‹‹ ሕዝብና መንግስት የጣለብንን ሕግ የማስከበር ተግባር እየተወጣን ነው ››

አቶ ተክሌ በዛብህ – የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ

መሰረታዊ ከሚባሉ የሰው ልጆች ፍላጎቶች መካከል ፍትህ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል። በእርስ በእርስ አለመግባባትም ይሁን በሌላ ጉዳይ ሰዎች ፍትህን ሊሹ ይችላሉ ፡፡ ይህንን ፍትህ ሊያስከብር የሚችል በዳይን የሚጠይቅ ተበዳይን የሚክስ ተቋም ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮም መንግስትና ሕዝብ የጣሉበትን ፍትህን የማስከበር ስራ እያከናወነ ይገኛል። እኛም ከቢሮ ኃላፊው ከአቶ ተክሌ በዛብህ ጋር ቆይታን አድርገናል።

አዲስ ዘመን፦ የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ አደረጃጀትና ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ተክሌ ፦ ቢሮው በ1995 ዓ.ም በፊት ጀምሮ ባለው ሁኔታ የአቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ይባል ነበር። በኋላም በ1995 ዓ.ም በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361 ላይ አንቀጽ 28 መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት በሚል ተደንግጓል። ይህ ሲታወጅ ሁለት ንዑሳን አንቀጾች የነበሩት ሲሆን አንደኛው በከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ የወንጀል ጉዳዮችን የመከራከር ወይም የማየት፤ የማቅረብ ኃላፊነት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ስልጣንና ተግባሩ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በሚወጡ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ሆኖ በአዋጅ ይወጣል በሚል የተቀመጠ ነው።

ከዛም በአዋጅ ቁጥር 4/2000 ላይ የፍትህና ሕግ ጉዳዮች ቢሮ በሚል የሰራተኛና አሰሪ እንዲሁ ማኅበራዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማካተት የፍትህና የሕግ ቢሮዎች በሚል በአዋጅ ቁጥር 4/2000 ላይ ተደራጀ ። ከዛም ከአንድ ዓመት በኋላ በአዋጅ ቁጥር 15 /2001 ላይ ፍትህ ቢሮ የሚለውን ስም ይዟል። በዚህም የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤትና የማኅበራዊ ፍርድ ቤት አስተዳደር ጉባኤ ጽህፈት ቤትን በማካተት እንዲደራጅ ይሆናል።

በዚህ ሳያበቃ ከ 3 ወይም 4 ዓመት በኋላ በአዋጅ ቁጥር 35 /2004 ላይ ከላይ የተጠቀሱትን ተቋማት በመያዝ ዳግም ፍትህ ቢሮ በሚል ስያሜ ተቋቁሟል። በዚህ ሁኔታ ቆይቶ ከአዲሱ ለውጥ ማግስት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ኃላፊነት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/2011 መሰረት የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ በሚል ብቻውን ተደራጅቷል።

ከላይ ያነሳናቸውን ተጠሪ እንዲሁም አብረው ሲደራጁ የነበሩትን ተቋማት አውጥቶ ከሁለት ዓመት በኋላም አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ኃላፊነት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ሲሻሻል በአዋጅ ቁጥር 74 /2014 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታክስ ይግባኝ ተቋምን ይዞ ፍትህ ቢሮ በመሰኘት ተደራጅቷል። በዚህ ዓመት አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ኃላፊነት ለመተካት የወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016 መሰረትም ከላይ የተገለጸውን ተጠሪ ተቋም ይዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በሚል ተደራጅተቶ ስራ ላይ ይገኛል።

አዲስ ዘመን ፦ በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይም ተገልጋይን በማርካት በኩል የመጡ ለውጦች እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ ተክሌ ፦ የከተማዋ ነዋሪ ያለው የፍትህ ጥማትና ፍላጎት እንዲሁም የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆንም ይፈልጋል። ከተማ አስተዳደሩም ይህንን በመረዳት ከከተማዋ ከፍ ብሎ አዲስ አበባ የአህጉሩ ጽህፈት ቤት መቀመጫ እንዲሁም የተለያዩ ዲፕሎማቶች መቀመጫነቷን ታሳቢ ያደረገ ስራን ነው የሚሰራው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አዲስ አበባ ከተማ ከሁለት የዓለማችን ትልልቅ ከተሞች በመቀጠል ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ ሆና ነው የምትታወቀው። ከዚህ አንጻር የሕግ የበላይነት ከፍ ባለ ሁኔታ እንዲከበር ተቋሙ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተደባልቆ የሚፈለገውንም ለውጥ ሳያመጣ ስያሜውም ሳይጎላ ብዙ ትርጉም ያለው ስራ ሳይሰራ መቆየቱ የሚታወቅ ነው።

በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች ያልተመለሰ የፍትህ ጥያቄ ተቋሙም ራሱን እንዲያይና ወደ ሪፎርም ስራ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል። ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ብቃት ባለው የሰው ኃይል የተደራጀና ተቋማዊ ቁመናን የያዘ ሆኖ እንዲደራጅ ከመፈለግ አንጻር ኃላፊነቱና ተልዕኮውም ከበፊቱ በተሻለና ጥርት ባለ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ተቋሙም በዛ ሁኔታ ነው የተደራጀው። ይህንንም ለማሳካት ከዚህ በፊት በአስፈጻሚ አካላት ዘንድ ተገልጸው የማያውቁ ዘርዘር ያሉ የስራ ድርሻና ኃላፊነቶች ተቀምጠውለታል።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ በወጡ አዋጆች ላይ በዝርዝር ተቀምጠው ይገኛሉ። ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ደግሞ የሰው ኃይልን በሚፈለገው ልክ የማደራጀት ተቋማዊ ቁመና የማላበስና በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራም ያስፈልግ ስለነበር ይህንን በማሳለጥ በኩል ከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ስራ ሰርቷል።

ይህ ተቋም በሰው ኃይል በኩል ሰፊ ክፍተት የነበረበት ባለሙያዎቹ ተረጋግተው የማይሰሩና ከፍተኛ የሆነ የሰራተኞች ፍልሰት የነበረበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ መፍትሔ ለመስጠት ከ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙ ራሱን ችሎ የሚመራበት ደንብ ወጥቶለታል። ይህንን ደንብ ተከትሎ የጉባኤ ጽህፈት ቤት አቃቤ ሕግ የስነምግባር (ዲስፒሊን) የቅጥርና ዝውውር እንዲሁም ሌሎች መሰል ተግባራትን የሚወስን ጉባኤ ጽህፈት ቤት ተደራጅቷል።

ደሞዙም አገራዊ ሁኔታን እንዲሁም የሌሎች ክልሎችን ስኬል በተከተለ መልኩ ከፍ እንዲል በማድረግ ባለሙያዎች ተረጋግተው የሚሰሩበትን የስራ አካባቢ በመፍጠር በኩል ትልቅ ስራ ተሰርቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ ገበያው ላይ ተወዳዳሪና ጥራት ያለው የሰው ኃይልን ለማግኘት ያስቻለ ከመሆኑም በላይ ለተቋሙ ጥንካሬም ከፍ ያለ አስተዋጽዖን አበርክቷል።

ይህንን ተከትሎ በሰው ኃይል ቁጥርም ሆነ ጥራትና ብቃት ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ስራ ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በማዕከል ደረጃ 56 የሚሆኑ አቃቤ ሕጎች ይገኛሉ፡፡ በክፍለ ከተሞች ደግሞ 418 የሚደርሱ አቃቤያነ ሕጎች ያሉ ሲሆን የቅጥራቸው የዝውውራቸው እንዲሁም ሎሎች ጉዳዮቻቸው የሚታየው በማዕከል መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።

በጠቅላላው 747 አቃቤ ሕጎች በስራ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በጥናት ምን ያህል የሰው ኃይል የሕግ ጉዳዮቹን ማካሄድ ይችላል የሚለውን ባማከለ መልኩ ወደ 77 በመቶ ገደማም መሸፈን የቻለ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የተቋሙን አቅም ከማሳደግ አንጻር ለባለሙያዎች አጫጭርና ረጃጅም ስልጠናዎችን እየሰጠን መጥተናል፡፡ በሂደትም በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሹ አሰራር የሚጋለጡ ባለሙያዎችንም ተጠያቂ በማድረግ በኩል ትልቅ ስራ ተሰርቷል።

ተቋሙ ራሱን በሰው ኃይልም ሆነ በቴክኖሎጂ ሲያዘምን ዋናው ዓላማ የከተማዋን ነዋሪ የፍትህ ጥያቄ መመለስ ነው። በዚህም ሕዝቡ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በሚሰጠው አገልግሎት ምን ያህል ረክቷል በሚል የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፤ የሕዝቡ እርካታ ከ60 በመቶው ያልበለጠ መሆኑን ደግሞ ውጤቱ ያሳያል።

ይህንን በመያዝም በአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራት ዘርዝረው ከላይ በጠቀስኳቸው ህጎች ለእኛ የተሰጡን ሰልጣኖችን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር መሰረታዊ የሚባሉ ስራዎችን እየሰራን ውጤትም እያገኘን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር በተቋሙ ላይ የተሰራው የሪፎርም ስራ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል?

አቶ ተክሌ፦ በእርግጥ ሂደቱን በአንድ ጊዜ መገምገም የሚቻል ባይሆንም ጥሩ እንደሆነ መናገር ይቻላል። እዚህ ላይ አንደኛው መለኪያችን የነበረው አገልግሎት ወሳጁ የከተማ ነዋሪ መሆኑ ሲሆን ሌላው ደግሞ የእርካታ ዳሰሳ ጥናትና ከተለያዩ አካላት የሚመጡ ጥቆማዎች ናቸው፤ ይህ አሰራር ደግም እስከ አሁንም የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው። ከዚህ በተጨማሪ ግን ብቃት ያለውን ክስ የመመስረት የመከራከርና ድርድር የማድረግ አቅም ያለው የሰው ሃይል እንድናደራጅ መንገድ ከፍቶልናል። ከለውጡ ወዲህ ተቋሙ ራሱን ችሎ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ በህግ እንዲመራ ስርዓት ተበጅቶለታል። ይህንን ተከትሎ የተቋሙን የሰው ኃይል ቁጥርም ብቃትም ከማደራጀት አንጻር መጠነ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል።

ሌላው ተቋሙን በዘመናዊ ቴክኖሊጂ የማደራጀት ሂደት ምንም እንኳን ጅምር ላይ ያለ ቢሆንም ከዚህ በፊት በተለያዩ ስያሜዎች እየተጠራ በህዝቡ ውስጥ መግባት ሳይችል መቆየቱን ታሳቢ በማድረግ ስሙን የማጉላት ስራዎችን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ሰርተናል። ይህንንም በቀጣይ በምናረቃቸው ሕጎች ߹ ክርክር በምናደርግባቸው ጉዳዮች ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ የሚለውን ከዚህ ጋር አያይዞ ማንሳት ይቻላል። ከዚህ አንጻር ከለውጡ ወዲህ በተቋሙ ላይ የተሰራው ስራ ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ ሲሆን የከተማዋን ነዋሪ እንዲሁም የመንግስት ተቋማትን ወክለን  በምናደርጋቸው ክርክሮች ላይ ይበል የሚያሰኙ ተጨባጭ ውጤቶችን እያየን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ከለውጥ ስራው ጎን ለጎን እንደ ከተማ የምንተዳደርባቸውን ህጎችና ደንቦች እንዲሁም ሌሎችን በማርቀቅና በማዘጋጀት ብሎም አጽድቆ ተግባራዊ በማድረግ በኩል ያለበት ቁመና እንዴት ይታያል?

አቶ ተክሌ፦ ደንብ ቁጥር 125 /2014 ትን ጨምሮ አራት ያህል ተቋሙ ራሱ የሚመራባቸውን ደንቦችን ሰባት ያህል መመሪያዎችን ዘርግተናል ። በዚህም በዘፈቀደ ይመራ የነበረውን በሕግ እንዲመራና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማድረግ በኩል ስራዎች ተሰርተዋል ።

ይህንን ተከትሎም በከተማ አስተዳደሩ የፍትህ ሂደት ላይ የሚስተዋሉ በርካታ የአሰራር ክፍተቶችን ለማሻሻል አጫጭር ጥናቶችን የሕግ ማሻሻያ ስራዎችን መስራት እንዳለ ሆኖ ሶስት ግዙፍ ጥናቶችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተጋገዝ አስጠንተናል። እነዚህ ጥናቶች ከጥናትነት ባሻገር የሚያስገኙት ፋይዳ ምንድነው ? የሚለውን የመዳሰስ ማንዋሎች እንዲዘጋጁ የማድረግ ባለሙያዎቻችን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የነቃ ተሳትፎን እንዲያደርጉ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል።

በሌላ በኩልም እንደ ከተማ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 20 አዋጆችን 52 ደንቦችንና 295 መመሪያዎችን የማርቀቅ ስራዎች ተሰርተዋል። ለህብረተሰቡም እንዲዳረሱ ግልጽ በሆኑ ፕላት ፎርሞች እንዲዘረጉ ሆኗል። ይህ ሁሉ ስራ በዚህን ያህል ደረጃ ሊሰራና መልክ ሊይዝ የቻለውም በመጀመሪያ ደረጃ ለውጡ እንዲመጣ በራሱ የሆነው የህዝቡ የፍትህ ጥያቄ እንደመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ተጨባጭና ለውጥ የሚያመጣ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ በበላይነት በመያዝና በቁርጠኝነት በመስራቱ ነው።

ተቋሙ በዋናነት ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ክፍተት ባለባቸው ሕጎች ዙሪያ ጥናት ማድረግ ነው፤ በዚህም ክፍተት ያለባቸው ነባር ሕጎች እንዲሻሻሉና እንዲተኩ ይደረጋል። አዳዲስ የሕግ ማዕቀፍ የሚያስፈልጋቸው በተለይም በተቋማት ጥያቄና በመስሪያ ቤቱ ተነሳሽነት የሚወጡ ሕጎች አሉ። በመሆኑም እኛ የሕጉን ረቂቅ አዘጋጅተን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ በካቢኔው ውሳኔ የሚያገኙ መመሪያዎች ሂደቱን ካለፉ በኋላ ለሕዝቡ ይፋ የሚሆኑበት እንዲሁም ለሕትመት በቅተው ተደራሽ የሚደረጉበት ሁኔታ ይሰራል።

ሕዝቡ ጋር በይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑም ከሕትመት ባሻገር የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን እንጠቀማለን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሕጎቹን የማስገንዘብና የማስረጽ ተግባር ተቋሙን የሚመለከት በመሆኑ በዳይሬክቶሬት ደረጃ የተለያዩ ክፍሎችን በማቋቋም ስራዎች እንዲሰሩ ይደረጋል። ሌላው የተቋሙ ትልቅ ስራ ክርክር ማድረግ እንደመሆኑ ክርክሮች ሲደረጉ ቆይተዋል ፡፡

በዚህም ተቋማት ይከሳሉ እንዲሁም ይከሰሳሉ ይህንን ተከትሎም ተቋማት የክሰሱልኝ ጥያቄ ሲያቀርቡ መረጃዎች ተሰባስበውና መዝገብ ተደራጅቶ በሚላከው መሰረት ተቋሙ ተገቢና ትክክለኛ ክርክሮችን ያደርጋል። ከክርክር ባሻገር ድርድርም ይደረጋል። ይህም የማያዋጣ ከሆነ አቃቤ ሕጎች ተወያይተው ፋይል የመዝጋት አልያም ክስ የማቋረጥ ስራም ይሰራል። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ 28 ሺ 521 የፍትህብሔር መዝገቦች ክርክር ያደረግንባቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 21ሺ 786 በሚደርሱ መዝገቦች ላይ መርታት ተችሏል። ይህ ውጤት በገንዝብ ሲተመን 7 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገደማ የሕዝብና የመንግስት ጥቅምን ማስጠበቅ ችለናል።

አዲስ ዘመን፦ እነዚህ ውጤቶች መመዝገባቸው ጥሩ ነው ነገር ግን ይህ ትልቅ የሕዝብና የመንግስት ኃላፊነትን የተሸከመ ተቋም በሰራቸው ስራ ፍትህ በማስፈን በኩል ምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ተክሌ ፦ ተቋሙ የሚከውናቸው 27 የሚደርሱ ዋና ዋና ተልዕኮዎች አሉት፡፡ በዋናነት ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ በሕግ ጉዳዮች ላይ አማካሪ ነው። በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ተቋማት በሚከሰሱበት ጊዜ መልስ የሚሰጥ፤ መክሰስ ባለባቸው ጊዜ ተቋማቱን በመወከል ክስ የሚያቀርብ ነው። ከዚህ በተጓዳኝም ምክሮችን በቃል በጽሁፍ የሚያቀርብ ነው የሚሆነው። እዚህ ላይ ግን ምክርን በቃልና በጽሁፍ የምናቀርበው ለተቋማት ብቻ ሳይሆን የፍትህ ጥማት ላለባቸው ነገር ግን በአቅም ውስንነት ምክንያት ባለሙያ ማማከር ላልቻሉ ግለሰቦችም ነው።

