
እናትነት ስስት ነው፤ እናት ለልጆቿ ያላት ስስት ጥግ የለውም። ይህም ለሴት ልጅ ብቻ የተሰጠ ፀጋ ነው። ሴት ልጅ በተፈጥሮ ከታደለቻቸው እልፍ በረከቶች መካከል ልጇን ዘጠኝ ወር በሆዷ መሸከሟ፣ አምጣ መውለዷና ጡቶቿን አጥብታ ማሳደጓ ሲሆን፤ ለልጆቿ ካላት ስስትና ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በልተው የሚጠግቡ፣ ጠጥተው የሚረኩ፣ ለብሰው የሚሞቃቸው አይመስላትም።
‹‹ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች›› እንዲሉ ሴት ልጅ እናት ስትሆን ልጆቿ የመኖሯ ትርጉም ይሆኑና እሷ አዳፋ ለብሳ ልጆቿን ፀአዳ ታለብሳለች፤ የእኔ የምትለው ሁሉ ቢጎድልም የልጆቿን ጎደሎ ግን ከአፍ እስከ ገደፉ ትሞላለች፤
እናትነት እንግዲህ ይህ ነው፤ በአባጣ ጎርባጣው በጠመዝማዛው መንገድ ሁሉ አልፋ የራቀውን አቅርባ በደበዘዘ ማንነቷ ውስጥ ልጆቿ ፈክተው፣ ደምቀውና ቀድመው እንዲታዩ ታደርጋለች። ይህ የእናትነት መገለጫ ነው። እርግጥ ነው በልጆች አስተዳደግ ላይ ወላጅ አባትም ጉልህ ሚና አለው። ወላጅ አባቶች በልጆች አስተዳደግ የድርሻቸውን መወጣት ከቻሉ የእናቶችን ድካም በብዙ እጥፍ ማቃለል እንደሚችሉ ይታመናል። ይሁንና ሴቶች ብዙ ጊዜ የማኅበረሰቡ ግፍ ሰለባዎችና የማኅበራዊ ፍትሕ ጉድለት ሰለባዎች ሲሆኑ ይስተዋላል። ያም ቢሆን ታዲያ ሴት ልጅ ጀግና እና ብልህ ናት። በተለይም እናት ስትሆን የቤተሰብ መሠረት የደስታ ምንጭ ናት።
የቤተሰብ መሠረት የደስታ ምንጭ የሆነችው እናት በቤት ውስጥ የሚኖሯት ኃላፊነቶች እጅግ ሰፊ፣ ጥልቅና ውስብስብ በመሆናቸው አባት በጎደለ ጊዜ ደግሞ ኃላፊነቶቹ ድርብ ድርብርብ መሆናቸው አይቀሬ ነው። እናቶች በተፈጥሮ ከታደሉትና ማኅበረሰቡ ከጣለባቸው ኃላፊነቶች በተጨማሪ በልጆች አስተዳደግ ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም የወላጅ አባቶች ሚናም እንዲሁ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። በመሆኑም መልካም አባቶች በብዙ መልኩ የእናቶችን ጫና ማቃለል እንደሚችሉ ሁሉ ልጆቻቸውን ያለ አባት የሚያሳድጉ እናቶች ደግሞ የሚወጡት ኃላፊነት እንደ ሰማዕታት ገድል እጥፍ ድርብ እንደሆነ ይታመናል።
እነዚህ እናቶች ታዲያ እጥፍ ድርብ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ወደኋላ የሚሉ አይደሉም። በብርቱ ጥረታቸው ልጆቻቸውን ያለአባት ያሳድጋሉ፣ ያስተምራሉ፣ ለወግ ለማዕረግ ያበቃሉ። ይህም በየአካባቢያችንና በየጓዳችን የምናስተውለው ሐቅ ነው። በዛሬው ዕለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113 በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48 ጊዜ እየተከበረ ያለውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (March 8) ምክንያት በማድረግ ልጆቻቸውን ያለአባት የሚያሳድጉ ጠንካራ እናቶችን ልናነሳ ወደናል።
በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሴቶች ዘርፈ ብዙ የሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ያሉባቸው ቢሆንም ጫናዎቹን ሁሉ ተቋቁመው ልጆች በማሳደግ ትልቁን ኃላፊነት ይወጣሉ። በተለይም የኢኮኖሚ ጥገኛ ሆነው ለልጆቻቸው ብዙ ዋጋ የሚከፍሉ እናቶችን ቤት ይቁጠራቸው።
እናቶች ልጆቻቸውን ከአባት ውጭ ለማሳደግ ከሚገደዱባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መካከል መደፈር አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ በሞት መለየትና ባለመግባባት መለያየትም ሌላው ምክንያት ነው። ይሁንና ከእነዚህ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ከሆኑ ምክንያቶች ባለፈ አሁን አሁን ደግሞ ልጅ ለመውለድ ብቻ ባል የሚያገቡና ልጅ ከወለዱ በኋላ ተለያይተው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች እየመጡ ነው። ነገር ግን እንደዚህ አይነት እናቶች ለጊዜው ጉዳያችን አይደሉም። ለጊዜው ጉዳያችን ይሁኑ ያልናቸው እናቶች ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ልጆቻቸውን ያለ አባት እያሳደጉ ያሉትን ነው። እነዚህ እናቶች ልጆቻቸውን ያለ አባት ሲያሳድጉ የሚገጥማቸው ችግር ምንድን ነው፤ እንዴትስ እየተወጡት ነው፤ ምን መልዕክትስ አላቸው የሚለው ዋናው ትኩረታችን ነው።
አርቲስት የትናየት ታምራት ወይም በቤት ስሟ ሚሚ ታምራት በመባል ትታወቃለች። በኪነጥበብ ውስጥ በነበራት የትወና ሥራ በበርካታ ፊልሞች መሪ ተዋናይት በመሆን ተውናለች። ከትወና ሥራዋ በተጨማሪም በጤናው ዘርፍ ተሠማርታ በአይነቱ ልዩ የሆነ የስዊዝ ዲያግኖስቲክስ የሕክምና ማዕከልን ያቋቋመች ብርቱ ሴት እንዲሁም እናት ናት። የትዳር ሕይወት ባይኖራትም ትዳር አክባሪና ትዳር ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠ ክቡር ስጦታ መሆኑን ታምናለች። ያም ቢሆን ታዲያ ሴት ልጅ ትዳር ካልተመቻት ልጆቿን ያለ አባት ማሳደግ ትችላለች የሚል ጽኑ አቋም አላት።
እግዚአብሔር በአራት ሴት ልጆች ባርኮኛል የምትለው አርቲስት የትናየት፤ ልጆችን ከአባት ጋር ሆኖ ማሳደግም ከችግር ነፃ የሚያደርግ እንዳልሆነ ጠቅሳ፤ በተለይም በአሁን ወቅት ልጆች ከወላጆች ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በራሱ እጅግ ጥቂት እንደሆነ ነው የገለጸችው። እሷ እንዳለችው ልጆቿ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በትምህርት ነው ከትምህርት መልስም ከአስጠኚ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በመኖሩ ከወላጆቻቸው ጋር የሚሳልፉት ጊዜ እጅግ የተወሰነና የተቆጠበ ነው ትላለች።
‹‹ወላጆችም በተመሳሳይ በሥራ የሚጠመዱ በመሆናቸው በተወሰነ ጊዜ ፕሮግራም አድርገው ካላገኟቸው በስተቀር አሁን ያለው ሁኔታ እንደቀደመው ጊዜ አይደለም። በተለይም ትምህርት ቤት ከገቡ ልጆቹም ጊዜ አይኖራቸውም። ይሁን እንጂ ወላጆች በተቻለ አቅም በየዕለቱ ለልጆቻቸው የሚተርፍ ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል›› በማለት እሷ በቀን ውስጥ ካላት ጊዜ አብቃቅታ ለልጆቿ የምትሰጥ መሆኗን ነው የገለጸችው።
ጊዜ ከመስጠት ባለፈም ልጆች የሚስፈልጋቸው ብዙ ጉዳዮች ስለመኖሩ ያነሳችው አርቲስት የትናየት፤ ያለአባት በማሳደጓ ግን ይህ ነገር ቀረባቸው ብላ የምትቆጭበት አንድም ነገር እንደሌለ ነው የገለጸችው። እሷ እንደምትለው፤ ለልጆች አስፈላጊ የተባሉ ማናቸውንም ሁኔታዎች በማሟላት እናትም አባትም በአንድ ላይ ሆነው ከሚያሳድጓቸው ልጆች ባልተናነሰና እንዲያውም በተሻለ ሁኔታ ልጆቿን እያሳደገች ነው። ‹‹ልጆቼን ያለ አባት በማሳደጌ ቀረባቸው ብዬ የምለው ነገር ቢኖር ‹‹አባባ›› ብሎ መጣራት ብቻ ነው›› ትላለች።
ጥሩ አባቶች እንዳሉ ሁሉ ጥሩ እናቶች አሉ የምትለው አርቲስት የትናየት፤ ለሰው ልጅ አባት መሆን የሚችለው እግዚአብሔር ነው የሚል ዕምነትም አላት። ‹‹እግዚአብሔርን አባት በማድረግ ልጆቼን ሳላጎድላቸው፣ እግዚአብሔርን አውቀው፣ የሥራን ክቡርነት ተረድተው፣ ጥገኝነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተገንዝበው እንዲያድጉ ትልቁን ድርሻ ወስጄ ማሳደግ ችያለሁ›› በማለት አንዳንድ ጊዜ በትዳር ውስጥም ሆነው ልጆችን ማሳደግ እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ታነሳለች።
ትዳር ባይኖራትም አራት ሴት ልጆቿን እናትም አባትም ሆና ማሳደግ መቻሏ ብዙም ፈተና እንዳልሆነባት ስትገልጽ፤ ለራሷ በቂ ጊዜ ባይኖራትም ለልጆቿ ግን ካላት ሁሉ ቀንሳ ጊዜ በመስጠት መልካም፣ ጥሩና ሀገራቸውን የሚወዱ ልጆች ሆነው እንዲያድጉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የምታሳድግ መሆኗን ነው ያስረዳችው።
ልጆችን በማሳደግ ሂደት ውስጥ አባት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የገለጸችው አርቲስት የትናየት፤ በዙሪያዋ የምታስተውለውም ይህንኑ እንደሆነና አብዛኞቹ አባቶች በልጆች አስተዳደግ ላይ ትልቁን ሚና ሲወጡና እናቶችን ነፃ ሲያደርጉ መታዘቧን ገልጻ፤ ሁሉም ሰው ግን አንድ አይደለምና ሁኔታዎች ካልፈቀዱ ሴቶች ልጆቻቸውን በብቸኝነት ማሳደግ ይችላሉ። አባቶችም እንዲሁ እናት ሳትኖር ልጆቻቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ትገልጻለች። በልጆች አስተዳደግ እናትም ሆነች አባት ትልቅ ድርሻ አላቸው። የምትለው አርቲስት የትናየት፤ ነገር ግን የአባት አለመኖር ልጆች ተጎድተው እንዲያድጉ ምክንያት መሆን የለበትም ባይ ናት።
ሴት ብቻዋን ሆና መሥራት፣ ልጆች ማሳደግ፣ አገር መምራት፣ ተፅዕኖ መፍጠርና ሌላም ሌላም ማድረግ እንደምትችል ለልጆቼ ማሳየት እፈልጋለሁ›› የምትለው አርቲስት የትናየት፤ ይህን ለማስተማር ጥሩ እናት መሆን ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነ ነው የገለጸችው። አለፍ ሲልም ሴቶች የአባትን ድርሻ ጭምር ደርበው መወጣት ሲችሉ ይህን እየተመለከቱ የሚያድጉ ልጆች በራሳቸው መቆም የሚችሉ ጎበዝና ጠንካራ ሆነው የሚያድጉበትን ዕድል ይፈጥራልም ብላለች።
በመጨረሻም በብዙ ችግር ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ያለአባት የሚያሳድጉ እናቶች የችግሮቻቸው መነሻ ባል መፍታታቸው አልያም ከትዳር ውጭ ልጅ መውለዳቸው አይደለም። በማለት በተለያየ አጋጣሚ ልጆቻቸውን ያለአባት የሚሳድጉ እናቶች አዕምሯቸውን ለሥራና ሥራ ብቻ ዝግጁ ማድረግ እንዳለባቸውና ከአባት ውጭ ልጆችን ማሳደግ እንደሚችሉ ትገልጻለች። ለዚህም ትላለች ለዚህም በየአካባቢው በርካታ ሴቶች ልጆቻቸውን እናትም አባትም ሆነው እንደሚያሳድጉና ስኬታማ እንደሆኑም ጭምር ማየት ይቻላል በማለት አንድ ምሳሌ እንደሆነች ገልጻ በልጆች አስተዳደግ ላይ የአባት ድርሻ የጎላ ቢሆንም እናት ደግሞ የበለጠውን በማድረግ ሁሉን ትችላላች በማለት ሃሳቧን አጠቃላለች።
ሌላኛዋ ባለታሪካችን ደግሞ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናዎችን ተቋቁመው ልጇን በብዙ ውጣውረድ እያሳደገች እንደሆነ የገለጸችው ወይዘሮ ፀሐይ ሞላ ስሟ የተቀየረ ባለታሪካችን ናት። ባለታሪካችን የ14 ዓመት ሴት ልጅ ያላት ሲሆን፤ ልጇን የምታሳድገው በብቸኝነት ነው። ‹‹ትዳር ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ትልቅ ፀጋ ነው። ልጆች ደግሞ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው›› የምትለው ወይዘሮ ፀሐይ፤ እናት ለልጆች እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ብትሆንም ልጆች በእናትና በአባት እቅፍ ውስጥ ሆነው ቢያድጉ መልካም ነው። ካልሆነ ግን ከባድ ነው ትላለች።
ከልጇ አባት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ተለያይታ በቤተሰብ እገዛ ልጇን እያሳደገች መሆኑን ስትገልጽ፤ ‹‹የቱንም ያህል ቢሞላላት አባት ከሌለ ጎዶሎ አለው›› በማለት ነው። የምታስረዳው። እሷ እንዳለችው ልጆች የእናት ፍቅርና እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ የአባት ፍቅርና እንክብካቤም የግድ ያስፈልጋቸዋል። ያ ካልሆነ ግን እናት አባትም እናትም ሆና የማሳደግ ኃላፊነት አለባት። በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ብዙ ፈተናዎች አሉ። እርግጥ ነው የሚያጋጥሙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፈተናዎች ሁሉ እናቶችን ያንገዳግዱን ይሆናል እንጂ ፈጽሞ አይጥሉም። ምክንያቱም እናትነት ሁሉን መቻልና ሁሉን መሆን ነውና በማለት ገልጻለች።
ልጇን ከአባት ውጭ የምታሳድግ እናት ከማኅበረሰቡ አመለካከት ጀምሮ ፈታኝ የሆኑ ብዙ ችግሮች እንዳሉ በመጥቀስ፤ ማኅበረሰቡ ትዳር ውስጥ ለሚፈጠር ልጅ እና ከትዳር ውጭ ለሚመጣ ልጅ እኩል ዋጋ የሚሰጥ አለመሆኑንና ይህም የሥነልቦና ጫና ያለው መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ፀሐይ፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ዋጋ ተከፍሎላቸው የሚያድጉት ልጆች አሉ። ያለአባት እናት ብቻዋን የምታሳድገው ልጅ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄው ቢመለስለት የማኅበረሰቡ ጫና በራሱ ሌላ ፈተና ነው ይላሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በተለይም እናት የገቢ ምንጭ ከሌላት ፈተናው ከባድ ነው። እርግጥ ነው የራሷን ፍላጎቶች ሁሉ ገድባ ለልጆቿ ቅድሚያ በመስጠት ጎዶሎውን ትሞላ ይሆናል። ነገር ግን ተፈጥሯዊ የሆኑና መመለስ የማትችላቸው ጥያቄዎች ግን ሁሌም በውስጣቸው ይኖራል ነው ያሉት።
እናትነት መልካም ገጽታዎችን አምቆ የያዘ የሴት ልጅ ትልቅ መገለጫ ነው የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይ፤ ለልጆች የማይከፈል መስዋዕትነት ባለመኖሩ ብዙ እናቶች ልጆች የሚያሳድጉት ብዙ ዋጋ ከፍለው እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይም ልጆቻቸውን ያለአባት የሚያሳድጉ እናቶች ብርቱ፣ ጎበዝና ጠንካራ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም