የገበያ ማዕከላቱን ለአርሶ አደሩና ለሸማቹ ተጠቃሚነት ምቹ የማድረግ ዝግጅት

መንግሥት እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለይም ከተሞች አምራች ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችን ከሚመረቱባቸው አካባቢዎች ወደ ከተማ በማምጣት ገበያን የማረጋጋት ሥራ ይሠራል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የማኅበረሰቡን የኑሮ ጫና ማቃለል ይችላሉ፤ ገበያን የማረጋጋት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ያላቸውን በርካታ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል።

ከተማ አስተዳደሩ ገበያን በማረጋጋት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እየሠራቸው ካሉ ተግባሮች መካከል የሰንበት ገበያ አንዱና ዋነኛው ሲሆን፤ በተለያየ ጊዜ የሚያዘጋጃቸው ባዛርና ኤግዚቢሽኖችም ገበያን በማረጋጋት የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ትላልቅ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት አምራቹ ምርቱን በነጻነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ወደ ገበያ ማዕከላቱ የሚያቀርብበትን፣ ሸማቹም ከዚህ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ገበያን በማረጋጋት የኑሮ ውድነት ጫናውን በማቃለል ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡

በከተማዋ የመግቢያ በሮች አካባቢ የተገነቡት የግብርና ምርቶች ከዚህ አኳያ ይጠቀሳሉ፡፡ የገበያ ማዕከላቱ ገበያን በማረጋጋትና የኑሮ ውድነቱን በማቃለል ረገድ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩ፤ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ የገበያ ማዕከላቱ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ወጪ መድቦ ያስገነባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ የገበያ ማዕከላቱን ለመገንባት ከስድስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መድቧል፤ ይህንን ሲያደርግም የተለያዩ ግቦችን በማስቀመጥ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከልም አንደኛው የማኅበረሰቡን የኑሮ ውድነት ጫናን ማቃለል ሲሆን፤ ይህንን ለማስቻልም በገበያ ማዕከላቱ የሚቀርቡት ምርቶችን ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት የሚችልባቸውን አስቻይ ሁኔታዎች በማመቻቸት ነው፡፡

የገበያ ማዕከላቱ ከተገነቡ በኋላ ወደ ሥራ መግባት እንዲችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ቢሮው ባወጣው ግልጽ ጨረታ መሰረት ተወዳደሪዎች ተወዳድረዋል፤ አሸናፊ የሆኑ አካላትም ውል በመፈጸም የገበያ ማዕከላቱን መደብሮች ተረክበዋል። ጨረታውን ያሸነፉ የጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች በገቡት ውል መሰረት የተለያዩ ምርቶችን ለከተማ ነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርቡ አመላክተው፤ ይህም የኑሮ ውድነቱን ለማቃለልና ገበያውን ለማረጋጋት አበርክቶው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ቢሮው በገበያ ማዕከላቱ ምርቶቻቸውን ማቅረብ ለሚችሉ የጅምላና የችርቻሮ ነጋዴዎች ግልጽ ጨረታ አውጥቶ ማወዳደሩን ጠቅሰው፣ ማንኛውም ነጋዴ ጨረታውን ተወዳድሮ ዕድሉን መጠቀም እንዲችል በተደረገው ጥረት በርካታ የጅምላና የችርቻሮ ነጋዴዎች ጨረታውን መወዳደር ችለዋል ብለዋል፡፡ ጨረታውን ከተወዳደሩት መካከል 57 የሚደርሱት የጅምላ ነጋዴዎች እንዲሁም 143 የሚደርሱት ደግሞ የችርቻሮ ነጋዴዎች ጨረታውን ማሸነፋቸውን ጠቅሰው፣ ነጋዴዎቹ በአሁኑ ወቅትም ምርቶቻቸውን ወደ ማዕከላቱ በማስገባት ወደ ሥራ እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የገበያ ማዕከላቱ ዋና ዓላማ ገበያን በማረጋጋት የኑሮ ውድነቱን ማቃለል እንደመሆኑ በተለይም የጅምላ ነጋዴዎችን ለማወዳደር የተለያዩ መስፈርቶች መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አንደኛ በኢንቨስትመንትም ሆነ በተለየ መንገድ መሬት ያለውና በተለያየ መንገድ የሚያመርት መሆን ይኖርበታል፤ ለዚህም ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ ማቅረብ መቻል አለበት፡፡ ሁለተኛው መስፈርት በተሰማራበት ዘርፍ ዓመቱን ሙሉ ለከተማው ምርት ማቅረብ የሚችል መሆን አለበት፡፡ ሶስተኛው መስፈርት የሚያቀርባቸውን ምርቶች ከመደበኛው ገበያ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ ማድረግ የሚችል መሆን ይኖርበታል። በመሆኑም እነዚህን መስፈርቶች ማሟላት የቻሉ 57 የጅምላ ነጋዴዎችና 143 የችርቻሮ ነጋዴዎች ወይም የንግድ ድርጅቶች አሸናፊ መሆን ችለዋል ነው ያሉት፡፡

በከተማዋ የመግቢያ በሮች አካባቢ የተገነቡት እነዚህ የገበያ ማዕከላት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙና የተለያየ አገልግሎት ያላቸው እንደሆኑ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ አንደኛው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኝና የሰብል ምርቶች የሚቀርቡበት የገበያ ማዕከል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛው ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ሲሆን፣ ሶስተኛውም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የተገነባው የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ነው፡፡

ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን የገበያ ማዕከላት ሲገነባ በዋነኛነት የኑሮ ጫናን ማቃለል ዓላማው እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ መሬት ያለውና አምራች የሆነ አካል በጨረታው እንዲሳተፍ መደረጉ በመሀል ያለውን ደላላ ከማስወጣት ባሻገር ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስና የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠር አበርክቶው የጎላ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ይህም የተለያዩ ምርቶች ከአምራቹ በቀጥታ ወደ ሸማቹ የሚደርሱበትን ዕድል እንደሚያመቻች አስታውቀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ እነዚህ የገበያ ማዕከላት ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር ሲገቡ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አላስፈላጊ የሆነ የደላላ ጣልቃ ገብነትን በማስወገድ ገበያን ለማረጋጋት ይረዳሉ። ምርትን በማጓጓዝና በክምችት ረገድ ይፈጠር የነበረውን የምርት ብክነት በመቀነስ ከፍተኛ የሆነ አበርክቶ ይኖራቸዋል፡፡ የገበያ ማዕከላቱ በተለይም አሁን ላይ በከተማው እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል ትልቅ አቅምና ጉልበት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በየሳምንቱ የዋጋ ጥናት እንደሚያደርግ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በገበያ ማዕከላቱ የሚቀርቡት ምርቶች ከመደበኛ ገበያው ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ ማድረግ መቻል አለመቻላቸውን በሚያቀርበው ዋጋ መሰረት ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ዓመቱን በሙሉ ምርት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህም በውላቸው መሰረት የሚተገበር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ዓመቱን ሙሉ ምርታቸውን ለማቅረብ ውል መግባታቸውን ጠቅሰው፣ ይህንንም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል፡፡

እነዚህ ስምምነቶች በከተማ ውስጥ የሚታየውን የኑሮ ውድነት በማቃለል እንዲሁም ገበያን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረው፤ የኑሮ ጫናው በተለይም በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ በሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለማቃለል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ያላቸውን ዕምነት አመልክተዋል፡፡

የገበያ ማዕከላቱ ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ እንደመሆኑ በፍጥነት ወደ ተግባር ገብተው የታለመላቸውን ግብ መምታት እንዲችሉ ቢሮው የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ጨረታውን ላሸነፉ አካላት ቢሮው ሱቆቹን እያስረከበ እንደሆነና ነጋዴዎቹም ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ነጋዴው ሱቁን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የሱቅ ኪራይ የመክፈልና ሌሎች ግዴታዎችን ጭምር የማሟላት ግዴታ እንዳለበት ጠቅሰው፣ በቶሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

‹‹አዲስ አበባ ከተማ ሸማች እንጂ፤ አምራች ከተማ አይደለችም›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ቢሮው በተቻለ መጠን ከተማ ውስጥ ገበያው እንዲረጋጋና ኅብረተሰቡ ዕለት ዕለት የሚጠቀምበት ምርት ዋጋው እንዲቀንስ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ በከተማ ውስጥ ያለው የአብዛኛው ምርት ዋጋ ተገቢነት የሌለው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም ዋናው ምክንያቶቹ በገበያ ውስጥ የተለያዩ ጣልቃ ገብነቶች መኖራቸው ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአትክልት ምርቶች ዋጋ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን አንስተው፤ በተለይም ሽንኩርት መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱንና ቲማቲምም እንዲሁ በከፍተኛ መጠን ቅናሽ እያሳየ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡ ቢሮው ቲማቲምም ሆነ ሌሎች ምርቶች ዋጋቸው አሁን ካለው ዋጋ በታች ወርዶ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት አርሶ አደሩ ይጎዳ ማለት እንዳልሆነና አርሶ አደሩ የልፋቱን ዋጋ አያግኝ ማለት እንዳልሆነ ተናግረው፣ አርሶ አደሩም የልፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ በኩል የገበያ ማዕከላቱ ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በገበያ ማዕከላቱ ምርቶቻቸውን ከሚያቀርቡት ነጋዴዎች መካከል አብዛኞቹ የአርሶ አደር ማኅበራት ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ምርቶቹን ወደ ከተማ በማምጣት ለሸማቹ በቀጥታ የማቅረብ ዕድል አልነበረውም። ለዚህም ዋናው ምክንያት ሶስትና አራት ደላሎች በመሀል ጣልቃ የሚገቡበት ሁኔታ ነው፡፡ አሁን ግን አርሶ አደሩ ምርቱን ካመረተበት ቦታ በቀጥታ ወደ ገበያ ማዕከሉ መጋዘኖች የሚያስገባበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ምርቱ ከአምራቹ በቀጥታ ወደ ሸማቹ ይተላለፋል፡፡ በዚህም በመጀመሪያ ደረጃ አርሶ አደሩን በተመሳሳይ መልኩም ሸማቹን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

ይህ ለአርሶ አደሩና ለሸማቹ ጠቃሚ እንደሆነ የታመነበት የገበያ አማራጭ በዋናነት በመሀል ያሉትንና ምንም እሴት የማይጨምሩ ደላሎችን የሚያስወግድ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ መሀል ላይ ያሉት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች ለብዙ ምርቶች ዋጋ መናር ብቸኛ ምክንያቶች ባይሆኑም ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል። እነዚህ ደላሎች አንዳንድ ጊዜ ወደ ከተማ የሚገባውን ምርት ዋጋና የምርት መጠኑን ጭምር የሚወስኑበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰው፣ እነዚህን አካላት በአካል ማግኘት እንደማይቻልም ነው ያመላክቱት፡፡

በከተማዋ መግቢያ በሮች የተገነቡት የገበያ ማዕከላት እነዚህን እና መሰል የገበያ ችግሮችን ለማቃለል ትልቅ አቅም እንደሆኑ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፤ አርሶ አደሩንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ የገበያ ማዕከላት እንደሆኑ ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ማቅረብ፣ ገበያውም ዋጋውን መወሰን የሚችልበት ዕድል ከተፈጠረ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው አሁን ያለው ሁኔታ አርሶ አደሩን ብዙም ተጠቃሚ የሚያደርገው አይደለም፡፡ ወደ ከተማ ሲመጣ ደግሞ ሸማቹ ተጠቃሚ አይደለም፡ ፡ ይህ የሚሆነው መሀል ላይ ባለው ረጅም ሰንሰለት ሳቢያ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ማእከላት ይህንን የረዘመ የደላላ ሰንሰለት በማሳጠር ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው።

ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ከተሸጋገሩት አራት የገበያ ማዕከላት በተጨማሪም ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ሌሎች የገበያ ማዕከላት በከተማዋ እየተገነቡ እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከተገነባው የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ጋር በተመሳሳይ ደረጃ የሚገነባ የገበያ ማዕከል ግንባታም እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም እነዚህ የገበያ ማዕከላት ከዚህ ቀደም ተገንብተው ወደ ስራ ከገቡ የገበያ ማዕከላት ተሞክሮ በመውሰድ የታለመላቸውን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ ከማድረግም ባሻገር ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር ጭምር ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You