የወላይታ ዞን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከሰላም አኳያ ፈተና ውስጥ እንደነበር የሚታወስ ነው። የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ያልነበረበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ከ”ክልል እንሁን” ጥያቄ ጋር ተያይዞ የመጣ ሲሆን፤ ለጥያቄው ምላሽ እስከሚገኝም በሕዝቡ መካከል በብዙ መልኩ ሰላም ታጥቶ ቆይቷል። ዛሬ ግን የ“ክልል እንሁን” ጥያቄው ምላሽ አግኝቶ የወላይታ ሶዶ ከተማ የደቡብ ኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ በመሆኗ ለሰላም መስፈን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በዞኑ የሰፈነው የሰላም ሁኔታ ብዙዎቹን ባለሀብቶች ወደአካባቢው መሳብ በመቻሉም ልማት በመፋጠን ላይ ይገኛል።
ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በመስክ ስራው አንዱ መዳረሻው ወደሆነው ወደዚሁ የወላይታ ዞን አቅንቶ በነበረበት ወቅት ከዚሁ ከልማት ጋር በተያያዘ እና በዞኑ እየተካሔደ ባለው የሰላም፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አስመልክቶ ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ያለው የሰላም ሁኔታና እየተካሔደ ያለው ልማት ምን ይመስላል?
አቶ ሳሙኤል፡– በዞኑ የ2016 በጀት ዓመት በመንግሥት የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦች አሉ። እነዚህም በጥቅሉ ስናያቸው የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፍ ናቸው ማለት ይቻላል። በእነዚህ ዘርፎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል በቂ እቅድ ታቅዶ በተግባር እየተተረጎመም ይገኛል። በተለይም ያለፈውን 2015 በጀት ዓመት ፈትሸን እና የዘንድሮውንም እቅድ በዝርዝር ገምግመን የነበረውን ጉድለት የእቅድ አካል በማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ ፈጻሚ አካላት ጋር መግባባት ላይ በመድረስ ወደሥራ መግባታችን የሚታወቅ ነው። ወደሥራ የገባነው የሕዝባችንን የመልማት ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ ነው።
እንደ ሀገር፣ ክልል እና ዞን መሰረታዊ ችግሮች ናቸው ተብለው የተለዩ ጉዳዮች አሉ። እነዚህም አንደኛው የሕዝብ ሰላምና ደህንነት፤ ሁለተኛ የኑሮ ውድነት፤ ሶስተኛው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ አራተኛው የሥራ አጥነት ችግር እና አምስተኛው የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ ናቸው። እነዚህ በዋናነት እንደ ሀገርም እንደ አካባቢያችን የሕዝብ ጥያቄ የነበሩ ናቸው። በመሆናቸውም የእቅድ አካል ተደርገው የተያዙ ሲሆን፣ እነርሱን መፍታት የሚያስችል የመውጫ መንገድ ሊሆን የሚችል ስትራቴጂ ቀይሰን ወደ ተግባር ገብተናል።
የመጀመሪያው የሕዝብን ሰላም እና ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ ነው፤ ይህ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ዜጎች በነጻነት ወጥተው ሰርተው መግባት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የግድ ይለናል። ወላይታ አጠቃላይ የሰላም ቀጣና እንዲሆን በቂ ዝግጅት ተደርጎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው። ከዚህም አንዱ ከጸጥታ ተቋማት፣ ከፖሊስ፣ ከሚሊሻ እና ከአጠቃላይ ከሕዝቡ ጋር የሚደረግ ውይይት ነው። ይህ የሚደረገውም የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሲሆን፣ ሕዝቡ ራሱ የሰላም ባለቤት እንዲሆንና ሰላም በራሱ ከራስ እንደሚጀምር ግንዛቤ የመፍጠር ውይይት ተካሂዷል። ከሰላም ጋር ተያይዞ የሰላም አደረጃጀት ከገጠር እስከ ከተማ ተዋቅሯል። ከዚህም የተነሳ ዜጎች 24 ሰዓት በነጻነት የሚንቀሳቀሱባት ዞን ለመፍጠርም በቂ ዝግጅት በመደረጉ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
የጸጥታ የስጋት ምጣኔ ከመቀነስ አኳያ የተሰራው ሥራ ሰፊ ነው። ስለዚህ የወንጀል ስጋት ያለባቸው ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ተለይተው ተሰርቶባቸዋል። ወደ 153 ቀበሌዎች ከወንጀል ስጋት ነጻ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። እነዚህ በወረዳዎች ውስጥ ያሉ ቀበሌዎች ከዚህ በፊት የወንጀል ስጋት ያለባቸው ናቸው። በቀበሌዎቹ በስጋትነት የሚጠረጠሩ ግለሰቦች በመኖራቸው ዝርፊያና ንጥቂያ የነበረባቸው ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ግን እነዚህ ቀበሌዎች ለሀገር ጭምር ተሞክሮ በሚሆኑባቸው አይነት ሁኔታ ከወንጀል ስጋት ነጻ መሆን የቻሉ ናቸው። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተሞክሮ ከዞናችን መቅሰም ችለዋል። ስለዚህ በዞናችን አንጻራዊ ሳይሆን አስተተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ የወንጀል ስጋት ያለባቸው ቀበሌዎች ተለይተው ከ150 በላይ ቀበሌዎች ከወንጀል ስጋት ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።
አሁን ባለን ተጨባጭ መረጃ አጠቃላይ የወላይታ ዞን ከየትኛውም አካባቢ ማንም በነጻነት የሚንቀሳቀስበት የሰላም ቀጣና ብሎም የሰላም ተምሳሌት መሆን ችሏል። ሶዶን ብንወስድ የክልሉ የአስተዳደርም የፖለቲካም መቀመጫ ናት። ስለሆነም ይህ ታሳቢ ተደርጎ ለነዋሪውም ሆነ ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል። ከዚህ የተነሳ በስድስት ወር አፈጻጸም ግምገማችን ወላይታ ከስጋት ነጻ የሆነ ዞን ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሀገራችንን ሁኔታ ስናስተውል የሰላሙ ሁኔታ የሚያሰጋ መሆኑ የተሰወረ አይደለም። ለምሳሌ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂ ቡድኖች አሉ። በሰሜኑ አካባቢም ሆነ በኦሮሚያ አካባቢ የሰላም ጸር የሆኑ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ደግሞ የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ ናቸው። ይሁንና በእኛ አካባቢ እንዲህ አይነት ነገር የለም። ስለዚህ ሁሉም የየራሱን አካባቢ ሰላም እንዲሆን በመስራት የሀገርን ሰላም ማረጋገጥ የግድ ይላል።
ወላይታ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት እንዲህ ሰላሟ የተጠበቀ አልነበረም። የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያንጸባርቁ ነዋሪዎች ስለነበሩ ከፍተኛም ስጋት የሚስተዋልባት ነበረች። በተለይም በ2013 ዓ.ም ክልላዊና ሀገራዊ ምርጫ በሚደረግበት ወቅት ከፍተኛ ስጋቶች ነበሩ። ይሁንና ከሕዝብ ጋር በተፈጠሩ መድረኮች ላይ መግባባት በመደረሱ ወደተሻለ የሰላም ቀጣና ማምጣት ተችሏል፤ ከዚህ የተነሳም አካባቢው ሁሉ የሰላም ተምሳሌት ለመሆን በቅቷል። እንዲያም ሆኖ በሰላሙ በኩል ሁሉም ተሰርቶ አልቋል ማለት አይደለም። አሁንም እየተሰራ ይቀጥላል።
ዋናው ነገር ሰላም ነው፤ ሰላም ካለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል። ሰሞኑን ደግሞ እንደሚታወቀው በዞናችን በወላይታ ሶዶ ከተማ ከየካቲት 9 እስከ 15 ቀን 2016 ዓ.ም “የዘመነ ከተማ ለብልጽግና ጉዞ” በሚል መርህ እየተካሔደ ባለው የሀገር አቀፍ የከተሞች ትብብር ፎረም ላይ ከመላ የሀገሪቱ ከተሞች የተውጣጡ ከ160 በላይ ከተሞች ተሳታፊ የሆኑበት ነው። በተጨማሪም ከሃያ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ድርጅቶች ተሳታፊ ናቸው። ከተማዋም የምታስተናግደው ከሃያ ሺ በላይ እንግዶችን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ዜጋው እየተፈተነ ያለው የኑሮ ውድነት ነው፤ ከዚህ አንጻር ዞኑ ምን ይመስላል?
