የአምስት ዓመቷ ልጅ ከእኩዮቿ ጋር እየተጫወተች ነበር። በጨዋታ መሀል አንድ ሕጻን ድንጋይ ወርውሮ መታት። ድንጋዩ ለዓይኗ ተርፎ ነበርና ዓይኗን ታመመች። ከዛሬ ነገር ‹‹ይሻላታል›› ተብሎ ቢጠበቅም ከሕመሟ ልትድን አልቻለም።
ሕመሟ እየባሰ ሲመጣ የተሻለ ሕክምና ፍለጋ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መጣች። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምናዋን መከተታል ጀመረች። ከህክምናው በኋላ ትንሽ ትንሽ ማየት ጀምራ ነበር። ነገር ግን ብዙም ሊቀጥል አልቻለም። የያኔዋ ሕጻን የአሁኗ ወይዘሮ አዳነች ተካው የዚህ ታሪክ ባለቤት ናቸው።
ወይዘሮ አዳነች አንድ አይናቸው ሙሉ በሙሉ ማየት አቁሟል። አንዱም ቢሆን በጭላንጭል ነው የሚያየው። ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የሰው ወይም የዓይነ ሥውራን በትር ይሻሉ።
የአንድ ልጅ እናት የሆኑት ወይዘሮ አዳነች በየዕለቱ የሚገጥማቸውን ነገር ወደ ጎን በመተው ራሳቸውን ለመቻል ጥረት ያደርጋሉ። በፍጹም የሰው እጅን ማየት አይመኙም። ‹‹ብራይት ወርልድ ፎር ብላይንድ ውሜን አሶሴሽን›› በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት የእጅ ሥራ ስልጠናዎችን ከአንድም ሁለት ጊዜ ወስደዋል። ብሬል ተምረው ማንበብም ችለዋል። ድርጅቱ ለዳንቴል እና መሰል የእጅ ሥራዎች የሚሆን የክር ድጋፍ ሲያገኙ የተለያዩ የዳንቴል ሥራ ውጤቶችን በመሥራት እና በመሸጥ በሚያገኙት ገንዘብ ሕይወታቸውን ይመራሉ። ይህም አጥጋቢ አይደለምና ተጨማሪ ጧፍ እና እጣን በመሸጥ ኑሯቸውን ይገፋሉ።
ወይዘሮ አዳነች ስልጠና ከመውሰዳቸው በፊት ‹‹ሊከብደኝ ይችላል ቢሆንም እወጣዋለሁ›› የሚል ተስፋ እና ስጋት ነበራቸው። የዳንቴል ሥራዎችን መሥራት እንደሚችሉ ከማመን ባላፈ በወሰዱት ስልጠና ዛሬ ላይ ብዙ ዲዛይኖችን ለመሥራት በቅተዋል። እንደ ሹራብ፣ ስካርፍ፣ ኮፍያ እና ሌሎችንም ጥንቅቅ አድርገው ይሠራሉ። ደጋግመው እንደሚያነሱት እርሳቸውም ይሁን እንደርሳቸው ያሉት ዓይነ ሥውራን ሴቶች ግን የሠሩት የዳንቴ ሥራ ውጤቶች ተሰርቶ ይቀመጣሉ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ
ገበያው እና ገበያተኛው የሚገናኙበት ዕድል ጠባብ በመሆኑ ነው። ይህ ዕድል ቢኖር ግን ወይዘሮ አዳነች ራሳቸውንም ሆነ አንዱ ልጃቸውን ያለምንም ስጋት ማስተዳደር ይችላሉ።
እንደ ምንጣፍ እና ስጋጃ ያሉ ምርቶችን ለመሥራት አቅሙም ፍላጎቱም እንዳላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አዳነች፤ የግብአት እንዲሁም የቦታ እጥረቱ የፍላጎታቸውን ያህል እንዲሠሩ አልፈቀደላቸውም። ስለዚህም መንግሥት የገበያ ትስስር በመፍጠር እና የመሥሪያ ግብአቶችን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
ብዙ አካል ጉዳተኞች እጃቸውን ለልምና ሲዘረጉ ይስተዋላል። ለዚህም የተመቻቸ ነገር አለመኖር በምክንያትነት ይጠቀሳል። ይህንን በተመለከተ ወይዘሮ አዳነች ሲናገሩ፣ አካል ጉዳተኞች ወደ ልመና እንዳይገቡ እንዲሁም የገቡትንም ከልመና ለማውጣት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል። አካል ጉዳተኞች ሠርቶ መብላት ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን በሚገባ መምራት እንደሚችሉ ብዙዎች በተግባር አሳይተዋል ይላሉ ።
ሌላው ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ችግሮች መካከል የማሕበረሰቡ አመለካከት በዋነኝነት ይጠቀሳል። ጧፍ እና እጣን ሲሸጡ የሚያበረታታቸው እንዳለ ሁሉ ማየት አይችሉም ብሎ የሚያጭበረብሩ ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አዳነች፣ ባለማየታቸው ምክንያት እቃ ሲጥሉ የማይገባ ስድቦችን ተሰድበው እንደሚያውቁ ያስታውሳሉ። የዚህ ሁሉ ችግር የግንዛቤ እጥረት ነው። ሕብረተሰቡ ዓይነ ሥውራን ላይም ሆነ ሌሎች አካል ጉዳተኞች ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያስተካከል ብዙ መሥራት እንደሚገባ ይናገራሉ።
በመሠረተ ልማት ችግር፣ በጦርነት፣ በኑሮ ውድነት እና በሌሎች ምክንያቶች የአካል ጉዳተኛው ሕይወት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን የሚናገሩት ወይዘሮ አዳነች፤ በመንግሥት በኩል ለአካል ጉዳተኛው የተመቻቸ ነገር መሥራት ቢቻል ችግሮችን ማቅለል እንደሚቻል ያምናሉ።
ስንዱ ስለሺ ከፊል የእይታ ችግር ያለባት ሴት ነች። ከ15 ዓመት በፊት ሁለቱም ዓይኖቿ ማየት ይችሉ ነበር። በገጠማት የነርቭ ሕመም ግን እይታዋ ተስተጓጎለ። ነገሮችን ወደ ዓይኗ ካላቀረበች በቀር ማየት አትችልም። ዛሬ ራሷን ለማብቃት ብዙ ጥረቶችን ታደርጋለች። የኮምፒውተር እና የብሬል ስልጠናዎችን ወስዳለች። በተጨማሪም እንደ ወይዘሮ አዳነች በ‹‹ብራይት ወርልድ ፎር ብላይንድ ዉሜን አሶሴሽን›› የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት ባገኘችው የጥልፍ (የዳንቴል) ሥራ ስልጠና ወስዳ ለሶፋ፣ ለረከቦት፣ ለመሶብ፣ ፤ኮፍያ እና ለአንገት የሚሆኑ ስካርፎችን በመሥራት ላይ ትገኛለች። የሠራቻቸው ምርቶች ሲሸጡ ደግሞ የድርሻዋን ክፍያ ታገኛለች።
መጀመሪያ የእጅ ሥራ ለመሰልጠን ፍርሃት እንዳደረባት ያልሸሸገችው ስንዱ፣ በመማሯ እና በመሰልጠኗ የሙያ ባለቤት ከመሆን በተጨማሪ ብዙ ሰዎችን እንዳገኘችበት እና ብዙ እውቀት እንድትገበይ እንዳገዛት ትናገራለች። አካል ጉዳተኞችም ያገኙትን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መማር እንዲሁም መሰልጠን ቢችሉ የሙያ ባለቤት ከመሆን ባሻገር ሌሎችን እስከማስተማር እንደሚችሉ ትመክራለች።
የማየት እክል ላለበት ሰው ከባዱ ሥራ የሚመስለው እንደ ዳንቴል ያለ የእጅ ሥራዎችን መሥራት ነበር። እርሷ ግን ይህንን ማድረግ ችላለች። ይሁን እንጂ የሠራቻቸው ኮፍያም ሆነ ሌሎች ምርቶችን ለመሸጥ ድርጅቱ ከሌሎች የሚሰጡት የባዛር ተሳትፎ ወይም ሌሎች ዕድሎችን ለመጠበቅ ትገደዳለች። መንግሥት የገበያ ትስስሮችም ሆነ ሌሎች አማራጮችን ካዘጋጀላቸው ግን የበለጠ ለመሥራት ፍላጎቱ እንዳላት ታስረዳለች። እርሷም ሆነች ሌሎች አካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎች ከተመቻቸላቸው መሥራት እንደሚችሉ ምስክር መሆን እንደሚቻልም ገልፃለች።
በአጠቃላይ መንግሥት ዓይነ ሥውራንንም ሆነ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ የሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ቢደግፍ፣ የመሥሪያ ቦታዎችን ቢያመቻችላቸው እና የገበያ ትስስር ቢፈጥርላቸው ከዚህ የበለጠ መሥራት እንደሚቻል ትገልፃለች።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም