ዘመናዊ የቅንድብ አሰራር – «ኦምብሬ»

የሴት ልጅ ውበት በብዙ መንገድ ይገለጻል፤ እንደየሰው ምርጫም ይለያያል፡፡ በሀገራችንም የሴት ልጅ ውበት በተለያየ መልኩ ይደነቃል፤ አንዳንዶች ምንም የማይወጣላት ውብ መሆኗን ሲገልጹ ‹‹ ልቅም ያለች ቆንጆ›› ይሏታል፡፡

ሴቶቹም የተፈጥሮ ውበታቸውን ለመጠበቅ፣ ይበልጥ ተውበውም ለመታየት የተለያዩ መዋቢያዎችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ራሳቸውን ለማስዋብ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ ቅንድብን ማስዋብ ነው፡፡

ለእዚህም የተለያዩ የመዋቢያ መንገዶች ያሉ ሲሆን፣ ዘመናዊ የመዋቢያ ግብዓቶችን ተጠቅመው ራሳቸውን የሚያስውቡ ሴቶች ከሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች አንዱ የቅንድብ ማስዋቢያ ነው፡፡ ‹‹ ቡኒ ኩልን ›› አልያም ደግሞ ለእሱ ተብሎ የተዘጋጀ ዱቄት መሰል መዋቢያን በመጠቀም ቅንድባቸውን ያስውባሉ፡፡

ለወትሮው ቅንድብን ለማስዋብ አንደኛውና በብዙዎች ዘንድ የተለመደው አማራጭ ‹‹ መቀንደብ ›› ወይንም የቅንድብን ቅርጽ ማስተካከል ነው፡፡ ይህ የቅንድብን ቅርጽ የማስተካከል ወይም የመቀንደብ ፋሽን ቅርጹ ከጊዜ ጊዜ እየተለያየ እና እየተሻሻለ ፋሽኑም እየተለወጠ ይገኛል፤ ቀጭን እና ወጥ ከሆነ የቅንድብ ቅርጽ የእንስቷን የቅንድብ ተፈጥሮ በመመልከት ያልበዛ ተፈጥሯዊ ቅርጹን የጠበቀ አቀነዳደብ የዚህ ወቅት ፋሽን ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ከምልከታ መረዳት እንደተቻለውም፤ እስከ አሁን ሲደረግ የቆየው በአብዛኛው የሌለን ውበት መጨመር፣ ማጉላት ነበር፤ አሁን ላይ ግን የመዋቢያ ግብዓቶችን ተጠቅመውም ቢሆን ተፈጥሯዊነቱን ያልለቀ አልያም ያልተጋነነ ሜክ አፕ መጠቀም ጊዜው የሚጠይቀው ፋሽን ሆኗል፡፡

ታዲያ እንስቶች ቅንድባቸውን በሚሰሩበት ወቅት በየእለቱ ግብዓትን በመጠቀም ማስዋብ ጊዜ የሚወስድ እና ችሎታንም የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በተለያዩ የውበት ሳሎኖች ውስጥ የሜክአፕ ባለሙያዎች እንደሚገኙ ሁሉ፤ አሁን ላይ ደግሞ ቅንድብን በሒና የሚያስውቡ ባለሙያዎች መጥተዋል፡፡

የሒናው ዱቄት በሚያስፈልገው መልኩ ከተበጠበጠ በኋላ በእንስቷ ምርጫ እና የቅንድብ ቅርጽ ልክ ይቀባል፤ ብዙም ደቂቃ ሳይወስድ እንዲለቅም ይደረጋል፡፡ ከዚያም እንስቷ ለፈለገችው ፕሮግራም ቅንድቧን ለማሳመር መጨነቅ ሳይጠበቅባት ቅርጹን እንደያዘ የሚቀመጥ በመሆኑ እስከ አንድ ሳምንት ለሚዘልቅ ጊዜ ትጠቀምበታለች፡፡

