የተጀመሩ የሠላም ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ!

ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች የተጋረጡባት ሀገር ነች፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ካሳረፈባት ቁስል ገና አላገገመችም፡፡ የአካባቢ መራቆት የፈጠረው ድርቅም እየፈተናት ነው፤ የኑሮ ውድነቱም ሌላው ፈተና ነው፡፡ ሥራ አጥነት ገና ያልተፈታ ችግር ነው፤ ለዘመናት የተከማቸ የዕዳ ጫናን መክፈልም እንዲሁ የዚህ ዘመን የቤት ሥራ ነው፡፡ እነዚህን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ሠላም ያስፈልጋል፡፡

ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ሠርቶ ለመኖር፤ በሀገር ለመኩራት፤ ወልዶ ለመሳም፤ ወጥቶ ለመግባት ሠላም ያስፈልጋል፡፡ ሠላም በሌለበት ነግዶ ማትረፍ፤ ተምሮ ለቁም ነገር መብቃት፤ በዜግነት መኩራትና የዕለት ተዕለት ኑሮን መምራት አዳጋች ነው፡፡ በአጠቃላይ ያለ ሠላም ሕይወት የምድር ሲዖል ናት፡፡

ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሠላም ስምምነት እንዲቋጭ አድርጓል። «ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ» የሚለው የአሕጉራችን መርሕ በተግባር ተፈትሾ ውጤታማ እንደሆነ ማሳየት ተችሏል። ስምምነቶቹም ወደ ተግባር ተቀይረው መልሶ ግንባታ በመከናወን ላይ ነው ። ይህ ሂደት ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት ሆኖ አልፏል።

የሰሜኑን ጦርነት በንግግር ለመፍታት መቻሉ ብዙ ዜጎችን ከእልቂት እና ሰቆቃ የገላገለና እፎይታን የፈጠረ ነው። ከዚህም ባሻገር ከዚህ በኋላ በሀገራችን በጠብመንጃና በኃይል ልዩነቶችን የመፍታት አማራጭ ማክተም እንደሚኖርበትና እንደሚችልም በተግባር ያሳየ ነው። በዚህም መንግሥት ምንጊዜም ከማንኛውም ኃይል ጋር ችግሮችን በመወያየትና በንግግር የመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለው በተግባር ያስመሰከረበት ነው። መንግሥት ልክ እንደ ትግራይ ክልል ሁሉ በመላ ሀገሪቱ ሠላም ለማስፈንና የታጠቁ ኃይሎችም ወደ ሠላምና ወደ ልማት እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ሆኖም መንግሥት ባደረገው የሠላም ጥሪ እና ለሠላም ባለው ምኞት ልክ የተለያዩ አካላት ተገቢ ምላሽ ሲሰጡ አልታዩም፡፡ ይልቁንም አንዳንዶች መንግሥት ለሠላም ያለውን ቀናዒነት በማጣጣልና እንደ ደካማነትም በመቁጠር በየጫካው ጦር ሲመዙ ታይተዋል፡፡ ሠላምንም ወደ ጎን በመተው ግጭትና ሁከትን አንግሠዋል፤ ጦርነትም በማወጅ ለበርካታ ዜጎች ዕልቂትና ለሠላም መደፍረስ ምክንያት ሆነዋል።

በየጫካና በየዱሩም ነፍጥ በሚያነሱ ቡድኖች ምክንያት አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዳያከናውን፤ ገበሬው ነግዶ እንዳያተርፍ፤ ተማሪው በዕውቀት ገበታ ላይ እንዳይገኝ፤ ሰዎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ ተደርገዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ነፍጥ ባነሱ ቡድኖች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል፤ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፤ ሕይወታቸውንም አጥተዋል፡፡

ስለሆነም ከግጭትና ጦርነት ምንም እንደማይገኝ አውቆ ፊትን ወደ ሠላም እና ልማት መመለስ ይገባል፡፡ ዛሬ ሥልጣን ለመያዝ ብረት ማንሳት አያስፈልግም፡፡ ብረት አንስቶ ጫካ ቢገባም ትርፉ ሕይወትን መገበር፤ ወጣቶችን ማስጨረስና ሀገርን ማዳከም እንጂ ሥልጣን በጠብመንጃ የሚያዝበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡

ዛሬ ሥልጣን ለመጨበጥ የሚያስፈልገው የተሻለ ሃሳብ አምጥቶ ዕውቀትን ለገበያ ማቅረብ ብቻ ነው። በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በመመካከርና በሃሳብ የበላይነት በማሸነፍ ያለሙትን ማሳካት ይቻላል። በመሣሪያ ከማሸነፍ በሃሳብ የበላይነት ማሸነፍ ዛሬ ግዝፍ ነስቷል፡፡ ስለሆነም አማራጩ ፊትን ወደ ሠላምና ልማት መመለስ ብቻ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር በአማራ እና በኦሮሚያ የተጀመሩ የሠላም ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡ ፡ በሁለቱ ክልሎች ሠላምን ማዕከል አድርገው እየተከናወኑነ ያሉ ሕዝባዊ ውይይቶች ፍሬያቸው እየታየ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ በቤኒሻንጉል፤ በጋምቤላ እና በደቡብ ምዕራብ የታየው ሠላምም ዘለቄታ እንዲኖረው ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

በመንግሥትም የተጀመሩ የሠላም ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት በውጤት እስኪታጀብ ድረስ ቀጣይነት ያለው ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You