“እኛ ከተቆጣጠርንበት ዘመን ይልቅ ለገበያው የለቀቅንበት ዘመን የተሻለ ሆኖ ነው የተገኘው” አቶ ገ/መስቀል ጫላ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር

በንግስና አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው ላይ የሚታዩ አሠራሮች፣ አሠራሮቹ የፈጠሩት ችግሮች፣ ችግሮቹን ለመከላከል የተወሰዱ የእርምት ርምጃዎች፣ ርምጃዎቹ ያስገኙት ውጤቶች፣ እንዲሁም ዘርፉ ዛሬም ያልተሻገራቸው ችግሮች እና በተለይም በንግድና ግብይቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የቀጣይ አቅጣጫዎቹ ላይ ትኩረት በማድረግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። እኛም ይሄንኑ የሚኒስትሩን ምላሽና ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

 ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት በጣም ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ ይታወቃል። የንግድ ሥርዓቱ ከእድሜው እና ከኢትዮጵያውን ታሪክ አኳያ ምን ያህል ዘምኗል ይላሉ?

አቶ ገብረመስቀል፡- ኢትዮጵያ የንግድ ስልጣኔ ካላቸው ሀገሮች አንዷ ናት። ከብዙ ምዕተ ዓመታት በላይ የንግድ ልምድ ያላት ሀገር ናት። የስልጣኔ መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ንግድ ነው። የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት እንደየሥርዓተ ማህበሩ /በሀገሪቱ እንደነበሩት መንግሥታት ሁኔታ/ የተለያየ ሲሆን፤ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እያለ ፤እየተዘጋ እየተከፈተ የመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወጥ የሆነ ሥርዓት አለው ማለት በጣም ያስቸግራል።

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የንግድ ሕግ አላት። ይህ የንግድ ሕግ በብዙ ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ አገልግሎት ሰጥቷል። በንጉሱ፣ በደርግ፣ በኢህአዴግ እና በለውጡ መንግሥት በከፊል አገልግሏል። ይሄ የንግድ ሕግ አሁን ከምንፈልገው ዘመናዊ ሥርዓት ጋር አብሮ የሚሄድ ባለመሆኑ፤ በተቋሙ ከተካሄዱት ሪፎርሞች አንዱ በንግድ ሕጉ ላይ የተካሄደው ነው። ስለዚህ 50 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ተሻሽሎ እንዲወጣ ተደርጓል። አንዱ የንግድ ሕጉ ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው ያደረገው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ከ50 ዓመት በኋላ መሻሻሉ ነው።

ሁለተኛው እንደሚታወቀው የንግድ ሕጉን ዘመናዊ የሚያሰኘው ተገልጋዩ ማህበረሰብ በተለይ ነጋዴው ማህበረሰብ ካለበት ሆኖ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ማድረግ በሚያስችል መልኩ መሻሻሉ ነው። ተገልጋዩ በየቢሮው፣ በየወረዳው ፣ በየቀበሌው እየተመላለሰ አገልግሎት በሚያገኝበት ሰዓት በተለይ የግብር ክሊራንስን ካገኘ በኋላ ወይም ከዚያ ወጪ ያሉ የንግድ አገልግሎቶችን በቀጥታ በራሱ ዘመናዊ ሞባይል እንዲያገኝ የሚያስችል አሠራር ተተግብሯል። ይሄ ከምዝገባና ፈቃድ ጋር ተያይዞ በቀደሙት ዓመታት በጉቦ ፣ በምልጃና በመሳሰሉት ጭምር በብዙ ሰልፍ በተለይ ፈቃድ የሚታደስበት ወቅት ሊያልፍ አካባቢ በብዙ ሰልፍና ወረፋ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ተለውጧል፤ በአሁኑ ጊዜ ከጠቅላላው ነጋዴ 89 በመቶው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ደንበኛው ባለበት ቦታ ሆኖ እንዲያገኝ ተደርጓል።

ሦስተኛው፣ ከማዘመኑ ጋር ተያይዞ ያለው ነው። ተዘግቶ የቆየው የንግድ ሥርዓት ክፍት የሚሆንበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፤ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ይፈቀድ የነበረውና የውድድር ሜዳውን ጠባብ ያደረገው፣ ኢኮኖሚውንም ውጤታማ በማያደርግ መንገድ ዝግ የነበረው ኢኮኖሚ በተለይ ከነፃ የንግድ ቀጣናው እውን መሆን ጋር በተያያዘ ክፍት የማድረግ እድሎች ተፈጥረዋል። ስለዚህ ይህን ተከትለው በሚመጡ ጉዳዮች ኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት እየዘመነ የመሄድ እድሉ እየሰፋ መጥቷል ማለት ነው።

ጥያቄ፡- የንግድ ሥርዓቱ በገበያ ፍላጎትና በገበያው ብቻ ከመመራት ይልቅ በደላሎች የሚመራ ነው ተብሎ ይተቻል። አሁንም ድረስ የቁም እንስሳት የሰብል ምርቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግዱ በደላላ እንደሚወሰን የሚጠቁሙ አሉ፤ በእዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ገብረመስቀል፡- እኛ በአዲሱ መንግሥት በ2014 ዓ.ም ወደ ሥራ ስንገባ ተቋሙ በሚገባ ተደራጅቶ ሳያበቃ በጥናት ላይ ተመስርተን አሁን ባልካቸው የሥራ ዘርፎች ላይ በትኩረት ሠርተናል። በዚህም ከደላላ ጋር የተያያዙ የንግድ ፍቃዶችን ከሥርዓት አስወጥተናል።ድለላውን ከቁም እንስሳት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ ከሰብል ግብይት አውጥተናል። ሦስት ሺህ 300 የሚደርሱ የንግድ ፈቃዶችም ተሰርዘዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የእነዚህ አካላት ፈቃድ ማደስ አቁመናል።

ስለዚህ እነዚህ ፍቃዳቸው እስካልታደሰና ፍቃድ እስከሌላቸው ድረስ ሕገወጦች ናቸው። ሌሎችም ደላሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ራሱ ገበያው የማያቀርባቸውን ነገሮች ሦስተኛ ወገን ሊያቀርብ ስለሚችል በጥናት ላይ ተመስርተን ይሻላል ብለን ኅብረተሰቡ በየእለቱ በሚገለገልባቸው ዘርፎች ላይ ያሉ ፍቃዶችን በሲስተም ብሎክ አድርገን የእድሳት ሥራ እናከናውናለን።

ሁለተኛ፣ ይሄንን ነገር በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ፤ በምናደርጋቸው የተለያዩ መድረኮች፤ ከክልሎች ጋር የጋራ ግምገማ አድርገናል። ከዚያ በኋላ ክልሎች እነዚህን አካላት መከታተል አለባቸው፤ ዘርፋቸውን እንዲቀይሩና ወደ ሌላ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ አለባቸው። ይህንንም እምቢ ብለው በሚሰሩት ላይ በተለያየ መንገድ በጥናት ላይ በመመስረት ርምጃ እንዲወስዱ ተደርጓል። ስለዚህ በሚኒስቴሩ በኩል በእነዚሀ አካላት ላይ መሠረታዊ የሚባል በተለይ ከንግድ ሥርዓቱ የማስወጣት ርምጃ ተወስዷል። ከዚያ ውጪ ያሉት ሕገወጦች ስለሆኑ ክትትል እየተደረገባቸው ከዚያ ሥርዓት ውጪ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።

በዚህ ረገድ እኛ ብዙ ጊዜ በየሩብ ዓመቱ ከክልሎች ጋር ስብሰባ እናደርጋለን። በተለይ በቁም እንስሳት ግብይት ላይ ግብይቱ በበረት የሚፈጸም ስለሆነ በአካል ቁጥጥር ማድረግ ስለሚቻል የንግድ ፍቃድ የሌላቸውን ከሥርዓቱ ማስወጣት ይቻላል፤ አስቸጋሪ የሚሆነው ጊዜው የዲጂታል ስለሆነ በሞባይል ስልክና በሌሎች የተለያዩ መንገዶች የሚሠሩ ሊኖሩ ይችላሉ። በእነዚህም ላይ ቢሆን ከተለያዩ የመረጃ አካላት ጋር በመሆን የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራ በቀጣይ ይሠራል።

አዲስ ዘመን፡- በተለይ የቁም እንስሳት ላይ እናንተ ልትደርሱባቸው በማትችሉባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ሕገወጥ ንግድ እየተከናወነ ስለመሆኑ የሚመጡልን ጥቆማዎች ያሳያሉ፤ እናንተ ምን ድረስ ነው ችግሩን ለመፍታት የምትሄዱት?

አቶ ገ/መስቀል፡– ኅብረተሰቡ ካላገዘን እንደሌባና ፖሊስ እያንዳንዱን ተከታትሎ በጣም አስቸጋሪ ነው። ልክ ለእናንተ ጥቆማ እንደሚመጣ በየደረጃው ያለው የኅብረተሰብ አካል መቆጣጠር መከታተል አለበት። እዚህ እንዲያግዝ ከታች ከወረዳ ጀምሮ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበር ክልል፣ ከዞን ከወረዳ ከከተማ ጀምሮ አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰሞኑን እየተዋቀረ ነው ያለው።

ይሄ በይፋ እውቅና የሚኖረው ጠንካራ ቦርድ ነው። ቦርዱም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ የሚሠራ፣ ኅብረተሰቡን እያነቃቃን ነው። ከእኛ ጋራ አብሮ ይሠራል፤ በመሆኑም ኅብረተሰቡ ይበልጡኑ ተጠቃሚ ስለሆነ በጥቆማም በሌላም መንገድ እንዲያግዘን ነው።

ሁለተኛ፣ ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከልም አለን። እሱንም ለማዘመን እየሠራን ነው፤ በዚያም ጥቆማ በቀጥታ እንዲደርሰን እናደርጋለን፤ ችግሩ በመሠረታዊነት የሚፈታው ሕዝቡ በዚህ ጉዳይ ላይ አብሮ ሲሳተፍ ሲያጋልጥ ነው፤ በዚህም ሕገወጡ አካል መቆሚያ መሸሸጊያ በሚያጣበት ጊዜ መፍትሔ ይመጣል።

እኛ ለእዚህ በመሠረታዊነት ጥሩ አማራጭ ነው ብለን የምንወስደው የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበር ነው። ይህም ከሀገር አቀፍ ጀምሮ እስከ ወረዳ፣ ቀበሌ ድረስ እንዲቋቋም ማድረግ ነው። ይሄንን በክልሎች ያቋቋምን ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃም አሁን አቋቁመናል። በሚቀጥለው ሳምንትም ለሕዝቡ ይፋ ይሆናል። ስለዚህ ኅብረተሰቡ ያንን በመጠቀም መብቱን ለማስከበር ጭምር ያግዘናል።

ጥያቄ ፡- በገበያ ውስጥ በስፋት የሚታዩት ትክክለኛ የሆነ የአቅርቦት ችግር ሳይኖርባቸው እና የምርት ወቅታቸው በጣም ጥሩ በሚባልበትና በስፋት ወደ ገበያ በሚገቡበበት ወቅት ሳይቀር በተመሳሳይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያሳዩ ምርቶች አሉ። በተለይ መሠረታዊ በሚባሉ እና መንግሥትም አሁን ድረስ ድጎማ እያደረገባቸው ያሉና በኅብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለሸማቹ መቅረብ ያለባቸው ምርቶች በየመንገዱ እየተሸጡ ይገኛሉ። ይህን ለመከላከል ምን ያህል ቁጥጥር ታደርጋለችሁ?

