የተቀመጠውን ሀገራዊ ግብ ዕውን ለማድረግ የአመራር ቁርጠኝነትና የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው!

ኢትዮጵያ የአጭር የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ ነድፋ ብልጽግናዋን እውን የማድረግ ጉዞዋን ጀምራለች። የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድም የዚህ አካል ሲሆን፤ እቅዶቹን እውን ከማድረግ አኳያ በየዓመቱ ተሸንሽኖ ቀርቧል። በዚህም የየዓመቱ አፈጻጸም በመቶ ቀን እየተለካ እንዲፈጸም አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፤ ሂደቱን እየተገመገመ በመፈጸም ላይ ይገኛል።

ከሰሞኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት ሀገራዊ እቅድ አፈጻጸምና የመቶ ቀናት ተግባራትን የገመገመ ሲሆን፤ በዚህም በተለይ በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የተጣለውን ግብ ማሳካት የሚያስችል አፈጻጸም መመዝገቡ ነው የተገለጸው።

በግምገማው ወቅት እንደተመላከተው፣ የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል። በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ለማሳካት የተጣለውን ግብ እውን ማድረግ የሚያስችል የተሻለ አፈጻጸም ነው።

በተመሳሳይ በግማሽ ዓመቱ እንደ ማክሮ ኢኮኖሚው ሁሉ፣ የመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ ዘርፍ አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን፤ በተለይ በበጀት ዓመቱ የሰባት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ ከማሳካት አኳያ ያሉበት ደረጃ ታይቷል። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያለው አፈጻጸም ዓመታዊ ዕቅዱን ማሳካት እንደሚቻል ያሳዩ ሆነዋል።

በዚህ ረገድ በሰብል ምርት የተገኘው ውጤት ተጠቃሽ ሲሆን፤ ለአብነትም በዚህ መስክ በምርት ዘመኑ የተሰበሰበው ምርት ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው የ480 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሎ 496 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ከዚህ በተጓዳኝ በሆልቲካልቸር፣ በእንስሳትና ዓሣ ልማት እንዲሁም በሌሎች የግብርናው ዘርፎች የተገኘው ውጤታማ አፈጻጸም ለእቅዱ መሳካት የራሱን አበርክቶ ያደርጋል።

በግብርናው መስክ ሌላው ትልቅ ውጤት እየተገኘ ያለው በመስኖ ልማት ሥራ ሲሆን፤ በዚህም በግማሽ ዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል። ይሄ ደግሞ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበትና የላቀ ውጤትም እንደሚገኝበትም ይጠበቃል።

ከዚህ ባሻገር በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በገቢ አሰባሰብ በኩል የነበሩ አፈጻጸሞች የታዩ ሲሆን፣ በእነዚህ ረገድ የተገኘው ውጤትም ለተሻለ ሥራ ያነሳሳ ሆኗል። በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ታግዞ የተሠራው ሥራ፤ በገቢ አሰባሰብም የግብር ከፋዩን አሳትፎ ገቢን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር፤ በአገልግሎት በኩልም ዘርፉ አንድ የኢኮኖሚ አቅም እንዲሆን የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተስፋ ያስጨበጡ ናቸው።

ይሁን እንጂ በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍም ሆነ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪውና ሌሎችም ላይ የተገኘው ውጤት አበረታችና የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ግብ ማሳካት የሚያስችል ቢሆንም፤ ይሄንን ሊገዳደሩ የሚችሉ በርካታ ችግሮች መኖራቸው የሚካድ አይደለም።

ለአብነትም፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለው ክፍተት ኅብረተሰቡ ላይ ያልተገባ እንግልትና ምሬት የሚፈጥር ነው። የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረቱም በተለይ ቋሚ ገቢ ያላቸውንና ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያለውን ሰፊ የሕብረተሰብ ክፍል በልቶ የማደር ሕልውናውን የሚፈታተን ሆኗል። በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ የሚስተዋለው ግጭትና አለመረጋጋትም፣ የዜጎችን ወጥቶ የመግባት፣ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ሠርቶ ንብረት የማፍራት፣ በጥቅሉም የሰዎችን የደኅንነት ሁኔታ በስጋት ያጠረ ሆኗል።

ከዚህ አኳያ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከኑሮ ውድነትና ከሠላምና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ማረም ለነገ የማይባል ሥራ ነው። አመራሩም ሕዝቡን ከጎኑ አሰልፎ እነዚህን ችግሮች መፍታትና ሕዝቡን መካስ የሚያስችሉት ሥራዎችን በቁርጠኝነት መሥራት ይኖርበታል።

በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለይቶ በየፈርጃቸው በመፍታትና የልማት እንቅፋት እንዳይሆኑ በማስቻል በኩል ሁሉም አካል ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ መሥራት ይኖርበታል። ለዚህም ከተቋማት መሪዎች እስከ ታችኛው መዋቅርና ፈጻሚዎች ድረስ ተቋማቸውን በሙሉ አቅም በአርዓያነት መምራት እና ሀገርን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ችግሮቹ ተቀርፈው የተቀመጠውን ሀገራዊ ግብ ዕውን ከማድረግ አኳያ ከአመራሩ ቁርጠኝነትና ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚጠበቅ አውቆ፤ ይሄንኑ በተግባር መግለጥ ይገባዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም የልማቱ ዋነኛ ኃይልና ተጠቃሚ የሆነው የሕዝብ ተሳትፎም የልማት ዕቅዱና ክንውኑ አንቀሳቃሽ ሞተር ሊሆን ግድ ይላል!

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You