የመስቀል ደመራ በዓል ታሪካዊ አመጣጥና አከባበሩ

በኢትዮጵያ በድምቀት እና በሽር ጉድ ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ መስቀል ነው። የመስቀል በዓል በወርሃ መስከረም በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለይም ደግሞ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዕምነት ተከታዮች በድምቀት የሚከበር ትልቅ በዓል ነው። በአብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ተከታዮች ዘንድ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መሣሪያ መስቀል ተብሎ እንደሚጠራ ይነገራል፡፡

“cross (ክሮስ)” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተወሰደው ‹‹ክሩክስ›› ከሚለው የላቲን ቃል ነው። ሆኖም የመስቀል አምልኮ ከክርስቶስ ዘመን በፊትም ጀምሮ የነበረ ለመሆኑ በርካታ የጽሑፍና የሥነቁፋሮ ማስረጃዎች ያስረዳሉ። ከክርስትና ዘመን በፊት ጀምሮ በሁሉም የጥንቱ ዓለም ክፍሎች የተለያየ የመስቀል ቅርጽ ያለባቸው የተለያዩ ዕቃዎች መገኘታቸው ይነገራል። ለአብነት በሕንድ፣ በሶሪያ፣ በፋርስና በግብፅ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መስቀሎች ተገኝተዋል። ከክርስትና በፊት በነበሩት ጊዜያትና ክርስቲያን ባልሆኑት ሕዝቦች መካከል መስቀልን እንደ አንድ ኃይማኖታዊ ምልክት አድርጎ መጠቀም በመላው ዓለም ላይ የተለመደ ልማድ እንደነበር የተለያዩ ድርሳናት ይጠቅሳሉ።

ቅዱሳን መጽሃፍት እንደሚያትቱት መስቀል ማለት ‘’ሰቀለ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መስቀያ ወይም መከራ ማለት ነው። መከራም የተባለበት የጥንት ሮማውያን ወንጀለኛን በሞት የሚቀጡት በመቀልያ እንጨት ላይ እየሰቀሉ ስለነበር ነው። አይሁድም ከገዥዎቻቸው በወረሱት ልማድ መሠረት ያለምንም ሀጥያት እና በደል አጥፊ ነው ብለው የፈረዱበትን እየሱስ ክርስቶስን ከወንበዴዎች ጋር በዕፀ መስቀል ሰቅለው በሞት ቀጡት፡፡

ይህ መድሀኒተ ዓለም የተሰቀለበት መስቀልም እንደማይጠቅም ሰባራ እቃ የትም ከተጣለ በኋላ እውራን፣ አንካሶች፣ለምጽ የያዛቸው፣ አጋንንት ያደረባቸው፣ ሰይጣን የለከፋቸው ሕሙማን ሁሉ እየሄዱ ሲዳስሱት ከየበሸታቸው ስለፈወሳቸው ይሁድ በክርስቶስ ገቢረ ታምር ይናደዱ እንደነበር ሁሉ የመስቀል ድውያንን መፈወስ ደግሞ ይበልጥ ስላበሳጫቸው ንዴታቸውን ለማብረድ ጉድጓድ ምሰው እንደቀበሩት ያስረዳል፡፡

የመስቀል በዓል ከዋዜማው ጀምሮ የሚከበር ሲሆን፤ የዋዜማው በዓል ደመራ በመባል የሚታወቅና በአደባባይ በድምቀት የሚከበር ነው። የመስቀል በዓል ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ብዙ ትርጉም ዓለው። በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ነጻ ለማውጣት ወደ ምድር በመምጣት ተሰቅሎ ጨለማን ወደ ብርሃን የቀየረበት በመሆኑ የእምነቱ ሊቃውንት አስተምሮ ያስረዳሉ።

እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በአረማውያን ለረጅም ዘመናት ተደብቆ ቆይቶ ነበር። እስራኤላዊዋ ንግስት እሌኒ በእግዚያብሄር መሪነት ይህን መስቀል በ16 በጭስ እየተመራች እውነተኛውን መስቀል ያገኘችበት ዕለት ነው።

የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እንደሚያስረዱት፤ መስቀሉ የተገኘበት ዕለት መስከረም 17 እንዲከበር በወሰኑት መሰረት በዓሉ ይከበራል። ምዕመናን በየዓመቱ መስከረም 16 ደመራን የሚያከብሩት የንግስት እሌኒ በጭስ ታግዛ መስቀሉን ያገኘችበትን ሁነት ለማሰብ ነው። እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ግማሹ በኢትዮጵያ ወሎ ውስጥ ግሸን ደብረ ከርቤ እንደሚገኝና ቀሪው የመስቀሉ ክፍል በተለያዩ ሀገራት እንደሚገኝ ያስረዳሉ። ይህ መስቀል ከተገኘ 5 ሺህ 500 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታምናለች የሚሉት ቀሲስ ታምራት፤ መስቀሉ በእስራኤል ውስጥ ጎለጎልታ ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ መገኘቱን ይናገራሉ።

ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከወደቀበት መርገም ያድነው ዘንድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በ33 ዓመቱ በራሱ ፈቃድ በመስቀል ላይ ተሰቀለ። በመገረፉ ቁስል እኛ ተፈወስን (1ጴጥ 2፥24):: በስቅለቱም ዲያብሎስን ድል ነሥቶ በወህኒ /በሲዖል/ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው (1ጴጥ 3፥18-19)። የሰው ልጅ በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ፍጹም ነጻ ወጣ:: ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ ሕዝብና አሕዛብን በአንድ አካል ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ (ኤፌ 2፥16)። ከፍተኛ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ብቻ ይሰቀሉበት የነበረው መስቀል ከጌታ ስቅለት በኋላ የመዳን ምልክት መሆኑን ቅዱሳን መጽሃፍት ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን በማድረጉ የታወኩ አይሁድ መስቀሉን ከሰዎች እይታ ለመሠወር ወስነው ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት:: መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል የቆሻሻ መጣያና ማከማቻም እንዳደረጉት ስለመስቀል በዓል የተጻፉ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ መጽሃፍት ይዘክራሉ። ምንም እንኳን አይሁድ ለጊዜው መስቀሉን ከዐይን ለመሰወር ቢችሉም ከክርስቲያኖች ልቡና ግን ሊያወጡት አልቻሉም:: የመስቀሉ ብርሃን በልቡናቸው የሚያበራ ክርስቲያኖች እየበዙ መጡና መስቀሉንም መፈለግ ጀመሩ:: ይህ ሂደት በንግስት እሌኒ ጋር ያለው ትስስር ምን እንደሆነ በዝርዝር መመለከት ያስፈልጋል።

የንግሥት እሌኒ ድካምና ፍሬ

ንግሥት እሌኒ ልጇን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ክርስትና ሃይማኖትና ስለ ክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ። ክርስትናም ብሔራዊ ኃይማኖት ሆነች። ንግሥት እሌኒም የተፈጠረውን አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችንን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ.ም ወደ እየሩሳሌም እንደሄደች ስለመስቀል የተጻፉ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ንግሥት እሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ እየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በእየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነፅ ለእግዚአብሔር ተሳለች። ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ.ም ተጠመቀ። ቅድስት እሌኒም ወደ እየሩሳሌም ሔደች እንደደረሰችም ስለ ክብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች። ቦታውን የሚያስረዳት ግን አላገኘችም። አይሁድ የተቀበረበትን ቦታ ለማሳየት ባይፈልጉም በኋላ ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመላከታት ዳሩ ግን ኪራኮስ ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከነበሩት ከሦስቱ ተራሮች ውስጥ መስቀሉ የሚገኝበት የትኛው እንደሆነ ለይቶ ማወቅ አልቻለም፡፡

ንግሥት እሌኒ ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ እርዳታ ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠል ጸሎት ተያዘ። የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት። ቅዱስ ያሬድም ጢሱ ሰገደ ብሎታል። ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች። ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ። የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡:

መስቀሎቹን ወስደው በሞተ ሰው በተራ ቢያስቀምጡ ጌታችን የተሰቀለበትና በዕለተ ዐርብ ተሰቅሎ የዋለበትና በደሙ መፍሰስ የተቀደሰው መሰቀል የሞተውን ሰው በማስነሣት በሠራው ተአምር ሌሎቹ ሁለቱ ታምራት ባለማድረጋቸው የጌታን መስቀል ለይቶ ማወቅ ተችሏል። እሌኒና ክርስቲያኖች ሁሉ ለመስቀሉ ሰገዱለት። በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ጊዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ። ንግሥት እሌኒ ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ ከሠራችለት ጊዜ ጀምሮ በመስከረም 17 ቀን አሁን በኢትዮጵያ እንደሚከበረው በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀል ይከበር ነበር።

ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጣ?

የጌታ መስቀል ለብዙ ዓመታት በእየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት መስቀሉን ለመውሰድ ጠብ ፈጠሩ። በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣ነየእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የኃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት:: ከዚያም አያይዘው በእየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ለዐራት ከፍለው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት:: የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በግብፅ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት የግብፅ ክርስቲያኖች በአማሌቃውያን ከሚደርስባቸው ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ በማድረጋቸው የግብፅ ፓትርያርክ የከበሩ ስጦታዎችን ላኩላቸው:: ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ወርቅ ሳይሆን ጌታ የተሰቀለበትን መስቀሉን እንደሆነ ገለጹላቸው:: በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች:: ይህ ግማደ መስቀል በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ኢትዮጵያን እየባረከ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስቀልን ከሐዋርያት በተማረችው መሠረት የወርና የዓመት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች:: መስከረም 16 ቀን ደመራ ደምራ ጸሎትና ምሥጋና ታቀርባለች። ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት መሬት በእሌኒ አማካኝነት መገኘቱን ስታስብ በአሁኑ ዘመን ከብዙ ሰዎች ልቡና የተሠወረው መስቀል እንዲገለጥላቸው ትጸልያለች::

በመስቀል የሚገኘውን በረከት እየተቀበለች በመስቀል የሚመሰለውን መከራ ሁሉ ትታገሣለች:: መስቀል በካህናት በምእመናንና በምእመናት ልቡና ተስሏል:: በአንገታቸውና ልብሳቸውም መስቀል አለ:: ሥራ ሲጀመርና ምግብ ሲቀርብ በመስቀል አምሳያ ይማተባል:: መስቀል ለሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ነው:: “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ 16፡24) እንዳለ ጌታችን ቤተ ክርስቲያናችን ዕለት ዕለት መስቀሉን ትሸከማለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የምትደምረው ደመራ አገራዊ አንደምታም አለው:: የመስቀል ደመራ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት: የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና ተሰጥቶት ዓለም አቀፋዊ ቅርስ ተብሎ ተመዝግቧል::

«የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚብሔር ኃይል ነው» (1ቆሮ 1፥18) በሚል መጽሀፍ ቅዱሳዊ አስተምሮ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል። በደመራ ደምረው ችቦ ለኩሰው የሆያ ሆየ ጭፈራ በዜማ በመጨፈር ይጫወታሉ። ይህ የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ የተመዘገበ በመሆኑ ከእምነቱ ተከታዮች በሸገር የሀገር የቱሪስት መስብ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያከብረውና ሊንከባከበው ይገባል እንላለን!።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You