‹‹ልጆችዬ!›› እንደምን ከረማችሁ? ዛሬ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ቆይታ እናደርጋለን። ለመሆኑ ፓርላማ ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? የምታውቁ ካላችሁ መልካም። የማታወቁ ብትኖሩ ደግሞ ከዛሬው የልጆች ዓምድ ላይ ጥቂት ግንዛቤ እንደምታገኙ ተስፋ አለኝ፡፡
ልጆች ‹‹ፓርላማ›› የሚለው ቃል የተገኘው ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ነው። በተግባሩ ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት በሚባለው ክፍል የሀገሪቱ የሕግ አውጭ አካል በመሆን ይሠራል። ስለፓርላማ ምንነት ጥቂት ከነገርኳችሁ እናንተን ስለሚመለከተው የዛሬው ርዕስ ስለ ሕጻናት ፓርላማ ደግሞ ጥቂት ላውጋችሁ ፡፡
በሕገ መንግስቱ ድንጋጌ አንቀፅ 25 ላይ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ስለመሆናቸው ተደንግጓል። በአንቀጽ 36 ላይ ደግሞ ሕጻናት በሕይወት የመኖርና የማደግ፣ ከማንኛውም የኃይል ጥቃትና ብዝበዛ፣ ከአድሎዓዊነት ነፃ የመሆን መብት እንዳላቸው ሰፍሯል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሕጻናት በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብቶቻቸው የተከበሩ ስለመሆኑ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ልጆችዬ! ለሕጻናት ከተሰጡ መብቶች መካከል ዛሬ የምንነጋገርበት የሕጻናት ፓርላማ አንዱና ዋንኛው ነው። በሀገራችን የሕጻናትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይህን መሠረት በማድረግም በ1999 ዓ.ም በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አማካኝነት በደቡብ ክልል ‹‹ኮንሶ›› ላይ የመጀመሪያው ሞዴል የሕጻናት ፓርላማ ሊመሠረት ችሏል ፡፡
የፓርላማው ዋንኛ ዓላማ የሕጻናትን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን መፍጠር ነው። ይህ አደረጃጀት ደግሞ ወደፊት እናንተን መሰል ልጆች በሀገራቸው የልማትና ዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ፡፡
በኢትዮጵያ መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የሕፃናት ፓርላማ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተውጣጡ አባላት ተሳትፎ ተደርጎበታል። በተለያዩ ክልሎችም ፓርላማ የሕጻናት ፓርላማ ተቋቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈርማ ያጸደቀቻቸው የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን ተግባራዊ እንዲሆን የዚህ ፓርላማ አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው። ፓርላማው በቀበሌ፣ በወረዳ በዞንና ክፍለ ከተሞች፣ በክልል ከተሞችና አስተዳደሮች፣ በትምህርት ቤቶች የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በየደረጃው መቋቋም ይችላል።
በሁሉም ክልሎች ደግሞ የራሱ አፈ ጉባኤ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ፣ ጸሐፊና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች አሉት። አባላቱ እንደማንኛውም የምክር ቤቱ ተመራጮች ከስማቸው አስቀድሞ ‹‹የተከበሩ›› የሚል መጠሪያ ይኖራቸዋል።
ፓርላማው ለሥራ የሚጠቀምበት ደግሞ ምክር ቤቱ የሚገኝበትን ክልል ቋንቋ ይሆናል። እነዚህ አካላት ሕጻናትን አስመልክቶ በሚነሱ ማንኛውም ጉዳዮች ላይ የመነጋገርና የመወሰን መብት አላቸው፡፡
ልጆችዬ! በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በተካሄደ አንድ ጉባኤ ስለ ሕጻናት ፓርላማ የተነሱ አበይት ጉዳዮች ነበሩ ። በጉባኤው ላይ ከኦሮሚያ ከልልና፤ ከተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ እንግዶች ተገኝተዋል። በዕለቱ የተከበሩ ተማሪ ቅዱስ ሞላ የፌዴራል ሕጻናት ፓርላማ አፈ ጉበኤ ለእንግዶቹ መልዕክታቸውን አድርሰዋል፡፡
ልጆች! የተከበሩ አፈ ጉባኤ ቅዱስ ሞላ ምን አሉ መሰላችሁ፡ – የዓለም ሕጻናት ኮንቬንሽን እንደ ኤሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በኅዳር ወር 1989 ላይ በተባበሩት መንግሥታት አፅዳቂነት በሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ይህን ስምምነት ፈርመው ከተቀበሉት ሀገራት መካከል አንዷ ስለመሆኗ ጠቁመዋል፡፡
አፈጉባኤው በትኩረት እንደገለጹት ሕጻናት በኮንቬንሽኑ የተሰጣቸውን መሠረታዊ መብቶችና መርሆች በሚገባ እንዲታወቁና እንዲተገበሩ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ መደረጉ ደግሞ የሕጻናትን ጥቅም በማስቀደም ማኅበራዊ ደህንነታቸውን ለማስከበር የሚያስችል ሥርዓትን ለመዘርጋት ያስችላል፡፡
በአሁኑ ግዜ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሕጻናት መኖራቸውን አፈጉባኤው አስታውሰዋል። ለነዚህ ሕጻናት ትኩረት ለመስጠትም ኅብረተሰቡን ጨምሮ መንግሥትና የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ ሊተባበሩ እንደሚገባም በአትኩሮት ተናግረዋል፡፡
ልጆችዬ! የኦሮሚያ ሕፃናት ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባኤና የፌዴራል ፓርላማ አባል የተከበሩ ተማሪ ሮማን ካዋ በበኩላቸው ‹‹አለኝ›› ያሉትን መልዕክት አድርሰዋል። እሳቸው እንዳሉት የሀገራችን ሕጻናት ጥራት ባለው ትምህርት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡
እንደ አፈ ጉባኤዋ አባባል ሕጻናት የሀገር ተስፋ እንደመሆናቸው በሀገራችን የሕጻናትን መብት ለማረጋጋጥ የሚያስችሉ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከነዚህ ተግባራት ዋንኛው ሕጻናት መብታቸውን የሚያስከብሩበት፣ ድምፃቸውን የሚያሰሙበት የሕጻናት ፓርላማ መመስረቱ ነው ፡፡
ልጆች! አፈጉባኤዋ የኦሮሚያ ክልል ተወካይ እንደ መሆናቸው ፓርላማው ከተመሠረተ ወዲህ በክልሉ የተከናወኑ ተግባራትን ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት የፓርላማው ኣባላት አቅመ ደካማ ለሆኑ እናቶች መኖሪያ ቤት በመገንባት በአረንጓዴው ልማት ችግኞችን ሲተክሉ ቆይተዋል። ከዚህ ባሻገር ሕጻናት በትምህርት ቤቶቻቸው የተለያዩ ክበባትን በማቋቋም ተሳትፏቸውን እንዲያሰፉ አድርገዋል። ለዚህም የፓርላማው አባላት ድጋፍና አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው።
አፈጉባኤዋ አክለውም በአሁኑ ግዜ በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች በጦርነትና ረሀብ ምክንያት በችግር ላይ የሚገኙ ሕጻናት ስለመኖራቸው አስታውሰው ሁሉም ዜጋ ስለነዚህ ሕጻናት ትምህርትና በሕይወት ስለመኖር ግድ ሊለው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ልጆችዬ በዚህ ጉባኤ የተለያየ ኃላፊነት ያላቸው የመንግሥት አካላት ተገኝተዋል። ከነዚህ መሐል ክብርት ዓለሚቱ ዑመድ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አንዷ ናቸው። እሳቸው ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ? ሕጻናትንና ሴቶችን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ በሕጻናት አያያዝና እንክብካቤ ዙሪያ ኅብረተሰቡ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመው፣ የተሟላ ሰብዕና ያለው አገር ወዳድ ዜጋን ለማፍራትም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል። የዛሬ ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች፣ የወደፊት ተስፋዎች ናቸውና መብታቸው ሊከበር ማኅበራዊ ደህንነታቸውም ሊጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ልጆችዬ! ለዛሬ ስለሕጻናት ፓርላማና በዙሪያው ስለሚነሱ ቁምነገሮች ጥቂት ግንዛቤ እንዳገኛችሁ ዕምነቴ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ቆይታ የምናደርግ ይሆናል፡፡ለሁላችሁም መልካም የእረፍት ቀን እንዲሆንላችሁ ተመኘሁ ሰላም !
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2016