ይህ ደግም እንደ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በከፍተኛ ኃላፊነትና በቁርጠኝነት የምንሰራው ስራ ከመሆኑም ባሻገር የትኛውም የአቅም ውስንነት ሰው በተለይም ሴቶች ሕጻናትና አረጋውያን የሕግ ድጋፍ ፈልገው ቢመጡ ምን ጊዜም በራችን ክፍት መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማሳወቅ እፈልጋለሁ።

ከዚህ ውጪ በሌሎች አማራጮች በተዘረጉ ቅሬታ፤ ጥቆማ መቀበያ የስልክ አድራሻዎችና በሌሎች መንገዶችም የሚመጡ ጉዳዮችን ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው። በሌላ በኩልም ከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ አስፈጻሚ ተቋማት በሙሉ የአሰራር ስርዓት ለማሳለጥ ውጤታማ ተግባርን ለማከናወን እንዲያስችላቸው የሚያግዟቸውን የሕህግ ሃሳቦች እናረቃለን። ከተማ አስተዳደሩ ላይ የግዢ የግንባታ እንዲሁም የዜጎችን ሕይወት እንዲቀይሩ በሚሰሩ የልማት ስራዎች ዙሪያ ከውጭም ከአገር ውስጥም በሚገቡ ውሎች ዙሪያ ምርመራ ይደረጋል። ተቋማትም እንዲያጸድቁ ተገቢ የሆነ የሕግ አስተያየትን እንሰጣለን።

መንግስትን ያልተገባ ወጪ ሊያስወጡ የሚችሉ ውሎች በሚኖሩበት ጊዜ አስተያየት እንሰጣለን፤ በመሆኑም የሚሰሩ የልማት ስራዎች በሙሉ በዚህ ቢሮ ማለፋቸው የግድ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ በተለይም ስራዎችን የሕግ ድጋፍ ሰጥቶ ከማሳለጥ አንጻር ሰርቻቸዋለሁ የሚለው ስራ ማሳያ ማንሳት እንችል ይሆን?

አቶ ተክሌ ፦ አዎ እንችላለን ። ለምሳሌ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የወንዝዳር ፕሮጀክቶችን ቸርችል ላይ የተሰሩ የልማት ስራዎችን እንዲሁም የጫካ ፕሮጀክቶችንን በሌሎች አልሚዎች የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ የሚመጡ በርካታ እግዶች ያሉ በመሆኑ እነዚህን በፍርድ ቤት ክርክር በማድረግና በአጠረ ጊዜ እንዲመለሱ በማስቻል ስራዎችን ሰርተናል። ይህ ሲሆን ደግሞ የመንግስትን ስራ ከማሳለጥ ባሻገር ዜጎች ሳይጎዱ የሚገባቸውን ይዘው አካባቢውን ለልማት ክፍት እንዲያደርጉ በዚህም መብቶቻቸው ተጠብቀው ልማቱ እንዲቀጥል የማድረግ ስራ ተሰርቷል።

ይህ እንግዲህ በአንድ ጎን የዜጎችን ሕይወት የሚቀይሩ የልማት ስራዎች ከመሆናቸውም በላይ ከተማዋ ሊኖራት የሚገባውን ገጽታ እንድትይዝ ብሎም ከልማቱ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና ያለው ነው ።

አዲስ ዘመን፦ ስራውን ከማሳለጥ አንጻር ተቋሙ ያጋጠመው ተግዳሮት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ተክሌ፦ በዋናነት የሚነሳው በፍትሃብሄር ጉዳዮች ላይ በብዛት እንከራከራለን፡፡ ልምድ ያላቸው በርካታ ባለሙያዎችም አሉን፡፡ እነሱም ተረጋግተው ኃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ኃላፊነቱንም ተወጥቷል ማለት ይቻላል። በዚህም ደመወዛቸው ወቅቱን ያገናዘበ ሆኗል። በሌላ በኩልም የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ስነስርዓት ተከትሎ ባለሙያዎች ስነስርዓት ያለው አለባበስ እንዲለብሱ ከማድረግ አንጻር ሁሉም ክፍለ ከተማ በማዕከል ያሉ አቃቤ ሕጎችም የአልባሳት ግዢ እንዲፈጸም ተደርጓል።

ነገር ግን የፍትሐብሔር ላይ እየተከራከርን ወንጀል ነክ ጉዳዮች ቢያጋጥመን እኛ መክሰስ የምንችለው ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ በመሆኑ የነዋሪውን የፍትህ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ እንዳናሳካ እንቅፋት ሆኖብናል። የወንጀል ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን ቢኖረን ውጤታማ የሆነ ስራን እንሰራ ነበር። ይህ እንግዲህ ከቻርተሩ ጀምሮ የተቀመጠና የተቀላቀለ ነገር ነው፤ አዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ የስራ ድርሻውን እንዲሁም የበጀት አመዳደቡን የሚያጸድቀው ከተማ አስተዳደሩ ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ ይላል ።

የከተማው አቃቤ ሕግ ቀጥታ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የማዘዝ ስራዎችን ከመፈጸም አንጻር ውስንነቶች አሉበት፡፡ በመሆኑም እነዚህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፍትህ ዘርፍ ከጀመረው ትራንስፎርሜሽን ስራ በከተማ አስተዳሩም እየተመራ ስለሆነ በዚህ መሰረት አንዳንድ ማሻሻያና ማስተካከያዎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባሻገር የተለያዩ የአቅም ግንባታዎች እየተደረጉ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ያልተፈታውና ተቋሙን በተለያየ አይነት ስም የሚያስነሱ የተወሰኑ ሰዎች ላይ ቢሆንም የስነ ምግባር ጥሰቶች አሉ፤ ይህንንም ለመፍታት እየሰራን ቢሆንም አሁንም ከችግሩ ስላልወጣን የተጠናከረ ስራን መስራት እንደሚፈለግብን እንገነዘባለን።

ከሀብት ውስንነት አንጻር ቴክኖለሎጂ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶች አሉ ነገር ግን ወደፊት ስራዎች ከእጅና ከወረቀት ንክኪ ነጻ ይሆኑ ዘንድ ስራዎችን በቴክኖሎጂ ለመስራት ከፍ ያለ ጥረትን እያደረገን እንገኛለን።

ሕብረተሰቡ በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች ሕጎች ይወጣሉ፡፡ እንዲያውቁትም ጥረት ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ተቋሙ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር ሕጎችን የማስረጽ ስራን እየሰራ ነው። ይህም በቂ ባለመሆኑ በቀጣይም ሌሎች አማራጮችን ለማየት እንሰራለን ።

አዲስ ዘመን ፦ የቢሮው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችስ ምንድን ናቸው?

አቶ ተክሌ፦ ቢሮው አርዓያ የሆነ የፍትህ ተቋም መገንባትን ግብ አድርጎ ነው የሚንቀሳቀሰው ፤ ይህንን ለማሳካትም በብቃትና በስነ ምግባር የበቃ የሰው ኃይል የማፍራት ስራ ይሰራል። ለዚህም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ባለሙያዎችን በመቀበል ሀብት በመመደብና ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ስራ አስገብተናል። ይህንን ልምድም የማስፋት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ተቋሙን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማደራጀት አገልግሎቶቹ በቀላሉ ሕብረተሰቡ ጋር ተደራሽ እንዲሆኑ የሚሰሩ ስራዎችንም የማስፋት እቅድ ተይዟል። በተለይም በሕገወጥ መንገድ ዜጎችን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት ጥቆማ መቀበያ ነጻ የስልክ መስመር የማዘጋጀት ስራ ተሰርተቷል፤ ይህም ከአይ ኦ ኤም ጋር የሚሰራ ሲሆን 6073 ነጻ የስልክ መስመር ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ተክሌ፦ እኔም አመሰግናለሁ

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You