አቶ ሳሙኤል፡– በእርግጥ የኑሮ ውድነቱ በዞን ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም፣ እንደ አህጉርም ሆነ እንደዓለም አቀፍ ፈታኝ የሆነ ችግር ነው። አሁን ያለው የዓለም አቀፍ ሁኔታ በራሱ ተለዋዋጭ ሆኗል። የፖለቲካው ሁኔታ አስገራሚ በሆነ መልኩ ተቀያያሪ ነው። ለአብነት ያህል ለመጥቀስ ሩሲያ ከዩክሬን፣ እስራኤል ከሐማስ ጋር እያደረጉ ያለው ጦርነትና ከዓመታት በፊት የነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ሁሉ ተደማምሮ ዓለምን ጫና ውስጥ የከተታት መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው።
የኑሮ ውድነቱ በዞን ደረጃ ለመቋቋም ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችል የግብርና ምርታማነት መጨመር ዋናው ነው። ግብርና ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሥራ ሳይሆን የግሉን ዘርፍም በማነቃቃቱ በኩል የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው።
ለምሳሌ ከምርታማነት አኳያ በግብርና በመኸር ወቅት በዞናች ከ110 ሺ ሔክታር በላይ መሬት ላይ የሰብል ልማት ማልማት ተችሏል። ከዚያም ወደ 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማግኘት ችለናል። ይህ ብቻ ሳይሆን መስኖ ላይ ከ35 ሺ ሔክታር መሬት በላይ ታቅዶ ወደ 37 ሺ ሔክታር መሬት ላይ በዋና ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የበጋ ስንዴን ጨምሮ ማልማት ችለናል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንሼቲቭ የሆነው አንዱ የበጋ ስንዴ ነው፤ ከዚህ ቀደም ጾሙን የሚያድር መሬት አይኑር የሚለውን የእርሳቸውን መርህ በመያዝ በጋ ላይ የውሃ ገብ መሬት በአግባቡ ታርሶ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ይገኛል። ስለዚህ ገበያን ለማረጋጋት አንዱ እና ዋናው ነገር ግብርናን ማዘመን ሲሆን፣ እዚህ ላይ እየተሰራ ነው። ይህን በማድረጉ በኩል ስትራቴጂዎችን ተከትለን እየሰራን ባለው ሥራ ብዙ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ እንገኛለን።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ እንደ አማራጭ የተጠቀምነው የሰንበት ገበያን ነው። የሰንበት ገበያ በዞኑ በሚገኙ ከተሞችና በወረዳ ከተሞች ሸማችና አምራች ቀጥታ የሚገናኝበትን ሰንሰለት መፍጠር ነው። ከዚህ የተነሳ በመሃል ደላላ ስለማይኖር የደላሎች ሰንሰለት የተበጠሰበት አሰራር ነው። ይህ የሰንበት ገበያ በገበያው ላይ ያለውን መረጋጋት በስፋት ያመጣ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ሌላው የኑሮ ውድነቱን ለመቅረፍ የወሰድነው ርምጃ ሕገ ወጥ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግን ነው። የምርት እጥረትን መነሻ አድርገው አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የሆኑ የዋጋ ጭማሪ ወይም ሰው ሰራሽ የሆነ የኑሮ ውድነት እንዳይፈጥሩ ቁጥጥር የሚደረግበትን ሥርዓት ዘርግተን በዛ ልክ እየሰራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ከሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ ዞኑ የሥራ እድል እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ሳሙኤል፡- ሥራ አጥነት እንደአጠቃላይ የሀገርም ችግር ጭምር ነው። ይሁንና እኛ አካባቢ ደግሞ
ችግሩ ትንሽ ከፍ ያለ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አንደኛ የተማረ የሰው ኃይል በተለይም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲግሪና በዲፕሎማ የተመረቁ ከ33 ሺ በላይ የሰው ኃይል ያለበት ዞን ነው። ዘንድሮን ልዩ የሚያደርገው አጠቃላይ 98 ሺ 471 የሥራ አጥ ቁጥር መለየት መቻላችን ነው። ይህ ተለይቶ በቋሚና በጊዜያዊ መንግሥት ባመቻቸው የሥራ አማራጮች ማለትም የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አማካይነት ወደታች የወረዱ የወጣቶች ፓኬጆች አሉ፡፡
አንደኛው በአስተሳሰብ ላይ መስራትን የሚመለከት ነው። የትኛውንም የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ላይ ወጣቶች ተሳትፈው የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ እና ሌላውንም ማሳተፍ እና መሸከም የሚችል አቅም እንዲፈጥሩ ስትራቴጂ ተቀይሶ ሥራ በመሠራት ላይ ነው። ከእነዚህ ውስጥ በዚህ ባሳለፍነው ስድስት ወር ውስጥ እንደ እኛ ዞን ወደ 28 ሺ 993 ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነት የሥራ እድል ሊፈጠር ችሏል፡፡
ለዚህ ሥራ የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት እንዲሁም አንዳንድ የግሉ ዘርፍም የሚያበረታታ ሥራ መጀማመራቸው የሚጠቀስ ነው። በተለይ በገጠር እርሻ በኢንቨስትመንት ላይ የሥራ እድል እንዲፈጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። በአነስተኛ እና በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በመደረጉም ጭምር ነው።
ሥራ አጥነትን ለመቀነስ በመንግሥት ብቻ የሚደረገው ጥረት በቂ አይደለም። የግሉ ዘርፍም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ማበረታታት አስፈላጊ ነው። በአሁኑ ወቅት እንደሚታውቀው ቅጥር የለም፤ የቅጥር አስተሳሰብን ሊቀንስ የሚያስችል ስራ በራሱ በአስተሳሰብ ላይ እየተሰራ ነው። በዚህ ላይ የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት አሉ። በጥቅሉ ግን ሥራ አጥነት እንደዞናችን ቀላል የሚባል አይደለም። ምክንያቱም ከፍ ያለ የሥራ አጥ ቁጥር የያዘ ዞን ስለሆነ በዚህ ላይ እንደዞን ሰፊ የሆነ ራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ምን ይመስላል?
አቶ ሳሙኤል፡– የተቋማት አገልግሎት ሲባል ለሕዝቡ የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን፣ የአገልግሎቱ አሰጣጥ ሕዝቡን ሊያስደስት አሊያም ሊያምርር የሚችል ነው። አንደኛ ራሱ የአገልግሎት አሰጣጥ የቅልጥፍና ጉዳይን የሚመለከት ነው። የአገልግሎት ቀና መሆን ተገልጋዩ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የአገልግሎት አሰጣጥ ነው። ከዚህ አንጻር ትልቅ ስራ እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ አኳያ ተቋም ከሚመሩ አካላት ጋር በስፋት ውይይት ተደርጎ መግባባት ተፈጥሮ በተለይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚታዩ አገልግሎትን ወደ ገንዘብ የመቀየር አስተሳሰቦችን የማክሰም ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡
ከዚህ ቀደም ሕዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሚማረርባቸው አንዱ ተቋም ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ነበር። በዚህ ተቋም በተለይ ከመሬት እና ሕገ ወጥነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ነበሩ። ከሕገ ወጥነት ግንባታ ጋርም የተያያዙ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ግን ያንን ችግር ነቅሰን አውጥተን በችግሮቹ ዙሪያ እየሰራን እንገኛለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ልማትን በአግባቡ ለማሳለጥ የከተማ ገቢ ወሳኝ ነው፤ ከዚህ አንጻር የገቢ አሰባሰቡ ምን ይመስላል?
አቶ ሳሙኤል፡– ከገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ዘንድሮ በተለይ ታማኝ ግብር ከፋይ ከመፍጠር አኳያ ሰፊ ስራዎች ተፈጥረዋል። ከዚያ ጎን ለጎን ደግሞ የገቢ ስወራ ላይ የተሳተፉ አካላት ላይ ርምጃ የወሰድንበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በሶዶ ከተማ ሰሞኑን ከ80 በላይ በሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ ወስደናል። በአረካ ከተማ ደግሞ ከ25 ባላይ ተቋማት፣ በገሱባ ከ15 በላይ ተቋማት ርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆኑ፣ አጠቃላይ እንደዞን ሲታይ ደግሞ ከ100 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ ወስደናል። የምንወስዳቸው ርምጃዎች ሁለት አይነት ናቸው። አንደኛው አስተዳደራዊ ርምጃ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሕጋዊ ርምጃ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ምን አይነት እንቅስቃሴዎች አሉ? ኢንቨስተሮችንስ የሚስብ ምን የተዘጋጀ ነገር አለ?
አቶ ሳሙኤል፡- ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት በአግባቡ የተገመገሙ ወደ 53 ፕሮጀክቶች አሉ። ፕሮጀክቶቹ ወደስራ እንዲገቡ ፈቃድ የተሰጣቸው ናቸው። እነዚህ ፕሮጀክቶች ጠቅላላ ያስመዘገቡት ካፒታል ሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን፣ 680 ሚሊዮን 185 ሺ 901 ብር ነው። እነዚህም ባለሀብቶች ከሚመለከተው አካል ፈቃድ እንዲያገኙ የተደረጉ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም ወደስራ የገቡና ገና በሒደት ላይ ያሉ አሉ፡፡
በዞኑ እየተከናወነ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ካለፈው ዓመት የኢንቨስትመንት ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም ጨምሯል። ለአብነት ያህል በገጠር እርሻም ሆነ በከተማ አገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጭምር መሻሻል አሳይቷል። እንደዞን ሲታይ ይህ ትልቅ ለውጥ ያሳየ ነው፡፡
የኢንቨስትመንት ፍላጎት ጨምሯል የማለቴ ምስጢር አንዱ ምቹ ሁኔታ የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ነው። ከዚሁ ከክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ ወላይታ ሶዶ የአስተዳደርና የፖለቲካ ማዕከል መሆኗ የሚታወቅ ነው። ከተማዋ ደግሞ ቀደም ሲልም ሰባት የመግቢያና የመውጫ በር ያላት ናት። ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባትም ጭምር ናት። በተለይም ከ13 በላይ የግል ባንኮች እንዲሁም ከሁለት በላይ የመንግት ባንኮች ያሉባት መሆኗ የገንዘብ ዝውውሩን የተሳለጠ የሚያድርግ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሔድበት ዞን ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በእጅጉ የተረጋጋ ነው። ከዚህ የተነሳም በአካባቢው የተፈጠረው ሰላም አስተማማኝ ነው። ከአካባቢው ሰላም መሆን ጋር ተያይዞ ለዳያስፖራው፣ ለአገር ውስጡና ለውጭ አገር ባለሀብት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የሚይዘውም የዳያስፖራው ማኅብረሰብ ነው።
ዳያስፖራው ከተሰማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ የሆቴል ቱሪዝም፣ የማኅበራዊ አገልግሎትና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ተጠቃሽ ሲሆኑ ተሳትፎውም በማደግ ላይ ይገኛል። በሌላ በኩል በማኑፋክቸሪንግ አግሮፕሮሰሲንግ ላይ እንዲሰማሩም ዘርፎች ተለይተውና የቢዝነስ አዋጭነታቸው ታይቶ እንዲገባባቸው እየተሰራ ነው፡፡
ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር ተያይዞ መሬት ወስደው አጥረው ያስቀመጡ አካላትን መለየት ተችሏል። በተለይ ባለፈው ዓመት ወደ 19 ፕሮጀክቶች ላይ ከባድ ማስጠንቀቂያ መጣል ተችሏል። በቀጣይም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማያለሙ ከሆነ የመቀማት እንቅስቃሴ ይጀመራል፡:
በዞናችን መሬትን ለኢንቨስትመንት ልማት መስጠት ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ውጤታማ መሆናቸውንም እንከታተላለን። የገበያውን ሁኔታ ምን ያህልስ ነው? የሚለውም የሚታይ ይሆናል። በዚህ ጉዳይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተናል፡፡
ይህን አስመልክቶ ዞናዊ የኢንቨስትመንት ፎረም የተካሄደ ሲሆን፣ በኢንቨስትመንት የተመዘገበው ውጤትም ምን ያህሉ ሕዝቡን አጋዥ እየሆነ ነው የሚለውን ተመልክተናል። በተመሳሳይ ሌሎችም ባለሀብቶች በተረከቡት ቦታ በአፋጣኝ ማልማት እንደሚጠበቅባቸውም አቅጣጫ ተቀምጧል። እንዲያም ሆኖ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መሰረተ ልማት ወሳኝ ነው፤ በአሁኑ ወቅት በዞኑ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ስራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ይገኛል፡፡
በዞኑ ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር አለ። ይህ የስራ አጥ ቁጥር ቀላል ግምት የሚሰጠው ባለመሆኑ ሥራ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት ወሳኝ የሆነው ኢንቨስትመንት ወደ ዞኑ መሳብ ነው። ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ደግሞ ሰላምና መልካም አስተዳደር ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው። ወላይታ በአሁኑ ወቅት ከሰላምም ሆነ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ መሆን የሚችል ነው።
ከሰላም አንጻር ሲታይ በዞኑ የሚገኙ ቀበሌዎች ከወንጀል ስጋት ነጻ እንዲሆን በመሰራቱ የትኛውም አካል ከአንድ ስፍራ ወደሌላ ስፍራ በሰላም መንቀሳቀስና መስራት ይችላል። ከዚህ አኳያ በዞኑ ወደየትኛውም አቅጣጫ ቢኬድ ዝርፊያም ሆነ ንጥቂያ የሌለበት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል።
ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ከሕዝቡና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በስፋት ውይይት መደረጉ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት ግን ወላይታ በተለይ ከክልል ጥያቄም ጋር ተያይዞ ፈተናዎች የበዙበት ነበር። ባለፉት ጥቂት ጊዜያት በተደረገው ውይይትም ምክክርም ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየት ጀምሯል። በአሁኑ ወቅትም ዞኑን ከዚህ በበለጠ የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- መልካም አስተዳደርን በተመለከተ ምን እየተሰራ ነው? መሰረተ ልማቱስ በምን አይነት ሁኔታ እየተተገበረ ነው?
አቶ ሳሙኤል፡- በሁሉም አካባቢ በቁጥር ከፍ ያሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሉ። የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት ጥያቄዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይም ጥያቄ አለ። ከመንገድ አንጻር ሲታይ የፌዴራል የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች በጥሩ ሁኔታ በመከናወን ላይ ናቸው። ለዘመናት ጥያቄ ሲጠየቅ የነበረው በፌዴራል መንገድ ታቅዶ የሶዶ ከተማ ከሌዊ እስከ ግብርና ኮሌጅና አረካ መውጫ ያሉ መንገዶች ከሰሞኑን የሳይት ርክክብ ተደርጎ ካሳ እየተገመተ ነው። የለውጥ መንገድ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ ወደተግባር እየገባ ነው። ከዚህ አኳያ ይህ የመፍትሔ ያገኘ ጉዳይ ሆኗል። ሌላ የሶዶ 84 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ በጥሩ ሁኔታ ሊጠናቀቅ የደረሰ ሲሆን፣ ከ90 በመቶ በላይ ደርሷል። ሌላው በወላይታ ዞን ከዲምቱ እስከ ብላቴ የልዩ ዘመቻ ማሰልጠኛ ያለው 27 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ስራው ተጀምሯል። በዚያ ውስጥ ደግሞ የሚሊታሪና የሲቪል አውሮፕላን ማረፊያ በፌዴራል መንግሥት ታቅዶ ወደተግባር መግባት ችሏል። ከመንገድ አንጻር በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ ያለ ቢሆንም አሁንም የሕዝቡን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ መቶ በመቶ አርክቷል ማለት አይቻልም።
ከንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ጋር ተያይዞ በከተማ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 67 በመቶ ሲሆን፣ በገጠር ደግሞ 41 በመቶ ነው። የሕዝቡ አዳጊ ፍላጎትና አሁን ያለው አፈጻጸም ሲታይ ገና ብዙ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ የሚያመላክት ነው። ከዚህ የተነሳ በውሃው ዘርፍ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ጋር ተጋግዘን እየሰራን ነው። አጋር ድርጅቶች የሰሯቸው በርካታ ስራዎች አሉ። የዞናችን ነዋሪዎች ንጽህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት በአማካይ በቀን እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ይሄዳሉ። ከዚህ የተነሳ ብዙ ስራ ይጠብቀናል።
ከመብራት ጋር ተያይዞ ያለው አቅርቦት የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን በፌዴራል መንግስት፣ በኢትዮጵያ መብራት ኃይልና በደቡብ ዲስትሪክት ታቅዶ እየተሰራ ነው። ይሁንና ከፍተኛ ውስንነት አለ። እንደሚታወቀው መብራት ምግብም ውሃም በጥቅሉ ሁሉም ነገር ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ትልቅ የሕዝብ ጥያቄ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት የኃይል እጥረት የለብንም። የግቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አጠገባችን ነው። ነገር ግን ኃይሉን መሸከም የሚችሉ መስመሮች አለመኖራቸው ነው። ከዚህ አንጻር የተዘረጉ መስመሮችን የመቀየር ስራ እየተሰራ ነው። ይህ ከፍጥነት አኳያ ችግር አለ እንጂ በአሁኑ ወቅት ስራዎች ተጀምረዋል። እንዲያም ሆነ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ብለን ለይተናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያና በራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ ጋር የተደረገው የባህር በር ስምምነት ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፤ እርስዎ እንደ አንድ የዞን ዋና አስተዳዳሪና ዜጋ ይህን ስምምነትና ያልተገቡ አመለካከቶችን እንዴት ያዩታል?
አቶ ሳሙኤል፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ የባህር በር የነበራት ናት። ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የአሰብም የምጽዋም ባለቤት የነበረች ናት። ይሁንና በመሪዎች ጥፋት ይሁን በመሪነት ሚናቸው ውስጥ የነበረ ችግርም ይሁን ወይም ደግሞ የውጭ ኃይሎች ሴራም ይሁን በታሪኳ የባህር በር የሆነች አገር የባህር በር አልባ መሆኗ የመላ ኢትዮጵያውያንን ልብ የሰበረና ትልቅ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀ ነበር።
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፤ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ናት። ይህች ትልቅ አገር የባህር በር አልባ መሆኗ ሁሌም የሚያም ሲሆን፣ በዚያ ዙሪያም ሁሌ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀ እንደነበርም የሚታወስ ነው። በእኔ አተያይ የነበረንን እንድናጣ ያደረገን የመሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት ያመጣው ችግር ይመስለኛል። በዚህም ሃብታችንን ለማጣት ተገድደናል።
ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ያሏት ናት። ስለዚህ የባህር በር ለማጣታችን አንዱ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ ሊሆን ይችላል የሚል አተያይ አለኝ። በአሁኑ ወቅት ግን በጠቅላይ ሚኒስትራችን እልህ አስጨራሽ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተነሳ ኢትዮጵያ ራስ ገዝ ከሆነችው ሱማሌ ላንድ ጋር የባህር በር እንድናገኝ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ላይ መፈረም መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
እንደ ዞንም የስምምነት ፊርማ በተካሔደ ዕለት የዞኑ ሕዝብ ደስታውን አደባባይ በመውጣት ገልጿል። እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ድረስም በጎዳና ላይ ቆይቶ ስሜቱን ማሳየት ችሏል። ይህ የመግባቢያ ሰነድ አገራችንን ካለችበት አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስፈነጥራት ነው። የዘመናት የሕዝባችን ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ነውም ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ይህን ያመጣው የዲፕሎማሲያዊ ሒደቱ ስኬታማ በመሆኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉትም ምንም አይነት የጦርነት አታሞ ሳይጎሰም፤ አንድም የጥይት ድምጽ ሳይሰማ በእልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲ ትግል የመጣ ለውጥ ስለሆነ መሪያችን ትልቅ አክብሮት ይገባቸዋል ማለት እወዳለሁ። በቀጣይም ይህ የባህር በር ስምምነት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
ኢትዮጵያ ያደረገችው ስምምነት በተሟላ ሁኔታ ወደተግባር እንዳይሸጋገር በተለየ ሁኔታ አቅደው የሚንቀሳቀሱ አይጠፉም። የሚያሴሩ አካላት አይኖሩም ብዬም አላስብም፤ አሉ። በመሆኑም ይህንን የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ነገር ግን ሱማሊያውያን ኢትዮጵያ እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ናት። ስለዚህ ይህ አይነት ስምምነት በጋራ መልማት ላይ የተንተራሰ እንደመሆኑ የየትኛውንም አካል ሊያስቆጣው አይገባም ባይ ነኝ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ግን ለዚህ ስምምነት ስኬት ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል። ከዚህ በኋላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሱማሌላንድ ጋር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ሌላም የባህር በር የሚያስፈልጋት እንደመሆኑ ከሌሎችም ጋር ልትሰራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ሳሙኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2016 ዓ.ም