 አቶ ገብረመስቀል ፡– በመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ሥራ በሕግ መመራት አለበት። ገበያ ሲባል ደግሞ ነጋዴው እንደፈለገ ዋጋ የሚወስንበት፣ ሸማቹ ደግሞ ነጋዴው የጠየቀውን የሚከፍለበት ሳይሆን የገበያው ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ የአሠራር ሕግ አለው።

በተለይ በሸማቾች ጥበቃ አዋጁ መሠረት እያንዳንዱ ነጋዴ የሚሸጣቸውን ሸቀጦች ዋጋ ዝርዝር የመለጠፍ ግዴታ አለበት። ይሄንን እንዲያደርግም በየክልሉ፣ በየወረዳው፣ በየከተማው በተለያየ መድረክ እንናገራለን።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ቅሬታም አለ፤ ዋጋውን ይለጠፉ እንጂ ከለጠፉት በላይ የሚሸጡ አሉ ይባላል። ይህ ችግር መንግሥት ባቋቋማቸው አንዳንድ ተቋማት ጭምር እንደሚስተዋል ይሰማል። ለእዚህም ነጋዴዎቹም የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች አሉ። ምርቱን ለማጓጓዝ ለትራንስፖርት እንከፍላለን፤ እነዚህ ወጪዎች ሲደመሩ ዋጋው አያዋጣም ይላሉ። መለጠፍ ያለባቸው ትክክለኛ የገበያ ዋጋ መሆን አለበት፤ ከዚያ በላይ ከሆነ ደግሞ በሕጉ መሠረት እርምጃ ይወሰድባቸዋል።

ዞሮ ዞሮ በግብይት ሥርዓት ውስጥ መንግሥት በጣም በተመረጠ አግባብ ካልሆነ በቀር የሚቆጣጠረው ነገር ገበያውን ሊረብሽ /ዲስፖርት ሊያደርግ/ ይችላል። ምርቶች በስውር እንዲሸጡ ፣ ዋጋ የበለጠ ስካሌት እንዲያደርግ/እንዲጨምር/ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል፤ ይህን ሁኔታ እኛ ከም ንም በላይ ከሲሚንቶ ተምረናል።

ስለዚህ የምናደርገው አንደኛ በተለይ የሸማቹ፣ የነጋዴው፣ የአምራቹ ማህበረሰብ ሕጉን በሚገባ እንዲያውቀው የማድረግ ሥራ ዘንድሮ ሠርተናል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ እርምጃ እንገባለን። ለምሳሌ ከዋጋው በላይ በሚሸጡት ላይ ድርጊቱ ሕገወጥ በመሆኑ ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ይኖራል።

ሕገወጥ ንግድ ትልቁ የሥርዓታችን አደጋ እየሆነ መጥቷል፤ በስድስት ወሩ በነበረን መድረክ አንዱ ያሰመርንበት ጉዳይ ሕገ-ወጥ ንግድን መቆጣጠር ላይ ነው። ይህንንም መንግሥት በመቆጣጠር ብቻ እንደሚፈታ ያምናል። በአንድ በኩል ነጋዴውን ማህበረሰቡን በማስተማር ሁለተኛ ቅድም እንዳልኩት ማህበረሰቡን የሚወክል የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበር በማቋቋም እና እሱ እንዲታገል እና እንዲያግዝ ማድረግ። ስለዚህ በዛ ነው ምንሄደው።

ከዚህ ውጪ የተከፋፈለ (ሴግመንትድ የሆነ) ገበያ/ ማርኬት የሚባል ደግሞ አለ። ቀደም ሲል ያነሳሁት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በተለየ መንገድ ለመታደግ ሲባል ገበያውን የምንቆጣጠርበት አለ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የሰንበት ገበያዎች ናቸው። የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ በ2014ዓ.ም ላይ ነው በ160 ቦታዎች የተጀመረው። አምና ወደ 600፣ አሁን 940 አካባቢ ደርሷል።

ይሄ ደግሞ አንደኛ፣ አምራቹ ቀጥታ እነዛ ቦታዎች ላይ አምጥቶ እንዲሸጥ ያግዛል። ኅብረት ሥራ ማህበራትም ምርቶቻቸውን እዛ አምጥተው እንዲሸጡ ያደርጋል። ሁለተኛ፣ ስፋት ላላቸው አካባቢዎች ምርቶችን ማድረስም ያስችላል። በ940 አካባቢዎች ምርቶችን ማድረስ መቻል ትልቅ ነገር ነው።

ይህን ሥራ እያሰፋንና አሠራር እየፈጠርንለት/ ስታንዳርድ እያደረግንም እንሄዳለን። የትኛውም ሀገር ያለ አሠራር ስለሆነም በገበያዎቹ በሚቀርቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችም ይሁኑ የግብርና ምርቶች ላይ ቁጥጥር እናደርጋለን። የሚገዙም የሚሸጡም ሰዎች በዚህ አሠራር አምነው የሚገቡ ናቸው። እኔም ብዙ ቦታዎች ላይ ለማረጋገጥ ሞክሬያለሁ። ዋጋውም ቢሆን ከአምስት በመቶ እስከ 50 በመቶ ከመደበኛ ገበያ የሚሻልበት ሁኔታ አለ።

ስለዚህ የመጀመሪያው መግዛት የሚችሉ ወይም የሕግ ሥርዓቱ የሚመራቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተከፋፈለ/ሴግመንትድ የሆነ ገበያ ላይም ተጨማሪ ቁጥጥር ከሸማቹ፣ ከነጋዴው ጀምሮ የሚገቡት አምራቹ ጭምር የሚታወቁ ሆነው እንዲገበያዩ እናደርጋለን።

ከዛ ውጪ ግን መዋቅራዊ /ስትራክቸራል/ ችግሩ የሚያመጣቸው የሎጂስቲክስ ጉዳዮች፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አሉ። እነሱን ትተን ክፍተቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ በሰንበት ገበያዎች ላይ ታች ላይ ያሉ የእኛ መዋቅሮች በጥብቅ እየተከታተሉ የሚያስፈፅሙት ጉዳይ አለ ማለት ነው።

ጥያቄ ፡- በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ያለው መዋቅራዊ ችግር እንዲፈታ ምን ዓይነት ሥራዎችን ሠርታችኋል? በቀጣይስ እነዚህን ችግሮች በመሠረታዊነት ለመፍታት መንግሥት ምን ያህል ትኩረት ሰጥቷል?

አቶ ገብረመስቀል፡- መዋቅራዊ (ስትራክቸራል) ችግሮች የምንላቸው በዋናነት የአቅርቦትና የፍላጎት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ የቲማቲም፣ ሽንኩርት በተወሰነ ደረጃ ዋጋቸው የመውረድ አዝማሚያ አሳይቷል፤ይህ ከየትም የመጣ ሳይሆን የምርት ጊዜ ስለሆነ ነው። በተለይ የሚበላሹ ምርቶች የትም ሊደበቁ ስለማይችሉ ወደ ገበያ ይመጣሉ።

ይሄ እኛ ስለገፋን፣ ወይም ደግሞ ነጋዴው ስለፈለገ ብቻ ሳይሆን ምርቶቹ ስለደረሱ መምጣት አለባቸው። አለበለዚያ በስብሰው ይቀራሉ። ሆኖም ምርት በወቅት ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም። ወቅትን ጠብቆ የሚመረት ምርት ቀጣይ በሆነ መልኩ የፍጆታ ሥርዓትን ጠብቆ በተጠና አግባብ መምጣት አለበት።

ለዚህ እኛ ዘላቂ መፍትሄ ብለን የወሰድነው ሁሉንም ምርቶች በዚያ ደረጃ መከታተል ስለማንችል በጣም ፈጣን ፍጆታ ያላቸውን 10 የግብርና ምርቶችን ለይተናል። እነዚህን የግብርና ምርቶች ከማሳ እስከ ማዕድ ድረስ እንዴት ተሰብስበው ሸማቹ ጋ እንደሚደርሱ በጥናት ለይተናል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራ ምን ያህል በተበጣጠሰ ማሳ እንደሚካሄድ ይታወቃል፤ እነዚህ ምርቶች ከአርሶ አደር ማሳ በመጀመሪያ ደረጃ ተሰብስበው፣ ተጓጉዘው ሸማቹ ዘንድ ይደርሳሉ የሚለው ነው በጥናት የተለየው።

ለዚህ ‹‹ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት ሲስተም›› የሚባል አሠራር አለ። አንዳንድ ሀገሮች ይህን ተግብረው ውጤታማ ሆነዋል። ለምሳሌ፣ ያህል ሕንድ ከምታመርተው ስንዴ 50 በመቶ ያህሉን በእንዲህ ዓይነት ሥርዓት ነው የምትወስደው። ሀገሪቱ ይህን ምርት የምትሰበስብበት፣ የምታከማችበት፣ ትራንስፖርት የምታደርግበትና የምታከፋፍልበት ሥርዓት አላት።

ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያው ሥርዓት ራሳቸው ዋጋ ይወስናሉ፤ የማምረቻ ዋጋ ወስነው፣ በማምረቻ ዋጋ ላይ ትርፍ ወስነው፣ አርሶ አደሩ የሚሸጥበትንም ዋጋ ይወስናሉ። ከዚያ በኋላ የትራንስፖርቱና ሌሎች ነገሮች ተደምረው እስከ ‹‹ፌይር ፕራይስ ሾፕ›› ድረስ ዋጋው ይታወቃል። አሁን ያን እናድርግ ቢባል ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል። ሌሎች የሚያስፈልጉ ጉዳዮችም አሉ፤ አሁን ይህን ማድረግ አንችልም።

እኛ አሁን ምርቶቹን ለይተናል፤ የት የት አካባቢም እንደሚመረቱም አውቀናቸዋል፤ እነዚህን ምርቶች በኅብረት ሥራ ዩኒየኖች አማካኝነት ለከተማ ሸማቾች፣ ለሰንበት ገበያዎች የሚቀርቡበት የአስተዳደር ሥርዓት ዲዛይን እያደረግን ( እያዘጋጀን) ነው።

በዚህን ጊዜም እንደ ትልቅ ጥያቄ ይነሳል፤ ጥያቄውም የተለያዩ ዩኒየኖች ምርቶቹን ሰብስበው ለሸማቹ ማቅረብ ይችላሉ ወይ? የሚል የአቅም ጥያቄ ነው። ይህንን ደግሞ አጥንተን ፍላጎቱን ለሚመለከተው አካል አቅርበን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ያላቸውን አቅም ይዘው እንዲመጡ ለማድረግ በዋናነት እየተሞከረ ነው።

ግን ዘላቂው መፍትሄ ልክ እንደ ህንድና ሌሎችም ሀገራት እንደሚያደርጉት በተወሰኑ ምርቶች ላይ የተደራጀ/ሬጉሌትድ የሆነ የማእቀፍ ሥርዓት /በሥርዓት የሚመራ አካሄድ/ መፍጠር የግዴታ ይሆናል። ከዘላቂ መፍትሄዎቹ አንዱም ይሄው ነው። ሁለተኛው ሁል ጊዜ የዘይትና የስኳር ዋጋ እየወሰንን፣ ስርጭቱን ኮታ እየሰጠን መቀጠል ከዘመናዊነትም አንፃር በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፤ የሚሻለው ኢኮኖሚውን በተወሰነ ደረጃ ክፍት ማድረግ ነው።

በዚህ ሊሰማሩ የሚችሉ የሀገር ውስጥም የውጪም ባለሀብቶች አሉ። እነዚህ ባለሀብቶች ተወዳድረው እነዚህን መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን እንዲያቀርቡ በተለይ ለሀገር ውስጥ ነጋዴ ብቻ ተብለው ለውጪዎች ዝግ የተደረጉ የገበያ አማራጮችን ለውጪውም ጭምር ክፍት አድርጎ መሞከር ነው።

ያንን አሁን ወደ አፍሪካ ነፃ ገበያ ስለገባን እና ሙከራና ተግባራም ስለምንጀምር በዚህ ሥርዓት አንዱ ጉዳይ ከሌሎች ሀገሮች ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ምርቶች መኖራቸው ነው። እኛም ስለምንልክ የኛን ስንልክ የእነሱን አታስገቡም ማለት ስለማንችል ድንበሮቻችንን በተወሰነ ደረጃ ነፃ አድርገን ምርቶቹ እንዲገቡና በዋጋም በጥራትም እንዲወዳደሩ ማድረግ ይኖርብናል። ይሄ ሲሆን ተጠቃሚውም የበለጠ መርጦ እንዲገዛ፤ በዋጋም በጥራትም ላይ መሥራት ያስፈልጋል።

ስለዚህ ሁልጊዜም መንግሥት ተቆጣጥሮ፣ ሁልጊዜ ኢኮኖሚውን ለዜጋው ብቻ ዝግ አድርጎ የማቆየትም ነገር አንዱ ችግር ነው። ስለዚህ ከዚያም አንፃር መንግሥት የሰጠው አቅጣጫ አለ፤ ደረጃ በደረጃ ኢኮኖሚያችን እየተከፈተ ይሄዳል፤ በዚህም ችግሩ ይፈታል ማለት ነው።

ጥያቄ፡- ከመሠረታዊ የግንባታ ግብዓት ጋር በተያያዘ እርሶም የሲሚንቶ ጉዳይ ብዙ ነገር አስተምሮናል ሲሉ ተናግረዋል። ሲሚንቶና ብረት አሁን ለጊዜው ዋጋቸው የቀነሰው ብሄራዊ ባንክ ነሃሴ አካባቢ በወሰደው እርምጃ ምክንያት ባንኮች ብዙ እያበደሩ ስላልሆነ ገበያ ላይ ያለው ገንዘብ ያዝ ስለተደረገ የመጣ እንጂ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር በሰራው ሥራ የመጣ ለውጥ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ። በእዚህ ላይስ ምን ይላሉ?

አቶ ገብረመስቀል፡- እንደዛ ብሎ መከራከር ይቻላል። ግን ምንድነው አንዳንዴ ቁጥጥር በሚበዛበት ጊዜ ያ ነገር በጣም ተፈላጊ የሆነ ይመስላል። ይህን ጊዜ ምርቱን የያዙ ሰዎች ይሸሸጋሉ። ስለዚህ በ2014/15 ሲሚንቶን ለመቆጣጠር በሞከርንበት ጊዜ ብዙ የተጠቀምነው ነገር የለም። አንዳንድ ቦታ ላይ የሰማነው ለግንባታ ተብሎ ሲሚንቶ የተፈቀደላቸው ባለሀብቶች ጭምር በግንባታው ስም ራሳቸው ሲሚንቶ ሲሸጡ ተገኝተዋል። በዚህም ዋጋው በመናሩ ምክንያት ለራሳቸው ልማት ከመጠቀም ይልቅ እሱን ሸጦ ማትረፍን ነው የመረጡት። የቁጥጥር ሥርዓቱ ሲጠብቅ እንዲህ አይነት ችግር ሊያስከትል ችሏል።

ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ለውጥ ታይቷል። ገበያው በሚለቀቅበት ጊዜም አንደኛ፣ አቅርቦቱ የጨመረበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ባሻገር ፋብሪካዎች ወደ ምርት ገብተዋል። ለምሳሌ፣ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ገበያ እየገባ ነው። በቀን እስከ 500 ቶን ያመርታል። ሌሎች ፋብሪካዎች ከበርካታ ችግሮቻቸው ወጥተው ምርታማነታቸውን እየጨመሩ መጥተዋል። ከመለዋወጫና ከጥሬ እቃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከሚያመርቱበት የሚቆሙበት ጊዜ ብዙ ነበር። ይህም ችግር አሁን በተወሰነ መልኩ ቀንሷል። የማምረት አቅማቸው ከጊዜ ወጀ ጊዜ እያደገ መጥቷል ።

ይሄ ለውጥ የገንዘብ ፖሊሲው ብቻ ያመጣው አይደለም። ከእሱም በላይ አቅርቦት በሚጨምርበት ጊዜ የመጣ ነው። ስለዚህ የመሰቦ መግባት ምርት ይጨምራል። አሁን ደግሞ ለሚ ይመጣል የሚል አለ፤ ይህ ሲሆን ምርቱ ገበያውን ስለሚያጥለቅለቅ አንዳንዶች ግንባታቸውን ያዝ አድርገው መርጠው ለመግዛትም ዕድል የሚሰጣቸው ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ግን እኛ ከተቆጣጠርንበት ዘመን ይልቅ ለገበያው የለቀቅንበት ዘመን የተሻለ ሆኖ ነው የተገኘው ማለት ነው።

ጥያቄ ፦ የሲሚንቶ ገበያው ዘላቂ መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?

አቶ ገብረመስቀል፦ ምርት መጨመር ነው። ከለሚ ናሽናል ስሚንቶ ፋብሪካ በጣም ከፍተኛ ምርት ይጠበቃል። በሀገሪቱ አሁን የሚመረተው እጥፍ በሚሆን መልኩ የሚያመርት ነው። ከዚህ በኋላ ምናልባት እኛ የጎረቤት ገበያ የማስተሳሰር ሀሳብ ነው እንጂ የሀገር ውስጥ ገበያ እንኳ ብዙ ስጋት አይኖርብንም። ውድድር ስለሚመጣ ሌሎች ፋብሪካዎችም ምርታቸውን እየጨመሩ ይሄዳሉ። ሲሚንቶን በተመለከተ በእኛ በኩል የቤት ሥራችንን አጠናቀናል ብለን እናስባለን።

ጥያቄ፦ አዲስ አበባ ላይ ሕገወጥ ንግድ በጣም ተስፋፍቷል። እንደ መገናኛ፣ ሜክሲኮና በመሳሰሉት አደባባዮች መተላለፊያ አሳጥቷል የሚሉ አካላት አሉ። ሕጋዊ ነጋዴዎች ጭምር በጎዳና ላይ ንግድ ለሚሸጡ ሰዎች እያወጡ እየሸጡ ነው፤ ከግብር እየሸሹ ሕገወጥ ንግድ እያስፋፉ ነው የሚሉ ምልከታዎች አሉ። እዚህ ላይ የእናንተ ምልከታ ምንድነው? ሚኒስቴሩ ይህን ሕገወጥነት ለመፍታት ምን እያከናወነ ይገኛል?

አቶ ገብረመስቀል፦ እኛ ሕገወጥ ንግድ የምንለው ሕጋዊ ፈቃድ ይዞ ሕገወጥ ሥራ ሲሠራ ነው። እነዚህ ጎዳና ላይ የምናያቸው ፈቃድ ያላቸው አይደሉም። መታወቅ ያለበት በመጀመሪያ ኢመደበኛ ነጋዴዎች (informal traders) ናቸው። ወደ መደበኛ ንግዱ አልመጡም። ስለዚህ እነዚህን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማምጣት ይገባል። ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል፤ ወይም በሌላም መንገድ ሊሆን ይችላል ወደ ሕጋዊ ሥርዓት መምጣት ያስፈልጋል። እኛ ሕገወጥ ንግድ የምንለው ፈቃድ አውጥቶ ከተፈቀደለት አሰራር ውጪ የሚንቀሳቀሰውን ነው። ይህ ነጋዴ የሚሠራው በሕገወጥ መንገድ ከሆነ፣ ሕገወጥ ንግድ እያካሔደ ነው ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህን በሚመለከት ፈቃድ የላቸውም። ስለዚህ በምን መንገድ ወደ ሕጋዊ መንገድ ይመጣሉ የሚለው መታሰብ አለበት።

ይህ ጥያቄ ደግሞ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ብቻ የሚመለስ አይደለም። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች አካላትም አሉ። አጀንዳ አድርገንም እየተነጋገርን ነው። ምክንያቱም ከዚህ ጋር የሚያያዝ ሌላም ገጽታ አለው። ምክንያቱም ጉሊት ላይ ያሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በየመንገዱ ዳር ሆነው የሚሠሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ዜጎች ናቸው። እነዚህ ዜጎች መደበኛ ነጋዴ ባይሆኑ እና ግብር ባይከፍሉም እንኳ (የሽያጭ መጠናቸው ወደ ግብር ያደርሳል አያደርስም የሚለው በጥናት የሚመለስ ሆኖ) ሥርዓት ኖሮ እንዲሰሩ የማድረግ ሥራ መስራትን ይጠይቃል።

በየቤታቸው ሆነው የሚሠሩ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች ብዙ ገቢ ሊያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን ሕጋዊ እና መደበኛ ላይሆኑ ይችላሉ። ይህንንም በጥናት ላይ በመመስረት መመለስ ይገባል። እንደዚህ ዓይነት ብዙ ጉዳዮች ስላሉ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ሌሎች ዘርፎች ጋር ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል።

በአዲስ አበባ ችግሩን በዛ ደረጃ እንዲሰፋ የሚያደርገው ከተማው ስፋት ስላለው እና የራሱ የዕድገት ሁኔታዎች ስላሉት ነው። ሜክሲኮ፣ መገናኛ ፣ ሳሪስ ላይ የዕድገት አካባቢዎች ስለሆኑ በዛው የሚታዩ ናቸው። በሌሎች ከተሞችም የዛን ያህል ባይሰፋም እንደየከተሞቹ ሁኔታ ሕገወጥነቱ ሊታይ ይችላል፤ እነዚህን ሁሉ ወደ ሕጋዊነት ማምጣት ይገባል። ኢመደበኛ ውስጥ ያሉትን ወደ መደበኛ ማምጣት ያስፈልጋል።

ጥያቄ ፡- በዚህ ረገድ የሚጠቀሱት አንዳንዶቹ መደበኛ በሆነው በንግድ ሥርዓት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ንግዳቸው ውጤታማ አለመሆኑን በመጥቀስ፤ ጎዳና ወጥተን እንሞክር የሚል ዝንባሌን የያዙ ናቸው፤ በእዚህ ላይስ ምን ይላሉ?

አቶ ገብረመስቀል፡– ዋናው ነገር አሠራሩን ማዘመን ነው እንጂ የጎዳና ላይ ንግድ የትም አለ። የሚነግዱበት ቦታ እና ስፍራ አለ። እቃዎች የሚይዙበት ሥርዓት አለ። መንግሥትም ጥበቃ የሚያደርግበት አግባብ አለ። ይህንን ሥርዓት ማስያዝ ነው ዋናው ነገር። ዞሮ ዞሮ በማባረር እና በመውቀስ የምንፈታው አይደለም። ከሌሎች ዘርፎች ጋርም የሚያያዙ ጉዳዮች ስላሉ እነዛን ጉዳዮች አጥንቶ ምን ቢደረግ ነው እነዚህ ሥራዎች መፍትሔ የሚያገኙት ብሎ ማጥናት ይገባል።

ቀደም ሲል ጉልትን በምሳሌነት አንስቻለሁ። ጉልት የራሱ ቦታ አለው። ነገር ግን ንግድ ፍቃድ ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ እነዚህ ሕጋዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል። በየደረጃው እያደጉ የሚሔዱበትን ሥርዓትም ማበጀት ያስፈልጋል። ከሕገወጦች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ሳይሆን ራሳቸው እኔም ዜጋ ነኝ በሚል ሠርተው ለማደር መጣር ይኖርባቸዋል። ‹‹ሠርቼ መግባት አለብኝ፤ በቀጣይም ግብር ከፍዬ መኩራት አለብኝ›› ወደሚለው አመለካከት መምጣት አለብን ማለት ነው። ችግሩ በማባረር አይፈታም። መደበኛ ያልሆነ ሴክተር በየትኛውም ሀገር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን መደበኛ በማድረግ ተበረታትተው ወደሥራ የሚገቡበት ሥርዓት አላቸውና ከሌሎችም አካላት ጋር አጥንተን ሥርዓት እንዲያዝ ማድረግ ይኖርብናል።

አሁን ያለው ሁኔታ እንደተባለው ለትራፊክም አስቸጋሪ ነው። ዜጎችም ራሳቸው ከሚያገኙት በላይ የሚወረሱት ሊበልጥ ይችላል። ስለዚህ ለእነርሱም ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም በማልፍ በማገድምበት ጊዜ ሲወረሱና ያንን ተከትሎ ሲያልቅሱ ተመልክቻለሁ። ዞሮ ዞሮ ወደሥርዓት ማስገባት ነው፤ ችግሩ እስካለ ድረስ ደግሞ መፍትሔ ማምጣት የእኛ ኃላፊነት ነው። ከከተሞችም ከክሎችም ጋር በጋራ ተነጋግረን ጥናት ላይ ተመስርተን እንዲፈታ የማድረግ ሥራ መሥራት ይኖርብናል።

ጥያቄ፡- የኬላዎች መበራከት አንዱ ለኑሮ ውድነቱና ለዋጋ ንረቱ መንስዔ ነው ብለው የሚጠቅሱ አካላት አሉ። ይህን ችግር አምራቾችም፣ አከፋፋዮችም የሚያነሱት ቅሬታ ነው። እናንተም በሕገ ወጥ ኬላዎች ላይ ርምጃ መውሰዳችሁን ግልጻችኋል። ታዲያ ይህ ርምጃ ምን ለውጥ አመጣ?

አቶ ገብረመስቀል፡- ይህ ጉዳይ እኛንና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንን ብዙ አታግሎናል። በብዙ መድረኮችም ስንገማገም ነበር። ከክልሎችም ጋር ብዙ ተወያይተናል፤ ብዙ ተጻጽፈናልም። ኬላዎች በአሁኑ ጊዜ በመሰረታዊነት ተነስተዋል። ይህ ኬላ የተነሳበት ምክንያት ምርትና የሰው እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆን ተፈልጎ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ግን አሁንም ኬላዎች አሉ። ሕጋዊ ኬላዎች ጭምር አሉ። ክልሎችም ያቋቋሟቸውንና ታክስ የሚሰበስቡባቸውን ኬላዎች እንደ ሕጋዊ ኬላዎች ይቆጥሩ ነበር።

በፌዴራል ደረጃ ከክልል መንግሥታት ጋር ተነጋግረን ያነሳናቸው የክልል ኬላዎችን ጭምር ነው። ክልሉ አምኖ ይህ ለጸጥታ ስጋቴ ነው ብሎ ለጉምሩክ ኮሚሽን አሳውቆ ካልሆነ በስተቀር በአሁኑ ጊዜ ከጉምሩክ ኬላ ውጭ ያሉ ኬላዎች እንዲነሱ ተደርጓል። ይሄም ምርት እንዲንቀሳቀስ እድል ከፍቷል ብለን እንድናስብ አድርጎናል።

በእኛ እምነት አሁን ምርት ከአንድ ቦታ ተጭኖ ወደሌላ ቦታ ይጓጓዛል። የጸጥታ ችግር አንዳንድ ቦታ ላይ አልፎ አልፎ ካልያዛቸው በስተቀር ምርቶች ይንቀሳቀሳሉ። ስለዚህ ለውጥ አለ ብለን ነው የምናምነው። እኛም ስለምንንቀሳቀስ የነበሩ ኬላዎች የተነሱበትን ሁኔታ እናያለን።

ከዚህ አኳያ በቅርብ ጊዜ የተነሳ ስለሆነም ጫናው ይህ ነው፤ ውጤት በዚህ ደረጃ አምጥቷል ማለት ቢያስቸግርም፤ ከነበረበት ግን ይሻላል። ምክንያቱም በየኬላው ከፍለን አሳልፈናል የሚሉት የገንዘብ መጠን በጣም የሚዘገንንና ያ ደግሞ በመጨረሻ ተጠቃሚው ላይ ስለሚጫን አሁን እንደእዛ አይነት ችግር በእኛ በኩል ተቀርፏል የሚል እምነት አለን።

ይሁንና ግን ይህንን ነገር ከክልሎች ጋር በደንብ ዝርዝሩን በጥናት ላይ ተመስርተን እንደዚህ ነበር፤ አሁን እንደዚህ ሆኗል የሚለውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ማለት ነው። ግን መሰመር ያለበት የጉምሩክ ኬላዎች እና በጸጥታ ምክንያት ክልሎች አልፎ አልፎ ያቋቋማቸው ኬላዎች ካልሆኑ በስተቀር የጫት ኬላን ጨምሮ ኬላዎች ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር ተነስተዋል።

ጥያቄ፡- በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለሕጋዊ ነጋዴው፣ በአጠቃላይ ለሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ምን ያህል ፈተና ሆኗል ብለው ያምናሉ?

አቶ ገብረመስቀል፡– እንዴ! ይህማ ሳይታለም የተፈታ ነው። ምክንያቱም ኮንትሮባንድ በወጪ ምርቶች ላይ ትልቅ ጫና አለው። በኮንትሮባንድ የተነሳ ከቁም እንስሳት ሀብታችን በጣም ብዙ እያጣን ነው። በጫት ብዙ እያጣን ነው። በጥራጥሬና በቅባት እህሎች ብዙ እያጣን ነው። ይሄ ተግባር ነጋዴው በተለይ ሕገወጥ ነጋዴው የበለጠ አተርፋለሁ፤ ሀገር ውስጥ መግባት ያለበትን የውጭ ምንዛሪ በውጭ ሀገር አስቀራለሁ ብሎ አቅዶ የሚያደርገው በጣም ከባድ የሀገሪቱ ፈተና ነው ።

ለምሳሌ ኮንትሮባንድ የያዘ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ቢውል ባለመኪናው ወይም ባለ እቃው ዞር ብሎ አያየውም። ከመኪናው በላይ ያገኘው ትርፍ ስላለ ሾፌሩ ይታሰር እንደሆነ እንጂ፤ መኪናው በቆመበት ይበሰብሳታል እንጂ መኪናውን ዞር ብሎ አያይም። ስለዚህ ኮንትሮባንድ የኢኮኖሚያችን ቁልፍ ችግር ነው።

ኮንትሮባንድ የንግድ ሥርዓታችን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ቁልፍ ችግር ነው። ኮንትሮባንድ በማአድን ዘርፍ ጭምር አለ። ስለዚህ ኮንትሮባንድ የማይነካው ዘርፍ የለም፤ በወጪ ንግድም፤ በገቢ ንግድም በአጠቃላይ ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ተፅእኖ እየፈጠረ ያለ ነው። ይህን ሕገወጥ ተግባር ለመቆጣጠር ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

በተለይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የቁጥጥር ግብረ ኃይል እየተከናወነ ያለውን የጸረ ኮንትሮባንድ ሥራ በየጊዜው እየገመገመ አቅጣጫ እያስቀመጠ እየሠራ ነው። የፀጥታ መዋቅሩም የፌዴራል ፖሊስም፤ የክልል ፖሊስም እንደዚሁም የጉምሩክ መዋቀሩን እያጠናከረ እየሠራ ይገኛል። ቀስ እያለ ደግሞ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መግባቱ አይቀርም። በተለይ ድንበሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በምንደግፍበት ጊዜ ወይንም በምናጠናክርበት ጊዜ ኮንትሮባንድ ደረጃ በደረጃ እየቀነሰ ይሄዳል። ኮንትሮባንድን ግን ዜሮ ማድረስ አይቻልም፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ረጅም ድንበር ያለበት ሀገር ላይ ኮንትሮባንድን ዜሮ ማድረግ ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል።

ሁለተኛው ኮንትሮባንዱን ሊቀንስልን የሚያስችለው መንገድ የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን ነው። ለእዚህም አሁን እየተቀላቀልን ያለነው የነፃ ንግድ ቀጣና ሥርዓት እገዛ ያደርግልናል።እያንዳንዱ የንግድ እንቅስቃሴ በሚገባ ተመዝግቦ ሥርዓት ባለው መንገድ ስለሚመራና ከዚህ ውጪ የሆነ ነገር ደግሞ ተቀባዩንም ሀገር ችግር ውስጥ ስለሚከት ኮንትሮባንድ እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው።

ሌሎች ሀገራት የአውሮፓ ሌሎች ሀገሮችን በምናይበት ጊዜ ኮንትሮባንድ የቀነሱት በዚህ መልኩ ነው። አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በሚባል ደረጃ ንግድንም ስላዋቀሩ የነፃ ገበያ ሥርዓቱንም በዛ ደረጃ ያግዘዋል።እኛም ይሄንን በማድረግ ችግሩን እንሻገረዋለን።

ጥያቄ፡- በሀገሪቱ የዲጅታል የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን ብዙ መልኩ የቀየረው ያሻሻለው ነገር እንዳለ ይገለጻል። እንዲያም ሆኖ የነዳጅ ኮንትሮባንድ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ውጪ የሆኑ የክልል ከተሞች ላይ ይተያል፤ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያህል መረጃው አላችሁ?

አቶ ገብረመስቀል – መረጃው አለን።ነገር ግን ዝንባሌው ምንድነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ዝንባሌው በፊት ከነቦቴው ወስደው ነበር የሚሸጡት። አርባ ሶስት ሺ ፤አርባ ስድስት ሺ ሊትር ወይም ሀያ ሶሰት ሺ፤ ሀያ አራት ሺ ሊትር ጭኖ ሄዶ ነው ጎረቤት ሀገር የሚሸጠው። ዞሮ ጎረቤት ሀገር መሸጥ ብቻ ሳይሆን ከጅቡቲ ጭነው ተመልሰው ጅቡቲ የሚሸጥበት አጋጣሚ ነበር። ያ ለምንድነው የሆነው የኛ ነዳጅ ሀገር የመሸጫ ዋጋ ከጎረቤት ሀገራት ዝቅተኛ ስለነበረ ነው። እና እነሱ ጋር ከፍ ባለ ዋጋ ስለሚሸጡ ነዳጅን የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ልክ እንድ ኮንትሮባንዱ ሁሉ ይወጡታል ማለት ነው።

አሁንም ባካሄድነው ሪፎርም የነዳጅ ዋጋ ቀስ በቀስ እያሻሻልን ስለመጣን ከጎረቤት ሀገራት ዋጋ ጋር የእኛ ተመሳስሏል። ለዚህ ነው የንግድ ሥርዓቱ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥርዓት ይከተል የምንለው። ዋጋውም ጥራቱም ተመሳሳይ ስለሚሆን በኮንትሮባንድ የሚወጣበት መንገድ አይኖርም።

አሁን ነዳጅ በበርሜል፣በጀሪካን ሊወጣ ይችላል። በተለይ ቤንዚል። ናፍጣ ገዥ ስለሌለው ብዙም አይወጣም። የእኛ ደግሞ 70 በመቶ እና ከዚያ በላይ ናፍጣ ነው። ነገር ግን እንደበፊቱ ነዳጅ በጅምላ፣ በገፍ ሰልፍ ይዞ የሚወጣበት ሥርዓት የለም። አይደለም እንደዛ፤ በወር ላይ የነዳጅ ዋጋ ልንቀይር ስንፈልግ ነዳጅ ከጅቡቲ ተጭኖ መተሀራ አካባቢ ወይንም ሞጆ አካባቢ ደርሶ ጥላ ሥር ለሶስትና አራት ቀናት ይቆም ነበር። አሁን ግን ቀርቷል።

ዋጋ እያስተካከልን ሥርዓቱንም እያዘመንን ስለመጣን ከነዳጅ ጋር ተያይዞ ይታይ የነበረው ኮትሮባንድም ሆነ ሀገር ውስጥ ያለው ሕገ ወጥ ንግድ እየቀነሰ መጥቷል። በቀጣይም ነዳጅ ተጭኖ መጥቶ ተራግፎ እስኪሸጥ ድረስ ሙሉ ለሙሉ በኦንላይን ለመከታተል የሚያስችል የማኔጅመንት ሲስተም ለመተግበር እየተዘጋጀን ነው። ሌብነትን መቶ በመቶ ማስቀረት በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንዴ ልምድም የሚሆንበት ነገር ስላለ ነው። ነገር ግን 95 እና 98 በመቶ መቀነስ ይቻላል።

ነዳጅ ላይ የታየው ለውጥ ለሌሎችም ምርቶች ጥሩ ምሳሌ ሆኗል። ዝንባሌውም እየቀነሰ ወደ ዜሮ ደረጃ የመድረስ አዝማሚያ ላይ እየደረሰ ነው። እሱንም ቢሆን ችግሩ ያለበት ቦታ ስለሚታወቅ በቁጥጥርም ፤በሥርአትም ለመዝጋት ጥረት እናደርጋለን።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ባላት የሀብት መጠን ልክ ሀብቷን እየተጠቀመችበት አይደለም። በሕገወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየወጣ ያለው የቁም እንስሳት ሀብት ጉዳይ ብዙዎችን እያሳሰበ ነው። የቁም እንስሳትና ሕገወጥ ንግድን ሚኒስቴሩ ፈትቸዋለሁ ችግሩ የለም በሚልበት ደረጃ ላይ ደርሷል?

አቶ ገብረመስቀል፤ አላልንም። ልንልም አንችልም። ከቁም እንስሳት ጋር ተያይዞ ያለው መሠረታዊ ችግር የኛን ቁም እንስሳትን በኮንትሮባንድ የሚቀበሉት ያሉት ድንበር ላይ ስለሆነ ነው። ይሄንን የሚያደርጉበት ምክንያት እነርሱ ዶላር የሚሰጡበት የኢትዮጵያ የገንዘብ መጠንና እኛ ዶላር የምንቀበልበት መጠን የተለያየ ስለሆነ ነው። ቀደም ሲል እንዳልኩት እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች እኛ ጋ መጥተው የቁም እንስሳት ገዝተው ኤክስፖርት እንዲያደርጉ ስለማንፈቅድላቸው ትይዩ ማርኬት ላይ ያለውን የገንዘብ ምንዛሪ መጠን በሕገወጥ መንገድ ተጠቅመው በኮንትሮባንድ የቁም እንስሳት እንዲወጡ ያደርጋሉ። አንዱ መሠረታዊ ችግር ይሄ ነው።

ለእዚህስ መፍትሔው ምንድነው? ልክ ነዳጁ ላይ ሪፎርም እንዳካሄድነው ሁሉ፤ የውጭ ባለሀብት ፈቃድ ወስዶ ኤክስፖርት ቢያደርግ፤ ምን እንጎዳለን? የሚለውን ማየት ይኖርብናል። ክፍት ካደረግን እርሱም ጉቦ እየከፈለ፣ ስቃይ እያየ፣ በረሀ ለበረሀ እየተንከራተተ፣ ቁም እንስሳቱንም እያንከራተተና እያሰቃየ ከሚሄድ እንደማንኛውም የሀገር ውስጥ ነጋዴ ፈቃድ አውጥቶ፤ ገዝቶ፣ አደልቦ፣ ኳራንቲን አስገብቶ እንዲሸጥ ማድረግ ነው። እንደዚህ አይነት ጥናቶች አሁን እንዲጠናቀቁና ደረጃ በደረጃ ገበያው እንዲከፈት ማድረግ ነው መፍትሔው።

የቁም እንስሳት፣ የጫት፣ የቅባትና ጥራጥሬ እህል ኮንትሮባንድ ቆሟል የሚል ድምዳሜ የለንም። በተለይም የቅባትና ጥራጥሬ እህልን በጥራት ለማስተካከል እየሞከርን ነው። የጫት፣ የቁም እንስሳት እና የማዕድናት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በጣም የምንሰቃይበት ስለሆነ ከአጭር ጊዜ አንፃር፤ ጫት እና የቁም እንስሳትን በተቻለ መጠን ለውድድር ክፍት የማድረጉ ጉዳይ ኢኮኖሚንም፣ ሀገርንም፣ ዜጋንም የሚጠቅም ነው ብለን ተስፋ እናምናለን።

ጥያቄ፡- ሚኒስቴሩ መዋቅራዊ ለውጥ አድርጓል፤ ቀጣናዊ ትስስር የሚል በአደረጃጀቱ ተካቷል። በቀጠናዊ ትስስር በኩልስ ምን እየተከናወነ ነው? ምን የመጣ ለውጥ አለ?

አቶ ገብረመስቀል፡– ቀጣናዊ ትስስር ያመጣውን ለውጥ በሁለት መንገድ ከፍሎ ማየት ይቻላል። በአንደኛ ደረጃ የምናነሳቸው የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቶች ናቸው። የንግድ ስምምነት ያው የጥቅም ጉዳይ ስለሆነ ድርድር ይፈልጋል። ተደራድረህ፣ የሀገርን ጥቅም አስከብረህ ነው ወደ ስምምነት የምትገባው። ከዚህ አንፃር ከተወሰኑ ሀገራት ጋር ወደ ሥራ የገባንበት ሁኔታ አለ። ተቋም ነበረን፤ በአወቃቀር /ስትራክቸራል/ ጥሩ መጥተናል፤ በዚህም በተወሰነ ደረጃ ተንቀሳቅሰናል። ከደቡብ ኮሪያ፣ ከፓኪስታን፣ ከሶማሊያ፣ ከሩዋንዳ ጋር የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት አድርገናል። በዚህም መሠረት ከፍ ያለ ንግድ ለማካሄድ ከእነዚህ ሀገራት ጋር ጥረት እየተደረገ ነው። ወደ ሥራም እየተገባ ነው።

ይሄንን ይዘን ከሌሎችም ሀገራት ጋር የጀመርነው ሥራ አለ፤ ለምሳሌ ከናይጀሪያ ጋር የጀመርነው አለ፤ ከቻይና ጋር ለማጠናከር እየሄድን ነው። ከሕንድም ጋር እንዲሁ። ሁሉም የራሱን ተጠቃሚነት ይዞ ስለሚመጣ፣ እኛም ልክ ከሌሎች ጋር እንደተፈራረምነው ሁሉ ከእነዚህም ጋር ለመፈራረም/ሀገሮቹ ትላላቅ ከሚባሉት ጋር ስምምነት የተፈራረሙ ናቸው/ ግንኙነታችን ለማሳደግ እየሠራ እንገኛለን። ይህ ከሁለትዮሽ ትስስር አንጻር ነው።

ሁለተኛው፤ ቀጣናዊ ትስስር የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ነው፤ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ያው በአፍሪካ የንግድ ማዕቀፍ አፍሪካ አንድ የነፃ ገበያ እንድትሆን በሀገራት መካከል ስምምነት ላይ ተደርሷል፤ ያንን ስምምነት ተከትሎ፣ በአባል ሀገራት መካከል ውይይቶች ተካሂደዋል።

በርካታ ሀገራት የዕቃዎች ታሪፍ /ኦፈር/ አቅርበዋል። የእኛ የግሉ ዘርፍ ተዘግቶ የቆየ ስለሆነ፤ በማወቅም ባለማወቅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሊካሄዱ ስለሚችሉ፣ ከመንግሥት፣ ከባለድርሻ አካላትም ጋር በመወያየት ጊዜ ወስደን፤ ከእኛ ከመጨረሻዎቹ ሰባትና ስምንት ሀገራት ሆነን ነው ዘንድሮ የዕቃዎች የታሪፍ /ኦፈር/ ያቀረብነው።

የዕቃዎች የታሪፍ ኦፈር በአፍሪካ የንግድ ቀጣና ተረጋግጦ/ቬሪፋይ ተደርጎ/ በአፍሪካ የንግድ ምክር ቤቶች ፀድቋል። ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤም ላይም ፀድቋል። ስለዚህ አሁን የሚቀረን በእነዚህ ዕቃዎች ታሪፍ መሠረት ከአቻ አገሮች ጋር በስምምነቱ መሠረት የሙከራ ንግድ ማድረግ ይሆናል።

ለምሳሌ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ የንግድ ሙከራ አላቸው፣ ኬንያ እና ጋና የሙከራ ንግድ አላቸው፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካም እንዲሁ የሙከራ ንግድ አላቸው፤ ስለዚህ እኛም መርጠን ከአንድ ሁለት ሀገራት ጋር እንጀምራለን። በዚያ ውጤታማ መሆናችንን ስናረጋግጥ የትግበራ ውጤታችንን እያዘጋጀን ስለሆነ፤ የአፍሪካ የንግድ ቀጣናን እንዴት መተግበር አለብን የሚለው ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው፤ በዚያ ስትራቴጂ መሠረት ሙሉ ለሙሉ ንግዱን እንጀምራለን ማለት ነው። ስለዚህ በዚያ ደረጃ እየሄደ ያለ ሥራ ነው ያለው እሱም እየተፋጠነ ነው ያለው ።

ጥያቄ፡- የአፍሪካ ኅብረት በንግድ ቀጣና ላይ ከደረሰበት ደረጃ አኳያ፤ ኢትዮጵያም የታሪፍ ዝርዝር አፀደቀች ሲባል ምን ማለት ነው?

አቶ ገብረመስቀል፡– የውጪ ንግድ ካለ ወይም የገቢ ንግድ ካለ የገቢ ንግድ ግብር ታክስ አለ። ይሄ ታስክ ኢምፖርት ታስክ የሚባል አለ 90 በመቶ ምርቶች የኢምፖርት ታስክ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ፕሮፖርሽን ተደርጎ ዜሮ ይሆናል። አንድ ጊዜ ዜሮ ቢደረግ የሃገራትን ገቢ ስለሚቀንስና ስለሚጎዳ በዚያ ደረጃ 90 ከመቶ ምርቶች የግብርናም የኢንዱስትሪም ምርቶች ስለዚህ ያንን ኢምፖርት ታስክ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ እየተቀነሰ ዜሮ የሚሆንባቸው እቃዎች ተይዘዋል። ወደ 6ሺ የሚጠጉ ዕቃዎች በስም ተለይተው ታሪፉ ዜሮ የሚሆንበት ዓመት ተቆርጦለት በየዓመቱ በዚያ ደረጃ ይሄዳል።

እኛ የምንልከው ምርትም በዚያ ደረጃ ሌላ ሃገር ሲገባ እንደዚያ ነው የሚሆነው። ስለዚህ አንዱ 90 በመቶ ምርቶች ናቸው 10 በመቶው የት ሄዱ ነው ጥያቄው። 7 በመቶ ምርቶች ደግሞ ይሄን ትግበራ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በ6ኛው ዓመት የሚቆጠርና በ13ኛው ዓመት የሚያልቅ ታሪፉ ዜሮ የሚሆኑ ዕቃዎች ናቸው። እነዚህ ዕቃዎች “ስትራቴጂካሊ” ለእኛ በጣም ጠቃሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ለውድድርም ብቁ ላይሆኑ ይችላሉ ስለዚህ ያንን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች፣ አርሶአደሮች ሊሆኑ ይችላሉ ምርቶቹን ለይተን ለውድድር ለማዘጋጀት ነው።

ከ6ኛ ዓመት በኋላ እነሱም ወደ ውድድር ይገባሉ በ13ኛ ዓመት የእነሱም ታሪፍ ዜሮ ሆኖ ሙሉ ለሙሉ እንገበያያለን። ሦስት በመቶ የሆኑ ምርቶች ግን በጣም ስትራቴጂክ የሆኑ የፖሊሲ ስፔስ ለአንድ ሃገር የሚሰጡ እና ክፍት መሆን የማይችሉ ምርቶች ናቸው። ይሄ ለሁሉም የተሰጠ ማዕቀፍ ስለሆነ አንዳንዱ ሃገር ከራሱ አንጻር 90 ከመቶ በ7 ከመቶና በ3 ከመቶ ምርቶቹን ለይቶ አቅርቦ ነው ያስወሰነው። እኛም በዚያ ደረጃ ውስጥ ነው የምንሆነው። ስለዚህ ታሪፍ ኦፈር ስንል፤ ምርቶችን በስም ለይተን በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ በ13ኛው እና ፍጹም የተከለከሉ ለገበያ ክፍት የማይሆኑና ከውጪ የማይገቡ ምርቶች ማለታችን ነው።

ጥያቄ፡- የአፍሪካ የነፃ ንግድ ስምምነት ንግድ ሲባል ገቢም ወጪም አለ፤ በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ የንግድ ሚዛን አለመመጣጠኑ ወደ 15 ቢሊዮን ነው። ከዚህ አኳያ ስምምነቱ ስምምነት አደጋ የለውም? በተለይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ ምርቶችን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ችግር እንዳያስከትሉ ምን አይነት እቅድ አለ?

አቶ ገብረ መስቀል፡– ይሄ ሥራ በአንድ ተቋም የሚሠራ አይደለም የሚመለከታቸው ሁሉ የሚካተቱበት ነው። ለምሳሌ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከስተምስ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የቨርቹዋል ፕሮፐርቲ ራይት እና ሌሎች ኢንዱስትሪውንም ግብርናንም ያጠቃለለ ነው። የትኞቹ ምርቶች ላይ ብናተኩር ነው የበለጠ ውጤታማ የምንሆነው፤ የትኞቹን ደግሞ ዝግ ብናደርግ ነው የተሻለ የሚሆነው የሚለው በዝርዝር ቴክኒካሊ ተጠንቶ፣ ከዛም በማክሮ ደረጃ በመንግሥት በዝርዝር ተገምግሞ ነው።

ልክ እንደ ነዳጅ መርጠን በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገቡ የእቃ አይነቶችን ጠይቀን ሪፎርም በማድረግ በቀጣይ በእቅድ ይዘን ነው የምንሠራው። ይህ ካልሆነ በቀር እስካሁን የምንሠራው ጥራትን መሠረት አድርገን፣ ደረጃውን ያላሟላ ምርት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ነው እየተሠራ ያለው። ግን ይሄ የገባውስ የተባለው፤ ባስፈቀደው ገንዘብ ልክ ነው ያስገባው? ገንዘቡ የት ነው የገባው? የሚለውን ከውጭ ከገቢም አንጻር በቀጣይ የምናየው ይሆናል። በዚያ ደረጃ እናያለን ማለት ነው።

ከማክሮ ኢኮኖሚ አንጻር ደግሞ ተገምግሞ ነው። የግል ዘርፉ ደግሞ ኮንሰልት ተደርጎ ነው። በእያንዳንዱ ፕሮዳክት አይነት ምርቶቻቸውን ከሚያመርቱ ማኅበራት ካላቸው ከእነሱም ጋር ደግሞ ውይይት ተካሂዶ ነው። ስለዚህ ድርድሩ በሚካሄድበት ግዜ ያንን ሁኔታ ታሳቢ አድርገን የብዙ አካላትን ሀሳብ ይዘን ነው እኛም የምንደራደርው ማለት ነው። ስለዚህ ያ ስለሆነ ‹‹ባላንስድ›› የሆነ ነገር ነው የምናቀርበው። በግብርና ምርቶች ላይ በአብዛኛው እኛ የምዳድር አቅም እንዳለን የሚያሳዩ ነገሮች አሉ።

ለምሳሌ፣ በኢንዱስትሪ ላይ አንዳንዶቹ በሦስት በመቶ የምንይዛቸው አሉ፣ አንዳንዶቹ በሰባት በመቶ የምንይዛቸው አሉ። ከግብርናም አንዳንዶቹን በዛ ደረጃ የምናያቸው አሉ። ግን በአመዛኙ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ነው ውድድር ስለሆነ። ሌላውም የአፍሪካ አገር ስለሆነ ከአብዛኞቹ ሀገራት ጋር የመወዳደር አቅሙ አለን ብለን ነው። እንደተባለው የምናቀርበው። ሁለተኛው ምክንያት ኢኮኖሚው ዝግ በሆነ መጠን ውድድሩ እርስ በእርሱ በአገር ውስጥ ስለሚሆን ሸማቹም ማኅበረሰብ ይሁን በዓለም አቀፍ ኬፕኤቭል የሆነ አምራችን ከመፍጠር አንጻር ዝግ የሆነ ኢኮኖሚ አይመረጥም።

ለምሳሌ፣ ቻይና ኢኮኖሚዋን ዘግታ ነበር። ከከፈተች በኋላ ግን ዕድገቷ በጣም የሌለ ነው። ስለዚህ ዝግ ማድረግ ይቻላል፣ ግን ለሰላሳ፣ ለአርባ፣ ለሀምሳ ዓመት ዝግ አድርጎ ማቆየት ኢኮኖሚውን ያቀጭጭ እንደሆነ እንጂ ኢኮኖሚውን የሚያበለጽግና የሚጨምር አይደለም።

ስለዚህ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ከወንድም ሀገራት ጋር እኛም ደግሞ ለአንድነቱም፣ ለኅብረቱም መሪ ሚና የነበርን ሀገር ሆነን ስናበቃ ታሪፉን ባለማቅረበችን ኢትዮጵያ የዚህ ሁሉ ነገር መሪ ሆና የአፍሪካ መቀመጫ ሆና እንዴት ፌልድ ከሆኑ ስቴቶች መደዳ ተሰለፈች በሚል ወቀሳ ነበርብን። የተባለውን ለመጋራት ብዙ ጊዜ ወስደን የመነጋገር ዕድል ሰጥተናል፣ ግን ክፍት አድርጎ ደግሞ የመወዳደር ጉዳይ ያው ግሎባል ነው።ግዴታ እየሆነ በመምጣቱ። ከዛ ደረጃ ቢታይ ጥሩ ነው።

ጥያቄ-፡- የገቢ ንግዳችንን ስንመለከተው፣ በአንዳንድ አስመጪዎች ለዚህ መዋል የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ላልተገባ ዓላማ የማዋል እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ይነገራል። እናንተም እንደ ሚኒስቴር መሥሪያቤት እርምጃ ስትወስዱ እንመለከት ነበር። ለመሆኑ ችግሩን በልኩ ተገንዝቦ ተገቢውን ቁጥጥር የማድረግ ሂደቱ ምን ይመስላል?

አቶ ገብረመስቀል፡– በነገራችን ላይ እኛ የገቢና ወጪ ምርት ጋር በተያያዘ ሥልጣኑ ቢኖረንም የገቢ ምርቶችን በተለይ ከጥራት አንጻር ካልሆነ በስተቀር እያንዳንዱን ምርት ገብቶ ለታለመለት ዓላማ ውሏል አልዋለም የሚለውን በሚፈለገው ደረጃ ቁጥጥር አድርገናል የሚል ዕምነት የለኝም።

ምክንያቱም የእኛ አደረጃጀት ራሱ ጥራቱን የመቆጣጠርና ጥራት የሌለው ምርት ወደሀገር ውስጥ እንዳይገባ ከማድረግ ውጭ፤ እና በስፋት የሚገቡና ገበያውን የሚይዙ ትላልቅ ምርቶች ካልሆኑ በስተቀር፤ ከውጪ የገቡ ዕቃዎች ለታለመለት ዓላማ ውለዋል አልዋሉም የሚለውን በሚኒስትሪ ደረጃ ወይም በሚኒስትሪ አደረጃጀት ደረጃ የሠራነው የለም።

በቀጣይ ግን ከጥራት ቁጥጥር ባሻገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶች ለታለመለት ዓላማ መዋል አለመዋላቸውን ማረጋገጥ አንድ ተግባራችን ይሆናል። ሁለተኛም ከሁሉም በላይ ደግሞ ዶላር አስፈቅዶ ፣ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ወጥቶ ገቢ ተደርጓል አልተደረገም የሚለውን ለመቆጣጠር አሁን ዝግጅት እያደረግን ነው። ምክንያቱም አንዳንዴ ገንዘብም ወጥቶ ዕቃዎች የማይመጡበት አጋጣሚዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ።

ስለዚህ በነበረን አንድ ሁለት ዓመት ቆይታችን እኛ ወጪ ንግድ ላይ አተኩረን ነፃ የንግድ ቀጣና ላይ እየሠራን ነው። በሀገር ውስጥ ንግድም እስከነችግሩም ለማዘመን እየሠራን ነው። ግን በገቢው ላይ በዛው ልክ “ኢንሼቲቭ” ቀርጸን ጠንካራ ነዳጅ ላይ ያተኮረ የሪፎርም ሥራ ተሠርቷል።

ጥያቄ፡- ከውጪ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ ከገቢ ምርቶች ላይ የሚፈጠር ጫናን ለመቀነስና ምንዛሪውን ለሚገባው ዓላማ ማዋል እንዲቻል ምን አስባችኋል?

አቶ ገብረመስቀል፡- ችግሩ ምንድነው የአሠራር ክፍተት አለ። እሱን ማጥራት አለብን። አሁን ለምሳሌ ኢምፖርት የሚያደርግ አካል እንዴት ነው ኢምፖርት የሚያደርገው፤ ኤል ሲ ሲከፈት የንግድ ሚኒስቴር ሮል ምንድነው፤ አሁን ለምሳሌ ኤል ሲ ሲከፈት እስካሁን የኛ ሚና የለውም። ኢምፖርት ኤክስፖርት የለውም። ሄዶ ባንክ ኤል ሲ ከፍቶ ያስገባ እንደሆን እንጂ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአሠራር ይሄን ነገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገና ሊንክ አላደረገም ማለት ነው።

ስለዚህ ከዚያ ላይ ጀምሮ በጥናት ተመስርቶ ሥርዓት መዘርጋት አለበት። ሥርዓት ሲዘረጋ እያንዳንዱን ነገር ፕረስ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው። አሁን ሥልጣን ያላቸው አካላት በሥርዓት ሲሠሩ፤ የሚሠሩት ነጋዴዎች ስለሆኑ የሚወጣው የሀገር ሀብት ስለሆነ ከእነዚህ አካላት ጋር በጋራ መሥራት ያለብን እንደሆነ ሴንስ ያደረግነው ስለሆን እንደዛ እናደርጋለን። የሚመለከታቸው ይሠራሉ ብለን፤ ያው ይሄንን የሚመለከታቸው ብዙ አካላት አሉ። ነገር ግን የኛም ኢንቮልቭመንት ቢኖር በጣም ይጠቅማል። ኢንፖርት ንግድ ስለሆነ ከንግድ አንጻር የምናያቸው ነገሮች ስለሚኖሩ፤ አቅደን ለቀጣይ፤ ያው ዘንድሮ ዝግጅት አድርገን ከሚመለከታቸውም ጋር መስማማት አለብን።

ይሄ ሥራ የኛ ሥራ አይደለም እንዴ የሚል ነገር ሊመጣም ስለሚችል፤ መግባባትም ስለሚያስፈልግ ከሚመለከታቸው ፋይናንሻል ተቋማትም፤ ከጉሙሩክም ጋር ተነጋግረን፤ ተቆጣጣሪ አካላትም አሉ በነገራችን ላይ ከእነርሱም ጋር ተነጋግረን የኛን ሚና ሥርዓቱ በሚፈቅደው መልክ ከቁጥጥር ባሻገር እንሠራለን ማለት ነው። ቁጥጥሯ የኛ ሥራ ስለሆነች እሷን ማንም ክሌም የሚያደርግም የለም። የሚቀረው እቃ እዛው ይቀራል፤ የሚመጣው እቃ ይመጣል፤ የገባው እቃ በትክክለኛ ዋጋ ነው የገባው ወይንስ የቀረ ነገር አለ፤ የሚለውን የመቆጣጠር ሥራ እንሠራለን። ባይገባስ ማን ነው የሚጠየቀው? የባንክ ሚና ምንድነው የሚለውን ከመወቃቀሳችን በፊት የጋራ ሥርዓት ዘርግተን ወደ እቅድ መግባት ስላለብን ነው።

ምክንያቱም መጀመሪያ እኛ በዚያ መልኩ አላየንም፤ የሌላ አካል ሥልጣን አድርገን ስለምንወስድ በኤል ሲ ብዙ ነገር ስለምንወስድ፤ ለምሳሌ የፎረም ሪትሬሽን አለ፤ ከዚያ ጋር አያይዞ ሁሉም ሰው ኤክስፖርት ያደረገ በቀረችው ዶላር የሚያስገባው አለ። እንደመብት ሲቆጠር ስለነበር ከመብት ባሻገር ደግሞ እንደ ንግድ ሚኒስቴር ከዚህ እረገድ ምን አይነት ሥራዎችን መሥራት አለብን ሥርዓት እንዘረጋለን። በዋናነት በ2017 ዓ.ም እንሠራለን ብለን እያሰብን ነው በእቅድ ውስጥ ነን።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛ ዶላር  እያጣችበት ያለው የፍራንኮ ቫሉታ ጉዳይም በጣም መሠረታዊ የሆኑ እንደ ስካር፣ ዘይት የሕፃናት ወተት በተመለከተ ምን ያህል ገመገማችሁ፣ ውጤታማነቱን እንዴት አያችሁት፣ በገበያው ላይ በድጎማ መንግሥት ትቶ የመጡት ምርቶች ከሌላው በመደበኛ ከመጡት ምርቶች ጋር እኩልና ከዚያም በላይ ባለ ዋጋ ገበያ ውስጥ ያለውና ምንድነው ፍራንኮ ቫሉታ ያተረፈልን?

አቶ ገብረመስቀል፡- ይታወቃል፣ ወደ 18 ቢሊዮን ብር ነው። አንድ ዓመት ተኩል የጉሙሩክ መረጃ እንደዛ ነው የሚያሳየው። መንግሥት “ታክስን ፎርጎ” ያደረገው። አሁን ዋናው እንደ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የምናየው አቅርቦት በኩል ያለውን ነው። ይሄንን በአቅርቦት በኩል ያለውን በምናይበት ጊዜ፤ ሁል ጊዜ ትዝ የሚለኝ 2014 ነው። 2014 የዘይት እጥረት አጋጥሞን ስለነበረ በሀገሪቱ ውስጥ በጣም ትልቅ ጩኸት ነበር። ምክንያቱም ሰው ዘይትን በተለያየ መንገድ ማግኘት ያልቻለበት ጊዜ ስለነበር።

ስለዚህ መንግስት ፍራንኮ ቫሉታ ለስኳር እና ለዘይት ሲፈቅድ ከሁኔታ ጋር ነበር። የራሳቸውን ዶላር በብሔራዊ ባንክ ተመዝግቦ በማስገባት የሚል ነበር። ያም በሚሞከርበት ጊዜ አቅርቦቱን አላጠገበውም ነበር። ስለዚህ ገበያው ላይ ሰው ዘይት እንደፈለገ ማግኘት አይችልም ነበር። ስለዚህ ዶላር ያለው ሰው ማንም ቢሆን የፍራንኮ ቫሉታ ማነቃቂያ መሠረታዊ ሸቀጦችን እንዲያስገባ በሚፈቀድበት ጊዜ አሁን ያየነው የተረጋጋ የገበያ ዋጋ መጥቷል። በተለይም የዘይት፤ የስኳር በቅርብ ጊዜ መንግሥት የሚያቀርበውን ስለጨመረ ዋጋው ከፍራንኮ ቫሉታ ጋርም ወደ መመጣጠን እየመጣ ነው።

በመሆኑም ለእኛ አቅርቦቱ እየጨመረ መጥቷል። አቅርቦቱ በመጨመሩ ምክንያት ቢያንስ ገበያ ላይ ምርቶችን ማግኘት ተችሏል። የሃገር ውስጥ አምራቾችን ፋብሪካዎቹ ደግሞ ድፍድፍ አምርተው እንዳያቀርቡ ባለን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዘንድሮ ሥራ አልጀመሩም። ከ50 ሚሊዮን ውጭ ስላተመደበላቸው በሃገር ውስጥ ማምረት አልተቻለም።

ሲመረትም ደግሞ ከፍራንኮ ቫሉታ ዘይት ጋር ተቀራራቢ ዋጋ ነው ያላቸው። ስለዚህ ዶላር ከመመደብ ውጭ ብዙ ጥቅም አልነበረውም ማለት ነው። ያ ጥቅም ምንድነው አንደኛ ብዙ የሃገር ውስጥ ምርት መኖሩ በሺ የሚቆጠር ሠራተኛ ሥራ ላይ ይሳተፋል። ደሞዝ ይከፈላል የሥራ እድል ይፈጥራል ዞሮ ዞሮ ነገር ግን፤ ከመጨረሻ ተጠቃሚው አንጻር ተቀራራቢ የሆኑ አንዳንዴም ደግሞ ከውጭ ከሚገባው ዘይት የተሻለ የሚሆንበት ሁኔታ አለ።

ስለዚህ ምንድነው አሁንም ፍራንኮ ቫሉታ የተባለበት ምክንያት በተለየ ሁኔታ ምርት እንዲገባ ስለተፈለገ ነው። ምርት እንዲያስገቡ የጅምላ ንግዱ ትንሽ ከፈት ቢደረግ ደግሞ የተሻለ ይሆን ነበር። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ዶላር በራሳቸው ዶላር ሊገዙ ይችላሉ፣ ዶላር ከጥቁር ገበያ ሊገዙ ይችላሉ። ያ ሁሉ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ አለው። ወደ 4 መቶ 20 አካባቢ ናቸው። ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ በተለይ ደግሞ ወደ አዳማ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ያሉ ናቸው። ስለዚህ ተደጋጋሚ ውይይት ነው የሚደረገው። ለእኛ አሁን እንደውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከ50 እስከ 100 የዘይት ዋጋ እየጨመረ ነው እንጂ ለዓመት ያክል የዘይት ዋጋ እዛው አከባቢ ተረጋግቶ የቆየበት ሁኔታ ነው ያለው። ለኛ በዛው ዋጋ አቅርቦት ስለጨመረ ጥራቱ ጨምሯል ብለን ነው የምናምነው።

ይሄ አንደኛ መንግሥት ቀረጥን ስለተወ ነው። ይሄ ብቻ አይደለም ደግሞ በግብርና ምርቶችም ላይ ማዳበሪያ አምና 15 ቢሊዮን፣ ዘንድሮ 21 ቢሊዮን፣ በነዳጅ ላይ አሁን ሪፎርም እያደረግን እየመጣንም 54 ቢሊዮን ብር ነዳጅ እስከ አሁን ተደጉሞ ነው ያለው። ይሄን ሁሉ ድጎማ መንግሥት የሚያደርገው ገበያው ላይ መረጋጋት እንዲፈጠር ነው። ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ነው። ከዚያ አንጻር ለእኛ የሚታዩ ለውጦች አሉ ብለን እንወስዳለን። እነዚያ ለውጦች ግን ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ ከኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር የተመጣጠነ ነው ብለን አናምንም። ድጎማው ባይደረግ ኖሮ ግን የት ይደርስ ነበር የሚለውን እንደንግድና ቀጣናዊ ትስስር እናስባለን ።

ጥያቄ ፡- ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የተነሳ ጥያቄ ነው፤ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ልትሆን ነው፤ ጫፍ ደርሳለች ይባላል፤ ምን ላይ ነው ያለው?

አቶ ገ/መስቀል፡- የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ወይም አባል ለመሆን ካመለከተች አንድ 20 ዓመት ይሆናታል። እንግዲህ የአንድ ሰው ግማሽ እድሜ እየሆነ ነው። ይሄ ለእኛ የተለየ አይደለም፤ ቻይና ራሷ 27 ዓመት ነው የተደራደረችው፤ ለምን ቢባል የሚደራደሩበት ሁኔታ ጠንካራ ስለሆነ ነው። የሀገራት ሁኔታም ስላለና እነዚያን አልፎ መሄድ ቀላል ስላልሆነ ነው። እኛ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ስንሆን ለአባልነት ብቻ ሳይሆን በሰፊው ገበያ የሀገራችንን ምርት እና አገልግሎት ተወዳድሮ ምን ያህል ተጠቃሚ ያደርገናል የሚለውን ነው ታሳቢ የምናደርገው።

ስለዚህ ያዝ ለቀቅ ሲደረግ ነው የነበረው። እስከ አሁን በሥራ ቡድን የሚባል አለ፤ በየጊዜው ከአባል ሀገራቱ በጣም ዝርዝር ጥያቄዎች ይቀርባሉ፤ እነዚያን ጥያቄዎች ከሀገራችን ፖሊሲ፣ ከንግድ ፖሊሲ፣ ከኢኮኖሚ ፖሊሲ አንጻር ከኢንተሌክችዋል ፕሮፐርቲ መብት አንጻር፣ ከኢንቨስትመንት ሕግ አንጻር፣ ከሴቶችን ወጣቶች ንግድ አንጻር፣ ከዲጂታል ተሬይኒንግ አንጻር አያይዘን የሚጠየቁ ጥያቄዎችን በሙሉ እንመልሳለን። አራት ጊዜ ጥያቄ ተጠይቀን አራቱንም ጊዜ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ጄኔቫ በመገኘት ተደራድረናል። አሁን አምስተኛ ዙር ላይ 181 ጥያቄዎችን ተጠይቀናል። ለእነዚህ ጥያቄዎችም ሰሞኑን መልስ እንሰጣለን።

ሰሞኑን አምስተኛው ዙር የሥራ ቡድን ውይይት አለን። ልክ አንደ ችሎት ነው፤ እነዚህ የጠየቁ አካላትም ሌሎችም ቀርበው ይጠይቃሉ። እነሱ ይጠይቃሉ እኛ አንመልሳለን፤ ድርድር ስለሆነ ይሄንን እስከመቼ ነው የማታደርጉት? እንዴትነው የምታደርጉት? በምን ደረጃ ነው የምትቀንሱት? የሚሉትን ያነሳሉ። ዋናው ነገር ከአፍሪካ ቀጣና የዓለም ንግድ ድርጅትን ለየት የሚያደርገው የገቢ ግብርን ዜሮ አያደርግም። ይልቁንም የገቢ ግብርን ፖዘቲቭ በአቬሬጅ እስከምን ድረስ ነው ኢምፖርት ታክስን የማታስቀምጡት ብሎ ነው የሚደራደረው።

በዚያ ውስጥ ነው ብዙ ነገር የሚወድቀው፤ ግን የተለያዩ ሁኔታዎች ስላሉት ከእኔ በፊት የነበሩትን በዚህ ሁኔታ አራት ስብሰባ አካሂደዋል እናም አሁን ለአምስተኛ ዙር የምናደርግ ይሆናል ይህ የመጨረሻ ቢሆንና ከሁለት ዓመት፣ ከሦስት ዓመት በኋላ አባል ብንሆን ደስ ይለናል። አንድ ዙርም ደግሞ ቢጨምር አባል መሆን ለኛ በጣም ጥቅም አለው በሚል በመንግሥትም ደረጃ እሳቤ ተወስዶ ይሄንን የሚመራ ኮሚቴ እንደገና እንዲቋቋም ተደርጎ፤ ብሔራዊ አስተግባሪ ኮሚቴ እንደገና ተቋቁሟል ። ቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጎ ማዕከሎች ደግሞ ኮሚቴው አጥንቶ የሚያመጣቸውን ውሳኔዎች ማረጋገጫ እየሰጠ እየሄደ ነው ያለው። አሁን የሚቀርቡ ዶክመንቶችን በዛ ሂደት ያለፉትን ቴክኒካል ኮሚቴ ያያቸው፤ ብሔራዊ አስተግባሪ ኮሚቴ በእኔ የሚመራው እያዩዋቸው በብሔራዊ ኮሚቴ በመንግሥትም የሚመራው በመንግሥት ደረጃ ታይተው እንደዚህ ቢቀርቡ ይሻላል ተብለው የሚቀርቡ ናቸው ።

ስለዚህ ብዙ ሀገራት 18፣ 20፣ 25፣ 27 አንዳንዶቹም 30 ቤት ተደራደረው የገቡበት ከገቡም በኃላ አብዛኞቹ ደግሞ ውጤታማ የሆኑበት ስለሆነ እኛም መግባቱ ይጠቅመናል። ኢኮኖሚውን እየከፈትን ስለሆነ ዘግተን መቆየት ስለማንችል ስንገባ ግን በጥንቃቄ የግል ዘርፉን በማያቀጭጭ መንገድ ኢኮኖሚያችንን ተወዳዳሪ በሚያደርግ መንገድ መግባት አለብን በሚል ነው ። ምክንያቱም ብዙ ነገሮችን ለገበያ እየከፈትን ስለሆነ መክፈታችን ላይቀር የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሆነን ብንከፍት የበለጠ ትርፋማ እንሆናለን የሚል እምነት ስላለን ነው። ስለዚህ ሁል ጊዜ ሰው እንደቀልድ ቢያወራም ሌሎችም ሀገራት ረጅም ጊዜ ተደራድረው የገቡበት እና የኢትዮጵያም ብቸኛ ልምድ ስላልሆነ በዛ ደረጃ ግንዛቤ ቢወሰድ ጥሩ ነው ።

ጥያቄ፡- ብረት ላይም ከፍ ያለ ችግር የሚታይ በመሆኑ ከብረት ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ ምን ይመስላል? የተወሰኑ ልምዶችን ብናነሳ?

አቶ ገ/መስቀል፡- ብረት ከውጪ የሚገባ ብረት አለ። ሀገር ውስጥ የሚመረት ብረት አለ። የሀገር ውስጥ ብረት በሚመረትበት ጊዜ ግብዓቱ ከውጪ ይገባል።

አንዳንድ ከውጪ የሚገቡ የአርማታ ብረቶች ዋጋቸው አንዳንዴ ከኛ አምራች ዋጋ ጋር ይቀራረባል። አምና በተወሰነ ደረጃ የውጪ ሀገር ብረት ዝቅ ብሎ የሀገር ውስጥ የብረት አምራቾችን ትንሽ ድምፅ ሲያሰማ ነበር። በኋላ ተከታትለን በምናይበት ጊዜ ወዲያውኑ ዋጋቸው ተቀራረበ።

እንዳውም የሀገር ውስጥ ብረት ዋጋ በተሻለ ደረጃ የሚሸጥበት ሁኔታ አለ። ለዚህ ነው ገበያ ላይ የሚመራ ሁኔታ የምንልበት ለዚህ ነው። አንዳንዴ ከፍና ዝቅ የማለት አንዳንዴም እኩል የመምጣት ነገር አለ። እነዚህ የአገር ውስጥ አምራቾች ቴክኖሎጂውን ምርታማነቱንና ተወዳዳሪነቱን እንዴት እየጨመርን እንሄዳለን የሚለውን ማየት ነው። እንጂ እዚህ ላይ አስተያየቶችም አይቻለሁ በተወሰነ ደረጃ የቱርክ ብረት ዋጋው ወረድ ብሎ በተከታታይ በወራት ውስጥ ወረድ ብሎ ደግሞ ከጊዜ በኋላ እኩል ሆኖ የእኛውም ደግሞ አንዳንዴ የተሻለ የተወዳዳሪነት ዋጋ እንደነበራቸው መረጃው ነበረኝ።

እነዚህ ነገሮች ሲኖሩ እኛም ገበያ ውስጥ ገብተን በጥናት ላይ ተመሥረተን እናያለን። ዋናው ነገር እየጨመረ ቢሄድ ምንድ ነው የምናደርገው የሚለውን ነው። የአገር ውስጥ ምርት እየተወደደ ቢሄድ። ለምሳሌ አሁን ቀይ ባሕር ላይ ያለ ክስተት አለ። የትራንስፖርት ዋጋ እየጨመረ ነው። መዘግየቶች የየበዙ ነው። ስለዚህ ኮስት ኦፍ ፕሮዳክሽን እየጨመረ በሚመጣበት ጊዜ ነው፡

እንደዚህ አይነት ችግር የሌለበት ሀገራት ደግሞ ምርቶቹን ቢያመጡ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ጭምር ለቀጣይ ማየት ያስፈልጋል ማለት ነው። ስለዚህ ኢኮኖሚውን ስንከፍት ደረጃ በደረጃ ነው የምንለው ለዛ ነው። የሀገር ውስጥ ባለሃብት እንዳይቀጭጭ እና ገበያውን ሙሉ በሙሉ ዝግ እንዳይሆን በተጠና አግባብ መመለስ አለብን የምንለው ለዛ ነው።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትላላቅ ኤክስፖዎች ላይ ትሳተፋለች እነዚህ ኤክስፖዎች ምን አይነት ልምድ ተገኘባቸው

አቶ ገ/መስቀል፡- ሁለት ጥቅም ነው። አንደኛው ብዙውን ጊዜ ዓለምአቀፍ ኤክስፖ ነው አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው። ከንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር ሆነን የምናዘጋጀው ኤክስፖና ኤግዚቢሽን አንደኛው ጥቅም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ልምድ ያገኛሉ። የውጭ ባለሀብቶች ማሽነሪና ቴክኖሎጂዎቻቸውን አሠራሮቻቸውን ጭምር ይዘው መጥተው ስለሚሳተፉ ልምድ ያገኛሉ። ጆይንት ቬንቸርም ይፈጥራሉ። ሁለተኛ ከትምህርቱ ባሻገር እኛ ጋር ያሉ ባለሃብቶች ከእነርሱ የገበያ ትስስር ያገኛሉ። እነርሱ የሚፈልጋቸው የእኛ ምርቶች እና እነርሱ የማያመርታቸው የሚፈልጋቸው ምርቶች ገበያ ያገኛሉ።

የእኛ ኤክስፖና ኤግዚቢሽን በዚህ ብቻ አይወሰንም። ውጭ ሀገር ሄደው የሚሳተፉም አሉ። ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሕንድ፣ ቱርክ፣ ጀርመን ላይ በብዛት ይሄዳሉ። የምንፈቅደው እኛ ነን። የተለያዩ የግል ሴክተሮች ከኛ ጋር አብረው ይሠራሉ። እዛም ሂደው የገበያ ትስስር ፈጥረው ይመጣሉ። ስለዚህ ኤክስፖን እኛ እናበረታታለን። ፕራይቬት (የግል) ሴክተራችም ደግሞ ትምህርት ያገኙበታል፤ የገበያ ትስስርም ያገኛሉ። አንዳንድ በጣም ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችንም ደግሞ ያመጣሉ። ኢንቨስትመንትም ይስባሉ፤ ኤክስፖ። ስለዚህ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሥራ ስለሆነ፤ ፕራይቬት ሴክተሩ ከኢንተርናሽናል ተቋማትም ጋር አብረን እንሠራለን።

ጥያቄ፡- ነጋዴው የሚደሰትባት፤ ሸማቹም የፈለገውን የሚያገኝባት፤ አቅርቦትና ፍላጎት የተጣጣሙባት ኢትዮጵያን በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ለመፍጠር ምን አይነት ሥራዎች እየሠራችሁ ነው?

አቶ ገ/መስቀል፡- ነጋዴው የሚደሰትባት፤ ሸማቹ የፈለገውን የሚገዛባት የሚል በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም ሁለቱን ማስደሰት ከባድ ስለሆነ። ግን ሁለቱን የሚያስደስተው ገበያው ነው። ገበያው ደግሞ የሚመራው ሁልጊዜ እኛ ብንወድም፣ ባንወድም፡ ብንፈልግማ፣ ባንፈልግም በአቅርቦትና በፍላጎት ነው። ይሄ ነው የገበያውን ዋጋ የሚወሰነው። የፈለገ ምርጥ እቃ ኖሮት፣ የፈለገ ጥራት ኖሮት ፍላጎት የማይኖረው ከሆነ ደንበኛው የማይጠቀመው ከሆነ በዛው ልክ ይረክሳል ማለት ነው።

ስለዚህ ሁልጊዜ ፈላጊውና ተፈላጊው፣ አቅራቢውና ተቀባዩ በገበያ ላይ ነው የሚዳኙት። ይሄ ገበያ ደግሞ ፍትሐዊ መሆን አለበት። ነጋዴውም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀምበት አቅራቢውም ደግሞ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀምበት መሆን አለበት። ፍትሐዊ ለመሆን ደግሞ መንግሥት መሐል ላይ ሥርዓት የሚዘረጋው። ይሄንን ለማድረግ እኛ በተለይ በንግዱ ውስጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የንግዱን ሥርዓት ማዘመን፣ የንግዱን ሥርዓት ከሰው ንክኪ ወጥቶ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ እናደርጋለን። አምራቹና ሸማቹን በሲስተም ተገናኝቶ ምርቶቻቸውን የሚቀባበሉበትን ሥርዓት ማድረግ ነው። የባንክን ሥርዓት፣ ትራንስፖርቴሽን ሥርዓት፣ የአምራቹ ሥርዓት፣ የሸማቹ ሥርዓት በሙሉ በዲጂታል ሲስተም እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ነው።

ለዚህ መጀመሪያ ይኸ ሀሳብ ሆኖ ሆኖ ለዚህ ሕግ ያስፈልገዋል ማለት ነው። ይህንን ሥርዓት ለመፍጠር ነው እየሄድን ያለነው። ይህ ሥርዓት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል፤ ከዚያ ውጪ ደግሞ እጠቀማለሁ የሚለውንም ሥርዓቱ ራሱ ስለሚቆጣጠረው ይጋለጣል ማለት ነው። ስለዚህ እኛ የምናደርገው ነጋዴውን የሚያስደስት፤ ሸማቹንም ደስ የሚያሰኝ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ተፈጥሮ ማየት ነው። ይህንን ደግሞ እናደርጋለን ብዬ አምናለሁ። ሥርዓቱ በሂደት ወደተሟላ ልክ አሁን ነዳጅ ላይ እንዳመጣነው፤ በዚህም በሸቀጥ ግብይትም ላይ፤ በአገልግሎት ግብይትም ላይ ወደዚያ ሥርዓት እናሳድጋለን። ምክንያቱም ግሎባል ኢኮኖሚ ላይ ስለሆንን። የሚገፋንም ወደዚህ እንድንገባ ነው። የሚገፋፉንም በርካታ ምክንያቶች ስለሆኑ ወደዚህ እንገባለን።

ሁለተኛ ይኸ ሥርዓት እስኪዘረጋ ድረስ ዘመናዊ ሥርዓት እስኪዘረጋ ድረስ ሁልጊዜ ደግሞ የሰው ንክኪ ስላለ፤ እናም በሰው ይሁንታ፤ በሰው ውሳኔ የሚፈጸሙ ጉዳዮች ስለሚበዙ የኅብረተሰቡ፣ የሸማቹ ማኅበረሰብ በጉዳዩ ላይ አጋዥ መሆን የሚዲያው አጋዥ መሆን በጣም ጠቃሚ ነው። ሚዲያው መረጃን በመስጠት፤ ሸማቹ ደግሞ በእያንዳንዱ ስርቻ የሚደረገውን የግብይት ሥርዓት ሁነቶችን በተደራጀ መንገድ መረጃ በመስጠት ለምሳሌ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበር በየደረጃው ስለተቋቋመ ይኸ የሸማቾች ጥበቃ ማኅበር እያንዳንዱ ዜጋ አባል የመሆንበትና እያንዳንዱ ዜጋ ደግሞ በተቋሙ አማካኝነት ላለው ለፀጥታ መዋቅር መረጃውን እየሰጠ፤ እየታገለ ሥርዓቱ የተሟላ ሥርዓት፤ ዲጂታል የሆነ ሥርዓት እስኪቆጣጠረው ድረስ ደግሞ ኅብረተሰቡና ሚዲያው ከጎናችን እንዲሆን ጥሪዬን ለማስተላለፍ ነው አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2016 ዓ.ም

Recommended For You