አዲስ አበባ፦ በሶስት ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ የምርጥ ዘር ሽፋንን ሃምሳ በመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የእርሻ የመሬት ሽፋንን በመጨመር እና በሄክታር የሚገኘውን ምርት በማሳደግ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ይቻላል። የምርጥ ዘር አጠቃቀም ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ጋር ያለው ግንኙተ ቀጥተኛ ነው። ሆኖም እንደሀገር ያለው የምርጥ ዘር ሽፋን ግን ከሃያ በመቶ አይበልጥም።
በዘንድሮ ዓመት ባለፉት ዓመታት የነበረው የምርጥ ዘር አጠቃቀም ሂደትን በመገምገም የሶስት ዓመት እቅድ ተዘጋጅቷል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ በዚህም በሶስት ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ የምርጥ ዘር ሽፋንን ሃምሳ በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የፌዴራልና የክልል ተቋማትን ያካተተ ሀገራዊ ኮሚቴ በሚኒስቴሩ የተቋቋመ መሆኑን ያነሱት አቶ ኢሳያስ፤ ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች የምንላቸውን እንደጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ያሉ ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በእቅዱ መሠረት በነዚህ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ምርት መሰብሰብ አለበት በሚል ተነሳሽነት ተግባራዊ ይደረጋል። ሌሎች ሰብሎች ላይም እቅዱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸው በሶስት ዓመት ውስጥ በተለዩ ምርቶች ማለትም በስንዴ፣ በጤፍና በበቆሎ ምርት ላይ የምርጥ ዘር ሽፋንን መቶ ፐርሰንት ለማድረስ ታቅዷል ነው ያሉት።
ከምርምር ተቋማት የሚወጣ መነሻ ዘር መጠን ዝቅተኛ ነው። ይህንን መጠን ማሳደግ የሚቻልባቸው መንገዶች በእቅዱ ተካቷል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ ባለፉት ዓመታትም በክልልና በፌዴራል ተቋማት የምርጥ ዘር አተገባበር ላይ ክፍተት የታየ ሲሆን ይህንንም ችግር እቅዱ እንደሚፈታ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በየዓመቱ ከሃያ እስከ ሰላሳ ሺህ ሄክታር በምርጥ ዘር በመሸፈን ሁሉንም የጥራት ቁጥጥር አልፎ የሚወጣው ዘር ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ያነሰ እንደነበር አንስተው፤ በዚህ ዓመት ሰፊ መሬትን በምርጥ ዘር መሸፈን እና ለሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ብዙ የመነሻ ዘር ማባዛት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ዘንድሮ ወደ 148 ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዷል። እስከ አሁን ድረስ ወደ 75 ሺህ ሄክታር በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በክልሎችና በዘርፉ በሚገኙ አካላት ተሸፍኗል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ ካለፉት ዓመታት አንፃር የዘንድሮ ዓመት የምርጥ ዘር ሽፋን በምርትና ምርታማነት ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
በዘንድሮ ዓመት የመነሻ ዘር ብዜት ከአንድ ሺህ 200 ሄክታር በላይ የተሸፈነበት ሲሆን ዘንድሮ የሚገኘው የመነሻ ዘር የዘር ብዜትን እንደሚያሳድግ ተናግረው፤ የመነሻ ዘሩ የሚባዛው በምርምር ተቋማትና ጥሩ የምርጥ ዘር ማልሚያ ግብዓት ባላቸው ድርጅቶች መሆኑን ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም