የወላጆች አርአያነት እስከምን ድረስ?

በአንድ አውቶብስ ውስጥ እያለሁ የተፈጠረ ክስተት ነው። እናት ልጇን አቅፋ የአውቶብሱ የመጀመሪያ ወንበር ላይ ተቀምጣለች። ልጇ እንቅልፉ መጥቷል። እያንቀላፋ በመሀል ብንን ብሎ ይነሳል። ‹‹ይኸውልህ ትተኛና አጋጭሃለሁ›› እያለች ታስፈራራዋለች። በዚህ መሀል እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርገው ተነሳ እያለች በመወዝወዝ ትቀሰቅሰዋለች። ይህን የምታደርገው ልጁ እንቅልፍ ከወሰደው ተሸክማው ለመሄድ እንዳይቸግራት አስባ ነው። ከቁጣ አልፋ ተሳፋሪውን የረበሸችውም ለዛ ነው።

እኔን ጨምሮ አውቶብሱ ውስጥ ያለን ተሳፋሪዎች ለእርሷ ባንነግራትም በድርጊቷ ‹‹ያማታል እንዴ?›› የሚል መልስ የማንጠብቅበት ጥያቄ ከሁላችንም ፊት ይነበባል። በዚህ ሂደት ‹‹ልጇን ማባበል አትችልም ነበር? ወይም ልጇ ቀስ ብላ ማስረዳት አትችልም ነበር?›› ሕፃን ነው! እንዲህ ነበር መቆጣት እና መጮህ ያለባት?›› እያልኩ ተደራራቢ ጥያቄዎችን ለራሴ እንድጠይቅ አደርጎኛል። ብቻ የእናት እና ልጅ መጨረሻ ምን እንደሆነ ሳላውቅ ቀድሜ ከአውቶቡሱ ወረድኩ። ሌሎች መሰል እንዲህ አይነት የልጅ ስነ ልቦና ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ድርጊቶችን በየቦታው እየተለመዱ ነው።

አብዛኛው ልጅ የወላጆቹ፣ የቤተሰቡ፣ የማኅበረሰቡ እንዲሁም ከፍ ሲል የአገሪቱ ነጸብራቅ ነው። ቤት ውስጥ ያየውን፣ የተመለከተውን እና የተነገረውን ነገር ነው በውጭ የሚያንጸባርቀው። ‹‹ልጆች ነጭ ወረቀት ናቸው። ›› የሚባሉትም ለዚህ ነው። የሳልንባቸውን ሁሉ ፍንትው አድርገው መልሰው ያሳዩናል። በእነሱ ውስጥ ራሳችንን በሚገባ እናይበታለን። ትምህርት ቤታቸውም ይሁን ሌላ ቦታ መሄድ ሳይጠበቅብን ድርጊታቸውን በማየት ውሏቸው ምን እንደሚመስል የመገንዘብ ዕድላችንም ሰፊ ነው። ወደድንም ጠላንም ልጆች እንደ አርአያ የሚያዩት በቅርባቸው የሚመለከቱን ሰው ነው። ለዚህ እኮ ነው እንቅስቃሴያቸው ሁሉ በቅርብ እንደሚያዩት ሰው የሚሆነው። እንደ እነርሱ መሄድ ይፈልጋሉ። አለባበሳቸው፣ አነጋገራቸው እና አንደበታቸው ሁሉ የእነርሱ ቅኝት ይሆናል።

አልተጠናም እንጂ የውጭ አገራት ፊልሞች ተተርጉመው በየቴሌቪዥኑ መቅረብ ከጀመሩ ወዲህ አዋቂዎችን ጨምሮ ብዙ ወጣቶችና ታዳጊዎችን ባህሪ በብዙ መልኩ ተቀይሯል። ታዳጊዋ የሰፈራችን ልጅ ናት። በወቅቱ ዕድሜ ዘጠኝ ቢሆን ነው። እናቷ ትርጉም ፊልሞችን በቴሌቪዥን ማየት አትፈልግም። ሰው የቱንም ያህል ሊያማልላት ቢሞክርም ምርጫዋ አልነበረም። አንድ ቀን ልጅ እናንተን ፊልሞቹ ላይ ያሉ ገፀ ባህሪያትን እየጠራች እንዲህ ሆነ እንዲያ? እያለች ስትጠይቃት ግራ ገባት። ቤት ውስጥ ስለማትከፍት እንዴት እንዳወቀች ጠየቀቻት። ልጅቷም ‹‹ኧረ ባክሽ አንቺ ብትከለክይንም የትምህርት ቤት ጓደኞቻችን እኮ ይነግሩኛል። ›› ብላ መለሰችላት። ምናልባት ከዚህ ንግግር ብዙ ነገር መረዳት ይቻላል። ልጆቻቸውን በአግባቡ ለማሳደግ ወላጆች ቢጥሩም በትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ተጽዕኖ የቤተሰብ ድካም ከንቱ ሆኖ ይቀራል። በልጅነት አዕምሯቸው ማወቅና ማድረግ የማይገባቸውን ነገር እንዲያደርጉ ይገደዳሉ። አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ምን ማስተማር እና ምን ማሳየት እንዳለባቸው ግንዛቤው እንደሌላቸውም ለመረዳት ቀላል ነው። ብቻ በአንዳንድ የቤተሰብ በኩል ግዴለሽነትን እንዳለ ይታያል።

ጭራሽ አሁን አሁንማ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ልጆችን ይዞ በመውጣት ግማሹ ለማሳቅ ግማሹ ደግሞ ራሱ የሚያደርገውን ድርጊት ልጁ እንዲደግምለት ሲጥር እንመለከታለት። ይህ ትክክል አይደለም። ልጆች እንደልጅነታቸው ተጫውተው እና ቦርቀው ነው ማደግ የሚገባቸው። እንዲህ ያሉ ወላጆች አስበውበት አይመስልም ይህን የሚያደርጉት። ምናልባትም በስሜት ሌላው ስላደረገው ብቻ ‹‹ለምን እኔስ ይቅርብኝ? በሚል ፉክክር ይመስላል ድርጊቱን የሚፈፅሙት ።

አንዳንድ ቤተሰብ ደግሞ ልጅን ከመጠን በላይ በመቆጣጠር፣ ነፃነት በማሳጣት እና የቤተሰቡን ሃሳብ ብቻ የሚሰማ ልጅ ብቻ አድርገው ማሳደግ ትክክለኛ የልጅ አስተዳደግ የሚመስለው ወላጅ ቁጥር አናሳ የሚባል አይደለም። ከእንዲህ አይነቱ ቤተሰብ የወጡ አብዛኛዎቹ ልጆች ግን ፈሪ፣ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ ጭምት፣ ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት የተገደበ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም። አፈንግጦ የወጡ ቀን ደግሞ ማንንም የማይሰሙ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት የማይችሉ ወላጆች መኖራቸውን በማሰብ ነው ልጆች ላይ ከሚሠራው ሥራ ባልተናነሰ ወላጆች ላይ መሠራት አለበት የሚባለው።

‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› አይደል የሚባለው፤ የዛሬው ትዝብት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተመለከትኩትን ነገር አስታወሰኝ። አንዲት ሴት ጧፍ እያበራች ነበር። በግምት ዕድሜው ከስምንት እስከ አስር ዓመት የሚሆን ልጅ አብሯት አለ። ጧፉ በርቶ ሳያልቅ ተቀበላትና አጠፋው። ከሴትየዋ ምንም አይነት ምላሽ አልተመለከትኩም። ቀጥሎ እየጠፋ ባለው ጧፍ እጇን ለማቃጠል ሲሞክር ‹‹ተው!›› ብላ ዝም አለች። በተደጋጋሚ ለማቃጠል ሲሞክር፤ ሌሎች ሰዎች ነበሩ ‹‹እረፍ እንዲህ ይደረጋል እንዴ?›› ብለው የተቆጡት። እርሷ ዝምታን የመረጠችው። ካላችበት ቦታ አንጻር ሌሎችን ላለመረበሽ ይሆናል ዝምታን የመረጠችው። ነገር ግን እንዲህ ያለው ቸልተኝነት ከተደጋገመ ነገ እናቱን የሚጦር ሳይሆን የሚደበድብ ልጅ እንዲፈጠር መፍቀድ ነው። ሲቀጥል ይህን ልማድ ለማዳበር የቻለው ከቤት ውስጥ የነበረው አያያዝ ምን አልባትም ጥሩ ባለመሆኑና በቁንጥጫ ያላደገ ሊሆን ይችላል።

ሁሉም እንደሚያስታውሰው ከጥቂት ዓመታት በፊት ልጆች የኅብረተሰቡ ነበሩ ለማለት ያስደፍራል። ጎረቤት የራሱ ያልሆነ ልጅ ሲያጠፋ ይገስጸዋል፣ ይቆጣዋል፤ ይቀጣዋልም። ዛሬ እንዲህ ያለው ነገር አለ ለማለት ያስቸግራል። ብዙዎች ‹‹ምን አገባኝን?›› ይመርጣሉ። ቢቀጣ ደግሞ ‹‹በእኔ ልጅ ምን አገባህ? ›› ሊባል እንደሚችል ያምናልና ። በግዴለሽነት ነገሩን ለማለፍ ይገደዳል።

ሌላው ልጆች መጽሐፍትን ገዝተው እንዲያነቡ፣ አንብበው ከጨረሱ በኋላም ምን እንደተማሩ ከመጠየቅ ይልቅ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ታብሌት እና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመግዛት ሳያውቁት ልጆቻቸው ግለኝነትን እንዲለማመዱና የ‹‹ጌም›› ሱሰኛ እና የመሳሱትን ችግሮች በልጆቻቸው ላይ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ወላጆችን መኖራቸውን እየታዘብን ነው።

በአገራችን ከልጅ ጋር የተያያዙ አባባሎች ብዙ ናቸው። ‹‹ልጅ እና ጫማ ወደ አልጋ››፣ ‹‹ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም›› ፣‹‹ከልጅ አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት›› እና መሰል አባባሎችን መጥቀስ ይቻላል። አሁን ላይ ደግሞ ‹‹ሁሉም ነገር ለልጆች›› የሚል ይመስላል አባባሉ። እንዲህ ጫፍ እና ጫፍ ያለውን አስተሳሰብ ማመጣጠን እንዲሁም ሚዛናዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ግን “ዘመኑን የተረዳ፣ እንዴት ይሁን? ቀጥሎስ ምን ላድርግ? የማደርገው ነገር ልጆቼን ይጎዳል ወይስ ይጠቅማል? ከእኔስ ምን ይማራሉ?” ብሎ የሚጠይቅና በብዙ መልኩ አርአያ የሚሆን ወላጅ መኖር አለበት። ታዲያ ልጆች በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ከሚሠራው ሥራ እኩል በእኩል ወላጆች ላይ መሥራት ግድ የሚልበት ወቅት ላይ የምንገኝ አይመስላችሁም?

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You