የኤሌክትሮኒክ ዘርፉን መምራት የሚያስችል ስትራቴጂ

‹‹ዘመነ ዲጅታላይዜሽን›› ዓለም በየዕለቱ አዳዲስ ክስተቶችን እንድታስተናግድና በፍጥነት እንድትጓዝ እያደረጋት ይገኛል። ዛሬም ጥቅም ላይ ውለው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ብዙ ሳይቆዩ በሌላ በተሻለ ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተተኩ ናቸው። በዚህ በኩል የዓለም አገራት በእኩል ደረጃ ለመወዳደር ባይችሉም፣ ወደ ሁዋላ የቀሩት የቀደሙት ላይ ለመድረስ የሚያደርጉትን ሩጫ በእጅጉ የፈጠነ እንዲሆን እያደረገው ነው። በቴክኖሎጂው ወደኋላ የቀሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት በዘመነ ቴክኖሎጂ በመዋጀት የፈጠነውን ዓለም ይቀላቀሉ ዘንድ የመወዳደሪያ ምህዳሮችን መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያም የዲጂታል ዓለምን ለመቀላቀል የሚያስችላትን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ረገድ በርካታ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተቀርጾ ዲጂታላይዜሽን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተሰሩ ናቸው። ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረጉን ሥራም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበላይነት እየመራው ይገኛል። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ዲጂታላይዜሽንን በማስፋፋት ረገድ ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጎ በርካታ ሥራዎች መስራት ተችሏል። በዚህም ከ526 በላይ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲፈጸሙ፤ የክፍያ ሥርዓቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እንዲሆኑ እና የተለያዩ መተግበሪያዎች እንዲለሙ ተደርገዋል።

በዲጂታል ቴክኖሎጂው በኩል የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ሊያሰፉ የሚችሉ ሥራዎችን መስራት ተችሏል። ባለፈው ወር መጨረሻም የዲጂታል ሳምንት በማካሄድ በዲጅታል ዙሪያ የተሰሩ ሥራዎችን ኀብረተሰቡ እንዲረዳቸውና እንዲገነዘባቸው ማድረግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መስራታቸው ተመላክቷል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ከተሰሩ ሥራዎች የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ አንዱ ነው። ስትራቴጂው በቀጣይ አምስት ዓመት የኤሌክትሮኒክ ዘርፉ የሚመራበትን አቅጣጫ ለማመላከት ታልሞ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ስትራቴጂውን አጠናቅቆ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የመጨረሻ ግብዓት ማሰባሰብ ተችሏል።

ስትራቴጂው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል ሲሆን፤ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የመተግበሪያ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ አወቃቀር እና በጀትን አካትቶ የያዘ መሆኑ ተገልጿል። ስትራቴጂው ከ2016 እስከ 2020 ዓ.ም ተግባራዊ ላይ የሚውል መሆኑም ተመላክቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶክተር) የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ለማፋጠን እንደሚያስችል ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ስትራቴጂው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ለማሳካት እና የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማቀላጠፍ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ስትራቴጂው የመንግሥትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግሥትን አገልግሎቶች በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመንግሥት አገልግሎቶች ቢያንስ 50 በመቶ ዲጂታል ማድረግ፣ ዲጂታል መታወቂያን በመጠቀም የኦንላይን አገልግሎቶችን በ25 በመቶ ለማሳደግ እና 50 በመቶ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ክላውድ ለማዛወር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ስትራቴጂ ቴክኒካል ሥራዎች አስተባባሪ ሊሻን አዳም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስትራቴጂው ከተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ አማካሪዎች ጋር ከተጀመረ አንድ ዓመት ማስቆጠሩን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ የመጀመሪያው የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ስትራቴጂ በ2002 ዓ.ም የተሰራ ሲሆን፤ ሁለተኛውም በ2007 ዓ.ም ተሰርቷል። ይህ ስትራቴጂም የቀደሙትን በመሞርከዝ የተሰራ ሲሆን፤ ለአምስት ዓመታት የተሰሩ ስትራቴጂዎችን በጥልቀት በመመልከት ወደፊት አሻግሮ ለማየት የሚያስችል ነው።

ስትራቴጂው ቀደም ካሉት ስትራቴጂዎች አንጻር ሲታይ ሰፋ ተደርጎ የተሰራ እና በቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱ የምትመራበት መሆኑን ጠቁመዋል። አሁን ላይ ስትራቴጂውን ከክልሎች፣ ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ ከግል ዘርፉ ለተወከሉ እና ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ የመጨረሻ ግብዓት ለመሰብሰብ መቻሉንም ያመላክታሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ስትራቴጂዎችና የመንግሥት እቅዶችን፣ (የአሥር ዓመቱን መሪ እቅድ፣ ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ፣ አምስት ዓመቱን አገር በቀል የኢኮኖሚ እቅድ እና ሀገሪቷ የምትመራባቸው እቅዶች በመመልከት የተሰራ ነው። አሁን ላይ ከታችኛው ቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው አካል ድረስ ያሉ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን እርስ በርሳቸው በማገናኘትና መረጃ በማለዋወጥ ለኀብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ትስስር ለመፍጠር ይጠቅማል።

‹‹ስትራቴጂው ሲሰራ የመንግሥት እቅዶችን፣ በየእያንዳንዱ መስሪያ ቤት እና በክልሎች ያለውን የቴክኖሎጂ አፈጻጸም በተመለከተ ጥናት በማድረግ፣ የዓለም አገራት ተሞክሮ እና የአገልግሎት ተጠቃሚውን ማኅበረሰብ መረጃ በመሰብሰብ ስትራቴጂውን ለመንደፍ ተሞክሯል›› ይላሉ። ከዚህ በፊት ለሚመለከታቸው አካላት የቀረበና ግብዓት የተሰበሰበት መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ለማጠቃለል የሚያስችል ግብዓት መገኘቱን ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ስትራቴጂው በአራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል። የመጀመሪያው መተግበሪያ (አፕሌኬሽን) ነው፤ አሁን ላይ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አንድ አገልግሎት ለመስጠት የሚጠቀሙት መተግበሪያ እንደየዘርፉ ይለያያል። እያንዳንዱ የመንግሥት መስሪያ ቤት የየራሱን መተግበሪያ በመስራት እየተጠቀመ ነው። ስትራቴጂው እነዚህን በምን መልኩ እርስ በርስ ማስተሳሳር ይቻላል? በሚቀጥሉት ጊዜያት እንዴት መቀጠል ይገባል? የሚለውን ማመላከት ያስችላል።

መተግበሪያዎች ስታንዳርድ ወጥቶላቸው በስታንዳርዱ መሰረት እንዲሰሩ ያስችላል። መንግሥት ለመተግበሪያ የሚያወጣውንም ወጪ በእጅጉ ይቀንሳል። ምክንያቱም ሁሉም መስሪያ ቤቶች የተለያዩ መተግበሪያዎች በሚያበለጽጉበት ጊዜ ብዙ ያስወጣል። መተግበሪያዎችን እየተጋሩ የሚሰሩ ከሆነ ግን የግድ በስታንዳርድ መመራት ስለሚጠበቅባቸው ወጪ ያስቀራል ሲሉ አብራርተዋል።

ስትራቴጂው ሁለተኛ ትኩረት ያደረገበት ጉዳይ ደግሞ መሠረተ ልማት ነው። መሠረተ ልማት በመዘርጋት የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን በኔትወርክ ማገናኘት ነው። ለአብነት አሁን ያለው ወረዳ ኔት የሚባለው ወረዳዎችን ከፌዴራልና ከክልል መንግሥት ጋር የሚያገናኝ መሰረተ ልማት ነው። ሌላኛው ደግሞ መረጃዎች የሚቀመጡበት ቋት (ዳታ ሴንተር) የመሳሳሉ ለመገንባት ምን መስራት አለበት የሚለውን በሰፊው የሚያሳይ ነው። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት መንግሥት በገነባቸው ዳታ ሴንተሮችም ይሁን በወረዳ ኔት መስራት የሚገባቸውን ሥራዎች ያመላክታል።

ሦስተኛው ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉት ነገሮች (ኢንኤብለር) እና በቀጣይ መንግሥት ለኀብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ምን ማድረግ አለበት? የሚለውን ይመለከታል። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚቀየሩ ፖሊሲዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ መሻሻል ያለባቸው የሕግ ማዕቀፎች ሊኖሩ ይችላሉ። የመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኞች በቴክኖሎጂ የተሻለ እውቀት እና የአሰራር ልምድ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው። በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) እንዴት ማሻሻል ይቻላል የሚለውን የሚዳስስ ነው። ምክንያቱም በተደረገው ጥናት እንደሚያመላክተው ብዙዎቹ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው ከተመረቁ በኋላ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ወደፊት ሲሄዱ አይስተዋልም።

ይህም ወደፊት ለመጓዝ የሚያስችል እወቀት እንዲኖራቸው፣ ማበረታቻ ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ምን መስራት ያስፈልጋል የሚለው ለማየት ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪም የግሉን ዘርፍ ከመንግሥት የቴክኖሎጂ ማደግ አቅም ጋር እንዴት አጣጥሞ ማስቀጠል ይቻላል? የግሉ ዘርፍ በምን መልኩ ሊሳተፍ ይችላል? እንዴት ማበረታታት ይቻላል? ለሚሉት ሀሳቦች ምላሽ የሚሰጥም ይሆናል።

ተመሳሳይ የትምህርት ተቋማት መንግሥት በቴክኖሎጂ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ በኩል እንዴት መርዳት እንደሚችሉ፣ ጥናቶችን በማካሄድም ሆነ ስርአተ ትምህርቱን በማሻሻል ተማሪዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲላበሱ በማድረግ በኩልም ብዙ ሥራዎች እንደሚጠበቅባቸው ይጠቁማሉ። አሁን ላይ ያሉት ጥናቶች የሚያሳዩት ቴክኖሎጂ በጣም እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ ስርአተ ትምህርቱ ግን ከዚህ እኩል መሄድ እንዳልቻለ ያመለክታሉ።

አራተኛውና የመጨረሻው ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች የተካተቱበት ነው። ከእነዚህም መካከል ዋንኛው ገንዘብ ነው። ኮምፒዩተር ለመግዛት፣ ዳታ ማዕከላትን ለማሻሻል፣ የሰው ኃይል ለማሰልጠን፣ የግሉን ዘርፍ ለማበረታታና መሰል ሥራዎች ለመስራት የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች ይጠቁማል።

ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የቀጣናዊ ትስስር አገራትን እርስ በርስ የሚያገናኝ ነው። በተለይ የአፍሪካ ሀገሮች በብዙ መልኩ እርስ በርስ የሚገናኙ ናቸው፤ ወደፊትም ትስስሩ በጣም እየሰፋ ሊመጣ ይችላል፤ ይህን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰራ ነው።

‹‹ስትራቴጂው ዓለም በዲጂታል ቴክኖሎጂው እየደረሰችበት ያለውን በመመልከት በሁሉም ዘርፍ ወደፊት ለማየት እንዲቻል ተደርጎ የተቀረጸ ነው›› የሚሉት አስተባባሪው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የሚያስችልና ዲጅታል ኢትዮጵያን የበለጠ የሚያስፋፋ መሆኑን ይገልጻሉ። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እየተከለሰ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ይህንን አካቶ የያዘ እንደሆነም አመላክተዋል።

ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሰው ኃይል ስልጠና፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ትስስር፣ ወጣቶች በቴክኖሎጂ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ እና መሰል ሥራዎችን ያካተተ መሆኑንም አንሰተዋል። ይህ ስትራቴጂ በዲጅታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትኩረት ከተደረገባቸው በአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመጨመር ዲጂታል ኢትዮጵያ አንዱ ክፍል የሆነው የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ስትራቴጂ ለማዳበር በስፋት ለማየት የሚያስችል መሆኑንን ያመላክታሉ።

ስትራቴጂ በቀረበባቸው መድረኮች ጥሩ የሚባሉ አስተያየቶችና ግብዓቶችን መሰብሰብ መቻሉን የቴክኒክ አስተባባሪው የሚገልጹት። በቀጣይ ስትራቴጂውን በማጠናቀቅ ለሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እንደሚያስረክቡና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ ማስተባባሪያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ብሩህተስፋ ታዬ በበኩላቸው፤ የኤሌክትሮኒክ ስትራቴጂ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል መሆኑን ይናገራሉ። ስትራቴጂው ስለዳታ፣ መተግበሪያ/አፕሊኬሽን ልማት/ እና በአጠቃላይ ዲጅታላይዜሽን በተመለከተ አሁን የት ነን፤ በቀጣይ የት መድረስ አለበን፤ በዚህ ሂደትስ ምን መስራት ያስፈልጋል የሚሉት ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ነው ይላሉ።

አሁን ላይ ጥናቱን ለማጠናቀቅና ስትራቴጂውን ወደ ተግባራ ለማስገባት የመጨረሻውን ግብዓት መሰብሰብ የተቻለ መሆኑ ይገልጻሉ። የስትራቴጂው ዓላማ በአገሪቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ የዲጂታል ሥራዎች ከየት ተነስተው ወዴት መድረስ እንዳለባቸው ለማሳየትና ለመጠቀም ያለመ ነው። በጥናቱ ቀደም ሲል የተሰሩት ሥራዎች፣ የሌሎች አገራት ተሞክሮዎችንና ተጠቃሚውን ኀብረተሰብ አስተያየት ለማካተት ተችሏል። በእነዚህ ጉዳዮች መነሻነት በአገሪቱ በቀጣይ አምስት ዓመታት በዲጅታላይዜሽን የሚሰሩ ሥራዎችን አካትቶ የያዘ ነው።

አቶ ብሩህተስፋ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ በ2010 እና በ2015 የተሰሩ ሁለት ስትራቴጂዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ እነዚህ ስትራቴጂዎች የተሰሩባቸው ዓላማዎች እንዳሉ ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ሥራዎች ሳይሰራባቸው የቀሩበትና እምብዛም ውጤታማ ያልሆኑ መሆናቸው ይናገራሉ። ይህ ሦስተኛው ስትራቴጂ ግን፤ የበፊቶቹ ጥናቶች ውጤታማ ያልሆኑባቸውን ምክንያቶች በማጥናት ወደፊትም መደረግ ያለበትን አካትቶ የተዘጋጀ መሆኑን አመላክተዋል።

የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ስትራቴጂና የኢንተር ፕራይዝ አርክቴክት ሰነድ በአንድ ላይ የሚዘጋጅ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ስትራቴጂ ተግባራዊ ሲደረግ የሚሰሩ ሥራዎች በጥናት ላይ የተሞረኮዙና ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው የሚጓዙ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን አቶ ብሩህተስፋ አስታውቀዋል፤ መንግሥት እንደ አንድ ተቋም ሆኖ በቅንጅት የሚመራበት መንገድን የሚያመቻች እንደሆነ ይገልጻሉ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ክልሎችና ተጠሪ ተቋማት ተቀናጅተው የሚሰሩበት ስለሚሆን ሁሉም እንደ አንድ ሆኖ አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ለአብነት አንድ ህንጻ አርክቴክቸር ተሰርቶ ሁሉንም በአንድ በማምጣት እንደ አንድ ሆኖ የሚያገለግል ነው።

ስትራቴጂው ለዜጎችና ለተጠቃሚዎች፣ ለንግድ ተቋማት እና መንግሥታዊ ላልሆኑ እና ለመሰል ተቋማት አገልግሎትን በተቀናጀ፣ ወጪን በሚቆጥብና ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚሰጥበትን መንገድ ያመቻቻል።

በስትራቴጂው የመጨረሻ ማጠናቀቂያ ወርክሾፕ ጥሩ ግብዓቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ስትራቴጂውን የማዘጋጀቱን ስራ በፍጥነት ለማጠቃለል እንደሚያስችል ተናግረዋል። ስትራቴጂው ተግባራዊ ሲደረግ በቀጣይ ጊዜያት በአገሪቱ በዲጂታል ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎች ውጤት የሚያመጡ እንዲሆኑ ያስችላል ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You