ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውሮፓ ቻምበር ለባለሃብቶች ለልማት በሚውል መሬት አቅርቦት ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ጥናት ሰነድ ይፋ አድርጓል። ‘የመሬት ተደራሽነት፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ ላሉ ባለሃብቶች የመሬት አሰጣጥ ሂደትን ማመቻቸት’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይኸው ሰነድ፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ዞኖች ውጪ በልማት ሥራ ውስጥ የተሰማሩ ባለሃብቶች የልማት መሬት ከማግኘት ጋር ተያይዞ እያጋጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን አመላክቷል። የፖሊሲ ሰነዱ በአውሮፓ ቻምበር እና በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም በጂአይዜድ ትብብር የተዘጋጀ ነው፡፡
ሰነዱ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ያሉ የቢሮክራሲ መዘግየቶች፣ ቀድሞ የተዘጋጀ በቂ የኢንቨስትመንት መሬት አለመኖር፣ ከመጠን ያለፈ የካሳ ጥያቄ እና የካሳ አሰጣጥ አስተዳደር ችግሮች (በቀጥታ ለሕብረተሰቡ ከመስጠት ይልቅ ወደ መልሶ ማቋቋሚያ ፈንድ ለማስገባት መወሰኑ) የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን አጉልቶ አሳይቷል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በክልላዊ መዋቅርና በመሬት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ላይ በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦች፣ በልማቱ አካባቢ ለመድረስ የመሰረተ ልማት አውታሮች ውስንነት፣ በፌደራልና በክልል ባለስልጣናት መካከል ያለው የቅንጅት ክፍተት፣ የማጭበርበር ተግባራት፣ የአስተዳደር አቅም ችግሮች እና የሃብት ውስንነቶች፣ የመሬት ድልድል ተመሳሳይ አለመሆን እና የባለሃብቶቹ መሬትን ተገቢ ላልሆነ ተግባር መጠቀም ችግሩን እንደሚያባብሱ በሰነዱ ላይ ተገልጿል፡፡
የፖሊሲ ሰነዱ በኢትዮጵያ መንግስት ሊታሰብባቸው የሚገቡ የውሳኔ ሃሳቦችን አመላክቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል ግልፅነትን፣ ፍትሓዊነትን እና ቀልጣፋ የመሬት አስተዳደርን በማስፈን ኢንቨስትመንትን እና የኢኮኖሚ ልማትን የሚያበረታታ ግልፅና ወጥነት ያለው ፖሊሲ መዘርጋት ይጠቀሳሉ፡፡ የመሬት አስተዳደር መሥሪያ ቤቶችን አቅም ማሳደግ፣ የፌደራልና የክልል መንግስት ቅንጅቶችን ማጎልበት፣ የፀረ-ሙስና ርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እና ግልፅነት ያለው የመሬት መዝገብ ማዘጋጀት ከተነሱት ሌሎች ዋና ዋና ሃሳቦች መካከል ናቸው፡፡
ተጨማሪ ምክረ ሀሳቦች የካሳ ክፍያን ለማስላት መመሪያዎችን ማዘጋጀት እና የመሬት ግምትን እንደ ግብርና ሚኒስቴር ካሉ አካላት ጋር ማስተባበር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አገልግሎት ውጤታማነትን ማሻሻል፣ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች የመሬት ምደባ መመሪያዎች ማዘጋጀት፣ ከተፈናቀሉ ግለሰቦች ጋር የምክክር ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ በክልላዊ የመሬት አስተዳደር ቢሮዎች የመሬት አሰጣጥ ሂደቶችን ማቀላጠፍ እና እንደ ቪዬትናም ካሉ ሃገሮች የተሳካ የመሬት አስተዳደር ማሻሻያዎች ተሞክሮ ማጥናትን ያካትታሉ፡፡
የፖሊሲ ሰነዱ በኢንተርኔት አማካኝነት የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ሲሆን፣ አንድ ለአንድ የተካሄዱ ቃለመጠይቆች እና ሚኒስቴር መስራቤቶችን፣ የንግድ ማኅበራትን፣ ባለሃብቶችን እና ምሁራንን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄዱ የትኩረት ቡድኖች ውጤቶችን ያካተተ ነው፡፡ በተጨማሪም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሣ የሚከፈልበት እና ተነሳች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን አዋጅም ቃኝቷል፡፡ የሰነዱ ዓላማ በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት መሬት ከማግኘት ጋር በተያያዘ የግሉ ሴክተር የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በመለየት በግሉ ሴክተር ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና የውጭ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ መሳብ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ቻምበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ተመስገን የፖሊሲውን ይዘት አስመልክቶ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳብራሩት፤ የፖሊሲው ዋና ዓላማ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የውጭ ባለሃብቶች የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት ነው፡፡ የፖሊሲ ሰነዱ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ የተሰራ ሲሆን በተለይም በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች ከመሬት አቅርቦት ጋር ተያይዞ እየተፈተኑበት ያሉበትን ሁኔታ በመዳሰስ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ነው፡፡
‹‹ለኢንቨስትመንት የግድ መሬት ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ሰፊ የመሬት ሃብት አላት፤ ይሁንና ይህንን ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ሰፊ ክፍተቶች ይታያሉ›› ይላሉ፡፡ ይህንን መሬት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ያስችል ዘንድ ምክረ ሃሳብ የሚሰጥ የፖሊሲ ሰነድ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ጥናት መነሻነት ሃገር ውስጥ ያሉ የአውሮፓ ሕብረት በተለይ በግብርና ላይ የሚሰሩ ተቋማት ያላቸውን ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ፍላጎት እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ የመሬት አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን አቶ ባህሩ አስታውሰው፤ በዚህ ረገድ በ2005 ዓ.ም የወጣው የመሬት አዋጅ በ2007 ዓ.ም በወጣ ማስፈፀሚያ አዋጅ መነሻነት ሥራ ላይ ውሎ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በኋላም ሌላ አዋጅ ቢወጣም የማስፈፀሚያ ዳይሬክቲቭ ባለመውጣቱ ምክንያት የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ ይስተዋላል፡፡ ማስፈጸሚያ ባወጡትም ክልሎች ላይ ወጥነት ያለው አሰራር ሲከተሉ አይስተዋልም፡፡ ከዚህ አንፃር የፖሊሲ ጥናቱ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ይናገራሉ፡፡ መንግስትም ከዚህ ጥናት በመነሳት ችግሮቹን እንዲፈታ በማለም የተዘጋጀ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት፡፡
በፖሊሲ ጥናቱ የቀረቡ አብዛኞቹ ችግሮች መንግስት የሚያውቃቸው ቢሆኑም ችግሮቹን ለይቶ ወደ መፍትሔ መምጣት ላይ ግን ክፍተት ይስተዋላል ይላሉ፡፡ ይህን ሲያብራሩም ‹‹መንግስት ሙስና እንዳለ ያምናል፤ ነገር ግን መሬት ላይ ወርዶ ሙስናን ከስሩ ማድረቅ ላይ ቁርጠኝነት አይታይበትም›› ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡ የመሬት ባንክ በወረዳ ደረጃ እንደሚቋቋም የተገለፀ ቢሆንም፤ ግን ኢንቨስተሮች ከመጡ በኋላ መሬት ለማቅረብ የመሯራጥ ሁኔታ ይታያል ሲሉ አመልክተው፣ ከዚያ ይልቅ በእያንዳንዱ ወረዳ ያለውን የመሬት ሃብት አስቀድሞ በአግባቡ በመለየት ልክ ሲመጡ መስጠቱ የተሻለ የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚስብ እንደሆነ በጥናቱ መቀመጡን ያስረዳሉ፡፡
አቶ ባህሩ እንደሚሉት፤ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት እንደትልቅ ተግዳሮት ሆኖ የሚቀርበው በመንግስት ተቋማት ውስጥ ያለው ቢሮክራሲ ነው፤ ከፍተኛ መዋለንዋይ ለማፍሰስ የመጣ የውጭ ባለሃብት ረጅምና የተንዛዛ ቢሮክራሲን በትዕግስት ለማለፍ ይገደዳል፡፡ በዚህ ረገድ የአንድ መስኮት አገልግሎት መዘርጋቱ እንደመፍትሔ የሚወሰድ ቢሆንም በሁሉም ደረጃ ያለመስፋቱ ውጤታማነቱን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በተለይ በአበባ ልማት ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ኩባንያዎች ቢሮክራሲው እየፈጠረ ያለው ችግር ካልተፈታ ባለሀብቶቹ አይናቸውን ወደ ሌላ የአፍሪካ ሃገር ሊያዞሩ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው፡፡
‹‹ለአበባ ልማት የሚያስፈልገው መልካም ምድርና ምቹ የአየር ንብረት መኖሩ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ያለው መንግስታዊ አሰራርም ምቹ መሆን ከሌሎች ሃገራት ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጋት በመሆኑ በተቋማቱ ያለውን አሰራር መፈተሽ ይገባል ሲሉ አቶ ባህሩ ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ረገድም የፖሊሲ ጥናቱ ያስቀመጣቸው ምክረ ሃሳቦች መኖራቸውንም ነው አክለው ያመለከቱት፡፡ በጥናቱ ላይ በተለይ የግብርና ሚኒስቴርና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መሳተፋቸውን ገልፀው፤ ከዚህ በኋላ በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች በመሳተፍ ለትግበራው አወንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ክፍል የመሬት ሕግ ባለሙያ አቶ አበባው አበበ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሚኒስቴሩ የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማበረታት የተለያዩ ሕጎችን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ውስጥ በተለይ ኢንቨስተሮቹ መሬት የሚያገኙበትን መንገድ የሚያሻሽል፤ መሬት ካገኙም በኋላ ኢንቨስት አድርገው ሀገሪቱን የሚጠቅም ሥራ እንዲሰሩ የቁጥጥር ስራዎችን ጭምር የሚያስቀምጥ ሕግ ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ የባለሃብቶቹን መብት የሚያስከብር ሲሆን፤ መሬት ካገኙ በኋላ መሬቱን የመጠቀም ባለመብትነታቸው እንዲመዘገብ የሚያደርግ ሕግ ነው፡፡ ይህ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ አሁን ላይ እየተነሱ ያሉትን ቅሬታዎች ይፈታል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡
በሌላ በኩል ቀድሞ የፀደቀውና ለሕዝብ ጥቅም ሲፈለግ መሬት ከባለ ይዞታዎች የሚወሰድበት ሕግ መኖሩን አስታውሰው፤ በዚህ ሕግ መሰረት ባለሃብቶች ሲመጡ በቢዝነስ ፕላናቸው መሰረት መሬት የሚያገኙበት፤ ያገኙበትን መሬት በተገቢው መንገድና በተቀመጠላቸው ውል አማካኝነት ኢንቨስት እንዲያደርጉና ራሳቸውን ጠቅመው ሃገርንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሕጎች መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
‹‹በመድረኩ ላይ እንደተነሳው በተለይ በሕጎች አፈፃፀም ላይ ችግሮች መኖራቸው የማይካድ ነው፤ የእኛ መስሪያ ቤትም በዋናነት ሕጎችን የማሻሻልና ክልሎችም ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን አውጥተው እንዲተገብሩ ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየሰራ ነው›› ይላሉ፡፡ በተለይም ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት ጋር በመሆን ክልሎች የወጣውን ሕግ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም ይገልፃሉ፡፡
ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ በመድረኩ ላይ የተነሳውን የሕግ አፈፃፀም ችግር አስመልክተው ሲያብራሩ አዋጅና ደንብ በፌደራል ደረጃ ነው የወጣው፤ መመሪያ ክልሎች እንዲያወጡ ነው የሚጠበቀው ብለዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ሁሉም ክልሎች መመሪያ እንዲኖራቸው ግፊት የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አመልክተው፣ በዚህ መሰረትም አማራ ክልል፤ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ደግሞ መመሪያውን አዘጋጅተው ይፀድቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ አብዛኞቹ ክልሎች አፅድቀው ወደ ተግባር አይሂዱ እንጂ ረቂቅ አዘጋጅተዋል ይላሉ፡፡
‹‹መመሪያው ዝርዝር ነገር ያስቀምጣል እንጂ አዋጅና ደንብን ለመተግበር የሚከለክል ነገር የለም›› የሚሉት አቶ አበባው፤ በዚህ መሰረትም ሚኒስቴሩ ክልሎቹ እንዲሰሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት፡፡
በአማራጭ ፖሊሲው የተቀመጡ አብዛኞቹን ችግሮች ሚኒስቴሩ የሚጋራቸው መሆኑን ያነሳሉ። አብዛኞቹ ከአፈፃፀም ጋር ተያይዘው የተነሱ ችግሮች በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታዩ ስለመሆናቸው ባለሙያው ያምናሉ፡፡ ብዙዎቹ አንኳር ጉዳዮች መንግስት የግብርና ኢንቨስትመንት አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየሰራ ላለው ሥራ እንደግብዓት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይም ሕጎችን ለማሻሻል እየተሰራ ላለው ሥራ የማይናቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያስረዳሉ፡፡ በየክልሉ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉም ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና ሕጉ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችንም በቅጡ ካለመረዳት የመነጩ አንዳንድ ሃሳቦች መኖራቸውን ያመለክታሉ፡፡ እንደ ችግር ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል አብነት አድርገው ሲጠቅሱ ‹‹ካሳ በሚከፈልበት ጊዜ ካሳውን ባለሃብቶች ለመንግስት ነው የሚከፍሉት፤ ከዚህ በፊት ግን ካሳውን በቀጥታ ለባለይዞታ ነበር የሚከፍሉት፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጉዳይ እኛ እንደ ችግር አናየውም›› ይላሉ፡፡ ‹‹ምክንያቱም መንግስት ከባለይዞታውና በባለሃብቱ መካከል ድልድይ ሆኖ የማገልገል ሚና የሚጫወት በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ያግዛል እንጂ ችግር ሊሆን አይችልም›› በማለት ተናግረዋል፡፡
በፖሊሲ ሰነዱ ከተነሱ አብይ ችግሮች መካከል ከላይኛው የመንግስት አካል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የተንዛዛ አሰራርና ቢሮክራሲ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንንም ጉዳይ በሚመለከት አቶ አበባው ‹‹ቢሮክራሲውን መቀነስ የሚቻለው በዋናነት ተጠያቂነትን ማስፈን ሲቻል ነው፤ የእኛ መስሪያ ቤት ሚና የአቅም ግንባታ ስራ መስራት ነው›› ይላሉ፡፡ ክልሎች ላይ ቢሮክራሲ ሳይኖር ሥራቸውን እንዲሰሩ ሕግ የማውጣትና አቅማቸውን የማጠናከርና ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑም ያብራራሉ። ተጠያቂነትን ማስፈን የሚቻለውም ሚኒስቴሩ ብቻ በሚያደርገው ጥረት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲታከልበት እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተወካይ እንዳሉት፤ የፖሊሲ ጥናቱ በዋናነት ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጪ ለሚለሙ እንደ ግብርና ያሉ የኢንቨስትመንት ሥራዎች መጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይ ባለሃብቱ ለኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ከሚጠይቃቸውና ዋነኛ ግብዓት የሆነው የመሬት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፈተሽ ይረዳል። በሃገሪቱ ሕግ መሬትን የማስተዳደር መብት ለክልሎች የተሰጠ እንደመሆኑ በየአካባቢው ያለው የመሬት አሰጣጥም ሆነ በኢንቨስትመንት ምክንያት ለሚነሱ ባለይዞታዎች ካሳ ክፍያ አሰራር ወጥነት የለውም። ይሁንና በጥናቱ ላይ እንደተነሳው ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ተገማች ዋጋና ጊዜ አስቀድሞ አውቆ መስራቱ ወሳኝ ነገር እንደሆነ ይታመናል፡፡
በዚህ ረገድ የፖሊሲ ጥናቱ ወደፊት ተቋሙም ሆነ እንደሃገር ለመስራት ለታቀዱ የልማት ሥራዎች ወሳኝ ሚና እንዳለው ይናገራሉ፡፡ በተለይም ባለሃብቶች ለልማት መሬት ሲጠይቁ ያለቢሮክራሲና የተንዛዛ አሰራር በቀጥታ መሬት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ያግዛልም ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ ኮሚሽኑ ባለኃብቶቹ የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች የሚቀበል መሆኑን ጠቁመው፤ ከሚነሱት ቅሬታዎች መካከል የመሬት ጉዳይ ዋነኛው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ መሬት ከተሰጣቸው በኋላም በተለያየ ምክንያት መሬቱ ላይ ያላቸው መብት የሚጣስበት ሁኔታ መኖሩም ተወካዩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ ይህ ችግር መኖሩን ያምናል፤ መሬትን የሚመለከት ችግር የለም ማለት አይቻልም፤ ይሁንና ተቋማችን ለመፍትሔም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ይሰራል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹በመድረኩ የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦች ወደፊት ለሚከናወኑት ሥራዎች ጥሩ ግብዓት ናቸው፤ እንደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተቀብለን የምናስተካክል ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡ ከሕግ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ የተነሱ ችግሮችንም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ያመለክታሉ፡፡ ተወዳዳሪ የሆነ ሃገር መፍጠር የመንግስት ቁርጠኛ አቋም መሆኑንም ጠቅሰው፣ ባለሃብቶቹ ወደ ሌላ ሃገር እንዳይሸሹ መስራት ይገባል የተባለውም ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ የሚቀበሉት እንደሆነ ነው ተወካዩ የተናገሩት፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም