ሰው ሠራሽ አስተውሎት- ለዲፕሎማሲው ዘርፍ ያለው ሚናና ተፅዕኖ

በየጊዜው እየረቀቀ የመጣው ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial intelligence) ለሰው ልጅ ዕድል ብቻ ሳይሆን ስጋት ይዞ መምጣቱ ይነገራል። በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰው ሠራሽ አስተውሎት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ‹‹የሰው ልጅ ከፈጠረው ሁሉ እጅግ ጠቃሚው፣ እጅግ አደገኛው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ነው›› ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። ይህም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እያደር መምጠቅ ዕድልን ብቻ ሳይሆን ስጋትንም ፤ ሁለቱንም በአንድ ላይ ይዞ የሚመጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

አሁን ላይ ግን የሰው ሠራሽ አስተውሎት በዓለም ወደ ረቀቀ ደረጃ እየደረሰ የበለጸጉት ሀገራት የተጠቀሙበትና የኢኮኖሚያቸው እድገት መሠረት እያደረጉ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የዓለም ኢኮኖሚ በስፋት እያንቀሳቀሰ ነው። እ.ኤ.አ 2022 ሦስት ነጥብ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ሀብት ያንቀሳቀሰ ሲሆን፤ እስከ እ.ኤ.አ በ2030 ለዓለም ኢኮኖሚ 15ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ሀብት ሊያንቀሳቅስ ይችላል ተብሎ ተገምቷል።

በዚህ ልክ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት የዓለም ኃያላን ሀገራት የሚባሉት ሳይቀር ፉክክር ውስጥ እየከተተ መሆኑ ይነገራል። ይህ ደግሞ በተለይ በቴክኖሎጂ የዳበረ ልምድ በሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ታዲያ እነዚህ ሀገራት ተፅዕኖም በመከላከል ቴክኖሎጂው በመጠቀም ረገድና መሥራት ያለባቸው ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥት የሰው ሠራሽ አስተውሎት በኢንስቲትዩት ደረጃ እንዲቋቋም በማድረግ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። በተለይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሀገሪቱ ተጠቃሚ ሆና ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንድትደርስና በሁሉም ዘርፎች ተጠቃሚ መሆን እንድትችል መደላድል የሚሆኑ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

በቅርቡም ዓለም አቀፋዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አስተዳደር ሥርዓት ጅምሮች እና የኢትዮጵያ ትልም ላይ ያተኮረ ምክክር በአዲስ አባባ ተካሂዷል። ምክክሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ተልዕኮ ላይ ያለውን ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ለማስገንዘብ ያለመ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ዓለም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንሲ) ወደ ረቀቀ ደረጃ ላይ ደርሳለች። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ጥቅሞች የማይተኩ ናቸው። ሆኖም ግን ሀገራችን በቴክኖሎጂ ከአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም ተጠቃሚ መሆን የምትችልበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰች ሀገር አይደለችም። በመሆኑም አሁን ላይ ዓለማችን ብሎም የሀገራችን ወሳኝ አጀንዳ የሆነው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምክክር አስፈላጊ ነው።

‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት በዓለማችን ብሎም በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥርዓት ውስጥ ወሳኝ ነው›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቴክኖሎጂው ተፅዕኖ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ዘርፎች ላይ በሰፊው እየተስተዋለ ይገኛል። በጤና፣ በፋይናንስ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ እና በሁሉም ዘርፎች ላይ መሻሻሎችን የሚያመጡና የኑሮ ሁኔታን ለማቅለል እየመጣ ያለ ወሳኝ ቴክኖሎጂ ነው።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሁሉም ዘርፍ አበርክቶ እንዳለው ሁሉ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳለውም የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ያደጉት ሀገራት በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመታገዝ የጤና፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርት፣ የፋይናንስና ሌሎች የሥራ ዘርፎች ማዘመን እና ውጤታማ ማድረግ መቻላቸው በበርካታ ጥናቶች ያሳያሉ ይላሉ።

እንደዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት አድርጎ የፖሊሲና ጥናት የሚካሄድና የዲፕሎማሲ ስልጠና የሚሰጥ ተቋም እንደመሆኑ ፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እና ተፅዕኖ እንዳለው ይረዳል። ቴክኖሎጂውን በወቅቱ ተረድቶ ጠቀሜታውን በማጉላት አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ቴክኖሎጂው አዲስ እንደመሆኑ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አስተዳደር ማዕቀፎች፣ ትብብሮችና ስምምነቶች ላይ በንቃት መሳተፍ ያስፈልጋል።

ምክክሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በውጭ ግንኙነትና በዲፕሎማሲያዊ ሊኖረው የሚገባ ሚና እና ተፅዕኖ በፍጥነት በመረዳት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እንዲቻል ከዘርፉ ምሁራን ጋር በመመካከር የመፍትሔ ሃሳቦችን በማመንጨት ያስችላል ተብሎ የታመነበት መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመላከቱት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት በተለያዩ ዘርፎች የዓለምን አሰላለፍ እየቀየረ ነው። ቴክኖሎጂው በዓለም አቀፍ በጂኦ ፖለቲካዊ ማህበረሰባዊ እና ኢኮኖሚያዊ የደህንነት ሥርዓቶች አጋዥም ተግዳሮት ፈጣሪም እየሆነ መጥቷል›› ይላሉ።

‹‹ሀገራችን ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በምታደርገው ጥረት አጋዥ እንዲሆን በዚህ መልኩ ግንዛቤዎች ማስፋት ይጠበቃል›› ያሉት አምባሳደር እሸቴ፤ ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደጊዜ በሀገራት መካከል ያለውን የኃይል አሰላለፍ ጭምር አዲስ ገጽታ እንዲኖረው እያደረገ ነው። ቴክኖሎጂው በዓለም መድረኮች በወታደራዊ አቅሞች ተፅዕኖ በማሳደር የአስተዳደራዊ ሥርዓትን በመቀየር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራ እንዲሁም ሌሎች ልዩ ገጽታን የሚያሳዩ ነገሮች እየመጡ እንደሆነ ያመላክታሉ። ይህም ቀደም ካሉት የቴክኖሎጂ አብዮቶች በጣም የረቀቀ በመሆኑ የሀገራት የበላይነትና የበታችነት በመፈጠሩ ፉክክር ውስጥ ማስገባቱ አይቀሬ መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላይ በዚህ የተነሳም ድርድሮች ሳይቀር መካሄድ የተጀመረበት ሁኔታ መኖሩ ለዲፕሎማሲው ተጨባጭ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱ ማሳያ መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹እንደዚህ ዓይነት በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚካሄዱ ውይይቶችን በማስፋት ጠቃሚ ግብዓቶች ለማግኘት ያስችላል። በተለይም በአፍሪካ አህጉር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የመሪነቱም ሚና ለመጫወት እንዲችሉ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እጅግ ጠቃሚ ነው›› ያሉት አምባሳደር እሸቴ ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መስፋፋት ከዓለም አቀፍ የደህንነት ሲስተም አንጻር ታይቶ የማያውቅ ፈተና እንደሚያመጣ እየተተነበየ ነው፤ አንዳንድ ምልክቶችም አሉ፤ ከዚህ በላቀ ሁኔታ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚመሩት ቴክኖሎጂዎች ወሳኝ ዘርፎች ወደሆኑ (የመሠረተ ልማቶች፣ መከላከያ፣ የደህንነት …) ሥርዓቶች እየገቡ የሳይበር ጥቃቶች እና የተሳሳቱ መረጃዎች እየደረሱ መሆኑ በጣም ስትራቴጂክ እየሆነ ይመጣል ማለት ነው። በተጨማሪም ቴክኖሎጂው የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው›› ይላሉ

እንደ አምባሳደር እሸቴ ማብራሪያ፤ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ረገድ ያለው ድርድር በውጭ ግንኙነትና በደህንነት ጉዳዮች ሚና በውሉ ተረድቶ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እንዲቻል የተጀመሩ ሥራዎችን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ አጠናክሮ መቀጠል አለበት። በተለይ አጀንዳ ቀረጻ ላይ የሚሠራው ሥራ ለሁለት ከፍሎ ማየት ይገባል። የመጀመሪያው በቴክኖሎጂው ትግበራ ሂደት ሀገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚያስችል አቋም መያዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው እንደ ሀገር ዓለም አቀፍዊ የማስተዳደር መንገዶችን ተቋማትን በማደራጀት ዝግጅት በማድረግ አቋም በመያዝ አካሄዶችን ማሳደግና ማዳበር ያስፈልጋል።

‹‹ሀገራችንን ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም እንዳናጣ ተወዳዳሪ ሆኖ በመገኘት ቴክኖሎጂውን መከታተልና የተጀመሩ ሥራዎችን ማሳደግ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይገባል›› ያሉት አምባሳደር እሸቴ፤ ይህ ሲሆን በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘትና የድርሻን ለመቋደስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። እንደዚህ ዓይነት ምክክሮች መደረጋቸውም ጠቃሚ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት እና ለፖሊሲ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦች የሚፈልቅባቸው መሆናቸውን ይገልጻሉ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) ‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት ያለውን ግዙፍ አቅም ስንመረምር በማህበረሳባችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ ያለውን በቀጣይ ሊፈጠር የሚችለው ተፅዕኖ ስናይ እንደዚህ ዓይነት ምክክሮች ለሀገር ወሳኝ ጉዳይ ነው›› ይላሉ

‹‹ሀገራዊ ፍላጎቶታችንን ለማሳካት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኃይለኛ መሳሪያ የሆነበት አዲስ ዘመን ላይ ደርሰናል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህ እውን ይሆን ዘንድ እንደ ሀገር ከሦስት ዓመት በፊት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል። ስትራቴጂው በተለይ በዲጂታል ዘርፍ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ማዕከል ለመቀየር ያለመና ኢትዮጵያ ከዲጂታል ኢኮኖሚ የምትጠቀምበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ስትራቴጂው የዲጂታል መሠረቶችን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ውጤት አምጥቷል። በተለይም የቴሌኮም መሠረተ ልማት በማስፋፋት ብዙ ኢትዮጵያውያን የዲጂታል ዓለም እንዲቀላቀሉ እና የዲጂታል ሥነ ምህዳር እንዲዳብር አድርጓል። ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገቡ አስችሏል። በቀጣይ በአጭር ዓመታት ከ90ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲኖራቸው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል። የዲጂታል ቀልጣፋ የክፍያ ሥርዓት እንዲኖርና ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸው፣ በርካታ ሀገራዊ የኢኮሜርስ ፕላትፎርሞች ከመልማታቸውም በላይ እነዚህን ፕላትፎርሞች ተጠቅመው ወደ ሥራ የሚገቡ ቢዝነሶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፣ በርካታ የመንግሥት ተቋማትም አገልግሎታቸውን ወደ ኤሌክትሮኒክ ዘዴ እየቀየሩ መሆናቸው እና የዲጂታል ትራንዛክሽኖችን ለማቀላጠፍ በርካታ አስቻይ የሕግ ሥርዓቶች እንዲኖሩ መደረጋቸው ዋና ዋና ስኬቶች ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ስኬቶች የተገኙት የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሁሉም ዜጎች የጋራ ጥረት ማሳያዎች መሆናቸው ይገልጻሉ። ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን የበለጠ ለማሳደግ እና ለማፋጠን የሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደ ካታሊስት ሆኖ የማይተካ ሚና ይጫወታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እድገት ለማፋጠንና የሀገር ተግዳሮቶች ለመፍታት ኃይለኛ መሳሪያን ሆኖ ይቀርባል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች መሥራት እንደሚቻል ጠቅሰው። ለአብነት፤ በግብርናውን ምርታማነት የሚጨመሩ፣ የጤና ተደራሽነት የሚያሻሽሉ፣ ትምህርትን የሚያሳድጉ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተደገፉ በማህበረሰቡ ፍላጎትን ጋር የሚስማሙ መፍትሔዎች መምጣታቸው፤ የመሠረተ ልማት የሀብት አጠቃቀምን የሚያሻሽሉ መተግበሪያዎች (አፕሌኬሽኖች)መምጣታቸው ለዜጎቻችንን ቀልጣፋና ግላዊ ፍላጎቶቻችውን መሠረት አድርገው ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ ማዋል በማስተዋልና በጥንቃቄ መያዝ ይገባል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም በሀገሪቱ ኃላፊነት የተሞላበትና የሕዝብ ጥቅምን የሚያረጋግጥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እንዲያድግ ድጋፍ ለማድረግ የበኩሉን እየሠራ ይገኛል። በተለይ ከአካዳሚ ተቋማት፣ ከግል ኩባንያዎች ጋር በመተባባር በዘርፉ የምርምርና የልማት ሥራዎችን መደገፍ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ወጣቶች በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተደገፉ መፍትሔዎችን በማበጀት የሚያስችል አቅም እንዲገነቡ ማስቻል በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ፈጠራን በሚያበረታታ ጠንካራ የሕግና ቁጥጥር ማዕቀፍ እንዲኖርና ባለድርሻዎች መካከል ትስስር በመፍጠር ጠንካራ የሥነ ምህዳር እንዲፈጠር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ያመላክታሉ። በተጨማሪ ቴክኖሎጂን ለልማት ለማዋል በሚያደረጉ እንቅስቃሴዎች ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰወ፤ ከዚህ አንጻር ከቴክኖሎጂ ልማት ጎን ለጎን የቴክኖሎጂ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎችን የመቅረጽ ሥራዎችን እየተሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ እንደዚህ ዓይነት በቴክኖሎጂ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ውይይት በሚካሄድባቸው መድረኮች በኢትዮጵያ የተስተካከለ የተቀናጀ እና የቴክኖሎጂ እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ወደፊትም መጻኢ የቴክኖሎጂ ዕድሎች መሰል ውይይቶች የሚካሄድ መሆኑን አስታወቀዋል። ስለዚህ የሰው ሠራሽ አስተውሎትና ሌሎች መጻኢ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ብልጽግናና እድገት ለማምጣት በጋራ እንሥራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You