የዓለም ቅርሱ ደመራ

የመስቀል በዓል ደመራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበር ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ይታወቃል።

የመስቀል ደመራ በዓል ንግሥት እሌኒ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍቅር ሲል መስዋዕትነትን የከፈለበትና ጠፍቶ የነበረውን መስቀል ለመፈለግ ያከናወነችውን ሥርዓት ለማሰብ የሚከበር መሆኑን የሃይማኖቱ አባቶች ይገልፃሉ።

በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላልፍ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ይጠቁማሉ።

ሊቀልሳናት መምህር የኋላወርቅ ኃይለስላሴ እንደሚናገሩት፤ የመስቀል ደመራ በዓል ክብረበዓል ብቻ ሳይሆን የኃይማኖት አባቶችና ምዕመናን በአንድነት ሆነው ለሀገር ሰላምና አንድነት ለፈጣሪ በንፁህ ልባቸው የሚፀልዩበት ነው።

እንደ መምህር የኋላወርቅ ገለፃ፤ የመስቀል በአል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላም፣ የመከባበር፣ የጠፋን ነገር የመግለጥ እንዲሁም የትህትና በዓል ነው። በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ ሊያስተላልፈው ይገባል።

የአሁኑ ትውልድ በተለይም ወጣቱ ከኃይማኖት አባቶች የሚሰጡ የፍቅር፣ የትህትና፣ የአንድነትና የሰላም ትምህርቶችን በመተግበር ለጠንካራ ሀገር ግንባታ በአንድነት መቆም እንደሚገባውም መምህር የኃዋላወርቅ ይመክራሉ።

መምህር የኋላወርቅ በዕምነት ተቋማት፣ በትምህርት ቤት፣ በቤተሰብና በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን የሚያጠናክሩ የግብረ ገብ ትምህርቶችን በተግባር መግለጥ ይገባል ነው ያሉት።

የበዓሉን ታሪክ በሚገባ በማወቅ፣ መንፈሳዊ ይዘቱን ሳይለቅ፣ ታሪኩንና ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ ማሻገር ከሁሉም ምዕመናን እንደሚጠበቅ የሚገልጹት ደግሞ መምህር ሃይለማርያም ቦንሳ ናቸው።

ትውልዱ የመስቀል በዓል ታሪክን በአግባቡ ማወቅና መጠበቅ እንደአለበት የሚጠቁሙት መምህር ሃይለማርያም ቦንሳ፤ መስቀል መንፈሳዊ በዓል በመሆኑ ምዕመናን በዝማሬ፣ በትምህርት፣ በኃይማኖታዊ ሥርዓትና አለባበስ እንደሚያከብሩት ይናገራሉ።

የመስቀል በዓል ንግሥት እሌኒ መስቀሉ ከተቀበረበት በርካታ ዓመታት ያወጣችበት ዕለት መሆኑን በመግልጽ፤ ይህ በዓል በኢትዮጵያ የሚከበረው ንግሥት እሌኒ ግማደ መስቀሉን ለማግኘት ያደረገቻቸውን ጥረቶች በተግባር እየተገለጠ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው መምህር ኃይለማርያም ያወሳሉ።

የፍቅር፣ ትህትና፣ ሰላምና አንድነት መገለጫ የሆነው የመስቀልን አስተምህሮት የአሁኑ ትውልድ በተግባር እንዲያሳይ የኃይማኖት አባቶች አርዓያነት ወሳኝ መሆኑን የሚጠቁሙት መምህር ኃይለማርያም፤ መስቀል የትህትና እና የአንድነት በዓል በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ለሀገር አንድነትና ፍቅር በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ሊተገብረው ይገባል ይላሉ።

መምህር አሮን ሱፋ በበኩላቸው፤ የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው። ከኃይማኖታዊ መገለጫነቱ ባሻገር የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ሀብት እንደሆነ በማንሳት፤ በዓሉ ሲከበረም በደስታና መንፈሳዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እንደሆነ ይገልፃሉ።

የመስቀል በዓል በኃይማኖታዊ መገለጫነቱ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የሚጠቁሙት መምህር አሮን፤ በዓሉ ሲከበርም በመስቀሉ የተገለጠውን የክርስቶስ ቤዛነት፣ ፍቅር እና እውነትነት አርዓያ በመከተል መሆን አለበት ይላሉ።

እንደ መምህር አሮን ገለፃ፤ በዓሉ የአንድነት፣ የአብሮነትና የጽናት ማሳያ ነው። በመዋደድ ልዩነትን፣ መራራቅን እና አለመግባባትን በማስወገድ አብሮነትን ማጠናከር የሚቻልበትን መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል።

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና ተሠጥቶት ዓለም አቀፋዊ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን በማስታወስ፤ የኢትዮጵያዊነት መገለጫና የጋራ ሀብት የሆነውን ይህን በዓል እሴቱን ጠብቆ በማክበርና ለትውልድ ማቆየት እንደሚገባ መምህር አሮን ይጠቁማሉ።

የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ኃይማኖት፣ ብጹዓን አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የእምነቱ ተከታዮችና የውጭ ጎብኚዎች በተገኙበት ተከብሮ አልፏል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You