የአዲሱ ክልል የግብርና ልማት ተስፋዎች

በኢትዮጵያ በቅርቡ ከተደራጁ ክልሎች ማዕከላዊ ኢትዮጵያ አንዱ ነው። መቀመጫውን ሆሳህና ከተማ አድርጎ የተመሰረተው ይኸው ክልል የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፤ ባህሎች፤ ምቹ ስነ-ምህዳር፤ የተለያዩ አዝርዕቶችን ማምረት የሚያስችል የአየር ንብረትና ውብ የቱሪዝም መስህብ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት እንደሆነም ይነሳል። ክልሉ እንደ አዲስ ከተደራጀ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም ለለውጥ ታትሮ በሚሰራው አመራሩና ስራ ወዳዱ ማህበረሰብ በግብርና ልማት መስክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ይነገራል።

የክልሉ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት ከሰሞኑ በክልሉ እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል። በመስክ ምልከታቸው በተለይ በተቀናጀ የግብርና ልምት አመርቂ የሚባል ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑ ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ አመራሩ ባደረገው የመስክ ምልከታ በግብርና ለክልሉ ብልፅግና መሰረት የሚጥሉ ውጤቶች ተገኝተዋል።

የመስክ ምልከታው ዋና ዓላማ የነበረው ከፍተኛ አመራሩ በየደረጃው በተቀናጀ ግብርና ልማት ዘርፍ የታቀዱ እቅዶች የተሰሩበት መንገድ ምን ይመስላል? ምን ውጤት አመጡ? ምንአይነት ማነቆ ገጥሟቸዋል? ከአመራሩ ምን ይጠበቃል? የሚሉ ጉዳዮችን በተግባር ለማየት እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህ መሰረት የክልሉ ከፍተኛ አመራር 13 ቦታዎች ላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ልማት ሥራዎችን የተመለከቱ ሲሆን፤ በዋናነትም በተቀናጀ የግብርና ልማት በአነስተኛ አርሶ አደሮች እየለሙ ያሉ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማሳዎች የዘርፉን ምርታማነት ሥር ነቀል በሚባል ደረጃ ውጤት እያመጡ ስለመሆኑ መገንዘባቸውን ነው ያብራሩት። እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብትና በአካበቢ ጥበቃ፤ በአረንጓዴ አሻራ ስራዎችም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በሌላ በኩልም በግል ባለሀብቱ እየተሰሩ ያሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራዎች በመስክ ምልከታቸው የተካተቱ ሲሆን፤ ባለሀብቱ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ በተለይም አረንጓዴ አሻራ፤ በእንስሳት ሀብት ልማትና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ረገድ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የኢኮኖሚ ብልፅግና መርሀ ግብር መሳካት አወንታዊ ሚና የሚጫወት ነው፡፡

‹‹በመስክ ምልከታው በተለይ የግብርና ልማት ስራችን ውጤታማ ጉዙ ላይ እንዳለ በልበ ሙሉነት እንድንናገር አድርጎናል›› ያሉት አቶ ኡስማን፤ ለዚህም እንደማሳያ ሊቀርብ የሚችለው በርካታ ወጣቶች፣ ሴቶች አርሶ አደሮች ፤ የግል ባለሀብቶች የተሰማሩባቸው የበጋ ወቅት የግብርና ልማት ምርታማነት ከመቼው ጊዜ በላቀ ሁኔታ መጨመሩ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዋናነትም በመስኖ በማልማት ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ዝኩኒ፣ ሃባብ፣ ቃሪያ፣ ሌሎችም አሁን ገበያው ላይ እጥረት የሚታይባቸውና የኑሮ ውድነት የሚንፀባረቅባቸው የግብርና ውጤቶች ከፍተኛ የሆነ ምርት መሰብሰብ መቻሉና ወደ ገበያ መድረሳቸው አጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱ በዘላቂነት እንዲያድግ መሰረት የሚጥል መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

‹‹በክልሉ 13ቱም ቦታዎች በስፋት እያለሙ፤ ገበያውን እየደረሱ ነው›› የሚሉት አቶ ኡስማን፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ከ80 ብር በላይ ይሸጥ የነበረው ቲማቲም ከ10 እስከ 20 ብር ድረስ መውረዱን ይናገራሉ። አማራጮቹ በሌሎቹም ምርቶች ላይ የዋጋ መቀነስ እንደሚስተዋል ያነሳሉ። ነገር ግን የምርት መጨመር ማሳው ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አቶ ኡስማን ይገልፃሉ። ለብዙ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን፤ በርካታ ወጣቶች ግብርና ላይ ለመሰማራት ተስፋ ሰንቀው እየታተሩ ጊዜያቸውን፤ ጉልበታቸውን ትርፋማ ለማድረግ እያደረጉ ያሉት ጥረት የሚበረታታ እንደሆነም ያስረዳሉ። በክልሉ የተገኘው ውጤት ግብርና ለሀገራችን እድገት፤ የብልፅግና፤ የሥራ እድል ፈጠራ ዋነኛ መንገድ መሆኑን ያረጋግጣል ሲሉም ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል ወጣቶች ተደራጅተው በተደረገላቸው ትናንሽ የድጋፍ ማዕቀፎች ለብዙዎች ሥራ እድል መልሰው መፍጠር መቻላቻውን በጉብኝታቸው ማየታቸው ሌላው ተስፋ ሰጪ ጉዳይ እንደሆነ ያነሳሉ። አብነት አድርገውም ‹‹ጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ላይ አምስት ወጣቶች በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ተደራጅተው 30 ሄክታር ማሳ ላይ የተለያዩ የአትክልት አይነቶችን በመስኖ እንዲያለሙ ከ100 በላይ ሌሎች የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ፈጥረውላቸው በተስፋና በጉጉት እንዲሁም ወኔ በተሞላበት ሁኔታ ሲናገሩ ማየት እጅግ ያስደስታል፤ ግብርናችን የእድገታችን ተስፋ የሚለውን በደንብ ያንፀባርቃል›› ሲሉ ይጠቅሳሉ።

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ከፍራፍሬ ልማት አንፃር የክልሉ መንግሥት አዲስ ክልል፣ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ምዕራፍ፣ አዳዲስ አሰራሮችና ለአዳዲስ ውጤቶች በሚል ያቀዳቸው የ30/40 የፍራፍሬ ልማት እቅዶች አሉት። በተለይ ከዚህ ቀደም ሙዝ፣ ፓፓያ ተመርቶባቸው በማያውቅባቸው አካባቢዎች በስፋት ተመርቶ የአካበቢው አርሶአደሮች ገቢ ማመንጨት፣ ሀብት ማካበት፣ ለወጣቶች ሥራ መፍጠር የሚያስችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል። በተለይ የሙዝ ችግኝና የሙዝ ምርቱንም በመሸጥ ትልቅ መነሳሳት ፈጥሯል። ከሁሉ በላይ አዳዲስ የሙዝ ኮሪደሮችና መንደሮች የተፈጠሩበት ሁኔታ መኖሩ ከሀገር ውስጥ ገበያ ከማረጋጋት ባለፈ ለውጭ ገበያም ዋና አቅራቢ የሚሆንበት እድል ታይቷል።

በተጨማሪም ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተያይዞ ወጣቶች ተደራጅተው በሚሰሩባቸው አካባቢዎች በርካታ የፍራፍሬ ችግኝ እያለሙ፣ ምርጥ ዘር የሆነ አቦካዶ እያፈሉ ለአካባቢው አርሶአደሮች የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ማምጣት መቻላቸውን በመስክ ጉብኝቱ መታየቱን ያስረዳሉ። በዋናነትም በጉራጌ ዞን ቡታጀራ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ለራሳቸው ሥራ ፈጥረው ሌሎችንም የሥራ እድሉ ተጠቃሚ ማድረጋቸው ትልቅ ምስክርነት የሚያሰጥበት እንደሆነ ገልጸዋል። ‹‹በአካበቢው ወጣቶች እየተሰራ ያለው ሥራ ግብርናችን ለእድገታችን ተስፋ እየሆነ መምጣቱን፤ ዜጎቿም ሀብት እንዲፈጥሩ፣ ካፒታል እንዲያከማቹ እድል እየፈጠረ ስለመሆኑ አረጋግጦልናል›› ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

እንደክላስተር አስተባባሪው ገለጻ፤ ከሌማት ትሩፋት ጋር ተያይዞ በርካታ ባለሀብቶች በወተት ሀብት ልማት ተሰማርተው ፤ የወተት ላሞችን እያራቡ፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ ወተት በማቅረብ ረገድ እየተገኘ ያለው ውጤትም በስኬት የሚመዘገብ ነው። በተጨማሪም ለአካበቢው ህብረተሰብ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው ጥጆችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ፤ የማማከር አገልግሎት እየሰጡ ለህብረተሰቡ ሀብት ለመፍጠር ምክንያት እየሆኑ ነው።

በግብርና ሽግግሩን ለማምጣትም የግል ባለሀብቱ አጋዥና አቅም መሆኑን ከንባታ አካባቢ ዳንቦያ ወረዳ ላይ እየታየ ያለው ልማት እጅግ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹ይህም በሁሉም አካባቢ የሚታዩ ተስፋ ሰጪ ስራዎችን ማዳረስ ከቻልን በእርግጠኝነት ክልላችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት የተሻገረ ህብረተሰብ የተፈጠረበት ክልል ይሆናል፤ ድህነትን ተረት ያደረገም ይሆናል›› ይላሉ። እንዲሁም ብልፅግናን ቀድሞ እውን ያደረገ ህብረተሰብ ለመፍጠር የተጀመረው ጉዞ እንዲሳካ ግብርና ትልቁን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉንም ያስገነዝባሉ። ለዚህም በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ እንድብር ከተማ አካባቢ ያሉ መንደሮች የዚህ አንድ ማረጋገጫ እንደሆኑ ያነሳሉ። በድምሩ ሲታይም የክልሉ የተቀናጀ ግብርና ልማት ሥራ ውጤታማ ጉዙ ላይ እንዳለ አመላካች ነው ይላሉ።

ከስኬቶቹ ባሻገር በግብርና ልማት ሥራው ማነቆዎች አጋጥመው እንደነበረም አቶ ኡስማን ይገልፃሉ። ባለሀብቶቹም ሆኑ አርሶአደሮቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንዳሉም ይናገራሉ። አንደኛውና ዋነኛው ጉዳይ የተመረተው ምርት ገበያ ላይ ፍትሐዊ ዋጋ ያለማግኘቱ እንደሆነ ያነሳሉ። በተለይ አዳዲስ ምርት በሚያመርቱ አካባቢዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በሚፈለገው ደረጃ ሚዛናዊ የሆነ ዋጋ ማግኘት እንዳልቻሉ ይጠቅሳሉ። የመሰረተ ልማት ሥራዎች መጓደልም ሌላው እንደማነቆ የተነሳ ጉዳይ እንደሆነ ያመለክታሉ። ‹‹ምርት አምርተው ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣት የገበያና የመንገድ መሰረተ ልማት ያለመኖሩ ልፋታቸውን ከንቱ እያደረገባቸው መሆኑን ለአመራሩ ገልጿል›› ይላሉ።

በተጨማሪም በመስኖ እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች አንዳንዶቹ ወንዝ ጠልፈው፣ አንዳንዶቹ አነስተኛ ጉድጓድ ቆፍረው፣ በቤኒዚንና ናፍጣ የሚሰሩ ጀነሬተሮች የሚጠቀሙ መሆኑ ዋጋው ተወዳዳሪ ለመሆን እንዳላስቻላቸው እንዲሁም በሚፈልጉት ጊዜ እንደማያገኙ ማንሳታቸውን ይናገራሉ። ይልቁንም ከጀነሬተር የሚያገኙት ኃይል ወደሃይድሮ ፓወር እንዲቀየር፤ ትራንስፎርመር እንዲገባላቸው መጠየቃቸውን ነው አቶ ኡስማን ያብራሩት። በአምራቾቹ የተነሱትን ጥያቄዎች በሚመለከት ‹‹መንግሥት እያጠና በየደረጃው እየታየ መልስ እንዲሰጥ አመራሩ የቤት ሥራ የወሰደበት ሁኔታ አለ›› በማለት ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው ከታዩ ሥራዎች ባሻገር በክልሉ ብዝሃነት ያላቸው የሰብል አይነቶቹን ከማምረት አንፃር እየተሰራ ስላለው ሥራ በዝግጅት ክፍሉ ተጠይቀው እንደተናገሩት፤ በክልሉ ሁሉንም የሰብል አይነት ምርቶች ማብቀል የሚያስችል የአየር ንብረትና ስነ ምህዳር ቢኖርም ከዚህ ቀደም የተለመደው የአመራረት ሥርዓት ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳና እንሰት ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። ይሁንና ካለፈው ሶስት ዓመት ወዲህ እንደ ብልፅግና አዲስ መንግሥት ሲመሰረት አዲስ መንገዶች ለመከተል ተሞክሯል። መንግሥት ለህዝቡ ቃል በገባው መሰረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ፤ የከተማ ነዋሪውንም ኑሮ የማሻሻል ፤ ገቢ የማሳደግና የስራ እድል መፍጠር የሚሉት አጀንዳዎች ቁልፍ ተግባር ተደርጎ ሲከናወን ቆይቷል።

‹‹በተለይም የምንመራው በአዲስ ክልል እንደመሆኑ አዲስ ምርትና አዲስ ተስፋ ብለን እንደጅመራችን ህዝባችንን ማዕከል ያደረገ እንዲሁም ካለን ምቹ ስነምህዳር በመነሳት ክልላችን ላይ ሊመረቱ የሚችሉ ተጨማሪ የሰብል ዝርያዎች ላይ ትኩረት አድርገን ሰርተናል›› የሚሉት አቶ ኡስማን፤ በዋነትም የአየር ንብረት ለውጥና ድርቅን የሚቋቋሙ እና የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ አቅም ሊያሳድግ የሚችሉ የልማት አይነቶችን መለየታቸውን ያስረዳሉ። ከእነዚህም መካከል አምስት የፍራፍሬ ዝርያዎች መለየታቸውን፤ እነዚህም አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣አፕልና ማንጎ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በተለይ ከማንጎ ውጪ በሌሎቹ ላይ ለአንድ ቤተሰብ 100 የፍራፍሬ ዛፍ በሚል የተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት ማስገኘቱን ነው ያስረዱት፡፡

በተለይም እነዚህ ፍራፍሬዎች ጭራሽ በማይታወቁባቸው አካባቢዎች ላይ በማልማት በርካታ የሙዝ፣ የፓፓያ፤ የአቦካዶ፣ የአፕል መንደሮች መፈጠር መቻላቸውን ይጠቅሳሉ። በእነዚህ አካባቢዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውን አንስተው፤ በተለይም የአርሶአደሩን ህይወት በዘላቂነት በመቀየር ረገድ የተሰራው ሥራ አበረታች እንደሆነ ይናገራሉ። በሌላ በኩል የክልሉ መለያ ምልክት፤ የክልሉ ፀጋ ተብሎ የሚጠቀሰውና ብርድ የማይበግረው የክፉ ቀን ደራሽ የሆነው የእንሰት ሰብልን ከመጥፋት ወደ ማስፋፋት በሚል ንቅናቄ እያንዳንዱ ቤተሰብ 100 የእንሰት ተክል እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ። በተለይ ቆላማና ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ኡስማን ያስገነዘቡት፡፡

ከዚህ ባሻገርም የክልሉ የአመራረት ስልት ዝናብ ጠብቆ ከማምረት፤ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ውሃን አሟጦ በመጠቀም በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረት ሥራ መጀመሩ አሁን ላይ እየተመዘገበ ላለው እመርታ አወንታዊ ሚና መጫወቱን ያመለክታሉ። በቀጣይም በክልሉ ያለውን ፀጋ በመጠቀም በቤተሰብና ማህበረሰብ ደረጃ አርሶ አደሩ ከድህነት መውጣት የሚያስችል ሥራ እንደሚሰራ ነው የጠቆሙት፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You