የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ መንፈሳዊ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው። መስቀል ኃይላችን፣ መስቀል ቤዛችን፣ መስቀል መመኪያችን በሚል የሃይማኖቱ አስተምህሮ ሥርዓቱ በሚፈቅደው አለባበስና አካሄድ የእምነቱ ተከታይ በተገኘበት በዝማሬና፣ በሌሎች መንፈሳዊ ዝግጅቶች ይከበራል።
የመስቀል በዓል ከመንፈሳዊ ቀለሙ ጎን ለጎን ብዙሀነት የሚታይበት የእርስ በእርስ ጉርብትና የሚንፀባረቅበት በዓልም ጭምር ነው። እንደእምነቱ አስተምህሮ መስቀል የሚከበርበት ዋና ምክንያት የክርስቶስ ግማደ መስቀል በንግስት እሌኒ ዓማካኝነት መገኘቱን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን የበዓሉ ዋና ዓላማ በመስቀሉ ጥልን መሻሩ፣ ፍቅርን ማብሰሩ ዋና ሆኖ ይጠቀሳል።
መስቀል ‹ሰቀለ› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መስቀያ ወይም መከራ የሚለውን ትርጉም ይይዛል። መከራ የተባለበት ምክንያትም የጥንት ሮማውያን ወንጀለኞችን በሞት ሲቀጡ በእንጨት ላይ እየሰቀሉ ስለነበር ነው። አይሁድም ከገዢዎቻቸው በወረሱት ልማድ ከጽድቅ በቀር አንዳች በደል የሌለበትን እየሱስ ክርስቶስን ወንጀለኛ በማድረግ በመስቀል ላይ ሰቅለውታል። ይህ ጻድቁን ጌታ የሰቀለ የድህነት መስቀል ብዙዎችን ከሀፅያትና ከበደል፣ ከአጋንትና ከለምጽ ሲፈውስ ያዩት አይሁዶች በብስጭት ጉድጓድ ምሰው ይቀብሩታል።
አይሁዶች በዚህ ሳያበቁ በእየሩሳሌም እና በይሁዳ ምድር ያሉ ሕዝቦች ማንኛውንም ጥራጊ መስቀሉን በቀበሩበት ቦታ ላይ እንዲጥሉ ትዕዛዝ በማስተላለፍ የቅዱስ መስቀሉ ስፍራ 200 ዘመናት ያህል የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ነበር። የመስቀሉ ፍቅር ያንገበግባት የነበረችው ንግስት እሌኒ ዘውድ በጫነ ልጇ ቆስጠንጥኖስ በኩል የወቅቱ የክርስቲያን ጠላት የነበሩ መክሰምያኖስ እና ድዮቅልጥያኖስ የተባሉ አህዛቦችን በመፋለም በስተመጨረሻ ደመራ ደምራ የጭሱን አቅጣጫ በመከተል መስቀሉ ከተቀበረበት እንዲወጣ ሆኗል።
‹አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም አታድክሚ እንጨት አሰባስበሽ፣ ዕጣን አፍሽበት፣ በእሳትም አያይዢው የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሸ አስቆፍሪ በዚህ ምልክት ታገኛለሽ› በሚል የኪራኮስ ምክር መሰረት ደመራ ደምራ የመስቀሉን ስፍራ ደረሰችበት። ከመስከረም 17 ጀምራ እስከ መጋቢት 10 ድረስ ቀንና ለሊት ለሰባት ወራት ያህል የቆሻሻውን ኮረብታ አስቆፍራ መስቀሉን አገኘች።
በጠላቶች እንደተራ ነገር የትም ተጥሎ ዓመታትን የዘለቀው መስቀል ጊዜው ደርሶ ለብዙዎች የደስታና የመዳን መንገድ ሆነ። መስከረም 16 የሚከበረው የደመራ በዓልም ያን መስቀሉን ከተሰወረበት ለማግኘት የተከፈለውን ዋጋ ለማስታወስ መሆኑን የሀይማኖቱ አስተምህሮ ይገልጻል። ደመራ የሚለው ቃል ‹ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተመዘዘ ሲሆን አንድነትንና ሕብረትንም ይወክላል።
የመስቀል በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (በዩኒስኮ) የተመዘገበ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ በዓል ከሆነ ሰነባብቷል። ይህ ማለት መንፈሳዊነቱን ሳይለቅ፣ በሕግና በቀኖና በተደራጀ መልኩ ‹‹ኢንታንጀብል›› በሚል የቅርስ መዝገብ ላይ ሰፍሯል። የመስቀል በዓል ከስም አጠራሩ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነት የተንጸባረቀበት ነው። ደመራ በሚለው የመደመርና የብዙሀነት ሥርወ-ቃል መሰረቱን ሲያቆም የነበረውን ካለውና ከሚመጣው ጋር በማስተሳሰር እንደሆነ አምናለሁ። አንድነትና አብሮነት በራቀን በዚህ ጊዜ የደመራ ጽንሰ ሀሳብ አስታራቂና አግባቢ ሆኖ መምጣቱ ዋጋው ብዙ ነው።
አንድነት ሰባኪ ክብረ በዓላት ሀገር በማቅናትና ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ሚናቸው የትዬየሌለ ነው። በፍቅርና በእርስ በርስ ጉርብትና የደረጁ እንደዚህ አይነት መንፈሳዊና የአደባባይ በዓላት ጥሩ መልዕክት በማስተላለፍ ከበጎ ማኅበራዊ እሴቶች ተለይተው የሚታዩ አይደሉም። መንፈሳዊነትን ለብሰው ከማኅበራዊ የተገለሉ ይምሰሉ እንጂ በዋጋቸውና እያደረጉ ባሉት አስተዋጽኦ የሀገር ካስማነታቸው ገዝፎ የሚታይ ነው።
መስቀል በደመራ ጽንሰ ሀሳብ አብሮነትንና ብዙሀነትን ከዋጀ ተለያይተን ለቆምነው ለእኛ መልዕክቱ የገዘፈ ነው። መንፈሳዊ በዓላት ከዝማሬና ከመንፈሳዊ ሥርዓታቸው ጎን ለጎን ሊያስተምሩን የሚገባ ብዙ ነገር አለ። እየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ሲል በመስቀል ላይ ከተሰቀለ፣ ተሰቅሎም ከሞተልን እኛስ ስለሌላው ምንድነው የሚሰማን? እሌኒ ፍቅር አስገድዷት መስቀሉን ከተሰወረበት ካገኘች የእኛስ የቤት ስራ ምንድነው? እና መሰል ጥያቄዎች የመስቀልን ክብረ በዓል እያከበርን አብረን የምንመልሳቸው ናቸው። በጥላቻና በመገፋፋት የፍቅር አምላክ እየሱስን ከሕይወታችን፣ ከቤታችን፣ ከሕይወታችን እናርቀዋለን እንጂ አናቀርበውም።
መስቀል መልካችን ነው፤ ጥንተ ወዛችን። መንፈሳዊ በዓሎቻችን በሥርዐትና በጨዋነት የተባ ኢትዮጵያዊነትን ካስገኙልን በረከቶቻችን መካከል ናቸው። እያከበርናቸው የመጣነው በዚህ መንፈስ ነው። ወደፊትም የምናከብራቸው በዚህ መንገድ ነው። መስቀል ከጽኑ ፍቅር መሃል የፈለቀ ክርስቶሳዊ ዋጋ ነው። ዋጋው በሁላችንም ላይ ተገልጦ ከጥል ወደፍቅር፣ ከክርክር ወደውዳዴ የምንሸጋገርበት ቢሆን ብዙ ትርፍን ያስገኝልናል።
በዓሎቻችን የነበረውን አጥብቀን በፍቅርና በወንድማማችነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ የምንሆንባቸው ናቸው። የመስቀሉ ፍቅር በዚህ ካልተተረጎመ በሌላ ቢተረጎም ልክ አይሆንም። መስቀል የፍቅር አደራ ነው ካልን፤ ፍቅራችን ወሰን ሊኖረው አይገባም። ፍቅር የክርስቶስ የእውነት ወዝ ያረፈበት ነው ካልን፤ ወዛችን ወደሌሎች ሊተላለፍ ግድ ይለዋል። መስቀል ሞት የሞተበት፣ ፍቅር የተወለደበት ነው ካልን ፍቅርን አምጦ መውለድ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
የወረስነው ውርሳችን ተከባብሮ አብሮ መኖር ነው። ውርሳችን አብሮ ማክበር፣ አብሮ መሆን ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በአንዱ በዓል ቤተኛ በመሆን አብሮ በማክበር ጥሩ ሥም ያለን ነን። የእኔ በሌለበት ኢትዮጵያዊነት ከትላንት ወደዛሬ ስንጓዝ ዋስትና ያደረግነው ጽኑ ጉርብትናችንን ነው። በአንድ መርፌና ክር የተጣፍንባቸው በልዩነት ውስጥ የደመቅንባቸው እልፍ ባህሎች እና መንፈሳዊ በዓላት አሉን። ከነዚህ ባሕሎች መሃል መስቀል አንዱ ሆኖ መጥቷል።
ልቦቻችን እንደነጠላዎቻችን ፀዓዳ ለብሰው ፍቅር መስካሪ እንዲሆኑ እና ከእዳ እንዲያወጡን ይገባል። እንደአለባበሳችን፣ እንደዜማችንና እንደመንፈሳዊነታችን ልናስተካክላቸው የሚገቡ የተዘበራረቁ ብዙ ነገሮች አሉ። መስቀል መንፈሳዊነት ከዓለማዊነት ጋር ሳያብር የቄሳርን ለቄሳር የክርስቶስን ለክርስቶስ የምንሰዋበት የመሰዊያ ሥፍራችን ነው። መንፈሳዊ በዓላት የንሰሀ እና የሱባዔ ስፍራ በመሆን የሚያገለግሉንም ናቸው። በደሎቻችንን ተናዘን ለተሀድሶ እንድንበቃ በዚያ በኩል ብዙ መንገዶች ይከፈታሉ።
በመስቀል ስለሀገራችን እንጸልያለን፣ ስለሕዝባችን እንማልዳለን። በመስቀል በዝማሬያችን ፈጣሪ ሰላም እንዲሰጠን፣ አብሮነታችንን እንዲያጠነክር እንጠይቀዋለን። የመስቀሉ ፍቅር እንዲህ ባለው ለሁሉ በሚተርፍ ሰላማዊ አካሄድ ካልተገለጠ የጣመ ትርጉም አይኖረውም። በመስቀሉ ስም ክርስቶስን ለብሰን አዲስ ለመሆን በፍቃዱ ስር ማረፍ ይኖርብናል። የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ፆምና ፀሎት የሚፈልግ ነው። መንፈሳዊ በዓላት ደግሞ ለዚህ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ናቸው። የመስቀል በዓልን ስናስብ እንዳለፈው ጊዜ ስለሀገራችን፣ ስለሕዝባችን፣ ስለትውልዱ በማሰብ መሆኑ የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው።
የመስቀል በዓል በየዓመቱ የአዲስ ዓመትን መግባት ተከትሎ የሚከበር የፍቅርና የመተሳሰብ በዓል መሆኑን መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው። እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ ብለን፣ በመስቀል ወፍ እና በአደይ አበባ ታጅበን የፍቅር መልክ የሆነውን የመስቀል በዓል በመስቀል አደባባይ ማክበር ልዩ ስሜትን የሚጭር ነው።
ብዙሀነት ጌጣችንና አርማችን ሆኖ ከሚቀጥልባቸው የአደባባይ በዓላት መካከል እንደመስቀል ያሉ ጉምቱ ማኅበራዊ ስርዓቶች የሚዳብሩባቸው ክብረ በዓላት አሉ። ከአዲስ ዓመት ወደ ደመራ፣ ከዚያም ወደመስቀልና እሬቻ የምናደርገው ጉዞ የኢትዮጵያዊነትን ቀለም የሚገልጡ ሕብረ ትውፊቶቻችን ናቸው። በቀጣይም በአብሮነት የምናከብራቸው በብሔር ብሔረሰብ አስተሳሰብና ባሕል የደረጁ የዘመን መለወጫ በዓላት ደጃፋችን ስር አድፍጠዋል።
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መስቀል የላቀ ቦታ አለው። የእምነቱ ራስ የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ከሚገለጽባቸውና ከሚከበርባቸው አጋጣሚዎች አንዱ መስቀል ነው። አማኙን ከሚያመልከው አምላኩ ጋር አስተሳስሮና አቆራኝቶ፣ በቅዳሴውና በሰዐታቱ፣ በማህሌቱና በወረቡ መሀል ለምስጋና መሰዊያ የሚቀርብ የእምነት ዋስትና ነው። ከጎለጎታ የራስ ቅል ጀምሮ ዛሬም ድረስ መስቀል እየሳምን፣ እየባረክን፣ እየያዝንና በአንገታችን ላይ በማንጠልጠል እምነታችንን ገልጠናል። ከእንዲህ አይነቱ ታሪካዊ ዳራ በመነሳት የመስቀል በዓል ለኦርቶዶክሳውያን ልዩ ትርጉም አለው።
በመስቀሉ ጥልን ገሎ፣ ሀፅያታችንን ይቅር ብሎ፣ በደላችንንም ሽሮ በሞቱ ታርቆናል ስንል፤ የተሰቀለውን ጌታ ከተሰቀለበት መስቀል ጋር አመሳጥረን ነው። አአትብ ገጽዬ በኩለንታዬ በትምህርተ መስቀል ብለን የምናማትበው ለመስቀል ካለን ፍቅር የተነሳ ነው። ክርስቲያንና መስቀል የአንድ አካል ፊትና ኋላ ናቸው። በልብሰ ተክኖ፣ በካባላንቃ፣ በአስኬማ፣ በድንቅ ዜማ ታጅበን ደመራችንን እንለኩሳለን።
መስቀል ለሰው ልጆች ሁሉ የድህነት ምልክት ሆኖ ይታሰባል። ‹በመስቀሉ ጥልን ገደለ› የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮት ላነሳሁት በኩረ ሐሳብ ምስክር በመሆን የሚያግዝ ነው። የትኛውም ሀይማኖታዊ በዓል ፈጣሪ የሚመሰገንበት፣ ክብሩ የሚገለጥበት መሆኑ ይታወቃል። የመስቀል በዓልም ፈጣሪ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዳግም ሕይወትን እንደሰጠንና ጥልን በፍቅር እንደሻረ አንዱ ማሳያ ነው። በመሆኑም የመስቀል በዓል የፍቅርና የይቅርታ፣ የእርቅና የጉርብትና ሃይማኖታዊ በዓል ነው ብል ተሳሳትክ አትሉኝም።
‹በመስቀሉ ጥልን ገደለ› የሚለው ኃይለ ቃል የመስቀሉ ኃይል ከተገለፀባቸው ግብር እና ንግግር መካከል ዋነኛው ነው። ይህ እውነት የመስቀል በዓል የክብረ-በዓሉ ዋና ዓላማ ሆኖ ከዘመን ዘመን ሲከበር መጥቷል። በመስቀሉ ጥልን ገደለ ስንል ፍቅርን ሰጠን፣ ከሀፅያት አነጻን፣ ከወደቅንበት አነሳን፣ ከዲያቢሎስ ግዞት ነጻ አወጣን እያልን ነው። በተዘዋዋሪ አንድነትንና ሰብዓዊነትንም እየሰበከን ነው።
ከክርስቶስ ስቅለት በኋላ ዓለም ዳግመኛ ተፈጥራለች። ዓለምን ለማዳን ከተጠበበው ጥበብ በላይ በሞቱ የሰውን ልጅ ያዳነበት ጥበቡ እንደሚበልጥ ቅዱሳን መጽሐፍቶች ይናገራሉ። ስለሆነም የመስቀል በዓል ትርጓሜው በዚህ ሚዛን የሚለካ በዓል ነው። ደመራ ደምረን፣ በችቦ ራስ ላይ እሳት ለኩሰን እሌኒን እንዘክራለን። በማግስቱ መስቀል ኃይላችን ነው ስንል ክብረበዓሉን በደመቀ መልኩ እናከብራለን።
በሚዛናዊነት ካየናቸው፤ ሁሉም መንፈሳዊ በዓላት ከጋራ ማንነት ውስጥ የተፈለቀቁ የጋራችን ናቸው። ለዚህም ነው በክርስቲያንና በሙስሊሙ ሀይማኖታዊ በዓላት ላይ ከምንም በላይ የአብሮነት መንፈስ የሚታየው። የሀይማኖት መቻቻል ምልክት ሆነን በዓለም አደባባይ የምንጠራው ብቻነትን በሻረ የእርስ በእርስ ትቅቅፍ ነው። መስቀልንም ፈጣሪን ባስቀደመ፣ ሰውነትን ባስከተለ መንፈሳዊ ሥርዓት እንደተለመደው በጋራ እናከብረዋለን።
የመስቀል በዓል የአከባበር ሥርዓትና የመንፈሳዊ ትርጓሜው አሁን ላለው ሀገራዊ ሁኔታ መልካም መንፈስን የሚያላብስ ነው ብዬ አስባለሁ። ከአከባበሩ ስንነሳ አንድነትና ራሮት ይታይበታል። ፍቅርን ያነገበ መንፈሳዊ መነሻ አለው። ትርጓሜውን ስናይ ደግሞ በፍቅር ጀምሮ በፍቅር የሚያበቃ እዝነተ ልብ ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ ፍቅር የቀዘቀዘበት፣ ቡዳኔና ጎራ የገዘፈበት፣ እኔነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያየለበት፣ ጥልና ክርክር፣ ጥላቻና ትርክት የሰፋበት ወቅት ነው። ታዲያ የመስቀል መንፈስ አያስፈልገንም ትላላችሁ? ጥልን በመስቀሉ እንደገደለ እኛም ፍቅርን ከመስቀሉ አምጠን መውለድ ይጠበቅብናል። መልካም በዓል።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም