ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። በተለይም ደግሞ ሀገር ሰላም ሁሉንም የሚነካ እና የሚመለከት ነው። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ሰጡትን ሰፊ ማብራርያ እንደሚከተለው አጠናክሯል፤መልካም ንባብ።
ጥያቄ ፦ የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተቋቋመ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። በዋናነት ግን በዚህ አምስት የተሠሩ ሥራዎችንና ዋና ተልዕኮ በማንሳት ብንጀምር ደስ ይለኛል።
አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፦ የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ሲቋቋም እንደገና በ2011ዓ.ም የተቋቋመበት አዋጅ ከዛ በኋላም 2014/11/63 በሚባለው አዋጅም ሲቋቋም ብዙ ዝርዝር ተግባራት ተሰጥተውታል፤ በጣም ሰፊ ነው። ግን እነዚህ ነገሮች ተጠቃለው ስታዩ በአራት ዋና ዋና ዘርፎች ተጠቃለው ሊታዩ ይችላሉ።
የመጀመሪያው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉዳይ ነው። እንግዲህ ያው እንደሚታወቀው ሰላም በአንድ ጊዜ ተገንብቶ የሚቆም ነገር አይደለም፤ ረዥም ጊዜ የሚወስድና ተከታታይ ትውልዶችን የሚጠይቅ ጭምር ነው። አንዴ ተሰርቶ የሚቆም አይደለም፤ የሆነ ግጭት ስለቆመ ብቻ ሰላም ተረጋግጧል ማለት አይቻልም።
በተከታታይ ለረዥም ጊዜ ሊሠራ የሚችል እና ምናልባትም የዕድሜ ልክ ሥራ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ምክንያቱም ዛሬ ለሰላም መታጣት ምክንያት የሆኑ ነገሮች ቢፈቱ እንኳ ነገ ደግሞ ሌላ ነገር ሊያጋጥም ይችላል።፡ በዛ ላይ የሰላም ሥራ አንድ ተቋም ወይም የተወሰኑ አካላት ብቻ የሚሰሩት አይደለም፤ የብዙ አካላትን ቅንጅትና ትብብር የሚጠይቅ ነገር ነው።
የሰላም ሥራ የማይገናኝበት ዘርፍ የለም ለምሳሌ፦ የኢኮኖሚ ችግር፣ የሥራ አጥነት፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወዘተ እያልን በጣም ብዙ ነገሮች ሊቆጠሩ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች ይያያዛሉ በቀጣይ የአንዱ ጉድለት ሄዶ ሄዶ ለሰላም መታጣት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የብዙ አካላት ቅንጅትና መናበብ የሚጠይቅ ተግባር በመሆኑ በሰላም ግንባታ ዙሪያ በተለያዩ አካላት የሚሰሩ ሥራዎችን የማስተባበር እና የማቀናጀት ተልዕኮን ያጠቃልላል ማለት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የሰላም ግንባታ ሥራ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳም ነው። በአንድ አካባቢ የሚከሰት የሰላም መታጣት ችግር በሌላው አካባቢ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ አሁን የምናያቸው በዓለማችን ላይ የሚካሄዱ ጦርነቶች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በሁሉም ሀገሮች ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው። ይህንን በአይናችን እያየን እየተመለከትን ያለነው ነገር ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ተጠቅልለው ሲታዩ የሰላም ግንባታ ሥራው ዘላቂነት ያለውና በየጊዜው ብልጭ ድርግም የሚል ሳይሆን ቢያንስ ቀጣይነት ያለው ሰላም ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲሰሩ ነው በአዋጅ ተልዕኮ የተሰጠው።
ሁለተኛ ከሀገር ግንባታ ጋር የሚያያዝ ነው። እንግዲህ የሀገር ግንባታ ሲባል የሚታወቀው የዚህ ሀገር የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጅምር ነው ወይም ደግሞ ያልተጠናቀቀ ሥራ ነው ተብሎ ይታመናል፤ ይሄ በብዙ ሰው ዘንድ የሚታመንበት ጉዳይ ነው። ስለዚህ የሀገረ መንግሥት ግንባታው ጠንካራ ሆኖና የተረጋጋ ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግሥት ሥርዓት እንዲኖረን እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ነው። ይህ ብሔራዊ መግባባትንም ያካትታል ማለት ነው። ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ይኑረን ሲባል በመሠረታዊነት ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ጉዳይ ነው። በጋራ በምንግባባቸው ጉዳዮች ላይ እንድንግባባ የሚያስችል ሥራ መሥራት ነው ሊባል ይችላል ሁለተኛው ተልዕኮ ማለት ነው።
ሦስተኛው ተልዕኮ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ጠንካራና እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት በዚህች ሀገር እንዲኖር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ በተልዕኮው ላይ ተቀምጧል። እንግዲህ ይህ ማለት ምንድነው ያው እንደሚታወቀው የኛ ሀገር የመንግሥት አወቃቀር ፌዴራላዊ ነው። በዚህ የፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ በዋናነት የፌዴራል ሥርዓት የሚታወቅበት ጉዳይ አለ።
ይህ ፅንሰ ሃሳብ ጀምሮ ዜጎች በተሟላ ሁኔታ የፌዴራል አወቃቀር ሥርዓትን እንዲገነዘቡ፤ ለዛም ደግሞ ለተግባራዊነቱ እንዲሠሩ ሊያደርግ የሚችል ሥራ እንዲሠራ ነው። የመንግሥታት ግንኙነት የሚባለው ለምሳሌ ክልል ከክልል ጋር የሚኖረው ግንኙነት፤ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት የሚኖራቸው ግንኙነት ሥርዓትን የተከተለና በሕግ የሚመራ ሁሉም የየራሳቸውን የቤት ሥራ ለይተው ያንን የሚሰሩበት እንዲሁም በትብብር የሚሰራው የጋራ እና የተናጥል ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችላቸው ነው።
አራተኛው ግጭት መከላከልና ግጭት ማስተዳደር የሚባለው ዘርፍ ነው። ይህም በሦስት ደረጃዎች ይታያል። የመጀመሪያው ግጭትን አስቀድሞ መከላከል ነው። ግጭት የመከላከሉ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራም አንዳንዴ በሆኑ ምክንያቶች ግጭት ሊፈጠር ይችላል። የትም ሀገር እንደሚታየው ማለት ነው።
ግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ የጉዳት መጠኑ በጣም ሳይሰፋ ቶሎ በቁጥጥር ስር የሚውልበት የግጭት አስተዳደር /conflict management/ የሚባል ሥራ አለ። ሦስተኛው ከዚሁ ጋር ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ የ conflict transformation የሚባለው ነው። ከግጭት በኋላ /post conflict / ያለው።
ግጭቱ ከተፈጠረ በኋላ የተለያዩ ጉዳቶች ማስከተሉ አይቀርም። ለምሳሌ የዜጎች መፈናቀል፣ ሞት፣ የንብረት መውደም የመሳሰሉትን ያስከትላል። ግጭት በባህሪው እነዚህን ያስከትላል። በግጭቱ የተጎዱ ዜጎችን፣ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መልሶ ማቋቋም /Restore ማድረግ/ አለ። ከግጭት በኋላ የሚከናወኑት ሥራዎች ዜጎች ወደቀደመው ሰላማቸው፤ አካባቢው ወደቀደመው ሰላሙ እንዲመለስ ለማድረግ የሚሠሩ ናቸው።
ስለዚህ ይሄ ከግጭት መከላከልና ከግጭት አስተዳደር አኳያ በእነዚህ ሦስት ምእራፎች፤ ቅድመ ግጭት፣ በግጭት ወቅትና ከግጭት በኋላ በሚባሉት ጉዳዮች ላይ ይሄንን ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ነው። በተቋሙ ተልእኮ ላይ የተቀመጠው። የሚኒስቴሩ ሥራም ጠቅለል ብሎ ሲታይ በእነዚህ አራት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ይቻላል።
ጥያቄ፦ እነዚህ አራት ዋና ዋና ተልእኮዎችን ከማስፈፀም ረገድ ባለፉት ዓመታት በተለይም ደግሞ ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው አፈፃፀም እንዴት ይታያል?
