ሕዝባዊ ውይይቶቹ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት አቅም ናቸው!

በአንድ ሀገር ውስጥ እንዲኖር የሚፈለግ ሰላም፣ እንዲመጣ የሚፈለግ ልማት፣ እንዲሰፍን የሚፈለግ የዴሞክራሲ ሥርዓት፤ በጥቅሉ እንዲሆን የሚጠበቅ ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን የሚሆነው የሰፊው ሕዝብ ይሁንታና ተሳትፎ ሲታከልበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ሀገር የሚከወኑ የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ይሳኩ ዘንድ ሕዝብን አወያይቶ የማሳተፍ አካሄዶች የተለመዱ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም ከዘመናት ሂደት ውስጥ እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ይሁንታና ተሳትፎን በሚሹ ጉዳዮች ላይ የተሳትፎው ደረጃ ቢለያይም፤ ሕዝብን ማማከርና ፈቃዱን ሰጥቶ እንዲሳተፍ የማድረግ ልምምዶች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን ተማክረው ያስቀሯቸው ችግሮች፤ የተሻገሯቸው ፈተናዎች የመኖራቸውን ያህል፤ ባለመነጋገርና መመካከር ምክንያት የከፈሏቸው ከፍ ያሉ ዋጋዎች መኖራቸውን መገንዘቡ ለዚህ አብነት ነው፡፡

ታዲያ እነዚህ መክረው በጋራ የከወኗቸው መልካም ተግባራት በዘመናት ውስጥ ለአብሮነታቸው መሠረት የሆናቸውን ያህል፤ ቁጭ ብለው ሳይመክሩባቸው በግብተኝነት የተፈጸሙ የሚመስሉ ጉዳዮቻቸው ደግሞ ዛሬም ድረስ የዘለቀ ችግር መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን የአብሮነታቸውን ያህል በሰላም ማጣት የሚቸገሩት፤ ከግጭትና ጦርነት አዙሪት አልወጣ ያሉት፡፡

ይሄን ችግር ከመሻገር አኳያ እንደ ሀገር ሕዝብ ሊመክር፣ ችግሮችን ነቅሶ ሊፈታ እና ቀጣይ ብዝሃነቱን ጠብቆ የጋራ የሆነች ሀገርን እውን ለማድረግ የሚያስችል ምክክር እንዲያደርግ እድል የሚፈጥርለት ተቋም ተመስርቶለታል፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚል የተቋቋመው ይሄ ተቋም፤ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት ቁጭ ብለው በችግሮቻቸው ላይ እንዲመክሩ፣ ቅራኔዎቻቸውን በይቅርታና እርቅ እንዲፈቱ፤ የነገ መንገዳቸውን በጋራ እንዲተልሙ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ በመንግሥት በኩል እየተካሄዱ ያሉ የሕዝብ ውይይቶች ደግሞ ሌላ የሕዝብን ስሜት ማዳመጫ፤ ችግሮችን በልካቸው አድምጦና ተገንዝቦ ለመፍታት ዕድል የሚሰጥ፤ እንዲሁም ሕዝቡ የመንግሥትን ፍላጎትና መንገድ ተረድቶ አጋዥ ኃይል እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ አበው ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ መንገድ ነው እንዲሉ፤ ከሰሞኑ በክልል ደረጃ በተለያዩ ከተሞች፣ በፌዴራል ደረጃም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ዘላቂ ሰላምን እውን ከማድረግ አኳያ የሚኖራቸው አበርክቶ እጅጉን የጎላ ነው፡፡

በተለይ በክልሎች በተለያዩ ከተሞች በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች (በሚኒስትሮች እና በክልል ፕሬዚዳንቶች ጭምር) እየተመራ ከተካሄደ ሕዝባዊ ውይይት ማግስት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የየክልሎችን እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችን በጽሕፈት ቤታቸው አቅርበው ማወያየታቸው፤ መንግሥት የሕዝቡን ስሜት ለመረዳት፣ ጥያቄዎቹንም ለማዳመጥ፣ እነዚህ ላይ ተመስርቶም የሚጠበቅበትን የቤት ሥራ ለማከናወን ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው፡፡

በሕዝባዊ ውይይቶቹ የተነሱ ሃሳቦች በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ስሜትና ቅሬታ፣ ጥያቄና መሻት በወጉ ለመገንዘብ ያስቻለ ነው፡፡ ሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱለት፤ የልማት ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን፤ አሁን እየታዩ ባሉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ያለውን በጎ ምልከታ እንዲሁም በቀጣይ የልማቱ ተሳታፊም ተጠቃሚም ለመሆን ያደረበትን ቀና እሳቤ የገለጸበት ጭምር ነው፡፡ መንግሥትም ከሕዝብ የሚጠበቀውን በሚገባ ያስገነዘበበት ነው፡፡

በዚህም ሕዝቡ ሰላሙን አብዝቶ የሚሻ፣ ልማትን የሚናፍቅ፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳይን በንቃት የሚከታተል፣ ለዴሞክራሲ መጎልበት የሚታገል… ስለመሆኑ ታይቷል፤ የልማት አጋርነቱንም በልበ ሙሉነት ገልጿል፡፡ ሕዝቡ ይሄን ሲል ደግሞ በመንግሥት በኩል ሰላም የማስፈን ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ፤ የተጀመረውን የልማት መንገድ ማጠናከር እንዲሚያስፈልግ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ መፍታትና የዴሞክራሲ ባህልን የሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ መሥራት እንደሚጠበቅ የጠቆመበት ነው፡፡

እነዚህ ደግሞ ለመንግሥት ቀጣይ የቤት ሥራዎች የእቅድም የፖሊሲም ግብዓት ጭምር የሚሆኑ፤ ለሰላምና ልማት እውን መሆን ለሚሠራቸው ሥራዎች አዳዲስ ምልከታዎችን የሚጠቁሙ፤ ሕዝቡ ምን ቢደረግለት በምን መልኩ የሰላሙም፣ የልማቱም አቅም መሆን እንደሚችል ያመላከቱ ናቸው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያዎች መረዳት የተቻለውም ይሄንኑ ሀቅ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አንዱ የቤት ሥራ ሰጪ፣ ሌላው የቤት ሥራ ተቀባይ ሆኖ ከችግር መሻገር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ጠያቂ ብቻ፣ መንግሥት ተጠያቂና መልስ ሰጪ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የእነዚህ ዓይነት መድረኮች አንዱ ዓላማም ከዚህ ዓይነት እሳቤ መውጣት ነው፡፡ ጠያቂው ጥያቄ እንዳለበት እንዲገነዘብ፤ ተጠያቂውም ጥያቄ እንዳለው እንዲታወቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በመድረኮቹ ላይ የነበረውም ይሄው መንፈስ ነው፡፡ ተሳታፊዎች መንግሥትንም ይጠይቃሉ፤ ራሳቸውንም ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ መንግሥትም ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ፤ ለተሳታፊዎች ደግሞ የቤት ሥራዎቻቸውን ምን ያህል ተገንዝበው እየተወጡ ስለመሆኑ ራሳቸውን እንዲጠይቁ ሲያደርግ ነበር፡፡

በዚህ መልኩ ሁሉም ጠያቂ፣ ሁሉም ተጠያቂ እና ሁሉም የቤት ሥራ ሰጪና ተቀባይ ሆኖ መገለጡ ደግሞ፤ እንደ ሀገር ይሄ ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ነው፤ ይሄኛው ደግሞ የሕዝብ ነው የሚል ጣት መጠቋቆም እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ሁሉም በጋራ መክሮ እና ለችግሮቹ የጋራ መፍትሔ እንዲያስቀምጥ፤ ለመፍትሔዎቹም በጋራ እንዲሠራ ዕድል ይፈጥርለታል፡፡ የሰሞኑ ሕዝባዊ መድረኮችም በዚህ መንፈስ ተቃኝተው የተከናወኑ እንደመሆናቸው፤ እንደ ሀገር የሚፈለገው ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን፣ ልማቱም እንዲፋጠን እና በጥቅሉ ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጉዞ አቅም ናቸው!

አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም

Recommended For You