መንግሥት በየበጀት ዓመቱ ሊያከናውናቸው ያቀዳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን አስመልክቶ ዕቅድ ይነድፋል፤ዕቅዱንም ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፤ያቀረበው ዕቅድ ተቀባይነት ካገኘም በጀትና ሰው ኃይል አንቀሳቅሶ ወደ ተግባር ይገባል። ይህ በየዓመቱ የሚተገበር የመንግሥት የአሠራር ሥርዓት ሲሆን፤ በዚህ ሥርዓት ውስጥም የታቀዱት ተግባራት ምን ያህል ውጤት እያመጡ ነው የሚለውንም የሚከታተልበት ሥርዓት ያበጃል።
ከእነዚህ የክትትል፣ድጋፍና ቁጥጥር ሥራዎች ውስጥ ተጠቃሹ ሰሞኑን የተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አርሶ አደሩ ቀዬ ድረስ በመውረድ የሚያደርጉት የምልከታ ሥራ ነው። በዚህ የምልከታ ሥራም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ከአርሶ አደሩ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኙበትና የተከናወኑና ያልተከናወኑ ተግባራትንም በተጨባጭ ለመገምገም የሚያስችላቸው ነው።
ከሰሞኑም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚባል መልኩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ሕዝብ ድረስ በመውረድ ምልክታ እያደረጉ ነው። የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እያደረጉት ያለው ምልከታ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ያሉ ሀብቶችና ጸጋዎችን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል እና የሚነሱ ቅሬታዎችንም ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ ለመፍታትም በር የሚከፍት ነው።
በማንኛውም መንገድ ሕዝብ መደመጥን ይፈልጋል። ለጥያቄዎቹ ተግባራዊ ምላሽ ይሻል፤ ካልሆነም ጥያቄዎቹ ምላሽ ያላገኙበትን ተጨባጭ ምክንያቶች ማዳመጥን ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ሰሚ እንዳጣ፤ ተገቢው ክብር እንዳልተሰጠውና እንደተዘነጋ ሊቆጥር ይችላል።ይህ ደግሞ የመጨረሻ ውጤቱ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መራራቅን ይፈጥራል።
በተለይም በዚህ የቴክኖሎጂና የግሎባላይዜሽን ዘመን ከሕዝብ ርቆ ሀገርን መምራት ከማይቻል ሁኔታ ላይ ደርሰናል። የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ዜጋም ጥያቄ ዕውቅና መስጠት ሊታለፍ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ተቀባይነት እያጡ፣ በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ተ ቀባይነት እያገኙ መሄድ ጀምረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ መለመድ ካለባቸው መልካም ተግባራት ውስጥ የሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ማክበር አንዱ ነው። ሀገር በመምራት ላይ ያለው ገዥ ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ማክበር ነው። ከሰሞኑ በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አርሶ አደሩ ድረስ በመውረድ እየተደረጉ ያሉ ክትትሎች አንዱ የሕዝብ እውነተኛ ስሜት ማግኛ መንገድ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው።
ከዚሁ ባሻገርም በየአካባቢው ያለውን የሰላም እጦት ችግር መንስኤና መፍትሔ ለመፈለግም ጉብኝቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በመንግሥትም የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ኅብረተሰቡም ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ ውስጥ የገቡ ኃይሎችን በአግባቡ እንዲገነዘብም በር ይከፍታል። የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የመስክ ምልከታና ጉብኝት ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍና ሙሰኞችንና የመልካም አስተዳደር ጠንቆችን ለመዋጋት እድል ይሰጣል።
በሌላ በኩል ደግሞ የተጀመሩ አመርቂ የልማት ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ የከፍተኛ አመራሮቹ ጉብኝት ፋይዳው የጎላ ነው። መንግሥትና ሕዝብ ተቀናጅተው ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው። የዓባይ ግድብ የመሳሰሉ ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶቹን በገንዘብና በዕውቀት በማገዝ ኢትዮጵያን ከብልጽግና ማማ ላይ ለማቆም በመታተር ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ትውልድ ጠንሳሽነት ግንባታው ከ95 በመቶ በላይ የደረሰው የዓባይ ግድብ በርካታ ፈተናዎችና አሜካላዎች ቢገጥሙትም በዚህ ትውልድ አይበገሬነት ዛሬ ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብርሃን መሆን ችሏል። ይህም የተስፋ ብርሃን ከዳር እንዲደርስ ክትትልና ድጋፍ ወሳኝነት አለው።
ኢትዮጵያውያን ከ32 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከልም ታሪክ ጽፈዋል። በዓለም ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውንና በቀጣይም የዓለም ሀገራት ስጋት ይሆናል ተብሎ የሚሰጋውን የበረሃማነት መስፋፋት ከወዲሁ ለመመከት ኢትዮጵያውያን እጃቸውን ከአፈር ጋር በማወዳጀት ምቹ ዓለምን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ የተተከሉ ችግኞችም የደረሱበትን ደረጃ መመልከትና ሂደታቸውን መከታተል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑ ሊበረታታ ይገባል። የስንዴ ልማቱም ትኩረት ካገኙ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው።
በአጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የመስክ ጉብኝት ልማትን ስለሚያፋጥንና ብልሹ አሠራሮችን ስለሚያስወግድ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም