራ እና አጋሮቿ ጊዜው አመቺ ሆነላቸው:: ገበያው ላይ በመውጣት ከሌሎች ጋር ተባብረው ማሰራጨታቸውን ተያያዙት::

አርክቴክት ሣራ በማምረቻ ቦታም ሆነ በዋናው መሥሪያ ቤት 15 ቋሚ ሠራተኞችን ቀጥራለች:: እንደ ሥራው ትንሽነት እና ትልቅነትም በብዛት ትዕዛዝ ሲኖር ከ30 እስከ 50 ሰዎች በጊዜያዊነት ትቀጥራለች::

ብዙ ጊዜ ከሴቶች ጋር እንደምትሠራም አርክቴክት ሣራ የገለጸችው:: ‹‹ሴቶችን ምርጫዋ ያደረገችው በተፈጥሮ ጠንቃቆች፣ አስተዋይ፣ ውበት እና ሞያ ነክ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት የሚያዩ እንዲሁም መጠንከር እና መበርታት ስላለባቸው ነው የሚል እምነት አለኝ›› ስትል ገልጻለች::

ለሰዎች የሚጠቅመው ገንዘብ ብቻ አለመሆኑን የምታስረዳዋ አርክቴክት ሣራ፤ አቅጣጫን ማሳየትም ትልቅ ነገር ነው ትላለች:: ‹‹ምንም እንኳ ሌሎች ሰዎች፤ ‹ ሥራሽን ጥለው የሄዱብሻል፤ አታስለምጂ› ቢሉኝም ያገኘሁትን ልምድ ለሰዎች በተለይ ለሴቶች ማካፈል እንዳለብኝ አምናለሁ:: ብዙ ሴቶች የኔን ሥራ እየለመዱ ራሳቸውን እንዲያወጡ አበረታታለሁ›› በማለት ትናገራለች::

አንዳንዴ ከሴቶች ጋር ስትሠራ እንደማትግባባ ገልፃ፤ የእዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሴቶች ከባዶ ተነስተው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደማይችሉ ማመን እንዳለባቸው አስገንዝባለች:: የመብራት ጌጦቹ ተሰቅለው ሲያዩ ‹‹እስኪ እኔንም አስለምዱኝ›› የሚሉትን ወንዶችንም ሆኑ ሴቶችን በራሳቸው እንዲሠሩ እንደምታለማምድ ጠቁማለች::

በፊት የግንዛቤ ክፍተት ያለባቸው ሰዎች ያጋጥሟት እንደነበር አስታውሳ፤ የመብራት ጌጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ሲባል መጀመሪያ ብዙ ሰው ግር ይሰኝ ነበር ብላለች:: ይህን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ከመናገር ከማስረዳት እና በፎቶ ከማሳየት ባሻገር ሥራው በአካል ሲቀርብ የተመለከቱ ደስተኛ እንደሚሆኑ ትናገራለች:: ኤግዚቢሽኖች ላይ ስትሳተፍ አንዳንዶች በጥራቱ እየተደነቁ ምርቱ ከውጭ የመጣ ነው ብሎ እስከ መደምደም የደረሱ እንዳሉም አስታውቃለች::

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስከሚቀርብ ድረስ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተ ስታስረዳ፤ የጥሬ ዕቃ እጥረት ዋነኛው መሆኑን ጠቁማለች:: ይህን ችግር ለማቃለል የእርሷ ምርት በተወሰነ ጊዜ ተገኝቶ እንዳይጠፋ እና የማይገኝ ዕቃ በመባል እንዳይለይ በማሰብ ጥሬ ዕቃዎችን የማሰባሰብ ሥራ እንደምትሠራ አመልክታለች::

ማሽን መግዛት ከፍተኛ አቅም እንደሚጠይቅ በመረዳት አማራጮችን አፈላልጋለች:: እያንዳንዱን በር በማንኳኳት ኤም ዲ ኤፍ፣ እንጨት እና ሌሎች የፕላስቲክ ግብዓቶችን የት ማግኘት እንደሚቻል ከማወቅ እና ዓይነታቸውን ከመለየት እንዲሁም ጥራታቸውን አረጋግጦ ከመግዛት በተጨማሪ፤ አንዳንድ የፕላስቲክ ቅርፆችን ለማውጣት ሙሉ ማሽን ያላቸውን አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን እየዞረች በማየት የማሽን አገልግሎት ጥናት በማካሔድ፤ ሥራውን ማስቀጠል መቻሏንም ትናገራለች::

ይህ ሥራ ቀላል ፈታኝ እንደነበርም አስታውሳለች:: በተለይ የፕላስቲክ ቅርፅ የሚሠሩትን ማነጋገር አንዱ አልችልም ሲል ሌላኛውን መጠይቅ ረዥም ጊዜ ወስዶባት እንደነበር ትገልፃለች::

እንደ አርክቴክት ሣራ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያመርት እና ያመረተውን ደግሞ ሕዝቡ እንዲጠቀም ግፊት እየተደረገ ነው:: መንግሥትም አሁን የሀገር ውስጥ ምርትን ደረጃው ከፍ እያደረገ ጥራቱን እያረጋገጠ፤ ሕዝቡ እንዲጠቀም ከማድረግ በተጨማሪ መንግሥትም ምርቶችን እየተጠቀመ ነው:: ይሄ ትልቅ ዕድል ነው::

እሷ እንዳለችው፤ የመብራት ጌጥ በአንድ ጊዜ የሚፈለገው ብዙ ነው:: አንድ ባለሁለት መኝታ አፓርታማ ከስምንት እስከ አስር የመብራት ጌጥ ይፈልጋል:: ጌጦቹን ሪልስቴት፣ ሆቴል እና ሌሎችም በብዛት ይፈልጋሉ:: ስለዚህ በቂ ክምችት ሊኖርም ይገባል::

ለእዚህ ደግሞ ቦታ እንደሚያስፈልግ ጠቅሳ፣ በአምራቾች በኩል ክፍተት ቢኖርም፤ የትኛው አምራች ምን ቸግሮታል በሚል ለትክክለኛው አምራች መሬት ማቅረብ ያስፈልጋል ብላለች:: ለማምረትና ጥሬ ዕቃ ለመያዝ እንዲሁም ያለቀ ምርት ለማከማቸት በቂ መሬት እና ፋይናንስ ማግኘት እንደሚገባ ተናግራ፣ በእዚህ በኩል ችግሮች እንዳሉ ጠቁማለች::

በአጠቃላይ የእርሷ የመብራት ጌጥ ሥራ ቀላል ቢመስልም፤ ብዙ ችግሮችን መፍታት እንደሚችል ጠቁማለች:: እርሷም ሆነች በአጠቃላይ አምራቾች የሚኖራቸው ሀገራዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑ ታይቶ ከተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አስገንዝባለች::

ገበያን በተመለከተ ለአምራቾች ባስተላለፈችው መልዕክትም፤ ‹‹ጥራት ያለው፣ የሰዎችን ፍላጎት የሚመልስ ሥራ ከተሠራ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭን ምርቶች ለመግዛት ሰዎች ዝግጁ ናቸው::›› ስትል አርክቴክት ሣራ አስገንዝባለች:: አምራቾች ጥራትን በማስጠበቅ፤ የምርት ቀጣይነትን በማረጋገጥ መጠባበቂያ ምርት በመያዝ እና ግብዓቶችን ቀድሞ በማሰባሰብ ላይ አተኩረው መሥራት እንደሚገባቸውም አስታውቃለች::

ምርቶቿን በመጠን፣ በብዛት፣ በቀለም፣ በጥራትና በሌሎች የተለያዩ አማራጮች እንደምታቀርብ ጠቁማለች:: ቤተ እምነቶችን ጨምሮ ከግለሰብ እስከ ትልልቅ ተቋማት ድረስ የመብራት ጌጦቹን ፍለጋ ወደ እርሷ እንደሚሄዱ ተናግራ፣ የገበያ እጥረት እንደሌለባት አስታወቃለች::

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You