ሴቶች በሁሉም ማኅበረሰብ ሊባል በሚችል ደረጃ ለዘመናት አድሏዊ ልዩነት እየተደረገባቸው እና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሳይከበሩላቸው መቆየታቸውን ከታሪክ መመልከት እንችላለን። እነዚህን የመብት አለመከበር እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶችን ለማስወገድ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ሀገር አቀፍ ሕጎች ቢኖሩም የሴቶችን መብቶች ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
እስከዛሬ በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች የተነሳ ጉልህ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ሙሉ በሙሉ የፆታ እኩልነትን ለማስመዝገብ ትልቅ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ በመቀጠል ላይ ነው። ሴቶች በተለያዩ የዓለም ሀገራት መድልዎ፣ ጥቃት፣ የትምህርትና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ውስንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ልዩነቶች ይደርስባቸዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሴቶች እና በወንዶች ያለው የኢኮኖሚ ልዩነት ስንመለከት፤ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ ከወንዶች በ23 በመቶ ያነሰ ገቢ ያገኛሉ። የሴቶች በአመራር ቦታዎች ላይ ያላቸው ውክልናም ዝቅተኛ ነው፡፡ በፓርላማ ውስጥም መቀመጫ ማግኘት የቻሉት 24 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል የሚታይበት ቢሆንም አሁንም በርካታ ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉት እሙን ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ የሴቶችን ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናና ከለላ እንዲኖረው በማድረግ ጭምር በከተማና በገጠር የሚኖሩ ሴቶች መብታቸው ተረጋግጦላቸው እንዲኖሩ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሴቶችን ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ መንግሥት እንደ አዲስ ባዋቀረው ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶውን ሴቶችን እንዲይዙ በማድረግ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ አርዓያነት ያለው ተግባር ማከናወን ተችሏል፡፡
የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ የተሠራውም ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ከጤና ጋር በተያያዘም ‹‹አንድም ሴት በወሊድ የተነሳ አትሞትም›› በሚል ሴቶች የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅምም ለማሳደግም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ትናንት ለምረቃ የበቃው የሴቶች የተሐድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የዚሁ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ማዕከሉ በዋነኛነት በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶችን በመቀበል ሙያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ፣ ክትትልና ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲሠማሩ የሚያስችል ሲሆን በአንድ ዙር ብቻም 10 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ የማሠልጠን አቅም ያለው ነው፡፡ “ለነገዋ” በሚል የተሰየመው ይኸው የሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የሴቶችን እኩልነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ሚና ይኖረዋል፡፡
ሴቶች በማዕከሉ ቆይታቸው ከሚያገኙት የሥነ ልቦና ድጋፍ በተጨማሪ በሥነ-ውበት፣ በከተማ ግብርና፣ በምግብ ዝግጅት፣ በከተማ ውበት አጠባበቅና በኮምፒዩተር ሙያ ሥልጠና በመውሰድ ወደ ሥራ እንዲገቡም ዕድል ይፈጥራል፡፡ ማዕከሉ በውስጡ የተሐድሶ ሥልጠና የሚሰጥባቸው የክህሎት ማበልፀጊያ፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የሥነ-ልቦና እና ምክር አገልግሎትንም ያቀፈ ነው፡፡
ይህ ማዕከልም መንግሥት የሴቶችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ካሉ ዘርፍ ብዙ ሥራዎች አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጾታ ተኮር የሆኑ ፖሊሲዎች መተግበር አለባቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሴቶች እኩል ክፍያ፣ ብድር የማግኘት ዕድል እና የሥራ ፈጠራ ድጋፎችን እንዲሁ ሊያገኙ ይገባል። የግል ሴክተሩም የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን እንዲያበረታታ እና አድሎአዊ ድርጊቶችን እንዲያስወግድ ማበረታታት አስፈላጊ ነው።
ሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም የተለያዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ እነዚህን ክፍተቶች ለማጥበብም የሕግ ማሻሻያዎችን መተግበር፣ የትምህርት እና ግንዛቤን ማስበጫዎችን ማድረግ፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ በማብቃት፣ ጤናን እና ደኅንነትን በማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጎልበት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነትን ለማምጣት መሠራት አለበት፡፡ እያንዳንዷ ሴት መብቷን የምትጠቀምበት እና አቅሟን የምታሳይበት ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቦች እና መንግሥታት በጋራ መትጋት ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2016 ዓ.ም