ገበያውን የማረጋጋት ጅምር ውጤቶችን ማጠናከር ይገባል!

ዛሬ ላይ የሚታየው የገበያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ንረት የዜጎችን የመሸመት አቅምና በልቶ የማደር ሕልውና እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ ይሄ ደግሞ በአንድ በኩል የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም የፈጠረው ስለመሆኑ ይነገራል። በሌላ በኩል፣ በአሰራርና ቁጥጥር ሊመለሱ የሚገባቸው ተግባራት በአግባቡ ባለመሰራታቸው ምክንያት የተፈጠረ ስለመሆኑም ይገለጻል፡፡

ይሄን ችግር ከመፍታት አኳያም በመንግስት በኩል ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ፤ የማሻሻያ እርምጃዎችም ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም፣ በምርትና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ድጎማ የማድረግ፤ የቀረጥ ነጻ አገልግሎት መፍቀድ እና አቅርቦትን ማሳደግ የመሳሰሉ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በእነዚህም መልካም ውጤት ማየት ተጀምሯል፡፡

ለምሳሌ፣ ገበያውን ለማረጋጋት ከተወሰደው ርምጃ አንዱ፣ ፍራንኮ ቫሉታን ለገቢ ምርቶች በተለይም ለመሰረታዊ ሸቀጦች ማስገቢያ ማዋል የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱ ነው፡፡ በዚህም በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ወደ 18 ቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ መንግስት ከግብር ማግኘት የሚገባውን ገንዘብ የተወ ሲሆን፤ ይሄም የሸቀጦች አቅርቦት እንዲጨምር የራሱን ሚና ተወጥቷል፡፡ አቅርቦት ሲጨምር ደግሞ ቢያንስ በገበያ ላይ ምርቶችን እንደ ልብ ማግኘት እንዲቻል አድርጓል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘይት እና መሰል ምርቶችን መመልከት ይቻላል፡፡

ከዚህ ባሻገር የሀገር ውስጥ አምራች ፋብሪካዎችን በመደጎምና አቅማቸውን በማጠናከር በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የተሰራው ስራ ገበያውን በማረጋጋት በኩል ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዘይት፣ በፓስታና ማኮሮኒን በመሳሰሉ የፍጆታ ምርቶች ላይ በዋጋም፣ በምርት አቅርቦትም ረገድ መልካም ውጤት ማየት ተችሏል፡፡

ሌላው የመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት ከመጨመር አኳያ፣ የግብርናውን ምርትና ማርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህም የግብርና ምርቶችን በስፋት ማቅረብ እና ቢያንስ የምርት እጥረት እንዳይኖር ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም በኪሎ እስከ 80 ብር ሲሸጥ የነበረ ቲማቲም፣ ወደ 15 እና 20 ብር እንዲወርድ፤ እስከ 140 ብር ሲሸጥ የነበረ ሽንኩርት፣ ወደ 70 እና 75 ብር እንዲወርድ ተደርጓል፡፡

እንደ ፍጆታ ምርቶች ሁሉ በገበያው ላይ የተወሰደው ርምጃ የግንባታ ግብዓት ቁሳቁሶች ላይም መሻሻልን አምጥቷል፡፡ በዚህ መልኩ በተለይም ሲሚንቶ እና ብረትን የመሳሰሉ የግንባታ ግብዓቶች ላይ ልጓም አልባ የዋጋ ማሻቀብ ተስተውሎ ነበር፡፡ ይሄንን የዋጋ ንረት ለመከላከልም የተለያዩ ርምጃዎች ተወስደው አወንታዊ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡

በዚህ በኩል የዋጋ ተመን ከማስቀመጥ ጀምሮ፣ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ችግር ፈጣሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን በተለይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ወደ ምርት እንዲገቡና፣ በሙሉ አቅማቸውም ማምረት እንዲችሉ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል፡፡ በዚህም የሲሚንቶ አቅርቦቱን ማሳደግ፤ የግንባታ ግብዓት ቁሳቁሶችንም ዋጋ በገበያው እንዲወሰን በማድረግ እንዲረጋጋ ማድረግ ተችሏል፡፡

በዚህ መልኩ ለታየው የዋጋ መረጋጋት ጅምር ውጤት ተደማሪ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ፣ በቅርቡ በብሄራዊ ባንክ የተቀመጠው የማክሮ ኢኮኖሚውን የማረጋጊያ አቅጣጫዎች ወደ ተግባር መግባት ነው፡፡ የበዛ የገበያ ሰንሰለትን መቀነስና የደላሎችን ጣልቃ ገብነት መግታት የሚያስችሉ ርምጃዎችም መወሰዳቸው ሌላው የችግሩ መቃለል ምክንያት ነው፡፡

በዚህ ረገድ፣ አላስፈላጊ አሰራርን በሚፈጥሩ ላይ የድለላ ፈቃድን ባለማደስ ደላሎች የሚፈጥሩትን ገበያን የመረበሽ ተግባርን ለመቀነስ የሚያስችል ርምጃ ተወስዷል፡፡ በሌላ በኩል፣ አምራቹና ሸማቹ ባጠረ የገበያ ሰንሰለት የሚገናኙበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡ በዚህም በ160 ቦታዎች የተጀመረው የሰንበት ገበያ አሁን ላይ በ940 የሰንበት ገበያዎች መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በቅርበትና በቀጥታ ለተጠቃሚ እየቀረቡ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ የተወሰዱ ርምጃዎች እና ጅምር ውጤቶች በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሰዋል ተብሎ አፍን ሞልቶ የሚያናግሩ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል፣ ዋጋቸው ቀነሰ የሚባሉ ሸቀጦች የቀነሰው ዋጋቸው አሁንም ቀድሞ ከነበረበት አኳያ ሲታይ ከፍ ብሎ ያለ ነውና፡፡

ለዚህ ሽንኩርትን ማየት ቢቻል፣ 20 እና 25 ብር ሲሸጥ የነበረው ነው 140 ብር የደረሰው፡፡ እናም አሁን ላይ ወደ 70 እና 75 ብር ወረደ ቢባልም፣ ቀድሞ ከነበረበት አኳያ ሲታይ አሁንም ዋጋው እንደጨመረ ያለ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ እንደ ጤፍ እና መሰል የግብርና ምርቶች ላይ አሁንም እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከወዲሁ ሊታሰብበትና እርምት ሊደረግበት የሚገባው ነው፡፡

በመሆኑም በአንድ በኩል ገበያውን ለማረጋጋት የተወሰዱ እና ውጤት እያስገኙ ርምጃዎችን ለይቶ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ተግባሩን አልቆ ማስቀጠል ይገባል፡፡ በሌላ በኩል፣ ርምጃ ተወስዶ ውጤት ከተገኘባቸው አሰራሮች ልምድ በመውሰድ አሁንም ፈተና ሆነው በቀጠሉ ዘርፎች የሚታየውን የገበያ ችግር ለመፍታት መሥራት ይገባል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከኅብረተሰቡም፣ የንግዱን ዘርፍ ከሚመራው አካልም፤ ከፀጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅ ኃላፊነት መኖሩን ተገንዝቦ በጋራ መስራት ይገባል፡፡ ይሄ የተቀናጀ አሰራር ሲፈጠር ደግሞ ከማሳ እስከ ማዕድ ያለው የግብይት ሂደት የተሳለጠ ይሆናል፤ ሕገወጦች ለክፋት ተግባራቸው የሚሆን ቀዳዳን እንዲያጡ ያደርጋል፤ ሸማችና አምራቹ በልኩ ተጠቃሚ የሚ ሆንበትንም እድል ይሰ ጣል!

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You