አቶ ብናልፍ አንዷለም፡- እንግዲህ ተልእኮዎቹ አሁን ያልኳቸው ስለሆኑ እቅዱም ይሄንን መሠረት አድርጎ ይዘጋጃል። በዚህም የአስር ዓመት፣ የአምስት ዓመት እና ዓመታዊ እቅድ አለው። ዋናው የእቅዱ ማጠንጠኛ በእነዚህ ላይ ይመሰረታል። እያንዳንዳቸው በውስጣቸው ዝርዝር ነገር አላቸው። ያንን መሠረት አድርጎ እቅዱ ይወጣል፤ እቅዱን ለመተግበርም ጥረት ይደረጋል። ከዚህ አኳያ የመጀመሪያው የሰላም ግንባታ ወይም ደግሞ ዘላቂ ሰላም የሚባለውን ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራው አንዱ ሥራ ማህበረሰቡ ላይ የተመሰረተ ነው። መሬት ላይ ወርዶ ሕዝቡ ዘንድ የሚሰራው ሥራ የማህበረሰብ ውይይት የምንለው አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ክልሎች፣ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የሰላም ስጋት ናቸው በሚላቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ችግሮቹ ወደ ግጭት፣ ጥፋትና ብጥብጥ ሳይሸጋገሩ ባሉበት እንዲቆሙ ሊያደርጉ የሚችሉ እና በመከላከል ላይ ትኩረት ለማድረግ የሚያስችሉ ሰፋፊ ውይይቶች (Community Dialogues) ተካሂደዋል። በዚህ ረገድ ዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች በነዚህ ውይይቶች ላይ ተሳትፈዋል።
ይህ በራሱ በእቅድ ግብ ተቀምጦለት የሚሠራ ነው። ይ።ሥራ በየአካባቢው የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ ችግሮቹን ለመፍታት የሚደረጉ ውይይቶችን አይጨምርም። ስለዚህ ይህ ትልቅና ሰፊ የሚባል ሥራ በየጊዜው ተጠናክሮ እየተሠራ ነው። ባለፉት ስድስት ወራት እዚህ ላይ ትኩረት አድርገን ለመሥራት ጥረት አድርገናል። ይህን ተከትሎም በተለያዩ አካባቢዎች የሚያበረታቱ ውጤቶችም ታይተዋል።
ሌላው ከትምህርት ተቋማት ጋር የሚከናወነው ሥራ ነው። የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሥራ የትውልድ ግንባታም ጭምር ነው። አብዛኞቹ ሕፃናትና ወጣቶች የሚገኙት በትምህርት ላይ ነው። ስለዚህ ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ፣ አንዳንድ ጊዜም ከመዋዕለ ሕፃናት (KG) ጀምሮ በዚህ ላይ መሠራት አለበት።
ትውልዱን ከታች ጀምሮ የመገንባት ሥራ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን። ለምሳሌ ያህል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሁሉም አካባቢዎች የሰላም ክበባትን (Peace Clubs) ለማቋቋም ተሞክሯል። እነዚህ የሰላም ክበባት ተማሪዎች ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ እንዴት መፍታት እንዳለባቸው፣ ልዩነቶችን እንዴት ማቻቻል እንደሚገባቸው በጣም ሰፊ ውይይቶችን ያደርጋሉ። የእኛ ሀገር የሃይማኖት፣ የባህል፣ የብሔርና የቋንቋ ብዝኃነት ያለበት ሀገር ነው፤ይህን ብዝሃነት አቻችሎ በማስኬድ ላይ ተሰርቷል።
በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎች የሚገናኙባቸው በመሆናቸው እነዚህ ልዩነቶች በአግባቡ ሊስተናገዱ ስለሚችሉበት አግባብ ውይይቶችን ያደርጋሉ። በዚህም ልዩነትን ለማቻቻልና ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመወያየት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሰላም ክበባቱ ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል።
ሌላው ጉዳይ በትምህርት ቤቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር የማድረግ ሥራ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሁከት የሚደረግባቸውና ዋነኛ የግጭት መቀስቀሻዎች እንዲሆኑ ሲደረግ ነበር። ይህ በጣም ከባድ ጉዳት ያስከተለም ጭምር ነው። ከዚያ መውጣት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተሠርቷል፤ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ሂደት ቢኖር ለራሳቸው ለትምህርት ቤቶቹ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብም አስተዋፅዖ ይኖረዋል።
ስለዚህ በዚህ ላይም ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ያደረግንበት ሁኔታም የጋራ እቅድም አለን።
በዚያ መሠረት ትምህርት ቤቶች ላይ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው። በረጅም ጊዜ የምናስበው በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ጭምር እንዲካተት ማድረግን ነው። የሰላም ግንባታ ሥራ በብዙ ሀገሮች ላይ ልምዱ አለ። የፒስ ቡይልዲንግ ኤዱኬሽን/ የሰላም ግንባታ ትምህርት/ የሚባል በብዙ ሀገራት ይሠራበታል፤ በትምህርት ቤቶች ላይ ይተገበራል። ይሄ ወደፊትም በእኛ የሥርዓተ ትምህርት አካል ሆኖ በዚያ ውስጥ ተካቶ ተማሪዎች የሰላምን ዋጋ ከታች ጀምሮ በአግባቡ እያወቁ እንዲመጡ የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት። ይሄም በእቅዳችን የተያዘ ነው፤ ግን በዚህ ዓመት የተሰራበት ባይሆንም በሚቀጥሉት ዓመታት ግን እያሰብን እየተዘጋጀንበት ያለ ጉዳይ ነው።
ሌሎቹ የሃይማኖት ተቋማት ናቸው። የሃይማኖት ተቋማት ከዘላቂ ሰላም ግንባታ አኳያ በጣም ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ተቋማት በመሆናቸው አብረናቸው እንሠራለን።
ብዙ ጊዜ ደጋግመን እንደምንናገረው ሰላም ከእያንዳንዱ ሰው ነው የሚጀምረው። ብዙ ጊዜ እዚህ ላይ ያለው የግንዛቤ ችግር አለ። ሰው ሰላምን በጣም ይፈልጋል፤ ሰላምን የሚጠላ ያለ አይመስለኝም ፤ሁሉም አካል ሰላም ይፈልጋል፤ ግን ሰላሙን እንዴት ነው የሚያመጣው? ሰላም ከየት ነው የሚጀምረው? የሚለው ላይ ግን ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት ይስተዋላል።
አብዛኛው ሰው ሰላምን የሚጠብቀው ከሌላ አካል ነው። ነገር ግን በትክክለኛው ነገር ከታየ ወይም ከተመዘነ ሰላም ከእያንዳንዱ ሰው ነው የሚጀመረው። ለምሳሌ ሰው ለራሱ ሰላም ካለው ለቤተሰቡም፤ ለጎረቤቱም ሰላም ምክንያት ነው የሚሆነው እንጂ ለግጭት ለፀብ ምክንያት አይሆንም።
ስለዚህ ከእያንዳንዱ ሰው ጀምሮ ሰው ከራሱ ጋር እንዲታረቅ ፣ ከፈጣሪው ጋር እንዲታረቅ ፣ የራሱ የውስጥ ሰላም እንዲኖረው ማድረግ ላይ የሃይማኖት ተቋማት ቁልፍ ሥራ መሥራት ይችላሉ፤ በጣም ትልቅ ሚናም አላቸው።
እንደሚታወቀው በኛ ሀገር አብዛኛው ሰው አማኝ ነው። የተለያየ ሃይማኖት ቢከተልም፣ ዞሮ ዞሮ በፈጣሪው ያምናል፤ ፈጣሪውን ይፈራል፤ ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎች የሃይማኖት ሥርዓቱ የሚያዘውን ነገር ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው። ከኢትዮጵያ አኳያ በዚህ ረገድ እድለኞች ነን ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ከሞላ ጎደል ሁሉም ማህበረሰብ እምነት ያለው እና ጠንካራ መንፈሳዊ ህይወት ያለው ነው። እዚህ ላይ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅርበት እንሠራለን።
የሃይማኖት ተቋማት በውስጣቸው ያሉ ችግሮችን በራሳቸው እንዲፈቱ እንደገና ደግሞ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር ጤናማ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከመንግሥት ጋር ባላቸው ግንኙነት መንግሥት ከእነሱ በሚፈልገው አገልግሎት ወይም ደግሞ ከሚፈልገው አኳያ እነሱም ደግሞ ከመንግሥት ከሚፈልጉት አገልግሎት አኳያ በጋራ በተናበበ ሁኔታ እንዲሠሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።
ስለዚህ እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ባለፉት ስድስት ወራት ከትልልቅ የእምነቱ አባቶች ጀምሮ በየደረጃው ካሉ በተለይ ደግሞ ከሃይማኖት ምሁራን ጋር በጣም ጠንካራ ሥራ ለመሥራት ተሞክሯል። በየሃይማኖቱ ምሁራን አሉ፤ የዛን ቤተ እምነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያውቁ የሚያስተምሩ የሚተነትኑ ፣ አስተማሪዎች ሰባኪያን እና የተለያየ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች አሉ፤ ከእነዚህ ጋር ጠንካራ ውይይቶች ስናደርግ ቆይተናል። መጨረሻ ላይ ሰነድም ማዘጋጀት ተችሏል።
የሁሉም የሃይማኖት ምሁራን በጋራ ሆነው በሰላም ዙሪያ እንዴት አብረን እንሠራለን? እንዴት ሰላምን የጋራ አጀንዳ እናደርጋለን? በየራሳችን አስተምህሮ ሰላምን እንዴት አድርገን የማስተማሪያ ትኩረታችን አድርገን እንወስዳለን? የሚሉትን በጋራ ቁጭ ብለው ሰነዶች አዘጋጅተው ማሰልጠኛ የሚሆኑ ማቴሪያሎችን አዘጋጅተዋል። ስለዚህ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የምንሠራቸው ሥራዎች ጠንካራ ሰላም ከመገንባት አኳያ ባለፉት ስድስት ወራት በጣም ጥሩ የሚባል ውጤት የተገኘባቸው ናቸው። ግን ይቀራል።
ገና ብዙ ሥራ ይፈልጋል። የሆነው ሆኖ በ6 ወር ውስጥ አንዱ ትኩረት አድርገን የሠራንበት ጉዳይ ይሄ ነው ማለት ይቻላል። ከዘላቂ ሰላም ግንባታ አኳያ እነዚህን ነው ባለፉት 6 ወራት ትኩረት አድርገን የሠራነው። ከሀገር ግንባታ አኳያ ያከናወናቸው መሠረታዊ የሚባሉ ተግባራት አንዱ የልሂቃን ውይይት ነው። እንደሚታወቀው እዚህ ሀገር በሰላም መታጣትም ሆነ በሰላም ግንባታ ላይ ልሂቃን ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ አላቸው።
በሀገር ግንባታ ላይም የሊሂቃን ተጽእኖ በጣም ከባድ ነው። ልሂቃን ሲባል የፖለቲካ ሊሂቃን፣ በትምህርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ልሂቃን አሉ። የማህበረሰብ መሪዎች አሉ፣ የሲቪል ማህበራት መሪዎች አሉ። ዞሮ ዞሮ ሊሂቃን ሲባል በዲግሪ ወይም ሌላ የትምህርት ደረጃ ያለው ማለት አይደለም። በየኅብረተሰቡ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ማለት ነው።
ስለዚህ ከእነዚህ ሊሂቃን ጋር በሀገር ግንባታ ላይ በጣም ትኩረት አድርገን ሠርተናል። በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ማዕከል ያደረጉ ትልልቅ ንቅናቄዎችን ሥንሠራ ነው የቆየነው። ለምሳሌ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በሀገር ግንባታ ላይ የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፋፊ ውይይቶች ተደርገዋል።
በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሀገር ደረጃም ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራን የተሳተፉበት በመድረኮች እየተከፈቱ ውይይቶች ተደርገዋል። በቅርብ ጊዜ እንኳን ባለፉት ሁለት ወራት የዓድዋ ድልን ታሳቢ በማድረግ ዓድዋን ለጠንካራ ሰላምና ለሀገር ግንባታ በሚል ሰፋፊ ውይይቶች ከምሁራን ጋር ስናካሂድ ነው የቆየነው። ከሞላ ጎደል በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ውይይት ሲያደርግበት ነው የቆየው።
ምንድነው የዓድዋ ትሩፋት? አባቶቻችን በጋራ አንድ ሆነው ተባብረው ልዩነቶቻቸውን ወደጎን አቆይተው በመጣባቸው አደጋ ላይ እንዴት አድርገው ነው? ድል የተቀዳጁትና ለዚህ ትውልድ ይህንን ሀገር ማሸጋገር የቻሉት? ከዛስ ይሄ ትውልድ ምን ይማራል? በዚህ ላይስ ምሁራን ምን ይጠበቅባቸዋል? በሚለው ላይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሰፋፊ ውይይት ሲያደርጉ ነው የቆዩት።
ይሄ አንዱ ከልሂቃን መካከል የዩኒቨርሲቲው የጎላ ስለሆነ ተነሳ እንጂ በሌሎች ሲቪል ማህበራትም በኪነጥበቡም ሌሎችም ዘርፎች ላይ ያሉ አካላት ሲወያዩበት ቆይተው በመጨረሻ ላይ ማጠቃለያውን በዓድዋ ዋዜማ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተወጣጡ አካላት አድርገን ነበር። ይሄ ንቅናቄ በሀገር ግንባታው ላይ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለማገዝ የሚያስችል ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።
ሌላው በ6 ወር ውስጥ በትኩረት የተሠራው ወጣቶቹ ላይ ነው፤ ሀገር ግንባታን ስናስብ ያለ ወጣቶች የነቃ እንቅስቃሴ ሀገርን መገንባት የሚታሰብ አይደለም። የዛሬ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ላይ ሚና አላቸው፤ ነገ የሀገር ተረካቢዎቹ እነሱ ናቸው። ስለዚህም እነዚህ ሚናቸውን በትክክል እንዲያውቁና እንዲገነዘቡ እንዴት ዓይነት ጠንካራ ሀገር ይኑረን? የምንመኛት ኢትዮጵያ ምን ዓይነት እንድትሆን ነው የምናስበው? እውን ለማድረግስ ወጣቱ ምን ይጠበቅበታል? ከዚህ አኳያ የወጣቶች ሚና ምን ይሆናል? የሚለውን ዶክመንቶች ተዘጋጅተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በቅንጅት ሆነን ወጣቶቹንም ለማነቃነቅ በዚህ 6 ወር ውስጥ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል። ጥሩ የሚባሉ ውጤቶችም የተገኙበት ነበር ማለት ይቻላል።
ከእነዚሁ ወጣቶች ጋር አንድ በጣም ቁልፍ ነገር ከሀገር ግንባታ ጋር በተያያዘ እየሠራን ያለነው የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚባልና በዚሁ ሰላም ሚኒስቴር በኩል የሚሠራ ሥራ ነው። በጎ ፍቃድ በሁሉም ተቋማት ይሠራል፤ መሠራትም አለበት። ሁሉም ነገር በመንግሥት በጀትና ወጪ የሚሠራ ስላልሆነ ወጣቶች ወይም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በነፃ ፍቃዱ፣ ጉልበቱና እውቀቱ አስተዋፅኦ በማድረግ በሀገር ግንባታ ላይ ይሳተፋል።
ይህን ለየት የሚያደርገው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች ይመለመላሉ። ከዛ አንድ ወር ስልጠና ይሰጣቸዋል። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብተው ነው ስልጠና የሚወስዱት። በአብዛኛውም የህይወት ተሞክሮ እንዲማሩና የሰላም አምባሳደር ሆነው በሀገር ግንባታው ላይ የአብሮነትና የተለያየ ልምድ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚሠራ ነው።
ስልጠናውን ለአንድ ወር ከወሰዱ በኋላ ከመጡበት ክልል ውጪ ባሉት ሌሎች ክልሎች ላይ እንዲሰማሩ ይደረጋል። ለምሳሌ ከሶማሌ ክልል ተመልምሎ የመጣ ወጣት የአንድ ወር ስልጠና ከወሰደ በኋላ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሌላ ክልል ላይ ይመደባል። ወይ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር ወዘተ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ ከሁሉም ክልሎች የመጡ ወጣቶች ለስደስት ወራት ሌላ ክልል ሄደው እንዲሠሩ ይደረጋል።
በዚህ ጊዜ የሚያገኙት ጥቅም የሌላውን አካባቢ ማህበረሰብ ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች ነገሮችን በጥልቀት እንዲገነዘቡ እድል ይሰጣቸዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርበው ብዙ ነገሮችን ተምረው ይመለሳሉ። ወጣቶቹ ከዩኒቨርሲቲ ወጥተው ወደተመደቡበት ክልል ከሄዱና ከተመለሱ በኋላ የተፈጠረባቸውን ስሜት ለማወቅ ጥናቶችም ተደርገው ነበር። የበጎ ፍቃድ ስምሪቱን ከጨረሱ በኋላ አንዳንዶቹ ኑሮ መስርተው እዛው ክልል የቀሩ አሉ። ይህ የኅብረተሰቡን አንድነት በማጠናከር ረገድ ትልቅ ውጤት የተገኘበት ነው። ምክንያቱም ፖለቲካው ወጣቶቹ ሲያድጉ እየተሞሉ ያደጉት ነገር ሌላውን አካል ሳያውቁ አሉታዊ በሆነ ነገር እየተሞሉ የማደግ ሁኔታ ነበር። ያ የፖለቲካ ውጤት ነው።
እውነተኛው ነገር መሬት ላይ ምን ይመስላል? የሚለውን ወደ ሌሎች ክልሎች ሄደው እንዲያዩ በማድረግ የሚሠራ ሥራ ነው። እንዲህ አይነት ነገሮች ከባለፈው ስድስት ወር ጀምሮ እስካሁን ወደ 50 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በዚህ ፕሮግራም ተሳትፈዋል። ባለፉት ወራትም እንደዚሁ ወደ ሰባት ስምንት ሺህ ያህል ወጣቶች ተሳትፈዋል። ይሄ ይቀጥላል። ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ማለት ነው። ከሀገር ግንባታ አኳያ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወነው ይሄኛውን ነው።
ከፌደራሊዝም አኳያ ሁለት ነገሮች ላይ ነው ትኩረት አድርገን የሠራነው። አንደኛው ቅድም እንዳልኩት የክልል ግንኙነቱ የተጠናከረ እንዲሆን የማድረግ ሥራ ነው። በርካታ ፎረሞችን አቋቁሙናል። ለምሳሌ አጎራባች የሆኑ ሁለት ወይም ሦስት ክልሎች አንድ ላይ ፎረም ይኖራቸዋል፤ አመራሮች በጋራ የሚሳተፉበት ማለት ነው። ፎረሙ ጽ/ቤት አለው። ባለሙያዎች አሉ። ክልሎች በጋራ የራሳቸውን በጀት መድበው እንደሴክሬተሪ የሚያገለግላቸውን ተቋም ያቋቁማሉ።
በዚያ መሠረት በቦርደር አካባቢ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየተገናኙ ለመፍታት የሚያስችል ነው። ከዚያ የአመራር ለአመራር ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ነው። አብሮነቱ እየጠነከረ እንዲሄድና ፌዴራላዊው ሥርዓት እንዲዳብር የሚያስችል ሥራ ለመሥራት እየተሞከረ ነው። የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ደግሞ እንዲሁ በጋራ የሚወስኗቸውና በራሳቸው የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ለይተው ሕግና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ እንዲሠሩ ለማድረግ እየተደረገ ያለ ጥረት አለ። ሆኖም ብዙ ክፍተቶች አሉት በፌዴራል አፈጻጸሙ ላይ ከግንዛቤ ጀምሮ፤ በርካታ ክፍተቶች ስላሉ ያንን ሊሞላ በሚችል መልኩና እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት በዚህች ሀገር እንዲኖር፤ ተልዕኮውንና ኃላፊነቱን ለይቶ ለመሥራት እንዲችል የሚያስችል ተግባር ለማከናወን ተሞክሯል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ነገር ለማምጣት እየተሞከረ ነው ያለው። የሚያበረታታ ውጤት ነው እየታየበትም ያለው።
ሌላው የመጨረሻውና አራተኛው ግጭት የመከላከሉ ላይ ነው። የግጭት መከላከሉ እሱን ለማጠናከር እንደ ቁልፍ ሥራ አድርገን የምንሠራው የቅደመ ማስጠንቀቂያና የፈጣን ምላሽ ሥርዓት የዘመነ እንዲሆን ማድረግ ነው።
ይሄን አሁን በቴክኖሎጂ ወደ ተደገፈ ዘመናዊ አሠራር እንቀይረው በሚል የሁኔታ መተንተኛ ክፍል ( Situation rooms) ማዘጋጀት ተችሏል። በላዕላይ መዋቅር ደረጃ (በሄድ ኳርተር ደረጃ) እዚህ ሰላም ሚኒስቴር ላይ አንድ ትልቅ የሁኔታ መተንተኛ ክፍል አለ፤ በየክልሎችም ይሄው ሁኔታ መተንተኛ ክፍል አለ፤ አንዳንድ ክልሎች ገና በመጠናከር ላይ ቢሆኑም አንድ ክልል ላይ ግን ተጠናክሮ ይገኛል።
በዚህ አሠራር መሠረት ባለሙያዎች (ዳታ ኢንኮደሮች) አሉ። በአካባቢው የሚያዩትን የፀጥታ ችግር ወይም ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ የሚሏቸውን ነገሮች ዳታውን ኢንኮድ ያደርጋሉ፤ እናም እዚህ ማዕከል ላይ ከመጣ በኋላ የመጣው መረጃ ይሰበሰብና ይተነተናል፤ ከተተነተነ በኋላ ግብረ መልስ ይሰጣል ማለት ነው።
የሆነ አካባቢ ላይ የማጣው ችግር ነገ ስጋት የሚሆን ከሆነ፤ ቀድሞ በእነማን ነው መፈታት ያለበት? የፌዴራል ተቋማት ናቸው ይህንን መፍታት ያለባቸው? ወይስ የክልሉ መንግሥት ነው? ወይስ አካባቢው ( ሎካል ) አስተዳደር ነው? የወረዳ ፣ የዞን ወይም ቀበሌ አመራሮች ናቸው የሚፈቱት? የሚለው ከተለየ በኋላ ግብረ መልስ እንዲሰጣቸው ይደረጋል ማለት ነው።
ስለዚህ የፌዴራል ተቋማት ሆነ ተቋም ከሆነ ለምሳሌ የፌዴራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ከሆነ የሚከታተለው ወይም ከልማትና ከሀብት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሆነ ተቋም ከሆነ የሚመለከተው፤ እነዚያ የሚመለከታቸው ተቋማት ቀድመው መረጃው ከደረሳቸው ቶሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ፤ ወደ ብጥብጥና ሁከት ከመሸጋገሩ በፊት እዚያው ላይ እንዲቆም የሚያስችል ሥርዓት እንዲኖረን ጥረት እያደረግን ነው።
ነገር ግን ገና ብዙ ይቀረዋል። ለወደፊት በጣም መጠናከር አለበት፤ ተደራሽነቱም በጣም መስፋት አለበት፤ አሁን በጅምር ላይ ያለና ገና እየተጠናከረ ያለ ነው። ለሚቀጥለው ጊዜ ግን እዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን በሚል እየሠራን ነው።
ግጭቶች ሲከሰቱ የፌዴሬሽን ሥራውን አምልጠው የሚከሰቱ ግጭቶች ካሉ ግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትል በተቻለ መጠን ለመከላከል ወይም ለማስቆም ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን ሥራዎች እንዲሠሩ ይደረጋል ማለት ነው።
ሌላኛው በድህረ ግጭት (ፖስት ኮንፍሊክት) ብዬ ቅድም ያነሳሁት ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ጉዳት ይደርሳል፤ የጉዳቱ መጠን ከቦታ ቦታ ከሁኔታ ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም፤ የዜጎች የህይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ ከቦታቸው የመፈናቀል፣ ንብረታቸውን የማጣት እንዲህ እንዲህ አይነት ነገሮች ይፈጠራሉ። ስለዚህ በተቻለ መጠን በተለይ የተፈናቀሉትን ሰዎች መልሶ ወደ ነበሩበት ቦታ ለመመለስ ጥረት ተደርጓል።
ባለፉት ስድስት ወራት አንዱ ትኩረት ተደርጎ የተሠራው ከቀያቸው ተፈናቅለው በየክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ ለየት ያለ ትኩረት ተሰጥቶት በሀገር ደረጃ እየተሠራ ነው። አሁን ክልሎች የጋራ ኮሚቴ እያቋቋሙ እየሠሩ ነው።
ለምሳሌ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በእነዚህ ሁለት ክልሎች በርካታ የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ። ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ የአማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰቦች ሁነው ተፈናቅለው አማራ ክልል ያሉ አሉ። እዛውም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተለያየ አካባቢ ላይ ያሉ አሉ። የኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑ እዛው ኦሮሚያ ውስጥ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ ተፈናቅለው ያሉ ዜጎች አሉ። እነዚህን ዜጎች ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሁለቱ ክልሎች ከፌዴራል ተቋማት ጋር (የሰላም ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት መከላከል ሥራ አመራር ኮሚሽን እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት) የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ፤ በዚህ ግብረ ኃይል አማካኝነት ዜጎች ወደ ነበሩበት አካባቢ፤ በተለይ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ነው የሚባለው፤ የተፈናቀሉበት አካባቢ ላይ ሰላሙን የማረጋገጥና የማረጋጋት ሥራ በተሠራባቸውና አስተማማኝ ናቸው በሚባሉ ቦታዎች እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ያለው።
በቅርቡም ከአንድ ሁለት ሶስት ሳምንት በፊት ከአማራ ክልል ወደ አንድ ሺህ 600 አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ተመልሰዋል። ሌሎችም ይቀጥላሉ። ሥራው እየቀጠለ ነው ያለው፤ በዚህ ዓመት ትርጉም ባለው ደረጃ አብዛኛውን ተፈናቃይ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ጥረት ይደረጋል። ምን አልባት የተፈናቀሉበት ቦታ የጸጥታ ሁኔታ “አሁንም አስተማማኝ” አይደለም። አሁንም ትንሽ ይቆዩ የሚባል ነገር ከሌለ በስተቀር የተሻለ ሰላም ተፈጥሮባቸዋል በሚባሉት ቦታዎች ላይ ግን ሁሉንም ተፈናቃዮች ወደዛ ለመመለስ፤ ከተፈናቃዮቹ ጋርም ውይይት እየተደረገ እየተሠራ ነው ያለው።
በሌሎች አካባቢዎችም እንደዚሁ ለምሳሌ ያህል ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በጣም በርካታ ተፈናቃይ የነበረበት ክልል ነው። ይህ ክልል አሁን አብዛኛውን ተፈናቃይ ከ475 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን (በእርግጥ ይህ ቁጥር የዚህ ስድስት ወር ብቻ አይደለም፤ ባለፈውም ዓመት ጀምሮ የሠራው ሥራ ነው) 19 እና 20 ሺህ ከሚሆኑት በስተቀር ሌሎቹ ወደ ክልሉ ተመልሰዋል። ጋምቤላ ላይ እንደዚሁ የመመለስ ሥራ እየተሠራ ነው።
በነገራችን ላይ እንደ ሀገር የተፈናቀሉትን ስናይ 70 በመቶ የሚሆነው በግጭት የተፈናቀለ ነው። ምክንያቱ ግጭት ነው። በተፈጥሮ አደጋ ለአብነት በድርቅ፣ በጎርፍ በመሳሰሉ የተፈናቀሉ 30 በመቶ ናቸው።
ስለዚህ እነዚህን ዜጎች ወደ ቀያቸው ለማስመለስ ከላይ በገለጽኩት መንገድ ጋምቤላም በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። አብዛኞቹም ተፈናቃዮች በተለይ በውሃ ሙላትና በጎርፍ በመሳሰሉት ነገር ተፈናቅለው የነበሩት ተመልሰዋል።
ደቡብ ምዕራብ በርካታ ተፈናቃይ የነበረበት አካባቢ ነው። በተለይ ትልቅ የጸጥታ ችግር የነበረባቸው እንደእነ ሚዛን ቴፒ፤ ቤንች ሸኮ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ግጭት የነበረበት ስፍራ ነው። እዚያ አካባቢ የነበሩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ክልል ነው። አሁንም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዜሮ ሊባል በሚችል መልኩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ የቻለ ክልል ነው። በሌሎች አካባቢዎችም እንደዚህ እያልን ልናየው የምንችለው ነው።
በዚህ ስድስት ወራት ወደ 111 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ይህ ሥራ በጣም ፈታኝ ነው። ብዙ ምክንያቶች አሉበት። አንደኛው የተፈናቀሉበት አካባቢ አሁን ሰላም እንዲሆን ማድረግ ያስፈልገዋል። ግጭት በተፈጠረበት ወቅት የወደሙ ንብረቶች ቤት፤ ተቋማት ለምሳሌ እንደ ጤና ተቋም፤ የትምህርት ተቋም፤ የውሃ ተቋማት የመሳሰሉት ጉዳት የደረሰባቸው አሉና እነርሱን እንደገና የመጠገን፤ በሚመለሱበት ጊዜ ችግር ሳይፈጠር ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ፤ የእርሻ ሥራቸው እንዲቀጥል ለማድረግ የተለያየ ግብዓት ይፈልጋሉ። ይህንን ማሟላት ፤ ሄደው ደግሞ አምርተው ምርት ማግኘት እስኪጀምሩ ድረስ ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ይህንን ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረብ ሥራዎች ሁሉ አሉ።
በዚያ ላይ ደግሞ ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ የሚሠራም አካል አለ። አንዳንድ ጊዜ ግራ የሚያጋባ ነው። ሰዎች ሲፈናቀሉ ዜጎች ተፈናቀሉ ብሎ ሚዲያውም የተለያዩ አካላትም ከፍተኛ ጩኸት ያሰማሉ። ይህ ጥሩ ነው። ነገር ግን ሊመለሱ ነው ተብሎ እንቅስቃሴ ሲጀመር ግን መልሰው እነዚያው አካላት፤ መልሰው እነዚያው ሚዲያዎች እንዳይመለሱ ደግሞ ቅስቀሳ ያደርጋሉ። እናም የሆነ የፖለቲካ ገበያ ጭምር አድርጎ የመጠቀም እንቅስቃሴ አለ።
በተፈናቃዮቹ ስም ያልተገባ ጥቅም የማግኘት ወይም ደግሞ በእነርሱ የመነገድ ፍላጎት አለ። ይህ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል አይወክልም። ጥቂት የሚዲያ ተቋማትና ጥቂት ግለሰቦች በዚህ ደረጃ ሥራውን ለማደናቀፍ ጥረት የሚያደርጉ አካላት አሉ። ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ ነው የማስመለስ ሥራው እየተሠራ ያለው። ቅድም የዘረዘርኳቸውን ተግባራት በማከናወን ማለት ነው። ይህንን ትኩረት ሰጥተንም እየሠራን ነው ያለነው።
ከዚሁ ጋር እርቀ ሰላም የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ፡- ጋምቤላ ከዚህ አኳያ የሠራው ሥራ ትልቅ ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚችል ነው። ሰላም ሚኒስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ በመቀናጀት ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች /ግጭቱ በማህበረሰብ ደረጃ እንዲወርድ ተደርጎ ስለነበር በብሔር ፣በጎሳ /ልዩነቶች እንዲፈጠሩና ግጭቱ ወደ ማህበረሰብ እንዲወርድ የማድረግ ሥራ ተሠርቶ ስለነበር ያንን የማቀራረብና እርቅ የመፈፀም ሥራ እየተሠራ ነው ያለው።
በቅርብ ጊዜ በአፋርና በሱማሌ ክልሎች ድንበር አካባቢ የነበሩ ችግሮች ላይ በሃይማኖት ተቋማትም ጭምር የእርቀ ሰላምና የመግባባት ሥራዎች እንዲሠሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። እነዚህ ከግጭት በኋላ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው። ባለፉት ስድስት ወራት ትኩረት አድርገን እየሠራንበት ያለ ጉዳይ ነው።
ጥያቄ፡- ግጭቶችን ለመፍታት የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም ድረስ ግን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የፀጥታ ስጋቶች አሉ። የሰላም ሚኒስቴር አሁን ያለውን የሰላም ሁኔታ እንዴት ይገመግመዋል?
አቶ ብናልፍ አንዷለም፡- በቅርቡ የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸም በሚኒስቴሮች ምክር ቤት አጠቃላይ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ ግምገማ ተካሂዶ ነበር።አሁን ያለው የሀገሪቱ ሁኔታ በአብዛኛው ክልሎች ተነጻጻሪ ሰላም አላቸው።
ለምሳሌ በምሥራቁ ቀጣና ላይ ያሉትን የአፋር፣ሱማሌ፣ሀረሪ፣ድሬዳዋ አካባቢዎችን ብንወስዳቸው ከሞላ ጎደል የተረጋጋ ሰላም አላቸው። አንጻራዊ ሰላም የምንልበት ምክንያት ምንድነው ዘላቂ የሰላም ግንባታው ገና ከዚህ በላይ ጥረት የሚጠይቅ ወደ ኋላ የማይል የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠርን ስለሚጠይቅ ነው።
እነዚህ አካባቢዎች በጣም የተረጋጋ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡባቸው ፤ሠርተው የሚኖሩባቸው፤ ግጭት የማይታይባቸው አካባቢዎች ተብለው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው።
በተመሳሳይ በምዕራቡም አካባቢ ቅድም የጠቀስኩት የቤኒሻንጉል፣ጋምቤላ፣ደቡብ ምዕራብ ትልልቅ ችግሮች የነበሩባቸው ክልሎች ናቸው። በእነዚህ ክልሎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች ነበሩ። የታጠቁ ኃይሎች ከመንግሥትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በሚፈጥሩት ግጭት ምክንያት በጣም ብዙ ጉዳት ሲያደርስ ነው የቆየው።
ቤኒሻንጉል በክልሉ ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር የፌዴራል ተቋማት እገዛ እንዳለ ሆኖ ተከታታይነት ያለው ውይይት ድርድር በማድረግ ታጣቂዎቹ ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ እና ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ ሠርተዋል። ይሄ ትልቅ ውጤት ነው። ያኔ ሰዎች በጅምላ ይገደሉበት፣ሲፈናቀሉበት የነበረ ክልል አሁን ከዛ እየወጣ ነው ያለው።ከዛ ወቶ አንጻራዊ የሰላም ሁኔታን ለመፍጠር የቻለ እና በጣም ጥሩ ለውጥ ያመጣ ክልል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ይህ ማለት ስጋት የለም ነገ ሊያገረሹ የሚችሉ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። ዋናው ቀጥሎ የሚሠራው ተከታይ ሥራ ነው።
በተመሳሳይ ጋምቤላም እንደዚሁ የታጠቁ ኃይሎች ሲንቀሳቀሱበት የነበረ ክልል ነው። የጋምቤላ ክልልም ልክ እንደ ቤኒሻንጉል ከታጠቁት ኃይሎች ጋር ውይይቶችን ድርድሮችን በማድረግ ትጥቃቸውን እያወለቁ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴቸው እንዲመለሱ ሠርቷል።አሁንም ጋምቤላ የተረጋጋ አንጻራዊ ሰላም እየተገኘበት ያለ ክልል ነው።
ደቡብ ምዕራብም ቅድም እንደጠቀስኩት ነው። በሽፍትነት፣በተለያዩ ሁኔታ መንገድ ሲዘጉ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሲያውኩ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎችን በአንድ በኩል ሕግን በማስከበር በሌላ በኩል ከእነዚህ አካላት ጋር ውይይትና ድርድር በማድረግ ወደ ሰላም እንዲመለሱ በማድረግ ደቡብ ምዕራብ አሁን በሀገሪቱ በጣም የተሻለ ፣ የተረጋጋ መሆን የቻለ ክልል ነው።
ደቡቡንና መሀሉን ብናየው የተረጋጋ ሰላም ያለባቸው ክልሎች ናቸው። ደቡብ፣ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ሲዳማና እዛ አካባቢ ያሉ ክልሎች አብዛኞቹ የተረጋጋ ሰላም ያለባቸው ክልሎች ናቸው። ስለዚህ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ሲታይ አብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ሰላም ያለበት ነው። ሙሉ በሙሉ ሰላም ያለበት ሆኗል እያልኩ አይደለም አንጻራዊ ሰላም የተረጋገጠባቸው አካባቢዎች ናቸው ማለቴ ነው።
ቢያንስ ኅብረተሰቡ የሚጉላላበት ሁኔታ የለም። መስራት፣ ወጥቶ መግባት ሰላማዊ እንቅስቃሴው ማድረግ ይችላል።ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ግጭት ያለባቸው የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ናቸው።በሁሉቱ ክልሎች ግጭት አለ።እነዚህም ቢሆኑ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ነው። አሁን አማራ ከዛሬ ስድስት ወር በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁን ያለው የተሻለ ነው።
ኦሮሚያ ክልልም ከዛሬ ስድስት ወር በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር አሁን እየተሻሻለ የመጣ ነው። ይሄም ሆኖ ግን አሁንም ግጭት ጉዳት አለ ።አሁንም ያልተፈቱ ፣ሰላማቸው ያልተመለሰ፣ያልተረጋጉ አካባቢዎች አሉ።እነዚህን ደግሞ ቀጣይነት ባለበት መንገድ ጥረት ይፈልጋል። ክልል እና የፌዴራል መንግሥት በጋራ ሆነው በእነዚህ አካባቢ የቀሩ የሰላም ሁኔታዎችን መመለስ ያስፈልጋል።
ከዚህ አኳያ የሰላም ውይይቶችን፣ ድርድሮችን ማድረግ ያስፈልጋል።ከዛ ጎን ለጎን የሕግ ማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው ያለው። በተለይም የሰላም ውይይቶችንና ንግግር በማድረግ ከግጭት የወጣ ሰላማዊ በሰለጠነ መንገድ ልዩነቶችን የመፍታት አቅጣጫዎችን መከተል ያስፈልጋል ብለን እንምናለን። የተጀመሩ ድርድሮችን ማስቀጠል ያስፈልጋል።
አማራ ክልል ላይ ተደጋጋሚ ጥሪዎች እየቀረቡ ነው ያሉት፤ ያንንም ወደ ውይይቶች ማምጣትና በሰለጠነ መንገድ መነጋገርና መፍታት ድርድር እና ውይይት ይጠይቃል። ነዚህን ነገሮች ከሠራን በቀሩት አካባቢዎች ላይ ማየት ይቻላል።ትግራይም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ አሁን ቢያንስ የጦርነት የግጭት ሁኔታዎች ቆመዋል።እዛም እፎይታ አለ። አሁን ዜጎች የበፊቱ አይነት ውድመትና የጦርነት ሁኔታ ውስጥ አይደለም ያሉት።
ሰሜኑም ሲታይ አንጻራዊ ሰላም እየመጣበት ያለ ነው። እነዚህ ቅድም የጠቀስኳቸው አካባቢዎች ላይ የሰላም ሁኔታዎች አሁንም አሳሳቢ ናቸው፤ አሁንም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚጠይቅ ነገር ነው።በአጠቃላይ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ በእነዚህ መንገዶች ሊታዩ የሚገባው ነው ማለት ነው።
ጥያቄ ፡- በእናንተ ግምገማ የግጭቶች መነሻ ምክንያቶች ምንድናቸው?
አቶ ብናልፍ አንዷለም፡– አጠቃላይ የሰላም መታጣት ምክንያቶች ብዙ ናቸው። በቅርብ ጊዜ አንድ ጥናት አካሂደን ነበር።ከገለልተኛ አካላት ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት የተሳተፉበት ጥናት አድርገን ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከሰቱ ግጭቶች ምክንያታቸው ምንድን ነው የሚለውን ለማጥናት ሞክረን ነበር ።
ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው ከማንነት ጋር፣ ከወሰን፣ አስተዳደር ጥያቄ ጋር የክልልነት የዞን፣ የወረዳ ጥያቄዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ግጭቶች አሉ። በሀብት አጠቃቀም ላይ የሚነሱ ግጭቶች ያሉ ሲሆን፤ በጣም በርካታ የግጭት መንስኤዎች እንዳሉ በዝርዝር በጥናት ተለይተዋል።
አሁን ላለው የኢትዮጵያ የሰላም ማጣት ችግር ዋናው ምክንያት ፖለቲካዊ ችግር ነው። ለምሳሌ ለውጥን የምናይበትና ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግበት መንገድ ላይ በጣም የተዛነፈ ነገር አለ። እዚህ ሀገር ታሪካችንንም ከኋላ ሄደን ስናየው ብዙ ለውጦች ተካሂደዋል። ለምሳሌ የመንግሥት ለውጥ የተካሄደባቸው ለውጦች ተካሂደዋል፤ እነዚህ ለውጦች የተካሄዱት በአብዮት ነው። አብዮት ደግሞ እንደሚታወቀው የነበረውን ከመሠረቱ አጥፍቶ እንደገና በአዲስ ሀ ብሎ የመጀመር እንቅስቃሴ ነው። ልምዳችን ባህላችን በዚህ የተቃኘ ነው። ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በኃይል አማራጭ ብቻ አድርጎ ማሰብ እንደባህል እየታየ የመጣ ነው።
ይሄ የጥቂት ቡድኖች ችግር ብቻ አይደለም። ባህል ከሆነ የብዙዎቻችን ችግር ነው ማለት ነው። ስለዚህ ችግር የምንፈታበት መንገድ ውይይት ፣ንግግር በሰለጠነ አኳኋን በሃሳብ የመፍታት ሳይሆን ያለ የሌለ ነገር ተጠቅሞ በጉልበት ነገሮችን ለመቀየር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የፖለቲካ ባህላችን።
ለምሳሌ ከ1960ዎቹ የፓርቲ ፖለቲካችን አንዱ አንዱን የማጥፋት ፖለቲካ ነበር የነበረው። የርእዮተ ዓለም ልዩነት ሳይኖራቸውና ይሄነው የተባለ ልዩነት ሳይኖራቸው ትውልድ የተላለቀባቸው እንቅስቃሴዎች ነበሩ። አንዱ አንዱን የማጥፋት በቀይ ሽብር በነጭ ሽብር ፣አብዮት ፀረ አብዮተኛ እየተባለ የመተላለቅና ትውልድ መስዋዕት እስኪሆን ድረስ የነበረ እልቂት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያስተናገድነው።
ይሄ የራሳችን ታሪክ ነው። ወደእዛኛው ትውልድ ሄደን ወደእዛኛው ትውልድ ጣታችንን ለመቀሰር አይደለም። ወይም ዛሬ ያሉ ችግሮች የዛኛው ትውልድ ችግሮች ብቻ ናቸው ለማለት አይደለም ።
እንደ ባህል ሲታይ ፖለቲካችን የሃሳብ ልዩነቶችን በጠላትነት የሚያይ ነው እንጂ በሃሳብ የተለያየ መሆን ጠላትነት አይደለም።ሃሳብ ምንጊዜም የተለያየ ነው የሚሆነው፤ እኔና አንተ በአንድ ጉዳዮች ላይ ብንጠየቅ ሃሳባችን የተለያየ ሊሆን ይችላል።ይሄ ማለት እኔና አንተ ጠላት ነን ማለት አይደለም።
እንዲሁም በሰለጠነ መንገድ ካየነው የሃሳብ ልዩነት ተጨምቆ የተሻለ ሃሳብ ሊያመጣ ይችላል እንጂ ለመጠፋፋት ምክንያት መሆን የለበትም።አሁንም ድረስ በዛ መንገድ ስለመጣን ከዚህ ባህል ልንወጣ አልቻልንም። ስለሆነ ዛሬም በትጥቅ፣ በግጭትና በኃይል ሥርዓት የመቀየር ወይም ያለውን መንግሥት የማስወገድ የመሳሰሉ ያሉ ነገሮች አሁንም እየቀጠሉ ያሉ ችግሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ የሰላም መታጣት ፖለቲካው ችግር። ይሄ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችና በኅብረተሰቡ እንደዚሁም በመንግሥት የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት መካከል የሚደረጉ ግጭቶችና በዚህ ላይ የሚከፈለው ዋጋ ከፖለቲካ ባህላችን አለመቀየር ጋር የተያያዘ ተደርጎ መወሰድ የሚችል ነው።
በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ የተጠቀምንባቸው ትርክቶች የፈጠሩትም ችግር አለ። ባለፉት ጊዜያቶች የተፈጠሩትና የተጠቀምንባቸው ትርክቶች አንድም አንድነትን ማዕከል ያደረጉና ልዩነትን የማይቀበሉ ልዩነትን የሚጨፈልቁ ወደጎን የገፉ፣እንዴት ነው አንድነት የሚመጣው የሚለውን በአግባቡ ያላስተዳደሩ ናቸው።
የሃሳብ፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣የሃይማኖት ልዩነቶችን የሚያካትት አካታች የሆነ ትርክት በመገንባት በኩል እንደ ሀገር ችግር ነበረብን። ያ ያስከተለው ችግር አለ። በዚህ ምክንያት ግጭቶች በተለያየ ምክንያት ሲፈጠሩ ነው የቆዩት።
ሌላኛው ትርክት ደግሞ አንድነትን ወደ ጎን የገፋ ልዩነትን ማዕከል ያደረገ ዜጎች በልዩነት ላይ ብቻ አተኩረው እንዲሠሩ ሲቀነቀን የቆየ የፖለቲካ ትርክት አለ። ይሄ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገራችን የነበረ ትርክት ነው።
እነዚህ ሁለቱ በአንድ በኩል አንድነት በሚል ልዩነትን በመቀበልና በማስተዳደር በኩል በሚታይ ችግር፣ በሌላ በኩል አንድነትን የሚያስተሳስረንን ገመድ አንድ የሚያደርገንን ነገር ለዘመናት የገነባናቸውን እሴቶች ወደ ጎን የሚገፋ ነገር ግን ደግሞ በልዩነቶች ላይ ብቻ ያጠነጠነ በጥላቻ እንድንተያይ የሚያደርግ አይነት ትርክት ስለነበር እነዚህ ትርክቶች የፈጠሩት ችግር አሁንም ድረስ ዋጋ እያስከፈሉን ነው ያለው።ስለዚህ እነዚህ ችግሮች በዋናነት የኢትዮጵያ ሰላም ችግር ፖለቲካው ነው ስንል በመሠረታዊነት ከእነዚህ ነገሮች በመነሳት ነው።
ጥያቄ -መፍትሄውስ ምንድን ነው?
አቶ ብናልፍ አንዷለም ፡- የመጀመሪያው ነገር የፖለቲካ ባህሉን መቀየር ነው።የፖለቲካ ባህሉ ከመገዳደል ወደ መደራደር መቀየር አለበት።በዚህ ሀገር እየተገዳደልን ለዘመናት አይተነዋል።ጥሩ ታሪኮች የምንኮራባቸውና ትውልድ ሁሌ እየተቀባበለ የሚዘክራቸው ያሉንን ያህል በግጭቶች ደግሞ የከፈልነው ዋጋ እንደሀገር በጣም ከባድ ነው።
አሁን ምንም ሌላ አስተማሪ አያስፈልገንም። እኛ ኢትዮጵያውያን ከበቂ በላይ ትምህርት አለን።በየትውልድ ዘመኑ የመጣ ያየነው የቀሰምነው ፣ያነበብነው ያወቅነው ታሪክ አለን።ይሄ የመገዳደል ወይም በኃይል የመጠፋፋት መንገድ ሀገሪቱን ወደ ፊት አላራመዳትም ። ኢትዮጵያ ዛሬም ድረስ በድህነት፣ በችግር ፣በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እንድትቀጥል ነው ያደረገው እንጂ ለሀገሪቱ መፍትሄ የሚሆን ነገር አላመጣም።
ከበቂ በላይ ሞክረነዋል። ያልሞከርነውን መንገድ ማየት ነው። ያልሞከርነው መንገድ ደግሞ ውይይት ፣ድርድር፣ንግግር ነው። ይሄንን ማድረግ አለብን።
ፖለቲከኞቻችን ፣ ልሂቃኖቻችን፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ መሪዎች ወደ መነጋገርና መደራደር መምጣት አለባቸው።ይሄ ባህል በኢትዮጵያ ውስጥ ካልተፈጠረ የፈለግነውን ያህል ዛሬ ግጭት ብናስቆም ነገም ሌላ ግጭት ይቀጥላል። ይህን የፖለቲካ ባህል መቀየር ቁልፉ መፍትሄ ነው ተብሎ ይታመናልና አንዱ እዚህ ላይ ነው መሥራት ያለብን።
ሁለተኛው ትርክቱ መቀየር አለበት። አዲስ ትርክት ያስፈልገናል።የበፊቶቹ ትርክቶች ያስከተሉትን ጉዳት በአግባቡ ያየ ፣የፈተሸ ያንን ሊያርም የሚችል ትርክት ያስፈልገናል።ታዲያ አዲሱ ትርክታችን ምን መሆን ነው ያለበት? አዲስ ትርክታችን ብዝሃነትን ማዕከል ያደረገ ፣ብዝሃነትን በማቀፍ ወንድማማችነትን ፣እህትማማችነትን፣አብሮነትን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት።መዳረሻው ደግሞ አንድነታችንን የሚያጠናክር መሆን አለበት ማለት ነው።ይሄ አንድነታችን ኢትዮጵያዊነታችን ነው ማለት ነው።አንድ የሆነች የሁላችንም ሀገር ሁላችንንም የምታቅፍ ፣ለሁላችንም የምትመች፣ ሀገር መፍጠር ነው። ሁላችንም ሌላ ሀገር የለንም ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት።ይችን ሀገር መጠበቅ መገንባት ያስፈልጋል የሚለው ላይ ብሔራዊ መግባባት እየፈጠሩ መሄድ ያስፈልጋል።
በመሠረታዊነት በሦስት ነገሮች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለብን ብለን እየሠራን ነው። አንደኛ በሀገራዊ ጥቅሞቻችን ላይ በሀገራችን ጥቅም ላይ በፍጹም መለያየት የለብንም። ምንም አይነት ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ፤ በሀገራችን ጉዳይ ላይ ግን አንድ መሆን አለብን።
እይታችን፣ አስተሳሰባችን፣ የፖለቲካ ፓርቲያችን ፣እምነታችን፣አካባቢያችን፣ጾታችን የተለያዩ ሊሆን ይችላል። ግን ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር ጥቅም ላይ አንድ መሆን ይኖርብናል።በሀገራዊ ጥቅማችን ላይ ከተለያየን ሀገር ግንባታ የሚባል ነገር አይሠራም።ስለዚህ እዚህ ላይ መግባባት ይኖርብናል።ዛሬ የምንነታረክባቸው በጣም ብዙ ጉዳዮች አሉ።ለምሳሌ በሕገ መንግሥት ጉዳይ፣ በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ፣በተለያዩ አይነት ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች አሉን። እነዚህ ልዩነቶች መፈታት፤ መቋጨት አለባቸው። የሚቋጩት ደግሞ ብሔራዊ መግባባት መገንባት ሲቻል እና የጋራ በምንለው ሀገር ላይ የጋራ አቋም ሲኖረን ነው።
ሕገ መንግሥትን የሠራው ሰው ነው። በማንኛውም ጊዜ እንደማንኛውም ሀገር ሕገ መንግሥት ሊሻሻል ሊለወጥ ይችላል።ሕገ መንግሥት ከነካችሁ በህልውናዬ ነው የመጣችሁ የሚባል ነገር አይሠራም።በጣም ኋላ ቀርና በየትም ሀገር የሌለ ነው። የኅብረተሰብ እድገት ተለዋዋጭ ነው።ኅብረተሰብ ይቀየራል። ትናንት የነበረውና ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ይለያያል።ለዛሬ ኢትዮጵያን የሚመጥን ነገር ያስፈልገናል የሚሻሻለው ነገር መሻሻል አለበት።
ሕገ መንግሥት ቀዳችሁ ጣሉ የሚልም ሌላ ጫፍ አለ። ሕገ መንግሥት ቀደህ በመጣል የሀገር ችግር አይፈታም።ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ጠቃሚ መሆን የሚችሉ ሁልጊዜ ሊቀጥሉ የሚችሉ ጉዳዮች ይኖራሉ። ለምሳሌ ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣አያያዝ፣ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት እነዚህ መብቶች መቼም ቢሆን የሚቀጥሉ መብቶች ናቸው።
ዋናው ነገር ሊሻሻል የሚችል ነው። የትኛው አንቀጽ የትኛው ሃሳብ መሻሻል ይኖርበታል፤ መለወጥ ይኖርበታል፤ ምን ደግሞ አዲስ ሃሳብ ሊካተትበት ይገባል የሚለው መለየት አለበት።
አሁን ከደረስንበት የእድገት ደረጃ አዲስ ልናስገባቸው የምንችል ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ብዝሃ ቋንቋ ይኑረን ብለን እናስባለን። የሥራ ቋንቋዎች አራትና አምስት ቋንቋዎች መሆን ይችላሉ፤ ይህ የትም ሀገር አለ። አንድነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳዮች ምንድናቸው? ሕገ መንግሥት ውስጥ አብሮነታችንን የሚያውኩ የሚከለክሉ ወይም እንዳንሆን የሚያደርጉ ነገሮች ምንድናቸው? እነሱ በጥናት ተለይቶ እዛ ላይ ውይይት ተደርጎ በምንግባባቸው ጉዳዮች ላይ ተግባብተን እንቋጫቸዋለን ።
የማንግባባቸው ጉዳዮች ካሉ ደግሞ ወደ ሕዝብ ይሄዳል፤ ሪፈረንደም ይደረግባቸዋል፤ ሕዝቡ ድምጽ ይሰጥባቸዋል ይወሰናል። ሕዝቡ የወሰነውን ማንም የመቀበል ግዴታ ይኖርበታል ያንን ይይዛል ልዩነቶችን መፍታት እንችላለን። በአጠቃላይ ሀገራዊ ጥቅማችን ላይ ያሉንን ልዩነቶች ወይም ደግሞ በሀገራችን አጠቃላይ ጉዳይ ላይ ያልተግባባንባቸው ጉዳይ ላይ እያሻሻልን እንዲሄድ የተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዝግጅቱን ከሞላ ጉደል እያጠናቀቀ ይመስለኛል። ይህ ወደ ተግባር ሲለወጥ ችግሮቻችን በሙሉ ይቀረፋሉ የሚል እምነት አለኝ።
ስለዚህ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን እያረጋገጥን መሄድ ይገባናል። አንዱ እዚህ ሀገር ያለ ትልቅ ችግር መንግሥትና ሀገርን ነጣጥሎ ያለማየት ችግር ነው። መንግሥት በምርጫ የሚመረጥ ከሆነ ዓመት ላይ ምናልባት በኢትዮጵያ ለምሳሌ በየአምስት ዓመቱ ሌላ ሀገር ላይ በአራትም በአምስትም ዓመት የሚመረጥ ነው። በምርጫ የሚቀየር ነው መንግሥት። ስለዚህ መንግሥት ዘላለማዊ አይደለም ፤ ቋሚ አይደለም።
የመንግሥት አወቃቀር ሊተች ይችላል፤ ጥንካሬ ይኖረዋል ድክመት ይኖረዋል። በድክመቱ ላይ ሊተች ይገባል፤ በጥንካሬው ላይ ደግሞ ይሄን አጠናክራችሁ ቀጥሉ በማለት ሊበረታታ ይገባዋል ።
የሚቀጥለው ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ ደግሞ ሕዝቡ ካልፈለገው አሁን ያለውን መንግሥታዊ ሥርዓት አልጠቀመኝም ካለ በምርጫ ይቀየራል ማለት ነው። ስለዚህ መንግሥት ተቀያያሪ ነው ማለት ነው። ስቴት የሚባለው ወይም ሀገር የሚባለውን ግን መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር አይደለም። ሀገር እስካለ ፣ዜጎች እስካሉ ድረስ ፣ሕዝብ እስካለ ድረስ የሚቀጥል ነገር ነው።
ያለውን መንግሥት ስለጠላሁና ባለው መንግሥት ላይ ተቃውሞ ስላለኝ ግን ሀገሬን ማፍረስ የለብኝም።ብሔራዊ ጥቅም ስንል እሱን ማለታችን ነው ።
ሌላው የጋራ ማንነታችን ጉዳይ ላይ ነው ። የጋራ ማንነታችን ላይ ወይም ኢትዮጵያዊነታችን ላይ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር ያለበት። ሁሉም ዝም ብሎ ባኮረፈ ቁጥር ኢትዮጵያ ለኔ ምኔ ናት የሚል ከሆነ አደጋ አለው። ሲመቸው ኢትዮጵያዊ ነኝ ሳይመቸው ኢትዮጵያ ለኔ ምኔ ናት የሚል ከሆነ አግባብ አይደለም። በቅርብ ጊዜ ያየናቸው ምልክቶች ያንን የሚያሳዩ ናቸው።
እኛ እስከገዛን ድረስ እኛ ስልጣኑ እስካለን ድረስ እኛ ምንፈልገው ነገር ሲሳካ ኢትዮጵያ የምትባለውን እንፈልጋታለን እኛ የማንፈልጋው ነገር ሲመጣ ወይም ደግሞ ሌላ መንግሥት ሲመጣ ኢትዮጵያ ለኔ ምኔ ናት የሚለው አባባል ቅቡልነት የለውም። ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር ናት ብለን ፤ ይልቁንም የሚጎድል ነገር በጋራ እየሞላን መሄድ አለብን።
ይህ የትውልድን ግንባታ ይጠይቃል።የትውልድ ግንባታ የሚባለው ከዚህ ጋር የሚመጣ ነው። ትውልዱን ከታች ጀምሮ በሀገሩ ጉዳይ ላይ በጋራ ማንነቱ ላይ ማነጽ ያስፈልጋል። ይህ ማለት የራሱ ማንነት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
ስለዚህ የጋራ ማንነት ላይ ወይም ብሔራዊነት ላይ ማንነታችን ላይ የማይደራደር ትውልድ መፈጠር አለበት። ሀገራዊ መንግሥት ግንባታ ገና ሥራ ይጠብቃል የሚባለውም ለዚህ ነው።
የጋራ እሴቶቻችን የምንላቸውም እንዲሁ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል። ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስሩን በጣም በርካታ ነገሮች አለ። ሰሜኑን ከደቡብ ምዕራቡን ከምሥራቁ ፣ መሐሉን ከዳር ሁላችንንም የሚያስተሳስረን በጣም ወርቃማ የሆኑ እሴቶች አሉን። እነዚህ እሴቶች መጠበቅ አለባቸው። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ አንድ ከሠራነው ሥራ በየአካባቢው ያሉ እሴቶች ምንድናቸው የሚለውን በጥናት ለመለየት ሞክረናል። ያሉን እሴቶች የተመለከተ መጽሐፍም አሳትመናል። የባህላዊ እርቅ አፈታት ለምሳሌ ግጭቶች ሲፈጠሩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች በሁሉም ክልሎች አሉ። እነዚህ ሥርዓቶች በጥናት ቢጠኑ፤ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ቢደገፉ፤ ምርምር ቢደረግባቸው ትውልዱ እንዲያውቃቸው ቢደረግ፣ የማስጠናት ሥራ በሰፊው ቢሠራ በጣም በርካታ ችግሮቻችን ሊፈቱ ይችላሉ።
ባህላዊ የአፈታት ስርአቱ አንዱ ከአንዱ ጋር የተዋሀደ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ አንዱን አካባቢ ከሌላው አካባቢ ለመነጣጠል በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ያልተዋለደ ፣ያልተጋባ ፣ያልተሳሰረ ህበተሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ይሄንን እሴት ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ ይኖርብናል። ፖለቲካው እነዚህ እሴቶች ላይ ጉዳት አድርሷል ።
ባለፉት ዓመታት የፖለቲካችን በሽታና ችግር ወደዚህም እየመጣ እሴቶቻችንም ላይ መሸርሸር አስከትሏል። ይሄንን እንዴት አድርገን ነው የምንጠግነው? እንዴት አድርገን ነው ወደ ነበረበት የምንመልሰው? የሚለው ላይ መግባባት አለብን። ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ስንል በነዚህ ጉዳዮች ላይ ነው ማለት ነው።
ከዛ ውጪ የቆዩ ቁርሾዎች ካሉ መፈታት አለባቸው። በየጊዜው በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ወደ ኅብረተሰቡም የወረዱ ቁርሾችም ካሉ መታየት ይኖርባቸዋል። ሊሂቃን መሐከልም ያሉ ግጭቶች ቁርሾ ሆነው እንዳይቀጥሉ እርቀ ሰላም፤ የሽግግር ፍትህ ማረጋገጥ በመሳሰሉ ጉዳዮች እልባት ማግኘት አለባቸው። አጠቃላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የምንችለው በዚህ መንገድ ነው።
ስለዚህ እነዚህን ተግባራት በማከናወን ነው የሀገሪቱን አጠቃላይ ችግር መፍታት የምንችለው።
ጥያቄ ፡- በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ግንባታ ውስጥ ተጽእኖ ካሳደሩ ጉዳዮች መሐከል ማህበራዊ ሚዲያው ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማል። በዚህ ረገድ ተጽእኖው እንዴት ነው የሚገለጸው ?
አቶ ብናልፍ አንዷለም ፡– ሚዲያው በሰላም ግንባታ ላይ ያለው ሚና የማይተካ ነው። የማይተካ ስል የራሱ የሆነ ቁልፍ ሚና አለው ማለቴ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታትም ቢሆን የተጫወተው ሚና በጣም ትልቅ ነው። ኅብረተሰቡን የሚያቀራርብ ፤ ቅድም ያልናቸውን የሚያስተሳስሩን አንድነታችንን የሚያጠናክሩ እሴቶቻችንን የበለጠ በማጎልበት ፣ ዜጎች እንዲያውቋቸው ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ፣የአብሮነት ጥቅምን ፣የሰላም ጥቅምን በማሳየት ረገድ ሚዲያ ትልቅ ጥቅም አለው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ጉዳትም ያስከትላል። በብዙ ሀገሮች የተፈጠሩ እልቂቶችና ዘር ማጥፋቶች መነሻቸው ሚዲያ ሲሆን ታይቷል። እንደ ሩዋንዳ አይነት ሀገሮች ለችግር የተጋለጡት በሚዲያ አማካኝነት ነው።ሚዲያ ባግባቡ ካልተጠቀምክበትና በተሳሳተ መልኩ ጥቅም ላይ በዋለ ጊዜ ሰውን ለጠብ፣ ለግጭት ፣ለመገዳደል ይዳርጋል።
ሶሻል ሚዲያ የዘመኑ ክስተት ነው። በነገራችን ላይ እኛ ስላልፈለግነው የምናስወግደው ነገር አይደለም። ዓለም ራሱ የወለደው ነው። ልክ እንደግሎባላይዜሽን።
ማንም ሀገር ሊያስወግደው የሚችል ነገር አደለም። ግሎባላይዜሽን ከቴክኖሎጂው፣ ከትራንስፖርቴሽኑ፣ ከመገናኛው፣ ከቴሌው፣ ከበይነ መረቡ ጋር የመጣ ነው። ይህም እንደዛው ነው። የኢንተርኔት ዘመን ያመጣው የእድገት ዘርፍ ነው። ደግሞም መነሻው በጎ ነው።
በጎ ነው የሚባለው ዞሮ ዞሮ የሰዎችን ሕይወት የማቅለል ዓላማ ስላለው ነው። ድሮ እሩቅ ሀገር ያለን ሰው በደብዳቤ የምንገናኝበት ዘመን ተቀይሯል። ዛሬ የትም ዓለም ያለን ሰው ድምጹን ብቻ አይደለም ምስሉንም እያየን የምናወራበት ዘመን ላይ ተደርሷል።
እንዲህ አይነት ነገር የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማቃለል፣ ምርታማነትን በመጨመር ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ያለአግባብ ስንጠቀምበት ደግሞ ያስከተለው ጉዳት አለ። በተለይ ከሰላም አኳያ በዚህ የሚዲያ ቴክኖሎጂ የጉዳት ሰለባ እየሆኑ ካሉት ሴክተሮች የሰላሙ ሴክተር ነው ብዬ አስባለሁ።
ምክንያቱም በቀላሉ በእነዚህ ሚዲያዎች አማካኝነት ሁሉም ጋዜጠኛ ነው። የሕዝብ ጋዜጠኝነት የሚባለው ማንም ሰው ዘመናዊ ስልክ በእጁ እስካለ ድረስ የፈለገውን መረጃ ማሰራጨት ይችላል።
የትም ሆኖ አንዳንዴ ያለበትን ቦታ ሳያሳውቅ በድብቅም መረጃ ሊሰጥ ይችላል። ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ሰጪም ነው። በእነዚህ ፕላትፎርሞች የሚሰራጭ መረጃ አደገኛ የሆኑ፣ የተሳሳቱ፣ መሠረት የሌላቸው የውሸት መረጃዎች ሲሆኑ ሀገርና ሕዝብ ላይ ጉዳት ያስከትላሉ።
በየሴኮንዶቹ በገፍ የሚቆጠር መረጃ ይለቀቃል። በዚህ በሚለቀቅ የሀሰት መረጃ ዜጎች እንዲገዳደሉ፣ አንዱ በሌላው ላይ በጠላትነት እንዲነሳ የሆነ ነገር ተቀርጾ ለመላው ዓለም እንዲሰራጭ ይደረግና አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ ከፍተኛ ቅስቀሳዎች ይሠራሉ።
እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ ጥበብ ባይኖረው፤ የሕዝቡ የአብሮነት እና የመቻቻል ባህል ጠንካራ ባይሆን ኖሮ በሌሎች ሀገራት የታየው እርስበርስ የመተላለቅ አደጋ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደማይመጣ ምንም ዋስትና የለም።
እናም በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። በዛው ልክ ደግሞ ቢዝነስ ሆኗል አሁን። በጣም ከባዱ ነገር አሁን ሚዲያው የቢዝነስ ተቋም ሆኗል። በአክቲቢስቶች፣ በዩትበሮች በተለያየ መንገድ አሁን ሚዲያ ለእውነት ከመሥራት ይልቅ የትኛውን ማስረጃ ባስተላልፍ ጥቅም ያስገኝልኛል ከሚል ዕሳቤ የሚሠራ ነው።
ይህ በጣም አደገኛ እና አስጊ ነው። ምክንያቱም በሰው ልጅ ጭምር ነው የሚነገደው። በሰው ሕይወት የሚነግድ ሚዲያ በበዛ ቁጥር በዜጎች ላይ አደጋ እያስከተለ መሄዱ አይቀርም።
አሁን ካለው ጊዜ በላይ መጪው ጊዜ ያስፈራል። አሁን አርቴፌሻል ኢንተለጀንስ እየመጣ ነው። እሱ ደግሞ እስከዛሬ ድረስ ካየናቸው ነገሮች በላይ በጣም ከፍተኛ ነገር ይዞ እየመጣ ነው።በጥቅም ደረጃ ብዙ ነገሮች ወደ ቴክኖሎጂ እየተቀየረ ነው። ከሚሊተሪው ጀምሮ የዓለም የወታደራዊ አሠራር ድሮ ብዙ ወታደር ከማሰለፍ ውጊያው በቴክኖሎጂ እየሆነ ነው።
ሌላም ብዙ ጉዳት የሚያመጣ የሳይበር ጥቃት ነው። ራሳችንን አዘጋጅተን ለዛ የሚሆን ትውልድ፤ ለዛ የሚሆን ቴክኖሎጂ እየሠራን ካልሄድን ጉዳቱ የከፋ ነው።
ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች በጥንቃቄ በማየት በአንድ በኩል የወጡ ሕጎችን መጠቀም መቻል አለብን። ለምሳሌ የጥላቻ ንግግር ሕግ አለ። ይህንን ደረጃ በደረጃ ወደ ተግባር በመቀየር፣ የኅብረተሰቡን የሚዲያ አጠቃቀም ግንዛቤ በማሳደግ፣ የመቆጣጠር ሥራውን በማሳደግ የተጋረጠብንን አደጋ መቀነስ ይገባናል።
በዚህ ጉዳይ የእኛ ሀገር ብቻ ሳትሆን ዓለም በጠቅላላው እየተፈነ ነው ያለው። አሁን ቴክኖሎጂው እያመጣ ካለው ስጋት አንጻር መንግሥታት በጠቅላላው እየተሽመደመዱ ነው ያሉት። ኅብረተሰብ በከፍተኛ ደረጃ ነው እየታወከ ያለው።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መሥራት ይኖርብናል፤ ብዙ ሥራ ነው የሚጠበቅብን። በአንድ አቅጣጫ ብቻ በማውገዝ መፍትሄ ሊመጣ አይችልምና ብዙ ስትራቴጂዎች መነደፍ አለባቸው።
ጥያቄ፡- መንግሥት በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች ከታጠቁ አካላት፣ ግጭት ውስጥ ካሉ አካላት ጋር ለሰላም መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። በዚህ ረገድ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እንዴት ያሉ ናቸው?
አቶ ብናልፍ አንዷለም፡- ቅድም አያይዤ ካነሳሁት ጋር ሊታይ የሚችል ነው። የዚህ ሀገር መፍትሄ ውይይት እና ንግግር ነው። መንግሥት በተደጋጋሚ ይህ ሀገር ከችግር የሚወጣው በመነጋገር እና በመወያየት ነው እያለ ይገኛል። እንነጋገር እንወያይ የሚል አቋም አለው።
ይሄ በአቋም ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሚረጋገጥ ነው። ለምሳሌ ቅድም እንደተናገርኩት፤ የሀገራዊ ምክክሩ ይሄንን ወደተግባር ለመቀየር የሚያስችል ተቋማዊ አሠራር እንዲኖር ነው እየተሠራ ያለው።
የሰው ልጅ እስካለ ድረስ ልዩነት ይኖራል። እነዛ ልዩነቶች ግን በሰው ልጆች ላይ ጉዳት ማድረስ የለባቸውም። በትጥቅ የተደገፉ ግጭቶች የሚደረግባቸው አካባቢዎች ላይ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በጣም ከባድ ነው። አንደኛ ግጭት ውስጥ ያሉ ዜጎችም ዜጎች ናቸው ራሳቸው፣ የዚህ ሀገር ሀብት ናቸው። በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያሉም ይሁኑ፤ በተፋላሚነት ትጥቅ አንግበው ያሉትም ሰዎች የኢትዮጵያ ሀብቶች መሆናቸውን ማመን ይገባናል።
ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን። ስለዚህም በሁላችንም ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው። ሰብአዊ ጉዳትም ሌላም። ሁለተኛ እና ዋናው በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ነው። በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እየተጎዱ። በዜጎች ሕይወት ላይ አደጋ እየተፈጠረ፣ በዜጎች አብሮነት ላይ አደጋ እየመጣ፣ በዚህ መንገድ መቀጠል የለብንም።መቆም አለበት ይህ ነገር አዋጭ አይደለም።
በማንኛውም መመዘኛ በትጥቅ የሚደረግና በአመጽ የሚደረግ የእርስ በርስ መገዳደል እና መተላለቅ ይሄን ሀገር እንደገና ወደ ኋላ ረጅም መንገድ ይመልሰው ካልሆነ በስተቀር ወደፊት ሊያራምድ የሚችል እድል የለውም።ይህ ደግሞ ከእኛ በላይ ምስክር የሚሆን የለም።
ስለዚህ ይህ የግጭት መንገድ ለሁሉም አክሳሪ ስለሆነ፤ ከዚህ ወጥተን የተሻለውን እና ለሁሉም አትራፊ የሆነውን ንግግርና ውይይት መከተል አለብን።ወደ መደራደር፣ መወያየት፣ መነጋገር መምጣት አለብን። አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ተደጋግሞ ሲነገር ለቃል እንዲያው ዝም ብሎ ለታይታ የሚባል ይመስላል። ግን ይህ ደጋግመን የምንለው ከሂደቱ የሚጠቀም አካል ስለሌለ ነው።
ተሳክቶላቸው እንፋለማለን የሚሉ ኃይሎች ወደ መንግሥት ስልጣን እንኳን ቢመጡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ነገ ደግሞ ሌላው በነሱ ላይ ይነሳል። እንደው ተሳክቶላቸው እንኳን ወደእዚህ ቢመጡ ማለት ነው። የመሳካት እድሉ ምንም እንደሌለ ሆኖ ማለት ነው። ቢሳካ እንኳን አይቆምም።
ይሄ በእኛ ታሪክም አይተነዋል፤ በሌሎች ዓለማት ላይ አይተናል። ለምሳሌ ሱዳን ባለፈው ከእኛ ጋር አብሮ ለውጥ እኩል ጀምሮ ነበር። አሁን ያለበትን ማየት ይቻላል።አንደኛው የጦር ክንፍ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ወደ ስልጣን መጣ ጥቂት ሳይቆዩ እንደገና እርስ በርስ ሌላ ውጊያ ውስጥ ገብተው ሀገር በጦርነት እየታመሰ ነው ያለው።
ምዕራብ አፍሪካም እንዲሁ በሰላም እጦት እየተሰቃየች ነው። በዓመት ሁለት ጊዜ ሁሉ መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባቸው ሀገራት አሉ። የሆነ ጊዜ የራሴ የሆነ ኃይል አለኝ መጣል እችላለሁ ብሎ ይነሳል።ሌላው በሌላ ጊዜ ሲዘጋጅ ይቆይና ወደ ግጭት ይገባል።እንዲህ እያለ ሀገር በዛ መንገድ እየቀጠለ የእድገት አማራጭ እየጠፋ ይሄዳል።ችግሩ የሁሉም ነው።
የሚሻለው ሥርዓት ነው።ሥርዓት በጣም ጠቃሚ ነው።አንድ ሀገር በሥርዓት ነው መመራት ያለባት።የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት። ሁሉ ነገር ሥርዓት መሆን አለበት።የመንግሥታት መለዋወጥ ሥርዓት ባለው መንገድ በምርጫ መሆን አለበት። በየጊዜው የሚደረጉ ምርጫዎች መንግሥታት መለዋወጥ አለባቸው።ይሄን ተከትልን ከሄድን ልክ በሌሎች ሀገራት እንደምናየው የሰለጠነ፤ የበለጸገ ዲሞክራሲ ገንብተዋል በሚባሉት ሀገራት የምናየው ይሄንን ነው።እኛስ ይሄንን መፍጠር ለምን ያቅተናል።
አቅሙ አለን፤ ይሄን ማድረግ የሚችል ሰፊ የሆነ ልምድ አለን።የረጅም ዘመን የመንግሥትነት ታሪክ ያለን ሀገር ነን። እኛ እንደሀገር መንግሥት ሲኖረ እንደ ሀገር ያልተፈጠሩ ሀገራት ናቸው እኮ ዛሬ ጠንካራ የመንግሥት ሥርዓት መፍጠር የቻሉት። እኛ ግን አሁንም ጠንካራ የመንግሥት ሥርዓት ያለው መንግሥት መገንባት አቅቶን አሁንም በጦርነት እና በሁከት እየታመስን እንገኛለን።ለምንድነው ከዚህ መውጣት ያቃተን ?
ከዚህ እንድንወጣ ዋናው መፍትሄ መነጋገር ነው ነው። ቁጭ ብሎ መወያየት፤ መነጋገር ነው። የፖለቲካ ባህሉን እንቀይረው። ይሄንን የፖለቲካ ባህል ከቀየርነው ለውጥ እናመጣለን። ስለዚህ በየትኛውም ክልል በአማራ፣ በኦሮሚያ ክልል ይሁን በሌሎች አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ወደ መነጋገር፤ ወደ መወያየት ፤ወደ መደራደር ሊመጡ ይገባል።ይህንን ተደጋጋሚ ጊዜ ስንለው የቆየነው ነገር ነው።አዲስ ነገር አይደለም። ግን የሁሉም ፍቃደኝነት ከመጣ ነው ውጤት የሚያመጠው።
ደጋግሜ እንደምናገረው የኢትዮጵያ ችግር ከውይይት እና ከንግግር ያለፈ አይደለም።ሁሉም ነገር በውይይት እና በንግግር የሚፈታ ነገር ነው ብዬ ነው የማምነው።ከዛ በላይ የሆነ ችግር አለብን ብዬ አላስብም ።የመንግሥት ስልጣንም፤ የሀብት ክፍፍልም ይሁን ምንም ይሁን በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው።ከዚህ ውጪ ለከፋ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ቀውስ እየተደረቡ እንዲሄዱ ከማድረግ በስተቀር ምንም የምናተርፈው ትርፍ የለም። እናም አክሳሪውን መንገድ ትተን እንደራደር፤ እንወያይ፤ እንነጋገር፤ እንቀራረብ ማለት እፈልጋለሁ።
የብሔራዊ ምክክሩም ሆነ ሌሎች መድረኮችም አሉ።ሌሎችም መድረኮች በዚህ መንገድ በመፍጠር እየተነጋገርን እና እየተወያየን ችግሮችን እየፈታን ብንሄድ አዋጭ ነው። በዚህ ረገድ የመንግሥት በር ሁሌም ክፍት ነው። መንግሥት ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት ከመሻትም ባሻገር ጥሪም እያደረገ ነው።
ስለዚህ ይሄንን ጥሪ ተቀብሎ ሁሉም ሰው በጎ ፍቃድ ኖሮት፤ ወደ አእምሮው ተመልሶ፤ በእውነት ከልቡ አምኖ ሁሉም አካል ለመነጋገር እና ለመወያየት ቢዘጋጅ ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።ይሄን ካደረግን እንዳልኩት ብዙ ችግሮቻችን ይቀረፋሉ።የተረጋጋ ሀገርም ይኖረናል። የጋራ ሀገርም ይኖረናል።
ማናችንም ወደ ስልጣን ብንሄድ ፤ብንመጣ እሱ ሁለተኛ ጉዳይ ነው ።ብቻ ዋናው ሀገር ይረጋጋ ፤ ሀገር ሰላም ይሁን፤ ዜጎች በሰላም ወጥተው ይግቡ። የትም ቦታ ሄደው ሠርተው ይኑሩ። ዜጎች በማንነታቸው ሳይገፉ፤ ሁሉም እኩል ፍታሐዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀምበት የእኔ ናት የምንላት ኢትዮጵያ ትኑረን።ለዚህ በጋራ እንሥራ ነው እኔ ያለኝ መልእክት ።
ጥያቄ፡- ጥያቄዎቼን ጨርሻለሁ። ያልተነሱ ሃሳቦች ካሉ ማከል ይችላሉ።
አቶ ብናልፍ አንዷለም፡– እንግዲህ ብዙውን ነገር ብለናል። ቅድም እንዳልኩት በአብዛኛው አካባቢዎች የተሻለ አንጻራዊ ሰላም ያላቸው ቢሆንም አሁንም የሰላም ችግሮች ያሉባቸው አካባዎች አሉ።እነዚህ አካባቢዎች ሰላም ማግኘት አለባቸው። ይህ እንዲሆን ደግሞ የባህል ለውጥ ማምጣት አለብን። ይሄ የባህል ለውጥ እንዲመጣ ደግሞ ዋናው ሕዝቡ ነው።
ለምሳሌ ቅድም እንዳልኩት የፖለቲካ ስልጣን የሚያዝበት መንገድ፣ችግር እና ልዩነት የሚፈታበት መንገድ ፣የፖለቲካ እይታችን፣ሃሳብ የመጨረስ ፣የሰዎችን ሃሳብ ቀና በሆነ መንገድ የማስተናገድ የመሳሰሉት ጉዳዮች የሚስተናገዱበት መንገድ ሊለወጥ ይገባዋል። ይሄን የባህል ለውጥ ለማምጣት ሕዝቡ በነቂስ መሳተፍ አለበት ብዬ አምናለሁ።ይሄን ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል።
እንደ ሕዝብ የባህል ለውጥ ስናመጣ ከዛ የሚቀዳው ሌላው አካል ያንን እየያዘ መምጣቱ አይቀርም። ለምሳሌ ፖለቲከኛ ከሕዝቡ ነው የሚወጣው።ፖለቲካችን ሲዘምን በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ያለው ችግር እየተቀረፈ ይመጣል።ስለዚህ ብዙ ነገሮቻችን ይቀየራሉ።ከዛ በኋላ ብዙ ሀገር የሚቸገርበት ችግር እየተወገደ እየቀነሰ ይመጣል።
ስለዚህ ሁሉንም ነገር በመሳሪያ የመፍታትን ባህል ማስወገድ ይገባል። ይህንን በእኛ እድሜ ብናየው ካልሆነ ለልጆቻችን ይህንን መሠረት ልንጥልላቸው ይገባል።ይሄን ስናደርግ ብቻ ስለሆነ መፍትሄ የምናመጣው ማለት ነው።ከዛ ውጪ ሰላም ከእያንዳንዱ ሰው እንደሚጀምር ማወቅ አለብን። ሁላችንም የውስጥ ሰላም ሲኖረን ለሌላም ሰው የሰላም ምክንያት እንሆናለን እንጂ የግጭት ምክንያት አንሆንም።
ሰላም ከሆነ ቦታ ተፈልጎ የሚመጣ ፤ተገዝቶ የሚመጣ ወይም የፀጥታ ተቋም እና የፀጥታ ኃይሎች የሚያመጡልን አድርገን ማሰብ የለብንም። ሰላማችንን የምንጠብቀው እኛ ነን። ሰላማችንን የምንከባከበው እኛ ነን።ሰላማችንን የምናሸጋግረው እኛ ነን። ስለዚህ ሁላችንም የሰላም ባለቤቶች ነን ብለን በየአካባቢያችን ያሉ የሰላም መታጣት ምክንያት ይሆናሉ የሚባሉ ጉዳዮችን እየለየን ፤በእነሱ ላይ እየተነጋገርን እየተወያየን ሰላማችንን ማረጋገጥ አለብን።
ጠንካራ ሀገር የሚኖረን በዛ መንገድ ከሠራን ነው። ይህቺ ሀገር የሁላችንም ሀገር ናት ።አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ የሚሆንባት ሀገር አይደለችም። ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን።ሁላችንም ስለዚች ሀገር ግድ ይለናል።ስለዚህ ለዚች ሀገር ቀጣይነት መሥራት አለብን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም