ለተቋማት የበለጠ ኃላፊነትን የሰጠ የሽልማት መርሀ ግብር!

በሀገሪቱ ተቋማት ያስመዘገቡትን ስኬት ትከትሎ እውቅና ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡ በገቢ አሰባሰብ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ በወጪ ንግድና በመሳሰሉት የታዩ ስኬቶችን ተከትሎ የተሰጡ እውቅናዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ፡፡ እውቅናዎቹ በየዘርፎቹ በተከናወኑ ተግባራት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ከማመስገን ጎን ለጎን በቀጣይም ውጤታማ ተግባር እንዲከናወን ኃላፊነት የተሰጠባቸው ናቸው፡፡

ከትናንት በስቲያም የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት መርሀ ግብር በዓድዋ ሙዚየም ተካሂዷል፡፡ በዚህም አምስት ተቋማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የግብርና ሚኒስቴር ባከናወኑት ተግባር ተሸልመዋል፡፡

በእርግጥም ተቋማቱ በስኬታማነታቸው ሲጠቀሱ የቆዩ ናቸው፡፡ ተቋማቱ ያስመዘገቧቸው እነዚህ ውጤቶች ናቸው ለሽልማት ያበቋቸው፡፡ አሁንም በዚህ መድረክ ላይ ስኬታማ ተግባሮቻቸው ተዘርዝረው ቀርበዋል፡፡ ካከናወኗቸው ተጠቃሽ ተግባሮች አኳያ ሽልማቱ ቢያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም፡፡

ሀገርን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማስተሳሰር፣ ተጠቃሽ የስንዴ ልማት ሀገር ማድረግ፣ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት ቀዳሚ መሆን ፣ ለሀገርም ለአህጉርም መብራትና ራት ሊሆን የሚችል ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ ሀገሪቱን በስንዴ ልማት ተጠቃሽ ሀገር ማድረግ መቻል፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ከውድቀት ወደ እድገት መገስገስ መቻል ከማሸለምም በላይ ሌላ እውቅና የሚያሳጩ ናቸው፡፡

መድረኩ የተቋማቱን ስኬት ደጋግሞ ለመግለጽ የተካሄደም አይደለም፤ ለተቋማቱ እውቅና በመስጠት ይበልጥ እንዲሠሩ ለማድረግ፣ ሌሎች ተቋማትም ይህን አርአያነት ያለው ተግባራቸውን ተመልክተው ጠንክረው በመሥራት ተጠቃሽ መሆን እንዲችሉ የሚያነሳሳ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት መርሀ ግብር የተሰጠው እውቅና ደግሞ ከዚህም የተሻገረና ተቋማቱ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዲቀበሉ የተደረገበትም ነው፡፡ በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስገነዘቡትም ይህንኑ ነው። የኢትዮጵያ ተቋማት በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ ተቋማቱ በሀገር ደረጃ በስኬታማነታቸው ይታወቃሉ፤ በዚህም እውቅናን ያተረፉ ናቸው፡፡ ይህ እውቅና እንደተጠበቀ ሆኖ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ መሆኑ ሁሌም ይገለጻል፡፡ በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስገነዘቡት ደግሞ፤ አየር መንገዱ ከአህጉራዊ እውቅናው ባሻገር መሥራት ይኖርበታል፡፡ ለእዚህም ተቋሙ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምም እንዲሁ በሀገር ውስጥ ያለውን ስኬት በአህጉር አቀፍ ደረጃም እንዲደግም የቤት ሥራ ተሰጥቶታል። ተቋሙ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እና ሀገሪቱን ከአፍሪካና ከዓለም በማስተሳሰርም ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ ኢንቨስትመንቱን በአህጉር ደረጃ በማስፋፋት ጭምር ተወዳዳሪነቱን ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡

በአጠቃላይ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ፣ በስኬት ተኩራርቶ ላለመዘናጋት ፣ ሰፋ ወደአለ አካባቢ በመውጣት ተወዳዳሪ ሆኖ ስኬታማ ለመሆን መድረኩ ትልቅ መልዕክት ተላልፎበታል፡፡

ይህን ማድረግ ያለባቸው ደግሞ እነዚህ ተቋማት ብቻ አይደሉም፡፡ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በንግድና በመሳሰሉት ሥራዎች የሚንቀሳቀሱ በርካታ ተቋማት አሏት፡፡ እነዚህ ተቋማትም ተወዳዳሪነታቸውን ከሀገር አልፈው በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያሳድጉ መርሀ-ግብሩ አመላክቷል፡፡

በሀገሪቱ በዚህ መንገድ መጓዝ ያለባቸው ተቋማት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በወጪ ንግድ፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት ዘርፎች አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ላይ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ ይህ ሽልማት እነዚህ ሁሉ ተቋማት ብዙ መትጋት እንደሚገባቸው ጠቁሟል፡፡

ተቋማት ባስመዘገቡት ስኬት ረክተው እንዳይቆሙም መርሀ-ግብሩ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የስኬት ዳር እንደሌለው ያስገነዝባል፡፡ በእዚህ የውድድር ዓለም ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብርቱ ሆኖ መገኘት፣ በአህጉር ደረጃም ተጠቃሽ ሆኖ መገኘት የመጨረሻ ስኬት ተደርገው መወሰድ እንደሌለባቸው ተመላክቷል፡፡

ከሀገር አልፎ በአህጉር ደረጃ ብርቱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲሠራ፣ በሀገር ደረጃ በቴሌኮም መሠረተ ልማት ማስፋፋትና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሹ ኢትዮ ቴሌኮም ለአህጉራዊ ውድድር ራሱን እንዲያዘጋጅ መልዕክት ሲተላለፍ ራስን ለበለጠ ውድድርና ስኬት ማዘጋጀትን ሁሉም ተቋም እንዲያስበው ተደርጓል፡፡

በመርሀ-ግብሩ አምስት ተቋማት ቢሸለሙበትም፣ በመድረኩ የተላለፈው መልዕክት ሁሉም ተቋማት በእርካታ ሳይዘናጉ፣ የበለጠ ለመሥራት እንዲነሳሱ የሚያደርግ ነው፡፡

አዲስ ዘመን መጋቢት   5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You