ገና በአፍላው የወጣትነት ዘመኗ ነበር የተሳሳተ ግንኙነት ውስጥ የገባችው። በወጣት ልቧ አፈቀረኩሽ ያላትን ሰው ተከትላ ከቤተሰቦቿ ኮበለለች። የተወለደችበትን አካባቢ የተወችለት አጋሯ አንዴ እጁ ካሰገባት በኋላ ያሰቃያት ጀመር። እሱ ቁጭ ብሎ እሷ ሰርታ እንድታኖረው ያደርጋል።
በልጅ አቅሟ የቻለችውን በሙሉ እየሠራች ቤታቸውን ለማሟላት ብትጥርም ያገኘችውን ገንዘብ እየተቀበለ በመጠጣት ጊዜውን ያሳልፍ ነበር። ሁሉን ትታ ወደ ቤተሰቧ እንዳትመለስ የወላጆቿን ፍቅር መግፏቷ እነሱን ማሳዘኗ እግሯን ወደ ቤተሰቦቿ ቤት እንዳታነሳ አድርጎ አሰራት።
በዚህ መካከል ነበር እያዞረ ሲጥላት ሕመሟን ለማወቅ ሐኪም ቤት የሄደቸው። ሐኪም ቤት ሄዳ የሰማችውን ማመን ያቃታት ወጣት ለተወሰኑ ደቂቃዎች እራሷን ስታ ነበር። ከዛሬ ነገ ሳላስብ ከገባሁበት ትዳር ተገላግዬ ያቋረጥኩትን ትምህርቴን እቀጥላለሁ የምትለው ወጣት የሶስት ወር እርጉዝ መሆኗን ስትሰማ ሰማይ ምድሩ ነበር የዞረባት።
በልጅነት ህልሟ ተምራ ትልቅ ደረጃ መድረስ ቢሆንም በገዛ እጇ ያደናቀፈችውን የስኬት መንገዷን እያሰበች ስታማርር ለከፋ የጤና እክል ተዳረገች። መታመሟን የተመለከተው አቶ ባል ሰጥ ለጥ ብሎ ሚስቱን መንከባከብ ጀመረ። ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ያየችው ወጣት እራሷን እያፅናናች ለወራት በሰላም ኖረች።
ከዛ በኋላ የአንዲት ቆንጆ ሴት ልጅ እናት ሆነች። ልጅቷ እንደተወለደች አካባቢም ተፍ ተፍ ብዬ መጣሁ የሚለው ባል በርከት ያለ ገንዘብ ለቤተሰቡ ማምጣት ጀመረ። ኑሯቸው እየተቀየረ ቢሄድም በአጭር ጊዜ ይህን ሁሉ ገንዘብ የማምጣቱ ነገር አልዋጥልሽ ብሏት ነበር።
ብትጠይቀውም የረባ መልስ ስለማይሰጣት ሳትጠይቅ ለልጇ የሚያስፈልጋትን እያሟላች የተደላደለ የሚባል ሕይወት መምራት ጀመረች።
አንድ ጠዋት ግን የላሰበችው ነገር ተፈጠረ። አመሻሽቶ አንድ የሞላ ሻንጣ ይዞ መጣ፡፡ እንደመጣም ድካም በተጫጫነው ስሜት ተኛ። በጠዋት ተነስታም ለቤተሰቧ ቁርስ ለመሥራት ጓዳ ውስጥ እየተንጎዳጎደች ሳለ በሩ በኃይል ተንኳኳ። በድንጋጤ ተንደርድራ ስትከፍት የፀጥታ ኃይሎች ቤት በመግባት ባለቤቷን ከተኛበት አንጠለጥለው ይዘውት ሄዱ።
ህልም በሚመስል ፍጥነት ሁሉ ነገር ሲከናወን በድንጋጤ አፏን ከፍታ ነበር የተመለከተችው። ነፍሷ መለስ ሲል በድንጋጤ የምታለቀሰውን ልጇን አንስታ አባብላ ቁርስ ማብላት ጀመረች። ወዲያው ደግሞ ፖሊሶቹ ባሏን እያዳፉ ይዘውት በመምጣት በሻንጣ የሞላውን ነገር ይዘው ሄዱ። ያኔ ልጇን አዝላ ተከተለች። ከኋላ ከኋላ በሩጫ የተከተለቻቸው ፖሊሶቸ ሌባ እንደሆነ አረዷት። ለሁለት ዓመታተ ሳይጎልባት ያኖሯት ባሏ ሥራው ስርቆት እንደነበር ስታውቅ ሁሉ ነገር ነው የጨለመባት። ከዛ ያላትን በሙሉ ለቃቅማ ጭና አካባቢ ቀየረች። በአዲሱ ሰፈርም ልጇን አዝላ የተለያዩ ሥራዎችን በተመላለሽነት ትሰራ ጀመረ።
ልጇም አድጋ ትምህርት ቤት ገባች። እሷም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ልጇን ለማሳደግ ያገኘችውን ሥራ በሙሉ ትሠራ ጀመረ። ልጇ አስራ አንድ ዓመት የሞላት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆነች። እያደገች በመሆኑ የተከራየችበት ቤት አካባቢ ልጆች እንዳይተናኮሏት በሚል የምትሰራበት ቦታ በሙሉ ትምህርት በሌላት ሰዓት ይዛት ትሄዳለች።
እናት በተመላላሽ ሠራተኝነት የምትሠራ ቤት ሕፃኗን ይዛት የምትሄድ ከመሆኑም በተጨማሪ እናቷ በሌለችበትም ጊዜም ልጅት በግለሰቡ ቤት ትላላካለች። አንድ እለት ነው ሕፃኗ እናቷ በምትሰራበት ግለሰብ ቤት ውስጥ TV እያየች እንቅልፍ የወሰዳት።
