በማስተዋል ሰላምን ወደሚያጸኑ መንገዶች እንራመድ!

ሰላም የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ሌሎች ለመኖር የሚያስፈልጉንን ጉዳዮች በተሟላ መልኩ ለመከወንና ለማግኘት የሚያስችለን መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ሰላም ከሌለ ምንም የለም፤ ሌላው ቀርቶ ወጥቶ የመግባት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ሠርቶ ሀብት ማፍራት፤ ወልዶ ልጅን በፍቅር ማሳደግ፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ጉዳይን መከወን የመሳሰሉ ጉዳዮች ደግሞ የቅንጦት ሆነው ይቀራሉ።

ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለውም ይሄው ነው። ሰላም ምን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ ብቻ ሳይሆን ተኪ እንደሌላት መገንዘብ የተቻለባቸው በርካታ የፈተና ወቅቶች፤ ግጭትና መፈናቀሎች፤ አልፎም የጦርነት ዓመታት አልፈዋል። በዚህም በብዙ ቢሊዮን የሚገመት የሀገር ሀብት ወድሟል፤ የማይተካው የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፤ አካልም ጎድሏል። በጥቅሉም ዛሬም ድረስ ዐሻራቸው የሚታይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ሥነልቡናዊ ተጽዕኖዎች ደርሰዋል።

በተለይ ከለውጡ ማግስት እንደ ሀገር የታየውን ከፍ ያለ የሪፎርም ተግባር ተከትሎ፣ የሕዝብ ተጠቃሚነት ሳይሆን የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት የበለጠባቸው ኃይሎች የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ በርካታ ሙከራ አድርገዋል። ይሄው ሁነት ከሃሳብ መወራወር እስከ ቃታ መሳሳብ ያደረሰን ክስተት ፈጥሯል። በዚህም በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭትና ጦርነቶች ነበሩ።

ለምሳሌ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ የታየው የጥፋት ኃይሎች ተግባር በርካቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለስደት፣ እንዲሁም ከፍ ያለ ግምት ያለው የግለሰቦችና የሀገር ሀብትን ለውድመት ዳርጓል። በዚህ አካባቢ ያለው ችግር እምብዛም መቋጫ ሳያገኝ ደግሞ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሌላ የጦርነት እሳት ተለኮሰ።

በተለይ የጥቅምት 24ቱን ጥቃት ተከትሎ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ጦርነት ታዲያ፤ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ጉዳት የከፋ ነው። በዚህ ጦርነት በመቶ ሺዎች ዋጋ ከፍለዋል፤ በቢሊዮኖች የሚገመት ንብረት ወድሟል፤ ማኅበራዊና ሥነልቡናዊ ተፅዕኖውም ጉልህ ነበር።

ይሄንን አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳረፈውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በመንግሥት በኩል በርካታ ጥረቶች ተደርገው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በአካባቢው የሰላም አየር መስፈን ችሏል። በስምምነቱ መሠረትም ሊፈጸሙ የሚገባቸው ጉዳዮችም በተለይ በመንግሥት በኩል በትኩረት እየተሠሩና ውጤትም እየተገኘባቸው ናቸው።

ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ በስምምነቱ መሠረት እየተጓዙ ያልሆኑ ጎታች ጉዳዮች አልታጡም። በዚህ ረገድ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ተሐድሶ ማዕከል በማስገባት ተገቢውን የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ልማት ሥራ እንዲገቡ ከማድረግ አኳያ ያለው ክፍተት ተጠቃሽ ነው። ይሄ ደግሞ ዜጎች በተለይም በአካባቢው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የናፈቁትን ሰላም፣ ልማትና ሌሎችም ጉዳዮች በሙላት የማግኘት ሂደት ላይ ስጋትን የሚደቅን ሊሆን ይችላል።

ከዚህ አኳያ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና እሱን ተከትሎ የተወሰዱ ርምጃዎች በሰላም፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያመጣውን ፋይዳ በመገንዘብ፤ በቀጣይ ቀሪ ሥራዎችን በተቀመጠው አካሄድ መሠረት መተግበር እና ለዜጎች ሰላም እውን መሆን ሁሉን አቀፍ ቁርጠኝነትን ማረጋገጥ ይገባል።

ከዚህ በተጓዳኝ አሁንም እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፤ መፈናቀልና ጦርነቶችን ለመቋጨት መንግሥት ለሰላም ሁሌም በሩን ክፍት አድርጎ የሕግ ማስከበር ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በአማራ ክልልም ያለው ችግር ብዙዎችን የሕይወትና አካል ዋጋ እያስከፈለ፤ ንብረትም እያወደመ ያለ ነው። እዚህ እና ሌሎችም ብቅ እልም እያሉ ያሉ የሰላም ችግሮች ታዲያ፤ እንደ ሀገር ለተጀመረው ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እውን መሆን እንቅፋት፤ ለዜጎችም ደህንነት ስጋት መሆናቸው እሙን ነው።

በመሆኑም ለሀገር ሁሉን አቀፍ ብልጽግና፤ ለዜጎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነልቡናዊ ልዕልና፤ ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስብ ኃይል ሁሉ፤ የሰላምን ዋጋ በመገንዘብ ለሰላሙ ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል። በዚህ ረገድ መንግሥት ቀድሞም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የቋጨባቸው አካሄዶች፤ አሁንም ስለ ሰላም እያደረጋቸው ያሉ ተደጋጋሚ ጥሪዎች የሚያስመሰግኑት ናቸው።

ይሁን እንጂ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሊመጣም፤ ሊጸናም አይችልም። የኅብረተሰቡን ንቁ ተሳትፎ፤ የግጭት ተዋናዮችም ለሰላማዊ ንግግር መዘጋጀትን አብዝቶ ይፈልጋል። ከዚህ አኳያ ስለ ሕዝብ ቆሜያለሁ ወይም እቆረቆራለሁ የሚል ማንኛውም ኃይል፤ ስለ ሀገሩ መጻዒ እድል እና ብልጽግና ግድ ይለኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ስለ ሠላም መምከር፤ ስለ ሰላም መሸነፍ፤ ስለ ሰላም ራሱን ማስገዛት ይኖርበታል። ሰላም ደግሞ መንገዷ ቀና ልብ፤ መዳረሻዋም የአዕምሮ እረፍት አለው። በመሆኑም ወደዚህ የሰላም መንገድ በማስተዋል መራመድ ከሁሉም ይጠበቃል!

አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You