ኢትዮጵያውያን በማንነትም ሆነ በኃይማኖታዊ ብዝሃነት ውስጥ ጎልቶ የሚታየው አንድነት የሚያስደንቅ፤ እንደ ሕዝብም የሚያኮራ እሴት ነው። ምክንያቱም የተለያየ አይነት አለባበስ፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት፣ ባህልና ትውፊት ቢኖራቸውም፤ ብዝሃነታቸው ውበት፣ በኅብር የደመቀው አብሮነትና አንድነታቸው ደግሞ አቅም ሆኗቸው የሚገለጡበት ነው።
ኢትዮጵያውያን በብዝሃነታቸው ውስጥ አንድ የሚያደርጓቸው ብዙ ትውፊቶች አላቸው። ማንነታቸው የበዛም የተሳሰረም፤ ኃይማኖታቸው የተለያየም የተገናኘም ሆኖ አሰናስሏቸዋል። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ የክርስቲያኑም፣ የሙስሊሙም የዋቄፈታውም ምድር ናት። ይሄ ለሺህ ዓመታት በልዩነት ውስጥ አንድነትን አስተሳስሮ የዘለቀው የኃይማኖት ብዝሃነት፤ ኢትዮጵያ በዓለም የኃይማኖቶች መቻቻል የሚታይባት ሀገር ሆና እንድትገለጥ አድርጓታል።
ኃይማኖቶች የሕዝቦች መገናኛ አውድ፤ የማኅበራዊ ትስስር ማጠናከሪያ መድረክም ሆነው ሲያገለግሉ ማየት በኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ዘንድሮ ደግሞ “የጻድቃን ቀጠሮ” እንዲሉ፤ የክርስቲያኑም (በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች)፣ የሙስሊሙም ፆም በተቀራረቡ ቀናት ይጀመራሉ።
በክርስትናው የዐቢይ ፆም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው፣ ከፈጣሪ በረከት ማግኛ ጾም ነው። በሙስሊሙም የታላቁ ረመዳን ፆም ከፍ ያለ የጽድቅ ሥራ የሚከወንበት ነው። በዚህ መልኩ የሚገለጹት እነዚህ ሁለት አጽዋማት ታዲያ በቆይታቸው ያለ ልዩነት ሕዝቦች ወደ ፈጣሪያቸው እንዲማጸኑ፤ ለመልካም ተግባር እንዲተጉ ለማድረግ ነገን የጋራ መከሰቻ አድርገው ደርሰዋል።
እነዚህ ወራት ደግሞ ፈጣሪን ማሰቢያ እና የመልካም ተግባር መከወኛ ተደርገው ስለሚወሰዱ፤ አማኙ ሕዝብ አጽዋማቱ የሚፈልጉትን እሴት ሊላበስ የተገባ ነው። ይሄ ደግሞ ራስን ማንጻት፤ ለይቅርታ መዘጋጀት፤ ለፍቅር ራስን ማስገዛት፤… የመሳሰሉ ተግባራትን የራስ መገለጫ ማድረግ ነው።
በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ ትልቁን የዐብይ ፆም፣ ሕዝበ ሙስሊሙ ደግሞ ታላቁን የረመዳን የፆም ሂደት ሲከናውኑ፤ የጾሙን ወራት እንደ ፈጣሪያቸው ፈቃድ የሀገር ሰላምና አንድነትን ሊያመጡ በሚችሉ ተግባራት ሊያሳልፏቸው ይገባል። የሠላም፣ የመቻቻልና በመከባበር አብሮ የመኖር እሴትን፣ ባሕልና ታሪኩን መግለጥ፣ ወደላቀ ደረጃም ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ረገድ ኃይማኖት ሽፋን አድርጎ የግልና የቡድን ፍላጎትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፈውን ነጻነት፤ ሠብዓዊ ሥርዓትና ማኅበራዊ እሴት ያስገኘለትን አብሮነት ለመሸርሸር የሚደረግ ማናቸውንም እንቅስቃሴ በንቃት መመልከትና ማክሸፍም ይጠይቃል።
በኃይማኖትና በብሔር ሽፋን የሚካሄደው የሽብርና የፀረ-ሠላም እንቅስቃሴ በሠላም ወዳድ ኃይሎች ጥረት እንዲጋለጥና እንዲመክን ለማድረግ ኃይማኖቶች ትልቅ ጉልበት አላቸው። የኃይማኖት ነፃነትና እኩልነት ባልተከበረባቸው ዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሠላም አብሮ በመኖር የዓለም ተምሳሌትነታቸውን አረጋግጠዋል። አሁንም በጋራና በሠላም ለሀገር እድገት የሚሠራበትን ሁኔታን ማጎልበት ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ይህን የቆየውን የመከባበር፣ የመቻቻልና አብሮ የመሥራት ባህል በሚጻረር መልኩ የሚታዩ ጉዳዮች አሉ። ከዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫዎች መካከል አንዱ ሃሳቦችን በመደማመጥና በመከባበር መንፈስ በጠረጴዛ ዙሪያ ማንሸራሸር መቻል ነው። የዴሞክራሲ ሥርዓት ከእኔ ብቻ ልደመጥ ፍጹም የተለየ የብዙሃን ሃሳብ እንዲንሸራሸርና በዛም የተሻለው ሃሳብ የጋራ ሃሳብ ሆኖ እንዲወጣ እድል የሚሰጥ ሥርዓት ነው። የግለሰብ ፍላጎትና አስተሳሰብን በተለይም ኃይልን አማራጭ ያደረገ አካሄድ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት ነው።
ሃሳብ ሀብት ነው፤ በሃሳብ ውስጥ ሰላም፣ መተሳሰብ፣ መከባበር፣ አንድነት፣ አጋርነት አለ፣ ይህ የማይካድ ሀቅ ነው። የሁሉም ሥራዎች መነሻ የሰዎች ሃሳብ ነው። ሰዎች ፈጣሪ በሰጣቸው አዕምሮ ተጠቅመው መልካም ነገሮችን ማፍለቅና ማምረት ሲጀምሩ ከእነሱ አልፈው ለህዝብና ለሀገር ጠቃሚ ሃሳቦችን ወደ ተግባር ይቀይራሉ። የሃሳብ ልዩነቶችን በመቻቻል ማስተናገድ መርህ ሊሆን የሚገባውም ለዚህ ነው።
የሃሳብ ብዝሃነትን በሚፈለገው ደረጃ ማስተናገድ ባለመቻሉ የከረሙ ችግሮች ተጠራቅመው ዛሬ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ላይ የራሱ የሆነ ጫና ሊያሳድር ችሏል። በሀገራችን በሃሳብ ልዕልና ወይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል ለማለት ቢከብድም ሁሉም ሰው የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት፣ ልማትና ዕድገት፣ ብልጽግናና አንድነቷ የጠነከረ እንዲሆን ፍላጎት አለው። ፍላጎቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዴሞክራሲያው ሥርዓት ግንባታ መዳበር ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
የጋራ መግባባት የሌለበት ማንኛውም እንቅስቃሴና ርምጃ ደግሞ ውጤቱ የከፋ ነው፣ በመሆኑም መግባባትና ወንድማማችነትን አጣምሮ ማስኬድ ይገባል። በመሆኑም ከሁሉም በላይ አርቆ አስተዋይ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ደግሞ ወጣቱ ትውልድ በአክራሪዎች አላስፈላጊ አስተሳሰቦች ሳይመረዙ የመተሳሰብ፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህላቸውን ሊጠብቅ ይገባል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልም ሆነ በጋራ በመሆን ጽንፈኝነት፣ አክራሪነትና ቂምበቀል በሀገሪቱ እንዳያቆጠቁጡ ሊረባረብ ይገባል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልኩን እየቀያየረ የመጣው በነፍጥ ልዩነትን ለመፍታት መሞከር ከተለያዩ አጀንዳዎችና ፍላጎቶች ጋር እየተያያዘ በሕዝቡ ሠላምና ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር መልካም እሴቶች ላይ የፈጠረውን ብዥታም ማስወገድ ይገባል። ለዚህም ሕዝበ ክርስቲያኑና ሕዝበ ሙስሊሙ የፆሙን ወራት ለሀገር አንድነትና ሰላም በፆምና በጸሎት የሚያስቡበት ሊሆን ይገባል። ለሰላም፣ ለፍቅርና ለይቅርታ ሊሰሩበት ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም