የእኛ ነገር!

የእኛ ነገር በጣም አስገራሚ ነው። ብዙ ነገራችን የተቃረነ ነው። የምንፈልገው እና የምንሆነው ለየቅል ነው። ነገሩ ሰፊ ስለሆነ ዛሬ እሱን አንተነትንም። ብቻ ከሚያስገርሙ የእኛ ባሕሪዎች መካከል አንዱን ብቻ ዛሬ ላንሳ። እሱም ምንድን ነው ከተባለ በቤት የሌለ ነገራችን በሀገር ደረጃ የምንጠብቀው ነገር ነው።

ይህ ነገር በምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፤ በቀደም ከአምባሳደር ወደ አራት ኪሎ የሚሄድ ታክሲ እየጠበቅኩ ነበር። ከብዙ ቆይታ በኋላ አንድ ታክሲ መጣ። ታክሲው ረዳት የለውም። ሹፌሩ መኪናውን አቁሞ የተሳፋሪ መግቢያውን ሊከፍት መጣ። ከዚያም በሰልፍ አስገባና ገንዘብ መሰብሰብ ጀመረ። ገንዘቡን ሰብስቦ ሲጨርስ በሩን ዘግቶ ወደ ቦታው ተመለሰ። መኪናውን አስነስቶ ሄደ። ገረመኝ። ለምንድን ነው ረዳት የሌለው። መቼም ረዳት አጥቶ አይደለም። ለረዳት ላለመክፈል ብቻ ነው የሚሆነው።

ከኮሮና ወዲህ ከተለመዱ ነገሮች መካከል አንዱ ይህ ነው። ሾፌሮች ረዳቶቻቸውን ቀንሰዋል። ያለ ረዳት መሥራት ተመችቷቸዋል። ገቢ የሚካፈላቸው አይኖርም። ግን ያለ ረዳት ሆኖ በሚያገኛት ገንዘብ የሚኖር ወጣትስ ምን ሠርቶ ይብላ። ያ ወጣት ነገ ሥራ ፈትቶ የሚበላው ሲያጣ የመኪናቸውን ስፖኪዮ ቢሰርቀው ይፈረድበታል?

የሚገርመው ረዳቱን ያባረረው ሰውዬም መንግሥት ለወጣቱ ሥራ እንዳልፈጠረ እና ሕዝብ እንደተቸገረ ሲናገር መስማት የተለመደ ነው። ወንደሜ አንተ ያባረርከውን ሰው መንግሥት ከየት ያመጣውን ሥራ ይቅጠረው፣ መንግሥት የራሱ ታክሲ ያለው እንዴት ነው ይህን ሰው ሥራ ሊሰጠው የሚችለው መልስ የለም። አንተ ማድረግ ያልፈለግከውን ነገር መንግሥት ሊያደርግ አይችልም።

ደግሞ ወደ ቦሌ ስሄድ አንዱ ባለሀብት ያሠራውን ሕንጻ የመኪና ማቆሚያ ሱፐር ማርኬት አድርጎት አየሁ። ሱፐር ማርኬቱ ያረፈበት የሕንጻው የታችኛው ወለል ቢያንስ 50 መኪና ሊይዝ የሚችል ነው። አሁን ባለመኪና ሰዎች መጥተው ከሱፐር ማርኬቱ እቃ ይገዛሉ።

መኪናቸውን በር ላይ አቁመው ለአላፊ አግዳሚ መንገድ ዘግተው ነው ገብተው የሚገዙት። የሕንጻቸውን የመኪና ማቆሚያ ለጭፈራ ቤት፤ ለጂምናዚየም፤ ለሌላም ያከራዩ ሰዎች ብዙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ጎዳናው በመኪና እንደተጨናነቀ እና በዚህ ምክንያት የፈለጉበት ቦታ በፈለጉት ሰዓት መድረስ እንዳልቻሉ ይናገራሉ። ወገኖቼ መንግሥት እነሱ ሕንጻ ጋር የሚመጣ ሰው መኪና የሚያቆምበትን ቦታ የት ይሥራ፣ በሀገሪቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መኪኖች አሉ። መንግሥት ለነዚህ ሁሉ መኪና ማቆሚያ መሥራት ይችላል አይችልም። አንተ በገዛ ንብረትህ ላይ ማድረግ ያልፈለግከውን መንግሥት በሕዝብ ንብረት ላይ እንዲያዝ ስለምን ትጠብቃለህ።

ደግሞ የቤት እመቤቶች አሉ። ሥራ በዛብን ብለው የቤት ሠራተኛ የሚቀጥሩ። ሠራተኛ የሚቀጥሩት እነሱ ዕረፍት ፈልገው ነው። ነገር ግን አንድም ቀን ሠራተኛቸው ዕረፍት እንደሚያስፈልጋት የማያውቁ። እንዲያውም በተደጋጋሚ የቤት ሠራተኞች ሥራ ሲበዛባቸው እንደሚወዱ እና እረፍትም ሆነ ክብካቤ ሊሰጣቸው እንደማይገባ የሚናገሩ ሰዎች አጋጥመውኛል።

እነዚሁ ሰዎች በመሥሪያ ቤታቸው ሥራ በዛብን ብለው የሚያማርሩ አሁንም አሁንም ዕረፍት የሚጠይቁ ሰዎች ናቸው። እነዚሁ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ መንግሥት የዜጎችን መብት ማክበር እንዳለበት የሚናገሩ ናቸው።

እነዚሁ ሰዎች በሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንዳለባቸው የሚወተውቱ ናቸው። እነዚሁ ዜጎች ናቸው ደግሞ የገዛ የሀገራቸውን ልጅ ጉልበት ከሰኞ እስከ እሁድ የሚበዘብዙት። እኛ በቤታችን ያላከበርነውን የሰው ልጅ መብት መንግሥት እንዲያከበር ስለምን እንጠብቃለን። አይሆንም። መጀመሪያ እና በግለሰብ ደረጃ ልንሠራው የሚገባ ሥራ በሀገር ደረጃ አይከበርም።

ብዙ ሰው መንግሥት የሚባለው ተቋም ከግለሰብ በሚሰበሰቡ መብት ድምር ጉልበቱን ያገኘ መሆኑን ይረሳል። መንግሥት ይህን ያድርግ ያን ያድርግ እያልክ የቤት ሥራውን ወደ መንግሥት ባበዛህ ቁጥር መንግሥትም ካንተ የሚወስደው መብት እየጨመረ ይመጣል። ከዚያም አምባገነን ሥርዓት ይፈጠራል።
በሠለጠነው ዓለም የመንግሥት ድርሻ ምን ይሁን በሚለው ላይ ሁሌም የጦፈ ክርክር አለ። መንግሥት ብዙ መብት ሲሰጠው አምባገነን እንደሚሆን ስለሚያውቁ የመንግሥት ሥልጣን በሕግ እንዲገደብ ለማድረግ ብዙ ርብርብ ይደረጋል።

እንዲያውም መንግሥት ከተቆጣጣሪነት ያለፈ ድርሻ እንዲኖረው አይፈለግም። እኛ ጋር በተቃራኒው ነው። መንግሥት ሁሉንም ነገር እንዲያደርግ እንጠብቃለን። እስኪ ይታያችሁ፤ የቤት ሠራተኞቻችንን እኛ ጉልበታቸውን ስለምንበዘብዝ መንግሥት ገብቶ የቤት ሠራተኛ አያያዝ የሚል ሕግ ማውጣት አለበት? እኛ ስግብግብ ሰለሆንን መንግሥት የፓርኪንግ ቦታዎች አስተዳደር የሚል መመሪያ ማዘጋጀት አለበት? እና ራስ ወዳድ ስለሆንን መንግሥት ሁሉም ታክሲ ረዳት እንዲኖረው የሚያስገድድ ደንብ ማዘጋጀት አለበት?

እንደዚያ አይነት ሂደት ውስጥ ከገባን እኮ መንግሥት ምን መብላት መቼ መተኛት የት መሄድ እንዳለብን ሁሉ የሚወስንበትን ሥልጣን ወደ ማግኘት ነው የሚሄደው። ይሄ ደግሞ የለየለት አምባገነንነትን ይፈጥራል።
ስለዚህም ጓዶች እንታረም። እኛ በቤታችን የማናረገውን ነገር መንግሥት እንዲያደርገው አንጠብቅ። እኛ በቤታችን የማናደርገውን ነገር መንግሥት ግን እንዲያደርገው ከፈለግን መንግሥትን ኃላፊነቱን እናበዛበታለን። መንግሥት ደግሞ ከኛ ኃላፊነትን ብቻ ሳይሆን መብትንም አብሮ ነው የሚወስደውና የእኛ መብት እየሟሸሸ ለመንግሥት በሰጠነው መብት የተነሳም የመንግሥት ጉልበት እያየለ ይሄዳል።

ይህ ነገር ከመንግሥት እና ሕዝብ ግንኙነት ባለፈም በሞራልም በመንፈሳዊም ዓይን ቢታይ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው። አንተ ልታደርግ የማትወደውን ነገር ሌላ ሰው እንዲያደርግ አትጠብቅ ከሚለው የሃይማኖትም የሞራልም ሕግ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው። አንተ ያባረርከውን ረዳት መንግሥትም ሆነ ሌላ ሰው እንዲቀጥረው አትጠብቅ። አንተ የዘጋከውን የመኪና መቆሚያ ሌላ ባለ ሕንጻ እንዲከፍት አትጠብቅ።

አንተ የሠራተኛህን የማረፍ እና የመዝናናት መብት እንዳላከበርክ ሁሉ ሌላው ሰው ያንተን የማረፍ እና የመዝናናት መብት እንዲያከብርልህ አትጠብቅ ማለት ነው። ስለዚህ እንታረም። እኛ መሆን አለበት ብለን የምናስበውን ነገር ራሳችን ከመፈጸም እንጀምር!
ቸር እንሰንብት!

አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You