የኑሮ ወድነቱ ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ወድነት አሁን ላይ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኑሮ ወድነት ተከሠተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው የመግዛት አቅም ሲዳከም ነው። በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እያሻቀበ ቢሆንም፣ የአብዛኛው የማኅበረሰቡ ከፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ግን ከዋጋ ግሽበቱ እኩል ማደግ አለመቻሉን የዘርፉ ባለሙያዎቸ ይገልጻሉ።
ለዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያቶች ከሚባሉት መካከል የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የገበያ ምኅዳር ብልሽት ወይም ሕገ ወጥ ደላሎች በገበያ ውስጥ የሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት እና የጥሬ ገንዘብ ሥርጭት መብዛት በቀዳሚነት የሚነሱ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ እየታየ ላለው የዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የምግብ ነክ ሸቀጦች፣ በተለይ የእህል ዋጋ መናር ነው።
ሌላው የኑሮ ውድነት አባባሽ ምክንያት ከማሳ እስከ ገበታ ያለው የግብይት ሰንሰለት እጅግ የተራዘመ እንደሆነ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ምርት ከአምራቹ ወጥቶ ወደ ሸማቹ እጅ እስኪደርስ ባለው ሂደት በሚፈጠሩ ህገወጥ አሰራሮች ምክንያት በየደረጃው የዋጋ ጭማሪ ይስተዋላል፤ ይህም የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ምክንያት ይሆናል።
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚናገሩት፤ የንግድ ሰንሰለቱ በተራዘመ ቁጥር ተዋንያኑ ብዙ ስለሚሆኑ ምርት በተፈለገው ጊዜ ወደ ተፈለገው ቦታ መድረስ አይችልም፤ ይህ ደግሞ የገበያ ቀውስ ይፈጥራል፣ ፈላጊው የፈለገውን ምርት በአይነት በመጠንና በጥራት እንዳያገኝ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ ሸቀጦች ከዋጋቸው በላይ ለገበያ እንዲቀርቡ ያደርጋል።
ይህ አካሄድ አቅርቦት ይቀንሳል፣ የምርት ፍሰት ያስተጓጉላል እንዲሁም የተሻለ ገበያ ይገኛል በሚል የምርት መከማቸት እንዲኖር በማድረግ በሚፈለገው ጊዜና ወቅት ለተጠቃሚው እንዳይደርስ ይሆናል። በተጨማሪ የምርት ጥራቱን ጭምር እንዲቀንስ ያደርጋል፤ በሌላ ጎኑ በሁሉም እርከን ላይ የአገልግሎት ክፍያ እየጨመረ ስለሚሄድ ምርት የመጨረሻ ተጠቃሚው ላይ ሲደርስ በጣም ውድ እንዲሆን ያደርጋል ይላሉ ምሁሩ።
አምራቹ ጋር ያለው ዋጋና የመጨረሻ ተጠቃሚው ኅብረተሰብ የሚገዛበት ዋጋ ስንመለከት ከግማሽ በመቶ በላይ ከፍ ያለ ዋጋ ነው ያለው የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ይህ የሚሆነው በደላሎች መብዛት እና እነርሱ ያልተገባ ጥቅም ለመግኘት በሚያደርጉት እሽቅድድም በመሆኑ ለዚህ መፍትሔ ማበጀት አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህንን ችግር ለመፍታት በተለያየ ጊዜ መንግሥት የሚጀምረቸው ሥራዎች ነበሩ የሚሉት ባለሙያው ለአብነት እንደ ምርት ገበያ ባሉ ተቋማት እንደ ቡና፣ ስንዴ ቦሎቄ አይነት ምርቶች ገብተው ግብይት እየተካሄዱባቸው ነው። በተለይ ቡና ላይ የነበረው መንዛዛት የቡና ንግድ ሰንሰለት አስቸጋሪ ነበር። አሁን ያ ሰንሰለት ታልፎ በቀጥታ ሻጭና ገዥ እንዲገናኙ የሚያደርግ ስርዓት ነው የተዘረጋው። እንደዚህ አይነት አሰራሮች በሌሎች ምርቶች ላይም ተግባራዊ እንዲሆኑ በፕሮጀክት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመደበኛ ሁኔታ ተግባር ላይ እንዲውሉ መንግሥት እስትራቴጂ ነድፎ ሥራ መሥራት አለበት ይላሉ።
ከአምራች ኢንዱስትሪ ወይም አርሶአደሩ ጋር የምርት ችግር የለም የሚል ዜና በተደጋጋሚ እንሰማለን የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ሆኖም የተመረተው ምርት በቀጥታ ሸማቹ ጋር ስለማይደርስ የዋጋ ንረት ይታያል። በተለይም መሃል ላይ ምርቱን አፍኖ የሚይዝ አካል ስለሚኖር በቂ ምርት ቢመረትም ሸማቹ ጋር የሚደርስው ግን ጥቂቱ ነው። ስለዚህም በእነዚህ ችግሮች ላይ ጠበቅ ያለ ክትትልና እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ችግሩ የሚቀጥል መሆኑን ይናገራሉ።
ማንም ሰው ምርት ላይ እሴት ሰይጫምር ገብቶ የሚዳክርበት ሁኔታ መኖር የለበትም የሚሉት ምሁሩ ሁሉም እንደፈለገው የሚዳክርበት የንግድ ስርዓት የንግድ ስርዓቱን ጤናማ እንደማያደርገውና አልፎ ተርፎም ለኑሮ ውድነት መንስኤ እንደሚሆን አስረድተዋል። ስለዚህ መንግሥት ጊዜያዊ ሳይሆን በደንብ በፖሊሲና እስትራቴጂ የተደገፈ ማን ምን ማድረግ አለበት ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን በመለየት ወደ ሥራ በመግባት ችግሩ በዘላቂነት የሚቀረፍበት መንገድ ማበጀት አለበት ይላሉ።
በሀገሪቱ በአንዳንድ ቦታዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በማምራት ደረጃም፣ ምርት በመሰብሰብ ደረጃ እና የተመረተው ምርት ወደ ገበያ እንዳይቀርብ በማድረግ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ግጭቶች የሚወገዱበትን መንገድ መተለም እንደሚገባ ጠቁመዋል። ‹‹ ይህ እንዳለ ሆኖ የምርት ሰንሰለቱን የሚያራዝሙ አካለት በአስፈፃሚው እራሱ የሚታወቁ አይመስለኝም፤ ሰው ሰራሽ ግሽበት የሚፈጥሩ አካለት ሕገወጥ በሆነ መልኩ የተደራጁ ናቸው ይህንን መሰረታዊ በሆነ መልኩ መፍታት ይጠበቃል›› ይላሉ።
ዶክተር ሞላ እንደሚሉት አርሶአደሩ ምርት ቤቱ ላይ እንዲቀመጥ የሚፈልግበት ምንም አይነት ምክንያት የለም። ቤቱ በቆየ ቁጥር ከጥቅም ውጭ ይሆናል እንጂ የሚሰጠው ፋይዳ አይኖርም። ስለዚህ አርሶአደሩ ያመረተውን ምርት ተጠቃሚው ጋር የሚያደርሱትና መሃል ላይ አንቀው በሚይዙት ደላሎች ነው። በጥራትም፣ በአይነትም፣ በብዛትም፣ በዋጋም እየተጎዳ ያለው የመጨረሻ ተጠቃሚው እንደመሆኑ ደህንነቱን ለማስጠበቅ የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት የሚመሩ አካላት ተቋማዊ የሆነ አሰራር መከተል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ዶክተር ሞላ እንደሚያስረዱት፤ የችግሩን አሳሳቢነት ሁሉም ሊረዳው ይገባል፤ አሁን ያለው የኑሮ ውድነት የህዝቡን አቅም እየተፈታተነ ነው ያለው፤ ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ እንዳነሳነው ከተራዘመ የግብይት ስርዓት የመጣ ችግር ነው። ይህ ባይሆን በአንድና በሁለት ዓመት ልዩነት የምግብ እህል ዋጋ በአማካይ ከመቶ ፐርሰንት በላይ አድጎ የሚገኝበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።
የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ብቻ ሳይሆን የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር የምንስበው ስርዓት ያለውና የተቀላጠፈ የግብይት ስርዓት ሲኖረን ነው። ይህንን ለማድረግ ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህንን ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ በሆነ መልኩ መረባረብ አለባቸው ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ምርት ቀጥታ ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው የሚደርስበት ሁኔታ አለ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ከጅምላ አከፋፋይ ወደ ደንበኛ የሚደርስበት አጋጣሚ ይኖራል። በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ሰዎች እየገቡ ግብይቱን የሚያራዝሙበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ የገበያ ሰንሰለት ላይ አንዳንዶቹ እሴት የሚጨምሩ ናቸው፤ በገበያ ሰንሰለቱ የሚሳተፍ አካል እሴት የሚጨምሩ ከሆነ ለኢኮኖሚው ጠቃሚ ነው ለአምራቹም በተዋረድ የሚሰጠው ጥቅም ይኖራል ይላሉ። ሆኖም ብዙዎቹ ምንም አይነት እሴት የማይጨምሩና አልፎ ተርፎም ለግሽበቱ ዋነኛ መንስኤ ሲሆኑ ይታያሉ።
ዶክተር ዳዊት ለአብነት ሲያነሱ፤ አንድ አምራች አዲስ አበባ ያለ ቢሆንና ተጠቃሚው ደግሞ ሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ቢሆን ተጠቃሚው አንድ እቃ ገዝቶ ለመምጣት አዲስ አበባ ከተማ መሄድ አዋጭ አይሆንለትም። አንድ ነጋዴ ግን ተጠቃሚው ወዳለበት ከተማ ምርቱን ሲያቀርብ እሴት ጨምሯል ማለት ነው። በተቃራኒው ግን ምንም አይነት እሴት ሳይጨምር አንዱን ወደ ሌላው እየተቀባበለ ዋጋ ብቻ እየጨመረ የሚሄድበት ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ በፍጹም ተገቢነት የሌለው አካሄድ እንደሆነ ይናገራሉ።
ባለሙያው እንደሚናገሩት፤ እንደነዚህ አይነት ትክክለኛ ያልሆኑ አካሄዶች ናቸው የኑሮ ጫና ይዘው የሚመጡትና ጉዳት የሚያስከትሉት። ጉዳቱም የመጨረሻ ተጠቃሚ በሆነው ኅብረተሰብ ላይ እንደመሆኑ አየር በአየር የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎች ከጠቀሜታቸው ይልቅ ጎጂነታቸው ስለሚበዛ እነዚህ አካሄዶች የማሳጠር ብሎም ሕገወጥ አሰራር የማስወገድ ሥራ መሠራት አለበት ይላሉ።
አምራች አካል ገበሬም ሆነ ፋብሪካ ያመረተው ምርት ለተጠቃሚው በተመጣጠኝ ዋጋ መድረሱን መረጋገጥ መቻል አለበት፤ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ከአምራቹ ይጠበቃል። በሌላ በኩል መንግሥት እንደ ተቆጣጣሪ አካል ይህ የተራዘመ የግብይት ስርዓት እንዲያጥር ከተቻለም ደግሞ እንዲጠፋ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ይናገራሉ።
ዶክተር ዳዊት አክለውም፤ በአሁኑ ወቅት በገበያ ስርዓቱ ውስጥ የሕገወጥ ደላሎች ሚና በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም በትክክል ይህን ያክል ነው ለማለት ጥናትን ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። እነርሱ የሚያገኙትን ጥቅም ብቻ ለማጉላት የምርት ዋጋ እንዲጨምር የማድረግ ሁኔታው በግልጽ የሚታይ ነው። ለምሳሌ የቤት ኪራይ ብንመለከት በብዙ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ አከራይና ተከራይ የሚገናኙት በደላላ ነው። በዚህ ወቅት ከሁለቱም ወገን ገንዘብ የሚቀበሉ እንደመሆናቸው የሚያገኙትን ገንዘብ ከፍ ለማድረግ አነስተኛ ገቢ ባለው ተከራይ ላይ ጫና በመፍጠር የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግ ይገፋፋሉ። ይህ ዘርፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በደላሎች እጅ ላይ እየወደቀ መጥቷል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው አካሄዱ በቶሎ መገታት ያለበት እንደሆነም ተናግረዋል።
እነዚህን ሕገወጥ አካሄዶች ሻጭና ገዢው በቀጥታ የሚገናኝበት መንገድ በማመቻቸት አነስተኛ ገቢ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል በኑሮ ውድነቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ ሆኖ እንዳይቀጥል ለማድረግ በዋናነት መንግሥት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካለት ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ዳዊት ገለፃ፤ የሸማቹን ጥቅም ለማስጠበቅና አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶችን ለማስወገድ የተለያዩ ሀገራት ማለትም ህንድ፣ ቻይናና ሌሎች የላቲን አሜሪካ ሀገራት በስፋት የሄዱበት መንገድ አለ። ያንን ልምድ መውሰድ ይቻላል፤ ይህም ልምድ ምንድነው፦ አንድን ምርት ማንም ያምርተው ለተጠቃሚው የሚደርሰው የመጨረሻ የመሸጫ ዋጋ ታውቆ ነው ወደ ገበያ የሚቀርበው። ያንን ምርት በምንም ተዓምር ከተተመነለት ዋጋ በላይ መሸጥ አይቻልም።
ተቆጣጣሪ ተቋማት የሻጩንም የገዢውንም መብት ማስጠበቅ ግዴታቸው ነው የሚሉት ባለሙያው፤ የተለያዩ ሀገራት ልምዶችን ከሀገሪቱ ነበራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ የግብይት ስርዓቱ የመጨረሻ ተጠቃሚው በማይጎዳበት ሁኔታ እንዲቀርብ ማስቻል እንደሚገባ ይገልፃሉ።
የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸው ምርቶች በቅናሽ የሚገኙባቸውን መጋዘኖች ያዘጋጃሉ። ማንኛውም ዜጋ ከእነዚህ ተቋማት ሄዶ የፈለገውን የሚገዛበት አሰራር አላቸው፤ ኢትዮጵያም ከራሷ አቅም አንፃር በተለያዩ ከተሞች ዜጎች በቅናሽ የሚፈልጉትን ነገር የሚገበያዩበት እንደ የእሁድ ገበያ አይነት ያሉ አሰራሮች ጠንካራ መሠረት ኖሯቸው በቀጣይነት ቢተገበሩ የሚኖራቸው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ሌላው በኢትዮጵያ የሸማቾች ማኅበር ተብሎ ምርትን ከአምራች ተቋማት እየወሰደ ለተጠቃሚ በተመጣጠኝ ዋጋ ማድረስን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመው ተቋም የተጠናከረ አለመሆንና ሸማች በሚፈልገው መጠን ምርት ከማቅረብ አንፃር ሰፊ ክፍተት ያለበት እንደመሆኑ ይህ ተቋም በተደራጀ መልኩ ሥራውን እንዲሰራ ማድረግ ሌላኛው አማራጭ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ዶክተር ዳዊት እንደሚናገሩት፤ በገዢው ኅብረተሰብ አካባቢ ያለው የመረጃ እጥረት ለኑሮ ውድነቱ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። አንድ ምርት ከገበያ ሊጠፋ ነው ወይም ነገ አይኖርም ተብሎ አሉባልታ ሲነገር ተሻምቶ ያንን ምርት ለመግዛት የሚካሄድበት መንገድ ከመረጃ እጥረት የሚመነጭ በመሆኑ በሀገሪቱ የሚገኙ ሚዲያዎች ማኅበረሰቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ የራሳቸው ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ባለሙያዎቹ እንዳነሱት ጊዜ የማይሰጠውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት ችግሮችን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መስራት ይገባል። በግብይት ሰንሰለቱ የሚስተዋሉ ማነቆዎች ምንድናቸው? በምን አይነት ሴክተር ላይ በብዛት ይታያሉ? መገለጫቸው ምንድነው? የሚለውን ጥናትን መሰረት አድርጎ መለየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። <<ችግሩን በአግባቡ መለየት የመፍትሔው ሃምሳ በመቶ ድርሻ ይወስዳል>> እንደሚባለው የችግሩን መንስኤ በጥናት መለየት ያስፈልጋል፤ በመቀጠልም ችግሩ አንገብጋቢ እንደመሆኑ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አካላት በጉዳዩ ላይ ተቆጥሮ የተሰጣቸውን የራሳቸውን ሚና በተገቢው መልኩ መወጣት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም