በኢትዮጵያ በዓመቱ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች ሥራ ፈላጊ ይሆናሉ፤ ወይም ወደ ሥራ ዓለም ይቀላቀላሉ። ለእነዚህ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ዜጎች በመንግሥት ወይም በግል ተቋማት እና ድርጅቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ አብዛኛው ቁጥር ያለው ወጣት ለሥራ አጥነት ይደረጋል። ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ሆኖ መገኘት የሚጠቅም ነው።
ሆኖም በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎች ቢሆኑም የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል የመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የገበያ ትስስር አለመኖር እና የክህሎት ክፍተቶችና መሰል ችግሮች እንቅፋት ሆነው ሲገጥሟቸው ይስተዋላል። አንድ ሰው የተሳካለት ሥራ ፈጣሪ ወይም ኢንተርፕርነር ለመሆን አዲስና የተለየ የቢዝነስ ሃሳብ ወይም ዘዴ ይዞ ቢነሳም ተግባራዊ ማድረጊያ ገንዘብ ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም። ሆኖም እነዚህ ሁለቱ ብቻቸውንም ሥራ ፈጣሪው የተሳካለት የቢዝነስ ሰው እንዲሆን አያስችሉትም።
ሥራ ፈጣሪው፣ ስኬትን መቀዳጀት እንዲችል ወይም ጉዞው ወደ ስኬት የሚገሰግስ እንዲሆን፤ ዓይነተኛ የሆኑ የሰብዕና መገለጫዎች ያስፈልጉታል። እንደ ሥራ ፈጣሪ፣ እነዚህ የሰብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ካሉት ሊያዳብረቸው፣ ከሌሊት ደግሞ እንደ አዲስ በውስጡ ኮትኩቶ ሊያሳድገቸው ይገባል።
በዛሬው የወጣቶች ዓምድ በሥራ ፈጠራ ውጤታማ ከሆኑ ሁለት አብሮ አደግ ጓደኞች ጋር ቆይታ አድርገናል። ወጣት ደረጀ ባቢሶና ወጣት ሳሙኤል ተስፋዬ ይባላሉ። ውልደትና ዕድገታቸው በሲዳማ ክልል አለታ ጩኮ ወረዳ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት አንድ ላይ ያደጉት ደረጀና ሳሙኤል ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው ተከታትለዋል። ወጣት ደረጀ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምህንድስና በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል። ወጣት ሳሙኤል ደግሞ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሮ መካኒካል ምህንድስና ተመርቋል።
ወጣት ደረጀ ከጓደኛው ጋር በመሆን አዲስ የሥራ ሃሳብ በማመንጨት ወደ ሥራ የገቡበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው በተመለሱበት ወቅት በቆዩባቸው ጊዜያት በመኖሪያ አካባቢያቸው ከሚያዩት ነገር በመነሳት ወደ ሥራ እንደገቡ ይናገራል።
በወቅቱ ከእነርሱ ቀደም ብለው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቀው በመንግሥት ሥራ ተቀጥረው የሚሰሩ ጓደኞቻቸውን በሚመለከቱበት ወቅት የሚሰሩት ሥራ አጥጋቢ ካለመሆኑ ባሻገር በሚሰሩት ሥራ ደስተኛ እንዳልነበሩ መታዘባቸውን የሚናገረው ደረጀ ‹‹ትምህርት ጨርሰን ከወጣን የእኛም ዕጣ ፈንታ ይህ ነው ብለን አሰብን ስለዚህ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በመነጋገር አካባቢው ላይ ምን አለ ሰው ማግኘት የሚፈልገው አገልግሎት ምንድነው የሚለውን ማጥናት ጀመርን›› ይላል።
ብዙ ሰው የማስዋብ /የዲኮሬሽን ሥራ ሲፈልግ አገልግሎቱን የሚያገኘው ሀዋሳ ወይም ሌላ ከተማ ሄዶ ነው የሚለው ደረጀ፤ ለምን ይህንን ነገር እዚሁ በመሥራት ለህብረተሰቡ አናቀርብም በሚል ሥራውን እንደጀመሩ ይናገራል። ሥራው ከተማሩት የሙያ ዘርፍ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው በመሆን በመጀመሪያ አካባቢ በሥራው ውጤታማ እንሆናለን ወይ በሚል ፍርሃት የነበረባቸው ቢሆንም በእጃቸው በነበረ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ሥራውን በተመለከተ ከተለያዩ ድረ ገጾች ትምህርት በመውሰድ ራሳቸውን በማስተማር ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ይገልፃል።
በሥራው ጅምር ወቅት ትርፍ ማግኘትን ከማስቀደም ይልቅ ስለሥራው ማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ከተለያዩ የወዳደቁ ነገሮች የሰሯቸውን የመኖሪያ ቤት ማሰማሪያ ዕቃዎች በነፃ በማቅረብ ወደ ሥራው መግባታቸው በእጅጉ እንደጠቀማቸው የሚናገረው ደረጀ፤ በዛው አካባቢ ምርታቸውን ለማሳየት ብሎም ለሽያጭ ለማቅረብ የሚሆን ሱቅ በመክፈት በሙሉ ትኩረታቸው ወደ ሥራ እንደተሰማሩ ይገልፃል።
ይህንን ሥራቸውን የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያና ድረ ገፆችን በመጠቀም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በማስፋፋት የቀጠሉት ሁለቱ ወጣቶች ይህንኑ መነሻ በማድረግ ዛሬ በተለያዩ የግል ሥራዎች ላይ ተሰማርተው በውጤታማነት እንደቀጠሉ ይናገራል።
በአሁኑ ወቅት በእነርሱ ስር በጊዜያዊነት የቀን ሥራ እየሠሩ ገቢ ከሚያገኙ ሰዎች ውጭ በየወሩ ደመወዝ የሚከፈላቸው 14 ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩት ሁለቱ ወጣቶች፤ በዋናነት ሥራቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት መሥሪያ ቤቶችን፣ የመኖሪያ ቤቶች ማስዋብ ቢሆንም ከዚህ በተጨማሪ ካፌና ሬስቶራንት በመክፈት እየሠሩ የተሻለ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ወጣት ደረጀ ይናገራል።
‹‹ወደዚህ ሥራ የገባነው የሚለው ሃሳብ ብቻ ይዘን ነበር›› ወጣቱ፤ በ2013 ዓ.ም ከመንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት መንግሥት ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ብድር በመመቻቸት ትልቅ ድጋፍ እንዲደረገላቸው ይህም ዛሬ ለደረሱበት ስኬት ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ በአሁኑ ወቅትም ይበልጥ ሥራውን ለማስፋት በሀዋሳ ከተማ የቦታ ጥያቄ አቅርበው በጎ ምላሽ እንዳገኙ ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት ‹‹እያየን›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የግል ድርጅት መስርተው በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚገኙ የሚናገረው ወጣት ደረጀ፤ የድርጅቱ የስም መነሻ ምክንያት ሲያስረዳ በኮቪድ 19 ምክንያት ከዩኒቨርሲቲ በመመለስ ከአምስት እስከ ስድስት ወር ቤተሰብ ጋር በመቀመጥ በሚያሳልፉበት ወቅት በወረርሽኙ ምክንያት በቤተሰብና፣ በጓደኞቻቸው ላይ የደረሰውን የኢኮኖሚ ችግር በመመልከት ‹‹ይህንን እያየን የመንግሥት ቅጥር መጠበቅ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ አስተማማኝ የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት የራሳችንን ሥራ ፈጥረን መሥራት አማራጭ የሌለው በመሆኑ <እያየን> እንንቃ ለማለት ለድርጅታችን ስያሜ ሰጠን›› በማለት ያስረዳል።
ድህንነት ለማሸነፍ ብቸኛው መንገድ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በማህበረሰቡ ውስጥ ስለሥራ ያለው አመለካከት ትክክለኛ አይደለም የሚለው ወጣት ደረጄ፤ ሥራ ማለት ቢሮ ተቀምጦ የሚሠራ ብቻ አይደለም፤ ያለን ደሃ ሀገርና ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን የዘመናችንን ጠላት ለማሸነፍ ደግሞ ሥራን ሰይንቁ መሥራት የውዴታ ግዴታ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ያለብንን ድህነት ለማሸነፍ ያለን መንገድ ጠንክሮ መሥራት ብቻ በመሆኑን ይህንኑ በመገንዘብ መረባረብ ይገባናል ይላል።
‹‹በአካባቢያችንም ሆነ እንደ ሀገር ያለን አብሮ የመብላት፣ የመጫወት በሀዘንም በደስታም ያለን አብሮነት የሚያስቀና ነው» የሚለው ወጣት ደረጀ፤ ይህንን ትልቅ እሴት አብሮ ወደ መሥራት በማምጣት መቀየር አለብን የሚል ትልቅ ራዕይ ስላለን ይህንን ሃሳብ በማስተማር ከሀገሪቱ ሕዝብ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣት ጠንክሮ ሰርቶ እራሱንና ሀገሩን መጥቀም እንዲችል ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግሯል።
በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የከተሞች ፎረም ልምዳቸውን ያከፈሉት ወጣቶቹ፤ በሚሰሩት ሥራ ትርፍ ማግኘትን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በመሥራት የማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ተናግሯል።
‹‹ተግዳሮትን እያነሱ ከመደርደር ይልቅ እያንዳንዳችን ከተለወጥን ሀገር የማትለወጥበት ምንም ምክንያት የለም›› የምለው ወጣት ደረጀ፤ አንድ ሰው የራሱን ኃላፊነት ወስዶ እራሱን ከለወጠ ይህ ለውጥ እያደገ ወደ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እየተቀየረ ከድህነት የተላቀቀች ሀገር እንድትኖረን ማድረግ የሚያስችል በመሆኑ፤ የሁሉም ያላሰለሰ ጥረት የግድ እንደሚል ይናገራል።
ወጣት ሳሙኤል በበኩሉ ሲናገር፤ አንድን ነገር ፈጠራ በተሞላበት መልኩ ወይም ከሌላ ሰው በተለየ መልኩ መሥረት ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል፤ የምንሠራው ሥራ አዲስ ነገር ያማከለ ጥራት ያለው መሆን ከቻለ በሰፊ ገበያ ውስጥ ተሰማርቶ አሸናፊ መሆን ከባድ አይደለም። በተለይ የውበት ሥራ ጥራትን በእጅጉ ስለምፈልግ ከምንም በላይ ለጥራት ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው ‹‹እኛም ውጤታማ መሆን የቻልነው በዚህ መርህ መጓዝ በመቻላችን ነው፡፡›› ይላል።
ኮቪድ 19 በተከሰተበት ወቅት የነበረው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነበር የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ የደረሰው የኢኮኖሚ ችግር ነገ እንዲህ ዓይነት ነገር ቢከሰት በምን መልኩ ማለፍ እንችላለን የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ፣ በመንግሥት ተቀጥሮ መሥራት ደግሞ የኢኮኖሚ ነፃነትን የሚያረጋግጥ ባለመሆኑ የግድ ወደ የግል ሥራ መሰማራት አማራጭ የሌለው አድርጎ በመውሰድ ዛሬ ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ይናገራል።
ያለነው ድህነት ተደግፈን ነው፡፡ ከወደቅን መነሳት የሚከብድ በመሆኑ፤ ነገ ላለመውደቅ ብቸኛው መንገድ ጠንክሮ መሥራት ነው የሚለው ሳሙኤል፤ ሥራ ሲበል የትኛውም ሥራ ክቡር ነው። የሚናቅ ሥራ የለም፡፡ ይህንን በተመለከተ ያለው የብዙዎቻችን አመለካከት ግን የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ይህም እራሳችንንና ሀገራችን ሰቅዞ ከያዛት ድህነት መውጣት እንዳንችል አድርጎናል፡፡ ይህ ደግሞ መቀየር ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ይላል።
በቅርቡ የተካሄደው የከተሞች ፎረም ሥራቸውን ለማስፋት መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ የሚናገረው ሳሙኤል፤ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር በተለያዩ ከተሞች ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚያስችል ድጋፍ እንዳገኙ፤ ይህም ድርጅታቸውን ከተወለዱበት አካባቢ ውጭ በመክፈት ወደፊት ለያዙት ሀገር አቀፍ ኩባንያ የመሆን ራዕይ መንገድ የሚከፍት አጋጣሚ በመሆኑ ደስተኞች እንደሆኑ ይናገራል።
ወጣት ሳሙኤል እንደሚናገረው፤ በትም ህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በሌሎችም የኢትዮጵያን ዕድገት በሚያሳልጡ ዘርፎች ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ቢገኙም ያላቸውን ራዕይ ወደ ተግባር ላይ ለመለወጥ በርካታ ተግዳሮቶች ይጋፈጣሉ፤ ስለዚህ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጿል።
‹‹ልንሰማራ ባሰብንበት የሥራ መስክ፣ አስተማማኝ ችሎታ እንዳለን በራሳችን መተማመን ያስፈልገናል” የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ ለራሳችን የሚታየን የችሎታ ክፍተት ካለብን፣ ራሳችንን ከማታለል ይልቅ ችሎታችንን ለማዳበር መነሣት ወይም ሌላ የሚስማማንን የሥራ መስክ መምረጥ ይኖርብናል። ነገር ግን ችሎታው እንዳለ ካወቅን በፍፁም መዘናጋት አይገባንም ”ይላል።
ስኬታማ ኢንተርፕረነሮች ከዛሬው እንቅፋት፣ ውጣ ውረድ ወይም ጊዜያዊ ድል ይልቅ የወደፊቱ ጊዜና የሚደርሱበት ከፍታ የሚታያቸው ናቸው የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ ሁልጊዜም ከወራት፣ ከዓመታት በኋላ ሥራችን የት እንደሚደርስ በማሰብ መቃኘት ይኖርብናል፤ ራዕይና ዓላማችንን ስናስብና የወደፊት ግባችንን መላልሰን የምናስብ ስንሆን፣ ዛሬ የሚገጥሙንን እንቅፋቶችም ሆነ ማታለያዎች ለማለፍ አቅም እንደሚሆን ይገልፃል።
ከሲዳማ ክልል ግንባር ቀደም ኢንተርፕራይዝ በመሆን የአንደኛ ደረጃን በመያዝ የዋንጫና ሰርተፊኬት ተሸላሚ እንደሆኑ የሚናገረው ወጣት ሳሙኤል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃም እውቅና በማግኘት ለሌሎች አርአያ መሆን እንደቻሉ ይህም ከምንም ነገር በመነሳት ውጤታማ መሆን እንደቻለ ወጣት ትልቅ ደስታ የሚሰጥ እንደሆነ ይገልፃል።
ከምንም ነገር በመነሳት በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገብ የቻሉት ሁለቱ ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲስ ሥራ ስንጀምር፣ እየሠራንም ከሆነ ሥራችንን ለማስፋት ስናስብ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆኑልናል ብሎ መጠበቅ ትክክል አይሆንም፡፡ ያለን ገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የሥራ ቦታ፣ የገበያ ትስስር ወዘተ በምንፈልገው ልክ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው። ስለዚህ ያሉንን ነገሮች ቅደም ተከተል በማስያዝና በሁነኛ መንገድ በማቀናጀት መሥራት መቻል አለብን። እንዲህ ማድረግ እንድንችል ደግሞ ነገሮችን የማቀናጀትና ውጤት የማምጣት ክህሎትን ማዳበር ያስፈልገናል ከመሥራት ውጭ አማራጭ የለንም ሁላችንም በሥራ እራሳችንን መለወጥ አለብን ሲል ለወጣቶች መልዕክት አስተላልፏል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም