በእድሜው ሳይሆን፤ እየሠራ ባለው ሥራ ከበሬታ የሚሰጠው አንደበተ ርቱዕ ሰው ነው። ለሃይማኖታዊ ሥርዓት መገዛት፣ የተማረውን፣ ያወቀውን፣ ያለውን ለሌሎች ማካፈል ከልጅነቱ የጀመረው በጎ ተግባር ነው። እርሱ በእምነቱ፤ ሌሎችም በእምነታቸው የፀኑ እንዲሆኑ፣ ለወገናቸው እና ለሀገራቸው ቀናኢ እንዲሆኑ እና በጎ ምግባር እንዲኖራቸው በማስተማርና በማንቃት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።
ይህ ሰው ተወልዶ ያደገው አውቶቡስ ተራ ኳስ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ጥሩ የልጅነት ትውስታ እንዳለውም ይናገራል። በአበበ ቢቂላ ኳስ ሜዳ ውስጥ ኳስ በመጫወት ነው ልጅነቱን ያሳለፈው። ከዘመናዊ ትምህርት ጎን ለጎን ሃይማኖታዊ ትምህርትም ይማር ስለነበር በእምነቱ የታነፀ ሰው ለመሆን ችሏል። ይህ ሰው ኡስታዝ ጀማል በሽር ይባላል።
ኡስታዝ ጀማል እንደሚገልጸው፤ ወደ ሃይማኖቱ ለማዘንበሉ በተለይ የወላጅ እናቱ ግፊት ቢኖርም፤ እርሱም ፍላጎቱ ስለነበረው ትኩረቱን ወደ ሃይማኖቱ ሊያደርግ ችሏል። በልጅነቱ በተወሰነ ደረጃ በቄስ ትምህርት ቤት፣ በኋላም የቁርአን ትምህርት በሚሰጥባቸው በአንዱ በመስጅድ ውስጥ ተምሯል።
በሃይማኖቱ ላይ እንዲገፋ የቤተሰብም የእርሱም ፍላጎት ጠንካራ በመሆኑ ሃይማኖቱንም ዘመናዊውንም ትምህርት በአንድ ላይ በሚያስተምር አባድር በሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተማረ። ተወልዶ ባደገበት አካባቢ መስጊዶች መኖራቸው ሃይማኖታዊ ትምህርቱን ለማጠናከር አግዞታል።
የሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። የከፍተኛ ትምህርት ደግሞ ሳውዲ መዲና እስላሚክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሸሪኣ (ሎው ፋክልቲ) በመከታተል በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል። ከሳውዲ መዲና ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሊንጉስቲክ የትምህርት ክፍል ፊሎሎጂ በሚባል የትምህርት ዘርፍ በሁለተኛ ዲግሪ(ማስተርስ)ተመርቋል። በተጨማሪም በአሜሪካን ሀገር አጫጭር ስልጠናዎችንም በመውሰድ በተለያዩ ዘርፎች ክህሎቱን አዳብሯል።
ኡስታዝ ዘመናዊ ትምህርቱን በዚህ መልክ ቢያጠናቅቅም፣ ነፍሱ ያለው ሃይማኖቱ ላይ በመሆኑ እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ከእምነት ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም በተለያየ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥም ይሳተፋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ ነበር በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ወጣቶች ድርጅት በመግባት ተሳትፎ ማድረግ የጀመረው። በዚህ ውስጥም ከሃይማኖቱ ጋር በተያያዘ እውቀት ማግኘቱን ይገልጻል።
በዚህ ድርጅት ውስጥ ተሳትፎ ማድረጉም የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል። በወቅቱ ከመዲና እስላሚክ ዩኒቨርሲቲ አንድ ልዑክ በድርጅቱ ተገኝቶ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ያደርጋል። ኡስታዝ ጀማል ዩኒቨርሲቲው የሰጠውን ፈተና አልፈው የትምህርት እድሉን ካገኙት መካከል አንዱ መሆን እንደቻለ ነው የገለጸው። ያገኘው የትምህርት እድል በቅድስና ከመካ ቀጥሎ በሚጠቀስ ከተማ ውስጥ እንደሆነና ትምህርቱንም ለስድስት ዓመታት እንደተከታተለ ነው ያስረዳው።
ኡስታዝ ጀማል፤ የተማረውንና ያወቀውን ለራሱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎችም ማካፈል ያስደስተው ስለነበር ተማሪ እያለ ጭምር ነበር በትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ መድረኮችና በመስጊድም በመገኘት ሌሎችን በማስተማር በጎ የሆነ አገልግሎት ሲሰጥ የበረው። በተለይም በውጭ ሀገር በቆየባቸው ጊዜያቶች ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ ይንቀሳቀስ ነበር። በተለያየ ምክንያት አስተማሪ ክፍል ሳይገባ ሲቀር አስተማሪውን ለመተካት ያደርግ የነበረው ጥረት መሠረት እንደሆነለትም ያስታውሳል።
ኡስታዝ ጀማል እንደሚለው በቀድሞው ሥርዓት ወቅት በሙስሊም እምነት ተከታዮች ላይ የተለያዩ ጫናዎች ይደርሱ ነበር። በወቅቱም ድምጻችን ይሰማ በሚል እንቅስቃሴ ይደረግ ነበር። ይሁን እንጂ የወቅቱ መንግሥት የእምነቱን ተከታዮች በእስር በማንገላታት ጫናው እየበረታ ሲመጣ ከጫናው ለማምለጥ ወደ አሜሪካን ሀገር ለመሄድ ተገዷል።
በአሜሪካን ሀገርም የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ (የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ) ባቋቋሙት የሰላም ፋውንዴሽን ውስጥ በመቀላቀል ሃይማኖታዊ ትምህርቱ ላይ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን የሰላም ፋውንዴሽኑ ኢማም በመሆን በተሻለ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ አስተዋጽኦ አበርክቷል። መስጊዶች ላይም ኢማም ሆኖ ማህበረሰቡን አገልግሏል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በውጭ ሀገር ይደራጅ የሚል ሃሳብ ቀርቦ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩል አቡነ አባፋኑኤል የተባሉ አባት ሰብሳቢ ሆነው እርሱ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆኖ በአሜሪካን ሀገር ተመርጠው፤ በዳያስፖራው ማህበረሰብ የተቋቋሙትን አብይ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማትን በማሰባሰብና በማደራጀት ጉባኤው ይዞ የተነሳውን ዓላማ ለማሳካት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
በተጨማሪም በአሜሪካን ዋሽግተን ዲሲ ቨርጂኒያ ውስጥ የሰላም ፋውንዴሽን ኢማም ሆኖ እያገለገለ ነው። በግሉም የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፤ የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅም ነው።
እኛም የረመዳን ጾም ምክንያት በማድረግ ከኡስታዝ ጀማል ጋር ቆይታ ለማድረግ የወደድነው በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ ሆኖ ከሼሆዎች ባልተናነሰ በሃይማኖቱ ላይ ባለው እውቀት፣ ሌሎችም ሃይማኖታዊ ጽናት እንዲኖራቸው በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና በሚሰጠው ትምህርት፣ አልፎ ተርፎም ለሀገሩ በጎ አሳቢና ተሟጋች በመሆኑ ነው። በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ በግብጽ በኩል ለሚነሳው ፀብ አጫሪነት የአፀፋ ምላሽ በመስጠት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይጠቀሳል። ስለዚህም ከዚህ ሀገር ወዳድ ዜጋ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ እንላለን። መልካም የንባብ ጊዜ።
አዲስ ዘመን፤ በዚህ በምንገኝበት ረመዳን የጾም ወቅት ከአማኙ ምን ዓይነት ተግባራት ይጠበቃሉ?
ኡስታዝ ጀማል፤ ረመዳን የጾም ጊዜ ማለት ነው። በሃይማኖታችን፣ የእስልምና መገለጫዎች ወይንም የእስልምና ማዕዘናት ተብለው ከሚለዩት አምስት ዋና ዋናዎቹ መሠረቶች መካከል ረመዳን አንዱ ነው። በጌታና በመልእክተኛው መመስከር አንዱ ነው። ቁጥር ሁለት ላይ ስግደት ይቀመጥና በሶስተኛ ደረጃ ምጽዋት ወይንም ዘካ ነው። አንድ ሰው ከገንዘቡ ላይ የሚበቃውን ወጪ ካወጣ በኋላ ተርፎት ከሚያስቀምጠው ገንዘብ ላይ ቀንሶ መስጠት ግዴታ ይኖርበታል። ቀጥሎ ያለው ደግሞ ጾም እና የሀጂ በዓል መፈጸም ነው። ስለዚህ እነዚህ በሃይማኖቱ አምስት እርከን ተብለው ከተያዙት መካከል አንዱ ነው ማለት ነው።
የሃይማኖቱ ድንጋጌ በሌሎቹ መጻሕፍት በኦሪት፣ በወንጌልም ላይ የተሰበኩ የጾም ዓይነቶች ውስጥ አንዱና አዲስም እንዳልሆነ እኛም ያንን ተቀብለን እንደምናስተናግደው ነው ቁርአን መጽሐፍ የሚጠቅስልን። ልክ በእነርሱ ላይ እንደተጻፈው ሁሉ በእናንተም ላይ ተጽፏል ብሎ ነው የሚያስቀምጠው። በዚህ የረመዳን ጾም የሙስሊሙና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች በአንድ ላይ ጾም መያዛቸው ወይንም መጀመራቸው የዚህን ትርጉም ያያይዘዋል የሚል እምነት አለኝ።
ጾም ማለት በትክክለኛው የሃይማኖት ትርጉም፤ ሰዎች ሥ ጋዊ አካላቸውን በማድከም፣ መንፈሳዊ አቅማቸውን ከፍ የሚያደርጉበት ነው። እራሳቸውን የሚገመግሙበት፣ ለቀጣይ ጊዜ ደግሞ የሚዘጋጁበትና የሚነሳሱበት ሲሆን፣ በተለይም ቁርአን የወረደበት፣ ወይንም ራዕዩ በነብዩ መሐመድ ላይ መገለጽ የጀመረበት ወር ተብሎ ስለሚታሰብ ከቁርአን ጋር ያለን ግንኙነት ከፍ እንዲል ሃይማኖቱ ያስተምራል።
በቁርአኑ ላይ ያለንን አቋም፣ ቁርአኑ ላይ ያሉትን አስተምሮቶች በሙሉ እንድንመረምር፣ ቁርአንን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንድንቀራ፣ በተለይ ደግሞ በማታው ክፍለ ጊዜ ቁርአኑ ሙሉ ለሙሉ እየተቀራ ስግደት የሚከናወንበት ሥርዓት አለ። ቁርአን ወደ 604 ገጾች አሉት። አንድ ሰው ወይንም ኢማም፤ ቁርአኑን እያነበበ ከኋላ ያሉት ሰዎች እየሰሙት የሚከናወንና የቁርአኑ ጊዜ የሚታወስበት ነው። ቁርአኑ የተፃፈው በአረብኛ በመሆኑ በመካከል ላይ የመማማር ሁኔታ ስለሚኖር የቁርአኑ ሃሳብ እንዲታወስ ይደረጋል።
ስለጾም በቁርአን የተደነገገ ነው። ከጠዋት ጎህ ሲቀድ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ ባለው ጊዜ ከምግብ፣ ከመጠጥና ከግብረ ሥጋ ግንኙነትና ከሌሎችም ከሚከለከሉ ተቆጥቦ መጾም ይጠበቃል። ከቁርአን ጋርም ግንኙነቱን የበለጠ የሚያጠናክርበት የጾም ጊዜ ነው። ሌላው አንድ ሰው በመራቡ ምክንያት በሚሰማው ስሜት የረሃብን አስከፊነትና በዚህ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ምን ያህል እንደተጎዱ የሚረዳበት፣ ለድሆች ምግብ፣ ገንዘብ፣ ያለውን በማካፈል እንዲያሳልፍ ይጠበቃል። ረመዳን ጸሎትና ስግድትም በተለየ ሁኔታ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው።
አዲስ ዘመን፤ የእምነቱ ተከታዮች የረመዳን ጾምን በተለየ ሁኔታ ሲናፍቁ ይስተዋላል። የተለየ ምክንያት አለው?
ኡስታዝ ጀማል፤ እውነት ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮው መልካም መሆንን ይፈልጋል። ነገር ግን በመብላት፣ በመጠጣት ሥጋዊ ፍላጎት በጣም ሲበዛ እነዚህ ነገሮች ከሰይጣን ጋር ተባብሮ ወደማይፈገው ነገር ያስገቡታል ተብሎ ይታሰባል። ከህሊናው ጋር ጠብ ከሚያስገቡት ኢሞራላዊ ድርጊቶች ሁሉ እንዲቆጠብ
ያደርገዋል። ጾም በሚመጣበት ወቅት እነዚህን ሁሉ ክፉ ነገሮች ሰባብሮ ያስቀምጥለታል፤ ሰይጣንም ይታሰራል ይላል ሃይማኖቱ።
በመሆኑም ጾም ከነዚህ ሁሉ በማሳረፍ ልዩና ጥሩ የሆነ ስሜት ይሰጣል። ከጾም ውጭ ባለው እሳቤም ሰዎች በመጀመሪያዎቹ የጾም ጊዜያቶች የረሃብ ስሜት ቢሰማቸውም ነገር ግን በምግብ ጫና ምክንያት ከሚፈጠርባቸው የምግብ ዑደት እረፍት ያገኛሉ። በሁለቱም መንገድ ጾም ተቀባይነት አለው። በነፍስም፣ በሥጋም ደስታ ይገኛል ማለት ነው።
በመንፈሳዊው ከሰዎች ጋር የሚፈጠረው ተግባርም ሌላው ጥቅምና ደስታንም የሚሰጥ ነው። የተጣሉ ይቅር ይባባላሉ፤ በአፍጥር ሰዓትም ይሰባሰባሉ፤ ከጾም በኋላ ሰው በሚበላው ምግብና መጠጥም ይደሰታል። የሚዘጋጀው ምግብ ከአዘቦቱ የተለየ ሆኖ መቅረቡም እንዲሁ ደስታን ይሰጣል። በህብረት ሆኖ በመስገድ ፈጣሪን ማመስገንም ስላለ የረመዳን ጾም በጸሎትም፣ በመመገብም፣ ህብረት የሚበዛበት፣ መተሳሰቡ፣ መዋደዱ፣ ይቅርባይነቱ ጎልቶ የሚታይበት ነው። እነዚህ የረመዳን ጾም እንዲናፈቅና እንዲወደድ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
አዲስ ዘመን፤ አሁን ላይ ሀገር ውስጥ በተፈጠረው አለመረጋጋትና ጦርነት ምክንያት ጥሩ ኑሮ የነበራቸው በርካታ ወገኖቻችን ተፈናቅለው በመጠለያና በተለያየ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ ወገኖች በዚህ የጾም ወቅት በሚፈጸመው ዘካ ከምስኪኑ በተለየ የሚታዩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል?
ኡስታዝ ጀማል፤ ዘካ የሚሰጠው በምክንያት ነው። ለማን ምን ይሰጥ የሚለው ቀደሞ በቁርአን መጽሐፍ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። በቁርአን መጽሐፍ ላይ ለስምንት ዓይነት ሰዎች ነው ዘካ እንዲሰጥ የታዘዘው። ከነዚህ ስምንት ሰዎች አንዱ ስደተኛ (ሙሳፊር) የሚለው ነው። በጦርነት ወይንም በሌላ ችግር ምክንያቶች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከአካባቢያቸው ርቀው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ፣ በተሻለ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ ሀብታሞች እንኳን ሆነው ስንቅ ይዘው ከቤታቸው ወጥተው በመንገድ ላይ ስንቅ ቢያልቅባቸው ለጊዜው ባሉበት ቦታ ሆነው ተቸግረዋልና ለነዚህም ቢሆን ሃይማኖቱ ከሚያዘው የዘካ ገንዘብ ላይ ይገባቸዋል የሚል በቁራን ላይ ተቀምጧል። ስለዚህ ከስምንቱ ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ስደተኛን ታሳቢ ያደረገ ነው ማለት ነው።
ሌላው ቢቀር ገቢ እያላቸው ነገር ግን አንዴ የሚያገኙ፣ ሌላ ጊዜ የሚያጡ ከሆኑ፤ ወይንም ደግሞ ገቢ የሚያገኙበት ነገር ተቋርጦ ለምግብ መግዣ የሚያውሉትም ሆነ ለቤት ኪራይ የሚከፍሉት አጥተው በድንገት ኑሮአቸው ላይ ጫና ከተፈጠረ፣ እንዲሁም ለጤና ችግር ተጋልጠው በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ከወደቁ በዘካ እንድናስባቸው ታዘናል።
አዲስ ዘመን፤ በዚህ በረመዳን የጾም ወቅት እየተፈፀመ ካለው አንዱ በጎዳና ላይ በህብረት ማፍጠር ነው። ለጎዳና አፍጥር ተብሎ የሚዘጋጀው ምግብ ማግኘት ላልቻሉ ወገኖች ቢውል የሚል በአንዳንዶች ሃሳብ ይነሳል። በአጠቃላይ ይሄ በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እንዴት ይታያል?
ኢስታዝ ጀማል፤ በጋራ ሆኖ ወይንም አብሮ መመገብን በተመለከተ እስልምና ያስቀመጣቸው ልምዶች አሉ። ዋናው መሆን ያለበት አንድ ሰው ምግብን ጨምሮ ገንዘቡንና የመሳሰሉትን ማውጣት ያለበት ወይንም ርዳታ (ሰደቃ) የሚያደርገው ጽድቅ ለማግኘት ከሆነ፤ በጦርነት ወይንም በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ ለሚገኙ፣ ትክክለኛ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሲያውለው ነው።
ከምግቦች ሁሉ ተቀባይነት የሌለው ምግብ የሠርግ ምግብ ነው ይባላል። ለምን ቢባል። የማይፈልገው ተጠርቶ የሚጋበዝበት፤ መመገብ የሚፈልገው ደሃ ግን ከበር ላይ እንዲሄድ ስለሚገፈተር ነው። ይህ አባባልም የነብያችን ነው።
በኢትዮጵያ ከጎረቤት፣ ከወዳጅ ዘመድና ቤተሰብ ጋር በቤት ውስጥ ተሰባስቦ አብሮ ማፍጠር፣ መብላት የተለመደና የቆየ ባህል ነው። የጎዳና ላይ አፍጥር መርሃ ግብር ግን ከዚህ የተለየ ነው። ሕግም የለውም። ግን ደግሞ ክልክል ነው የሚልም ነገር የለውም። እንዲህ ያለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በቅርብ ነው። የማይተዋወቅ ሰው ሁሉ የሚታደምበት መሆኑ አዲስ ነገር ነው። በአጋጣሚው አብሮ መብላትን መሠረት ባደረገው በእዚህ መርሃ ግብር ላይ እንደሠርጉ ቤት የሚከለከል የለም። አብሮ ለመብላትም አይለምንም። የተዘጋጀው ለሁሉም በመሆኑ በደስታ ሁሉም ይካፈላል። ሁሉንም አካታች ነው።
የጎዳና ላይ አፍጥር መርሃ ግብር መንፈሱ ጥሩ ነው። ግን ደግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ወደ ሕክምና እና ወደተለያዩ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች የሚሄዱ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይሄን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሌሎችን እንቅስቃሴ በማይገድብ ሁኔታ መከናወን ይኖርበታል። የፀጥታ አስከባሪዎችና ከሌሎችም የመንግሥት አካላት ጋር የተናበበ መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፤ የረመዳን ጾምና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሚጾመው የፋሲካ ጾም በአንድ ቀን መሆኑ ምን ስሜት አለው? እንዲህ ያለ የታሪክ አጋጣሚስ አለ?
ኡስታዝ ጀማል፤ ብዙ ጊዜ የሁለቱም እምነት ፆም በቀናት ልዩነት ነው የሚጀመረው። በእኔ እድሜ እንዲህ ያለውን የግጥምጥሞሽ አጋጣሚ ግን አላውቅም። በእኔ እምነት ምናልባት ተከስቶ ነገር ግን አሁን ላይ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና እየጨመረ መምጣት፣ የተሻለ አብሮነት በመፈጠሩ ያስተዋልነው ነገር ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። የቀን መቁጠሪያ ያመጣው እንደሆነም መዘንጋት የለበትም።
ምናልባት በትንሽ ነገር ፀብ ለማንሳት የሚሞክሩ አንዳንዶች ይሄን አጋጣሚ ላያጎሉት ይችላሉ። ነገር ግን ባገኙት አጋጣሚ አንድነትን ፈጥረው፤ ሰዎችን በመግባባት፣ እርስ በርስም ለመማማር ልባቸው ክፍት የሆኑ ሰዎች ደስተኛ እንደሚሆኑ አምናለሁ። ናቸውም ማለት እችላለሁ። ጻድቅ የሆኑ ቄሶችም ይሁኑ ሼኮች ይህ አጋጣሚ ተአምር ነው። እኛንም ሊያስተምር የመጣ ነው ብለው ሊያነሱ ይችላሉ። እኔም ይህ ዓይነት መንፈስ ነው ውስጤን የሚሰማው።
አዲስ ዘመን፤ ለሀገር ሰላም አብዝቶ መፀለዩ በተለይም ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማት ሰላም ማጣት ወደ መረጋጋት እንዲመለስ ጸሎቱ የበለጠ መሆን አለበት የሚሉ ሰዎች አሉ። የሁለቱ እምነት ተቋማት በተመሳሳይ ጊዜ ጾም መጀመራቸውም ለዚህ መልካም አጋጣሚ እንደሆነም እንዲሁ ያነሳሉ። እዚህ ላይ ምን ሃሳብ አለህ?
ኡስታዝ ጀማል፤ በበለጠ ሁኔታ ወይንም ከተለመደ ውጭ በሚለው ሃሳብ አልስማማም። የሚያጋጥመው የችግር ሁኔታ እንደዘመኑ የተለያየ ይሆናል እንጂ ሀገር በተለያየ ጊዜ ችግሮች እያጋጠሟትና እያለፈች ነው አሁን ላይ የደረሰችው። ችግሮችን ነብያቶችም አስተናግደውታል። ጻድቃኖችም እንዲሁ በችግር ውስጥ አልፈዋል። ኢየሱስም ቢሆን መከራን አሳልፏል። መከራን ችግርን ተቀብለው ያሳለፉ ሁሉ አብረዋቸው መጥፎዎች በመኖራቸው ነበር።
ስለዚህ በዚያን ወቅት ያደርጉ ከነበረው ከሆነው አንዱ ለምሳሌ ነብዩ ኢብራሂም (አብረሃምን) ቁርአን መጽሐፍ ላይ ሲጠቅሰው፤ ጌታዬ አለ ይላል። ሀገሬን አማን አድርግልኝ ብሎ ጸለየ ይላል። በጣም ብዙ ቦታ አብረሃም ወይንም ኢብራሂም ከሁሉ ነገር አስቀድሞ ሀገሩን ሰላም እንዲያደርግለት ነው ጌታውን የጠየቀው። ጌታዬ ጌታችን እባክህን መጀመሪያ አማን ስጠን፣ ሰላም ስጠን፣ ጣኦት እንዳናመልክ እራሳችንን ጠብቀን እያለ ይፀልይ ነበር ይላል በቁርአን ውስጥ።
ስለዚህ ለሀገር መፀለይ፣ የምንፀልየው ነገር ደግሞ በፈጣሪ ዘንድ እንዲሰማ ወይንም ተግባራዊ እንዲሆን ፣ እኛም ሰላማዊ ለመሆን የምናደርገው ጥረት ሃይማኖታዊ ነው ከጥንት የጀመረ ነው። አቤልና ቃኤል ላይ ይጀምራል። ቁርአን መጽሐፍ ላይ አቤልና ቃኤልን ይጠቅሳቸዋል።
አንዱ አንዱን ገደለው ይላል። የገደለበትንም ምክንያት ይጠቅሳል። በቅናት የተነሳ ነበር የገደለው ይላል። ስለዚህ የቅናት መንፈስን ከመዋጋት ጀምሮ ነው የፀሎቱ አስፈላጊነት በቁርአኑም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተስማሙ ሃሳቦች በብዛት የሚንሸራሸሩት። ስለዚህ የሰው ልጆች ከቅናት መንፈስ ባነሰ፣ የእገሌ ዘር በዚህ ቦታ መኖር የለበትም፣ በሚል የራሱ ባልሆነ ነገር ነው አለመግባባት ውስጥ እየገባ ያለው። ዘር የሰጠን ጌታ ነው። አንድ ሰው ዘር ፈልጎና መርጦ አይወለድም። ይሄ በእኛ እጅ ያለ ጉዳይ አይደለም።
እውነተኛ ሃይማኖቱን ተቀብሎ የሚጾም ሰው ሊተገብራቸው ከሚገቡና ጾሙንም ከሚደግፉለት አንዱ ሰላማዊ መሆንና ለሰላም መጸለይ ነው። ስለዚህ ሁላችንም አማኞች በጸሎታችን ውስጥ ለሀገራችን ጸሎት ማድረግ ይጠበቅብናል። የጾሙም አካል ነው።
አዲስ ዘመን፤ በጾም ወቅት የነበረው ትህትና፣ የልብ መሰበር ለምንድነው የማይቀጥለው? ለሁሌም ሳይሆን ቀርቶ የሰላም ማጣትና መደፍረስ የሚኖረውና ወንድም በወንድሙ ላይ የሚነሳው ለምንድነው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። በዚህ ላይ ያንተ አስተያየት ምንድነው?
ኡስታዝ ጀማል፤ በእኔ እምነት ጾሙ የሃይማኖታዊ ጾም አልነበረም ማለት ነው። ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ጾም ደስታው የሚመነጨው ከሁለት ነገር በመነሳት ነው። አንዳንዱ ከምግብ ጋር ብቻ ያይዘዋል። ሌላው ደግሞ መንፈሳዊ ሁኔታው ደስታ ይሰጠዋል።
ስለዚህ ባሕላዊ የሆነ ጿሚ ወይንም ከምግብ ጋር የተያያዘ ጾም፣ ጾሙ ሲያበቃ ወደ ባሕሉ ይመለሳል ማለት ነው። እንደዚህ ሲሆን ያ ሰው በጣም ይቸገራል ማለት ነው።
ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚያዘውን ተከትለው የሚፈጽሙ ሰዎች ግን ሁሌም አንድ ናቸው። አይለወጡም። ጾም ሲመጣ የበለጠ ጠንካራ ነው የሚሆኑት። ይበረታሉ። ጾሙ ሲወጣ አብረው አይወጡም። እያንዳንዳችን አማኞች ይህን ፆም የተቀበልንበት አግባብ ምንድነው? ስሜታችንስ ምንድነው? ብለን እራሳችንን መጠይቅ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፤ ተጨማሪ መልዕክት ካለህ?
ኡስታዝ ጀማል፤ ጾም፤ ያለፈውን ገምግመን ለሚቀጥለው መልካም ለመሆን የምንዘጋጅበት መሆኑን ተገንዝቦ የሚጾም ሰው ተጠቃሚ ይሆናል። ያተርፍበታል። ጾምን እንደ ወቅት የሚያይ ሰው ግን አንድ ፋሽን መጥቶ እንደሚያልፈው ዓይነት ነው የሚቆጠረው። ስለዚህ እነዚህን ልዩነቶች ማስተዋል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፤ በጣም አመሰግናለሁ። መልካም የጾም ጊዜ ይሁንልህ
ኡስታዝ ጀማል፤ እኔም አመሰግናለሁ። የሙስሊሙም፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም በጾማቸው እንዲተጉ፣ መልካም የጾም ጊዜም እንዲሆንላቸውና ጾማቸውም ከፈጣሪ ዘንድ እንዲደርስላቸው እመኛለሁ።
በለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም