መተባበር ከመወያየት ይወለዳል

ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ እንደ ትልቅ የለውጥ አቅም አድርጋ ከያዘቻቸው የሰላምና የልማት አቅጣጫዎች ውስጥ የውይይት ባሕልን ማዳበር አንዱ ነው። እንደ ሀገርም ኢትዮጵያ በቀጠናውም ሆነ በዓለም አቀፉ መድረክ ሰላም እንዲሰፍን ስትሰራ በቆየችባቸው ዓመታት ውስጥ፤ ዜጎቿ ስለሌላው ሰላምና መረጋጋት ሲሉ በከፈሉት ዋጋ ውስጥ የጻፏቸው ወርቃማ ስሞች አሉ።

ልማትና ሰላም በአንድ ዛፍ ላይ እንደተንጠለጠሉ ፍሬና አበባዎች ናቸው። ፍሬና አበባው እንዴት መጣ? ብለን ስንጠየቅ የምናገኘው መልስ ዛፉ በላመ አፈርና በጣመ ውሃ ላይ ስር ሰድዶ የቆመ መሆኑን ነው። የዛፉ በበጎ መሬት ላይ መቆም ላማሩት ፍሬዎችና አበባዎች መፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል። ዛፉ በጭንጫና በመሬሬ አፈር ላይ ወይም ደግሞ በአለት መካከል የበቀለ ቢሆን እነዛ ሁሉ የአበባና ፍሬ ጸጋዎች አይኖሩም ነበር።

በዚህ ነፃ ሃሳብ ስር ዛፉን እንደሀገር፣ አበባና ፍሬዎቹን ደግሞ ከጠንካራ ሀገር የሚገኙ ሰላምና እንደልማት አልያም እንደ አንድነትና እንደ ተግባቦት ያሉ ጸጋዎች ናቸው ብዬ መስያቸዋለው። የላመ ሃሳብ እንደላመ አፈር ነው፤ በሁለቱም ውስጥ ሕይወት መብቀል ይችላል። የጥላቻ ሃሳብ እንደመርዛም መሬት ነው፤ በሁለቱም ውስጥ ሕይወት አይኖርም።

እንደ ሀገር እንድናድግና እንድንበረታ ዛፉን እንዳሳደጉት አሳድገውትም ያማረ ፍሬና አበባ እንደሰጡት መልካም ማዕድናት ሁሉ፤ መልካም ሀገርና ትውልድን ለመፍጠርም መልካም ሃሳብና በጎ የተግባቦት፣ ሰላማዊ አእምሮና ቀና ልብ ያስፈልገናል። ዛሬ ላይ እየተነጋገርን የማንግባበው፣ እየተወያየን የማንስማማው፤ አላማችን ሀገርና ሕዝብ አድርገን የምንነጋገር ባለመሆኑ ነው። ከዚህ በተጓዳኝም አሸናፊ ሆኖ መገኘትን (መሸናነፍን) ፊተኛ ስላደረግንም ነው። አሁን ላለነው ጥሩ ምስለ ተረት የሚሆነንም እየተነጋገሩ አለመግባባት ያለበት የአሸናፊነት ሞገደኝነት ነው።

ይሁን እንጂ በነቃ ሃሳብ የነቃች ኢትዮጵያን መገንባት ምርጫ ውስጥ የማይገባ ፊተኛ ግብር ነው። የነቃ ሃሳብ ለነቃች ሀገር፣ ለነቃ ማኅበረሰብ፣ ለነቃ ትውልድ፣ ለነቃ ፖለቲካ፣ ለነቃ ኢኮኖሚ፣ ለነቃ ዲፕሎማሲ የጀርባ አጥንት ነው። ሆኖም ተግባር፣ ህብረት፣ አንድነትና ወንድማማችነት ካልታከሉበት የነቃ ሃሳብ ብቻውን ትርጉም የለሽ ነው። አንዳንዴ እጅግ በበረታ ሀገራዊ ጉዳይ ስር መግባባት አቅቶን እዛና እዚህ እንቆማለን። ይሄ ማለት ሃሳቡ መልካምና አሻጋሪ ቢሆንም ህብረትና ወንድማማችነት ካልታከለበት የነቃ ሃሳብ ብቻውን ምንም እንዳይደለ አመላካች ነው።

በብሔር ለተቧደነች ሀገር፣ ከኢትዮጵያዊነት በፊት ማንነቱን ብሔር ላደረገ ሕዝብ፣ ይቅርታና ፍቅር ርቀውት በጥላቻ ካብ ለካብ ለሚተያይ ትውልድ የነቃ ሃሳብ ብቻውን ትርጉም አይሰጥም። ዛፉን በልምላሜ አቁመው ባማረ ፍሬና አበባ እንደከበቡት ለም አፈርና ውሃ፤ ሕይወት የሚያበቅል፣ ፍቅርና ይቅርታን የሚያጸድቅ ሰውነት ያስፈልገናል። ተነጋግሮ የሚግባባ፣ እኔ ያልኩት ይሁን ሳይሆን፤ በገዢ ሃሳብ ስር የወደቀ የመመካከሪያ መድረክ ያስፈልገናል።

ሰላምና ልማት በላቀ ሃሳብ የሚጸነሱ ሀገራዊ በረከቶች ናቸው። ካለ ፍቅርና ካለ ሕዝባዊ ውይይት እንዴትም ብንበረታ ትርፍ አልባዎች ነን። ለዛ ለምለም ዛፍ ጸጋው ፍሬና አበባው እንደሆኑ ሁሉ፤ ለእኛም ጸጋዎቻችን በተግባቦት በኩል የምንዋሃዳቸው የመልካም አፍ ውጤቶቻችን ናቸው። ሰው ምንም ያክል ብርቱ ቢሆን ብቻውን ምንም መፍጠር አይቻለውም። እኛ ደግሞ ብቻችንን እንዳንቆም ባደረጉን የታሪክና የባህል ውርስ ውስጥ ነን። እንዳንግባባ መሀከላችን ገንግነው በአጉል ትርክት ያለያዩን እንከኖቻችን ጊዜያዊ ስለሆኑ ወደ ራሳችን መመለስ ግድ ይለናል።

አሁን ላይ ሀገራችን በብዙ መስክ ራሷን በሰላም፣ በልማት፣ በዲፕሎማሲ፣ በጉርብትና፣ በአብሮ ማደግ በሌሎችም መርህ እየቃኘች ትገኛለች። ለዚህ ሀገራዊ ሂደት እንደዋና ቁልፍ አድርጋ የወሰደችው ደግሞ ከቀጠናው ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ የዘለቀ ሰላም ፈጣሪ የተግባቦት መርህን ነው።

በዚህ ረገድ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ አንድነትንና አብሮነትን ሊመልስ ከጫፍ በደረሰ ሀገራዊ ምክክር ስር ነን። እንደ አፍሪካ ቀንድ በቀይ ባህርና በሌሎችም የአብሮ መልማት ማዕቀፍ ስር የቆምን ነን። እንደ አፍሪካ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት አውድ ስር ነን። እንደ ዓለም ደግሞ ከተመድ ባሻገር ባሉ ብሪክስን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ስብስቦች ውስጥ ዐሻራችንን በማሳረፍ ላይ እንገኛለን።

ሀገርና ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ እኚህ ሂደቶች ከሰላም ጀምረው በአብሮነት የሚጠናቀቁ ናቸው። ሀገራዊ ምክክሩን ብንወስድ ዓመታትን በተሻገረ የዝግጅት ሂደት ኢትዮጵያዊነትን በማረቅና የወየቡትን በማጥራት አብሮነትን በመመለስ ሂደት ላይ ይገኛል። ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከደቡብ እስከ ሰሜን ልዩነትን አጥብቦ ወንድማማችነትን በማጽናት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ጥላቻ ወለድ የሆኑ ነባርና የቆዩ ቁርሾዎች ከነተረት ተረት ትርክቶች ጋር የሚቀበሩበትን ሕዝባዊ መድረክ ፈጥሮ በምትኩ አስታራቂና አንቂ ትርክትን በመቀበል የነበረንን ስም በመመለስ ላይ ይገኛል።

የዚህ ጉዳይ ቀጣይ አጀንዳ ደግሞ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ነው። ይሄ ወቅታዊና አሁናዊ አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮቻችን ፊተኛው ሲሆን፤ በአብሮ ማደግ መርህ አፍሪካን በተለይም ምሥራቅ አፍሪካን በኢኮኖሚና በፖለቲካ በዲፕሎማሲም ለማስተሳሰር የጀመርነው ርምጃ ነው። ርምጃው እንዳሰብነው አልጋ ባልጋ ባይሆንም እንቅፋት አለ ብለን ከጉዟችን ግን አልቆምንም፤ አንቆምም።

ምክንያቱም ሰላም ፈጣሪ እና በኩረ ነጻነታችንን ተጠቅመን ማንንም ሳንጎዳና ማንም ሳይጎዳን ተጠቅመን ልንጠቅም ረጅም አስበን እየተንቀሳቀስን ስለሆነ ነው። እድገታችንን የማይፈልጉ አንዳንድ ሀገራት ህጋዊ ጥያቄያችንን ለማኮሰስ ቢሞክሩም ከአላማው ዝንፍ የማይለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በአንድነት ቆሞ ታሪካዊ የተባለውን ስምምነት ከሱማሌ ላንድ ጋር አድርጓል።

ይሄ እንቅስቃሴያችን ለሀገርና ሕዝብ የሚበጅ ዋጋ እስኪያገኝ ድረስ ይቀጥላል። እስካሁንም ስለሀገርና ሕዝብ ብለን ጀምረን ያልጨረስነው፣ አስበንም ያልቋጨነው ምንም የለም። መነሻችን ሁሉንም ያቀፈ በአብሮ የማደግ ጅማሬ እንደመሆኑም፤ ጉዳዩን እኛ እንጀምረው እንጂ ለሌሎች እድል በመስጠት በጋራ አስበን በጋራ የምንጠቀምበት ነው። እንደሞራል ሕግም ሆነ እንደዓለም አቀፉ መርህ በጥያቄያችን በኩል የጣስነው ሕግም ሆነ የነካነው መብት የለም።

ያው እድገታችንን የማይፈልጉ መጮሀቸው አይቀርም፤ ይሄ የነበረና ያለ ወደፊትም የሚቀጥል የሰው ልጅ የራስ ወዳድነት ነጸብራቅ ነው። ግን ጮኸው አያስቆሙንም። ባለፈ ታሪኮቻችን እንዳላስቆሙን ሁሉ አሁንም አያስቆሙንም። ለሁላችንም የሚጠቅመው ነገር ተመካክሮና ተወያይቶ በሰጥቶ መቀበል ለአዲስ ታሪክ መሰናዳት ነው። እንዲህ ያለው ሀገራዊ መሻት መነሻውን ያደረገው ሰላማዊ ውይይትን ነው።

ቀይ ባህር የታሪካችን መሀል ነው። ኢትዮጵያ ብለን ቀይ ባህር ማለት የማንችልበት ስልጣኔ በአንድ ዘመን ላይ በደማቅ ነበር። እኛ ያደረግነው ታሪክን ማስቀጠል፣ ስምን ማደስ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ፍላጎትን መሠረት አድርጎ ለተነሳው የሕዝባችን ጥያቄ መልስ መስጠት ነው። ይሄ ነውር አይደለም።

ሌላው ከዓድዋ ጋር መሳ ለመሳ የቆመው ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ አብሮ የሚነሳው የሕዳሴ ግድባችን ነው። ከዛሬ አስራ ሶስት ዓመት በፊት መሠረቱን ሲጥልና ከዛ በኋላም ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ምን ያክል የአይችሉም፣ የአይሆንላቸውም እና መሰል የዛቻና የማስፈራሪያ ድምጾችን ስንሰማ ነበር። ዓባይ ግን እንሆ ትንሳኤውን ሊያይ የመጨረሻዎቹ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

የባለስኬት ስኬት ከጩኸት መካከል ነው የሚጀምረው። እንዳውም አንዳንድ የሥነ ልቦና ሊቃውንት አንተ ስትጀምር ሌሎች ካልጮሁና አይችልም ካላሉህ የጀመርከው ነገር ውጤት አያመጣም ይላሉ። የሌሎች መጮህ የእኛ መቻል እንደሆነ አይተናል። የሌሎች ዛቻና ማስፈራሪያ የእኛ ያለመቆም ማሳያ እንደሆነ ልብ ያልንባቸው ጊዜያቶች ብዙ ናቸው። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ሌሎችን ስለዓላማችን ለማስረዳት የተለያዩ የሶስትዮሽ ውይይቶችን አድርገናል።

ሌላው፣ ሰላም ተኮር ከሆኑ ሂደቶች ስር የሚመደበው የብሪክስ አባልነት ነው። የብሪክስ የአባልነት ጥያቄ ስናነሳ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከጤና፣ ከግብርና፣ ከሥራ ዕድል፣ ከደህንነት፣ ከመሠረተ ልማትና ከሌሎችም ጥቅሞች አንጻር ቃኝተን ነው። ቅኝታችን ፍሬ አፍርቶ ጥያቄያችን ተቀባይነትን አገኘ። ብሪክስን እንድንቀላቀል መንገድ ከጠረጉልን ሁነቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሠራነው ሀገራዊና አህጉራዊ ዓለም አቀፍም ግንኙነት ነው። ለሰላምና አብሮ ለማደግ ያለን ጽኑ ፍላጎት፣ በሄድንባቸው የእርስ በርስ ጉርብትና ላይ በጎ ጥላ አጥልተው ከጥቂቶቹ አንዱን እንድንሆን እድል ሰጥቶናል።

መነሻቸውን ሰላምና ተግባቦት አድርገው መድረሻቸውን አብሮ ማደግ ያደረጉ ሕዝባዊ መሻቶች ስለሰላምና ስለአንድነት ስለአብሮ መበልጸግም ተጠንስሰው እውን የሆኑና እየሆኑ ያሉ ተግባሮች ናቸው። ይሄን ሀገራዊ ፍላጎታችን አሁን የጀመረ ሳይሆን ረጅም አመታትን ያስቆጠረ የታሪካችን አንድ አካል ነው። በምስራቅ አፍሪካ ኢጋድን፣ በአፍሪካ የአፍሪካ ሕብረትን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግሥታትን ድርጅት ምስረታ ውስጥ ዐሻራችን የጎላ ነው።

ስለባሕር በር የአብሮ መሥራትና መልማት መርህ ያልተናገርንበት ጊዜ የለም። ብዙዎች አላማና እውነታችንን እያወቁ ነው የቀጠናውን አለመረጋጋት ለማወክ የሚሞክሩት። ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የሀገራት ዲፕሎማቶች ገለጻ ከማድረግ ጀምሮ ሁሉንም ዓይነት የውይይት ሙከራዎችን አድርገናል። የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ መፍታት ይገባል በሚል መርህ እልባት የሰጠንባቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ባለውም ሆነ በሚኖረውም የጋራ ጉዳይ ላይ ሌሎችን ጣልቃ ሳናስገባ በራሳችን መልስ መስጠት ሥልጡንነት ከመሆኑም ባለፈ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ሃሳብ አጎልባችነት እየተስተናገደ ያለ ተራማጅ አስተሳሰብ እየሆነ መጥቷል።

ጉዳዩን ስቋጭ እንደመነሻዬ በዛፉና በጸጋዎቹ ነው። ጸጋዎቻችን እንዲበዙ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ፣ አብሮነታችንና ወንድማማችነታችን እንዲመለስ አንቂ ሃሳብ ከንቁ አእምሮና ልብ ጋር ያሻናል። ሀገራችንን እንደዛ ዛፍ ብንመለከታት እኛና ትውልዱ፣ ህልምና ራዕዮቻችን አበባና ፍሬውን ይሆናሉ። ልክ እንደ አበባና ፍሬው ህልምና መሻታችን እውን እንዲሆን ዛፉን እንዳቆሙት ለም አፈርና ውሃ ለም ሃሳብና በጎ ምክር ከወንድማማች መተቃቀፍ ጋር ያስፈልገናል።

አንዳንድ ነገሮች ቅርባችን ሆነው የራቁን ናቸው። ለምን አላደግንም? ለምን ከድህነትና ከተረጂነት አልወጣንም? ብሎ መጠየቁ ብቻውን ትርጉም የለውም። ለመጠየቅ ለመጠየቅ እማ እስካሁንም እኮ እየጠየቅን ነው፤ ቁም ነገሩ ያለው መጠየቁ ላይ ሳይሆን ጠይቆ መልስ ማግኘቱ ላይ ነው። እስኪ የሀገራችንን ትላንት ለአፍታ ቃኘት እናድርግ፤ በጦርነት ያለፉ በርካታ ጊዜዎችን እናገኛለን። እነዚህ ጦርነቶች እንዴት መጡ ብለን ስንጠየቅ አለመግባባት እና እኔነት የፈነጨባቸውን ሃሳብና ግብር እናገኛለን።

ወደ አሁን ስንመጣ ደግሞ ጥላቻ፣ ጎጠኝነትና ራስ ወዳድነት በርትተው እናገኛለን። ራስ ወዳድነት ሀገርን የሚያወድም ትውልድ የሚያኮላሽ መርዝ ነው። የዘረኝነት አስተሳሰብ እንደጦርነት ሁሉ ጠባሳ የሚያስቀምጥ፣ አብሮነትን አላልቶ የቂም በቀል ቁርሾን የሚያስቀምጥ ነው። ሰው ተተኳኩሶ ስለተገዳደለ ብቻ ሀገርን መቀመቅ አይከትም፤ ጥላቻና ዘረኝነትም የጦርነት ያክል ጅምላ ጨራሾች ናቸው። እናም ስለሰላም ዋጋ መክፈልን እንለማመድ። እንዲህ ሲሆን ብቻ ነው ለዳግማዊ ድል የምንበቃው። ስንመካከር ብቻ ነው ለሰላምና ልማታችን በጋራ የምንቆመው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You