ክልሉ 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ እቅድ ተይዟል

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ መሬት እና ማዕድን ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ ግርማይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ እየተሠራ ነው። የማዕድን ምርት በሕጋዊ መንገድ እንዲሠራ ሕግ እና አሠራር ተዘርግቷል።

በክልሉ ከፀጥታ ጋር በነበረው ችግር ምክንያት ከማዕድን መገኘት የነበረበት ገቢ ሳይገኝ መቆየቱን በመጥቀስ፤ የነበረው ክፍተት በማስተካከል እና ሥርዓት መዘርጋት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት መቻሉን ተናግረዋል። በዚህም በአዲሱ በጀት ዓመት 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ እንዲሁም ስልሳ ኪሎ ግራም የሳፋየር ማዕድን ወደ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከማዕድን 35 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን ገቢው የሚገኘውም ለኮንስትራክሽን ግብዓት፣ ከኢንዱስትሪ እና ለጌጣጌጥ የሚውሉ ማዕድናት መሆኑን አስረድተዋል። ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ወዲህ ከቀድሞ ታጣቂዎች በክብር የተሸኙ አባላት ወደ ዘርፉ በሥርዓት ተሠማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

የማዕድን ዘርፍ ከበፊቱ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የነበሩት የአሠራር ድክመቶች በማሻሻል ጥሩ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሮው ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ ሲያቀርቡ የሚስተናገዱበት ደንብ መቀመጡን ጠቅሰው፤ በደንቡ መሠረት ሥራን ሲያከናውን ከዘርፉ የታሰበውን ገቢ ለማግኘት ያግዛል ብለዋል።

የ2017 በጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት እቅድ መያዙን ጠቅሰው፤ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል። በተጨማሪም ሌሎች የማዕድን ቦታዎችን በማጥናት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ወጣቶች እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል።

በክልሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት የማዕድን ዘርፉ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በመግለፅ፤ ለበርካታ ወጣቶች ተስፋ የሚሰጥ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውም መርዳት እንዲችሉ ታስቦ እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You