በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን የዘለቀው የትርክት ቅኝት፣ በአንድ በኩል ፍጹማዊ አንድነትን የሚሰብክ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍጹማዊ ልዩነትን የሚያቀነቅን ዋልታ ረገጥነት ተጫጭኖት የከረመ ነበር። በሚዛናዊነት ላይ ያልቆመው፣ በተንሸዋረረ የታሪክ እይታ የሚባዝነው የሀገራችን የተዛባ ትርክት በየጊዜው ለሚያጋጥሙን ችግሮቻችን ምንጭም ሆኖ ቆይቷል።
ኢትዮጵያውያን ከውጭ የተቃጡብንን ጦርነቶች በጋራ የመመከት ባህል ቢኖረንም፤ የውስጥ ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት ልምዱን አላዳበርንም። በመሆኑም በችግሮቻችን ላይ ተነጋግሮ መግባባትን ገንዘባችን ልናደርግ ይገባል፡፡ ይሄ ሲሆንና ከመጠላለፍ ይልቅ አብሮ መልማትን፣ ከመነቃቀፍ መተባበርን፣ ከመራራቅ መቀራረብን ምርጫችን ስናደርግ የወል ትርክታችን የተነሰነሰበትን አቧራ አራግፎ ይነሳል።
ከስሜታዊነት ይልቅ አስተዋይነትንና ሚዛናዊነትን፣ ከቂም በቀል ይልቅ ይቅር መባባልን፣ ባለፈ ትርክት ከመበላላት ይልቅ የነገን ታሪክ በጋራ መሥራትን፣ ጠብመንጃ ከመማዘዝ ይልቅ ለሰላም መንበርከክን ባህል ስናዳብር፣ የኅብረ-ብሔራዊነታችንን በረከት እንቋደሳለን።
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የባህል ወዘተ. ብዝሃነቶች ፀጋዎቻችን ናቸው። የራሳችንን ማንነት አክብረን የሌሎችንም ማክበር ብቻ ሳይሆን፤ ማስከበር ሰብአዊ ግዴታችን መሆኑን በተግባር እያጎለበትን ስንሄድ ለሰው ልጆች ክብር ሲሉ ራሳቸውን መስዋዕት እንዳደረጉት አባት እናቶቻችን የአርበኝነትን ክብር እንጎናፀፋለን።
በታሪካችን ካለፍንባቸው በላይ ችግሮችን የተጋፈጡ ሀገሮች ትርክታቸውን በአዎንታ በመቃኘታቸው የሀገረ-መንግሥት ግንባታቸውን አጠናቀዋል። ትርክትን በአሉታዊነት የቃኙት ደግሞ ተበታትነዋል፣ ተገዳድለዋል፣ ከነበሩበት ገናና ታሪክ ቁልቁል ተፈጥፍጠዋል።
በዚህ መልኩ በኅብረ-ብሔራዊነትና በአዎንታ የተቃኘ የወል ትርክት የአንድን ሀገር ሕዝብን አብሮነት የሚያጠናክርና የጋራ ሀገራዊ ዓላማ ለመሰነቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለውና የታሪክ ሁነቶችን ጭምር የሚያስተሳስር ነው። ምክንያቱም የወል ትርክት አብሮነትና አንድነትን የማጠናከር ፋይዳው የላቀ ነው፤ በንዑስ ትርክት ላይ አተኩሮ መሥራትና ጽንፍ የረገጠ ትርክት መያዝ ደግሞ የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በተለያዩ መድረኮች ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ሊያስተሳስር የሚችልና አንድነትን የሚያጸና የጋራ የሆነ ታላቅ ትርክት ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል። እናም የወል ትርክትን በመገንባት ማለት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጽናት፤ የጋራ ተጠቃሚነትና የሀገር ግንባታ መሠረቶችን ማኖር ማለት ነው፡፡ ወቅቱም እኛ (ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን) ከምንጊዜውም የበለጠ ይሄንን የምንሻበት ነው።
ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን እና ኅብረ ብሔራዊነትን የሚያጎለብት፤ የብሔራዊነትና የአርበኝነት ክብርን የሚያጎናፅፍ አሰባሳቢውንና ታላቁን ሀገራዊ ትርክት ለመገንባት የተጀመረው እንቅስቃሴ የአንድ ወቅት አጀንዳ ሆኖ እንደ ዘበት የሚቀር እንዳይሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ትርክትን የምንገራው የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት እና የመከባበር እሴቶቻችንን በማጎልበት ነው። ታላቁ ሀገራዊ ትርክት በቤተሰብ የምንነጋገረው፣ በትምህርት ቤት የምናስተምረው፣ በየሃይማኖት ተቋሞቻችን የምንሰብከው፣ በየሚዲያው የምናሰራጨው ሃሳብ ውጤት በመሆኑ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁላችንንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው።
አሰባሳቢውን ታላቁን ሀገራዊ ትርክት ከማስረጽ ባለፈ ይህ ትውልድ በላቡ መስዋዕትነት ታሪክ እየሠራ መሆኑን ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገአችንን አስተሳስሮ የያዘው የታላቁ ትርክት ውጤት የሆነው የዓድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየምን እና ታላቁ የዓባይ ግድባችንን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
የወል እውነት ላይ የተመሠረተና ብዝሃነትን ያከበረ ትርክት በመገንባት ሰላምን ማጽናትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል።
ኢትዮጵያውያን ከፋፋይ ትርክቶችን በመተው በኅብረ-ብሄራዊ አንድነት ላይ የተመሠረተ የወል ትርክት በመገንባት ሰላምን ማጽናትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባናል።
ከፋፋይ አጀንዳዎች ሰላም እንዳይጸና፣ ልዩነትና ተቃርኖ እንዲበረታ የሚያደርጉ በመሆናቸው ሕዝብንና ሀገርን ክፉኛ ይጎዳሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የወል እውነትን መሠረት አድርገን መሥራት ይገባናል።
ሐሰተኛ ትርክት በኢትዮጵያውያን መካከል ጥርጣሬና ግጭትን በመፍጠር ሀገር የሚያዳክም ነቀርሳ ነው። ብዝሃነትን ያከበረ የወል ትርክትን መገንባት ይገባናል የምንልበት ምክንያትም ይሄው ነው።
የተለያዩ የታሪክ አረዳዶችንና አገላለጾችን ለማቀራረብ ከታሪክ ምሁራን ጋር በትብብር መሥራት ይገባል። ፍጹም ጠቅላይነትም ፍጹም ነጣጣይነትም ለኢትዮጵያ የማይበጁ በመሆናቸው፤ ኅብረ-ብሔራዊነትን ያከበረ አሰባሳቢ መንገድን መምረጥና መከተል አስፈላጊ መሆኑን ለቅፅበትም መዘንጋት አይገባም።
ከታሪካችን፣ ከሕልሞቻችን፣ ከሀገራዊ ጥቅሞቻችንና ከእሴቶቻችን የሚመዘዝ የጋራ ማንነት ያለን በመሆኑ፤ ይህንን ማጠናከር ላይ መሥራት ተገቢ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያጌጠ የወል እውነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ ትርክት በመገንባት የጋራ ሰላምንና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሥራት አለብን።
የወል እውነት ለሀገር በጋራ በመቆም መሥራትን የሚያጎለብት፤ ይሄም ሉዓላዊነትን፣ ሰላምና አንድነትን የሚያጸና በመሆኑ ለዚህ መልካም ዓላማ በጋራ እንሥራ፤ የጋራ ትርክት እየፈጠርንም የነገ የወል ታሪካችንን እውን እናድርግ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም