
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የቲቢ በሽታ ስርጭትና የሞት ምጣኔን ለመቀነስ ያስቀመጠውን ግብ በማሳካት ውጤታማ ሥራ ማከናወኗን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
18ኛው ዓመታዊ የቲቢ በሽታ ምርምር ጉባኤና ዓለም አቀፍ የቲቢ ቀን “በርግጥም የቲቢ በሽታን መግታት እንችላለን!” በሚል መሪ ቃል ትናንት መከበር ጀምሯል።
በወቅቱ የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት እ.አ.አ. ከ2015 እስከ 2020 ድረስ የቲቢ በሽታ ስርጭትና የሞት ምጣኔን ለመቀነስ የተቀመጠውን ግብ አሳክታለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የሞት ምጣኔና ስርጭት መጠን እንዲሁም የበሽታውን የጉዳት መቀነስ የተቻለ ቢሆንም፤ የቲቢ በሽታን ሙሉ በሙሉ ለመግታት የሚደረገው ጥረት አሁንም መቀጠል አለበት ብለዋል።
እንደሚኒስትሯ ገለጻ፤ በተሠሩ ሥራዎች ስኬቶች የታዩ ቢሆንም አሁንም በየቀኑ 54 ሰዎች በበሽታው ይሞታሉ። በበሽታው ተጠቂዎች ላይ የሚደርሰው አድሎና መገለል አልተገታም። በዚህም ለቀጣይ ሰባት ዓመታት አዲስ ስትራቴጂ ተነድፎ የቲቢ በሽታን ለመግታት እየተሠራ ነው ያሉት ዶክተር መቅደስ፤ የቲቢ በሽታን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመግታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት የቲቢ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ በተደረገው እንቅስቃሴ የአየር ንብረት ለውጥ፤ ግጭት እና ኮሮና ቫይረስ ዋነኛ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አንስተዋል። በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት ሶሎሞን (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የዓለም ጤና ድርጅት በቲቢ በሽታ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በ31 በመቶ እና በበሽታው የሚከሰት የሞት ምጣኔን ደግሞ በ34 በመቶ ለመቀነስ ያስቀመጠውን ግብ ኢትዮጵያ ማሳካት ችላለች።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ 156 ሺህ ሰዎች በቲቢ በሽታ ይጠቃሉ ተብሎ ይገመታል ያሉት ዶክተር ሕይወት፤ በተሠሩ ሥራዎች 90 በመቶ የሚሆኑት ላይ በሽታው በምርመራ ልየታ እንደሚገኝ አመላክተዋል። የቲቢ በሽታ በጊዜ ታክሞ ሊድን የሚችል መሆኑን አስታውሰው፤ በወቅቱ ሕክምና ካለማግኘት የተነሳ በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 20 ሺህ ሰዎች በበሽታው ሕይወታቸውን ያጣሉ ሲሉ አስረድተዋል።
የሞት ምጣኔው ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጻር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ አሳይቷል። በቀጣይም በሽታውን ለመግታት ባለሙያዎችን የማሠልጠን፣ መድኃኒቶችን የማቅረብ፣ የሕክምና ሂደቱን የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በሀገሪቱ 42 ሺህ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መኖራቸውን የጠቀሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ፤ በባለሙያዎቹ በኩልም የግንዛቤ ሥራና ታማሚዎችን ከማኅበረሰቡ ለይቶ በማውጣት አስፈላጊው የጤና ክብካቤ ሥራ እንደሚሠራ አብራርተዋል።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2016 ዓ.ም