አንድ የፈጠራ ሀሳብ ባለበት ብቻ አይቆምም፤ በየጊዜው እየተሻሻለ እና እየተለወጠ ይሄዳል። በመሆኑም እንስቶች ቅንድባቸውን ለማስዋብ የሚወስድባቸውን ረዘም ያለ ጊዜ ማስቀረት የሚችል ሀሳብ በብዙዎች ተቀባይነት አግኝቷል። ይህ ሀሳብ ‹‹ ኦምብሬ ቅንድብ ታቱ ›› ይሰኛል። ይህም ንቅሳት ያልሆነ ነገር ግን ረዘም ላለ ጊዜ መጠቀም የሚችሉበት ቴክኖሎጂ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ከተሰሩት በኋላ ከአንድ ዓመት እስከ ሶስት ዓመት ድረስ የሚቆይ በመሆኑም በሚሰራበት ወቅት እጅግ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ ለሚሰሩ ባለሙያዎችም ስልጠና ይሰጣል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ወደ ኦምብሬ ቅንድብ ታቶ ባለሙያዎች የምትሄድ እንስት በቅድሚያ ከጤና አኳያ የሚቀርብላትን መጠይቅ ከሞላች በኋላ ለመሰራት ዝግጁ ትሆናለች። ከዚያም የመጀመሪያ ስራው የእንስቷን ፊት ማጽዳት ይሆናል፡፡ ፊቷ በአግባቡ ከተጸዳ በኋላ፣ እንደ እንስቷ የፊት ቅርጽ በባለሙያዋ ይለካል፡፡ ይህ የሚደረገው ሴቶች በተፈጥሮ ያላቸው ቅንድብ ቅርጽ የሚለያይ በመሆኑ ነው፡፡ የሚሰራው ደግሞ ልኬቱም ቀጠን ያለ ክርን በመጠቀም በቅንድቧ መጀመሪያ፣ መሀከልና፣ መጨረሻው ላይ ምልክት ይደረጋል። ባለሙያዋ ምልክት ባደረገችበት ቦታ ላይም በቅንድብ ማሳመሪያ ኩል ከተሰራ በኋላ ደንበኛዋ እንድትመለከተው ይደረጋል፤ በዚህም መውደዷን እና አለመውደዷን ትገልጻለች፤ አልያም ያላትን ሀሳብ ታካፍላለች፡፡

ኦምብሬ የቅንድብ ስራን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከሶስት እስከ አራት ሰዓት ይወስዳል፤ የሚሰራውም ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ቀጭን መርፌ ነው። የቅንድብ ስራውን አንድ ጊዜ ከተሰሩ በኋላ ከአንድ ዓመት እስከ ሶስት ዓመት ይቆያል፤ ይሁን እንጂ ቆይታው እንደየ ሰው የቆዳ አይነት እና አቀባበል ይለያያል፤ ይህን ለመከታተልም እንደ አስፈላጊነቱ ወደተሰሩበት ሳሎን አልያም ባለሙያ መሄድ ይቻላል፡፡

ኦምብሬውን ለመስራት ባለሙያዎች የሚጠቀሟቸው የግብዓት ቀለሞች ከእጽዋት የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ እንስቷ ከእነዚህ ቀለሞች የምትፈልጋቸውን እንድትመርጥ ይደረጋል፤ ቅንድቧ ተሰርቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሕመም እንዳይሰማት ማደንዘዣ መርፌ ትወጋና ስራው ይጀመራል፡፡ ሰርቶ ለማጠናቀቅም ከሶስት እስከ አራት ሰዓት ይወስዳል፡፡

ቅንድቧን ተሰርታ ከጨረሰች በኋላም የተሰራችው ኦምብሬ ቦታውን እንዲይዝ እና እንዳይለቅ አልያም ደግሞ ቆዳዋ እንዳይቆጣ ወይንም ኢንፌክሽን እንዳይፈጥር ከሰባት እስከ 10 ቀን ውሀ እንዳይነካው ትመከራለች፡፡ ከዚያም የሚቀባ ውህድ ይሰጣታል፡፡

እንስቷ በምትሰራበት ወቅት ባለሙያዋ የምትጠቀመው መርፌ ቆዳዋ እንዲከፈት ስለሚያደርገው እንድትቀባው የሚሰጣትን ውህድ እና የምታደርገውን ጥንቃቄም ለመከታተል እንዲቻል እስከ ስድስት ሳምንት ባለው ጊዜ ከቆየች በኋላ ተመልሳ ወደ ባለሙያዋ ትሄዳለች፡፡ ከዚያም ቅንድቧ ተፈጥሯዊ የሆነ እይታ ይኖረዋል፤ ይህ አሰራር ከሚጨምረው ውበት ባሻገርም ሴቶች ቅንድባቸውን ለማስተካከል የሚያጠፉትን ጊዜን ይቆጥባል፡፡

ውበትን ለመጠበቅ በየጊዜው የሚተዋወቁ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም እንስቶች መርሳት የሌለባቸው ጉዳይ በሚሰሩበት ቦታ እና በሚመርጡት ባለሙያ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም አንዲት ቅንድቧን ኦምብሬ የተሰራች እንስት ምንም እንኳን ቅንድቡ የሚሰራበት መንገድ ቀላል ቢሆንም በተገቢው መልኩ ካልተሰራ እና ጥንቃቄ ካልተደረገበት ለማስለቀቅ የሚደረገው ሙከራ የሚሰራበትን ያህል ቀላል አይሆንም፡፡

‹‹ኦምብሬ ቅንድብ ›› አሰራር በሌሎች ሀገራትም በተለመደ መልኩ የሚሰራ ሲሆን፣ ሙያውን የሚያስተምሩ ባለሙያዎችም በብዛት ይገኛሉ፡፡ በሀገራችንም ይህ ሙያ ያላቸው እና አገልግሎት የሚሰጡ የውበት ሳሎኖች እና ባለሙያዎች ቢኖሩም የመማሪያ ስፍራዎች ግን እምብዛም አይደሉም፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You