ግለሰቡ ቤቱ ሲገባ ሕፃኗ በተቀመጠችበት እንቅልፍ ወስዷት ሲመለከት ወትሮም ሕፃናትና አቅመ ደካሞችን የማጥቃት ሱሰ የነበረው ሰው በክፉ ዓይኑ ተመለከታት።
ሕፃኗ ስጦታ
የልጅነት ስጦታዎ ስለሆነች ስጦታ በሚል ስም የምትጠራው ሕፃን ሳቂታ የደስ ደስ ያላት ልጅ ነበረች። ከሁሉ ጋር ቶሎ የምትግባባ ለነገሮች ፈጣን ምላሽ የምትሰጥ ዓይነት ንቅት ያለች ልጅ ነበረች። በትምህርቷ ጎበዝ ስትሆን ስታድግ ሐኪም የመሆን ህልም እንዳላት ሁልጊዜ ስትናገር ትሰማለች።
የሕፃኗ እናት ልጇን ከአጠገቧ የምታርቃት ትምህርት ቤት ስታደርሳት ብቻ ነበር። በተመላላሽ ሠራተኝነት የምትሠራበት ቤት በሙሉ ሕፃኗን ይዛት የምትሄድ ከመሆኑም በተጨማሪ እናቷ በሌለችበትም ስትላላክ ትውል ነበር።
በእለቱም እቃ ለመግዛት ወጣ ስትል ልጇን ፀሐይ እንዳይመታባት የምትሰራለትን ግለሰብ ቤት ቲቪ ከፍታላት ወደ ገበያ ትሄዳለች። ልጅቷም ወደዚህ ወደዚያ ስትላለክ በመቆየቷ ቁጭ ባለችበት ነበር እንቅልፍ የጣላት።
እናቷን መርዳት የሚያስደስታት ሕፃን ስትላላክ ስለዋለች ደክሟት ነበር። ለወትሮው እርሳስና ጣፋጮች የሚሰጣት የእናቷ አሰሪ ከተኛችበት መሬት አንስቷት ወደ መኝታ ክፍሉ ሲያስገባት ያለ ምንም ስጋት ገልበጥ ብላ ነበር ወደ እንቅልፏ የተመለሰችው።
ይህ የዝሙት ልብ ያለው ሰው ግን ምንም ሳያመነታ እናቷ ተመልሳ ሳትመጣበት ልጅቷን ደፈራት። ሀገር ሰላም ብላ የተኛችው ሕፃን ሕመሙን መቋቋም አቅቷት በጩኸት ስታደበላለቀው ነበር እናቷ ወደ ቤት የተመለሰችው።
ልጇን ምን እንዳገኛት በድንጋጤ እየተወላከፈች ለመመልከት ስትሮጥ ሰውየው ጉዳዩን ፈፅሞ ወደ ደጅ ሲወጣ በር ላይ ተገጣጠሙ። ምንም ሳይናገር ወደ ውጭ የሚወጣውን ሰውን አልፋ የልጇን ድምፅ ወደ ሰማችበት መኝታ ቤት ሰትመለከት ያየችውን ማመን ነበር የተሳናት።
የልጅነት ልጇን፤ በችግር ተጠብሳ ያሳደገቻት ልጇን፤ ነገ ደርሳ ሰው የደረሰበት ትደርስልኛለች የምትላት ልጇ በደም ተለወሳ በሲቃ እያነባች ተመለከተች። ሁለቴ ማሰብ ሳይጠበቀባት ነበር በአቅራቢያው ያሉ ፖሊሶችን ጠርታ የሆነውን ያሳየቸው። ፖሊሶቹም ልጅቱ በአፋጣኝ የሕክምና ርዳታ ወደ ምታገኝበት አድርሰው ደፋሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ ጀመሩ።
ልማደኛው ደፋሪ
አላገባም፤ ሴት የማናገር ድፍረት ኖሮትም አያውቅም። የተማረ ጥሩ ሥራ ያለው ሰው ነው። አንገቱን የደፋ ሰው ቀና ብሎ የማያይ ጨዋ ሰው ነው ይሉታል የሚያውቁት ሁሉ። ነገር ግን ሕፃናት ሴቶችን ነበር በተለየ ሁኔታ የሚቀርበው። ልጆችን ማቀፍ መንከባከብ በሚመስል መልኩ መያዝ ያዘወትራል።
ከዚህ ቀደም አንዲት የ12 ዓመት ሕፃን ልጅ ላይ ባልተገባ ሁኔታ ንከኪ ሲያደርግ የተመለከቱትን ሰዎች ለመሸሽ ነበር ሰፈር የቀየረው። ቀደም ሲልም አንዲት ሕፃን ደፍሮ ማንም ሳያውቅ እንደቀረ ያስታውሳል። ሌሎች ያልተነገሩ በልቡ የያዛቸው ድፍረቶችም አሉት።
ጨዋ መሳዩ ሰው አድብቶ እኩይ ሥራውን ሲሰራ ማንም አይጠረጥረውም ነበር። የልጅቷ እናትም ከሌሎቹ አሰሪዎች በተለየ እሱን ታምነው ነበር። እምነቱን እስካጎደለባት ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ። እሷ አስቸጋሪ ነገር ሲገጥማት ሁሉ እሱ ጋር ልጅቷን ማስቀመጥ ታዘወትር ነበር። እንዲህ አስብቶ አራጅ ከመሆኑ በፊት።
ልዩ ቦታው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ደመካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር። በግምት ከቀኑ 8፡30 ሲሆን ቲቪ እያየች እንቅልፍ የወሰዳትን ልጅ አስገደዶ ነው የደፈረው። በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 627/1/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ እድሜዋ 11 ዓመት ከ8 ወር የሆነችን ሕፃን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል የፈፀመው ይህ እኩይ ሰው ቤቱ አካባቢ ጭር ያለ ሲመስለው ነበር ቤቱ የገባው።
የሠራውን ሰርቶ አረሳስቶ የመጣውን ሰው ተደብቀው ሲጠበቁ የቆዩት ፖሊሶች በቁጥጥር ስር አውለውታል።
የፖሊስ ምረመራ
ፖሊስ ተጎጂዋን ሐኪም ቤት ካደረሰ በኋላ ነበር ጊዜ ሳያጠፋ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተንቀሳቀሰው። በቡድን ተደራጅተው ፍለጋ የጀመሩት የፖሊስ አካላት ግማሽ ቀን ሲፈልጉት ቢውሉም ሊያገኙት አልቻሉም ነበር።
አመሻሽ ላይ የተወሰነ ኃይል ቤቱ አካባቢ አድፍጦ እንዲጠበቅ መድበው ሲጠባበቁ ቆዩ። ሁሉም ነገር ተረስቶልኛል ያለው ተከሳሽም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ ሹልክ ብሎ ወደ ቤቱ ሲገባ በቁጥጥር ስር ይውላል።
ፖሊስ የዓይን እማኞችን የሕክምና ማስረጃንም
አክሎ ተከሳሽ ዮሴፍ ሙህዬ የተባለው ግለሰብ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ደመካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከቀኑ 8፡30 ሲሆን በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 627/1/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ እድሜዋ 11 ዓመት ከ8 ወር የሆነችን ሕፃን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ክሰ አቅርቦበታል።
የዓቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር
ዓቃቤ ሕግም ፖሊስ አጠናቀሮ የላከለትን ማስረጃ በመያዝ ተጠርጣሪው ላይ ክስ መስርቶበታል። የክስ ዝርዝሩ እንደሚያስረዳው የሕፃኗ እናት በተከሳሽ ቤት በተመላላሽ ሠራተኝነት የምትሰራ ሲሆን ሕፃኗን ይዛት የምትሄድ ከመሆኑም በተጨማሪ እናቷ በሌለችበትም ጊዜም በግለሰቡ ቤት ትላላካለች። በእለቱም በተከሳሽ ቤት ውስጥ TV እያየች በተኛችበት በግምት ከቀኑ 8፡30 ሰዓት አካባቢ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈጸመባት እና ክብረ ንጽህናዋ እንዲገረሰስ ያደረገ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 627/1/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ሕፃናት ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረ-ሥጋ ድፍረት በደል ወንጀል ክስ መስርቶበታል፡፡
ውሳኔ
በቀረበው ክስ መሠረትም ተከሳሽም ፍ/ቤት ቀርቦ ዓቃቤ ሕግ የተከሳሽን ጥፋተኛነት ያስረዳሉ ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ የተከራከረ ሲሆን ተከሳሽ እንዲከራከር ብይን ቢሰጠውም ጥፋቱን ማስተባበል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱም ጥፋተኛ ብሎታል፡፡
በመጨረሻም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ሁኔታዎችን በማየት ተከሳሹ በአስራ አራት ዓመት ከአራት ወር በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም